ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 13:1-14

  • ለባለሥልጣናት መገዛት (1-7)

    • ቀረጥ መክፈል (6, 7)

  • “ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው” (8-10)

  • በቀን ብርሃን መመላለስ (11-14)

13  ሰው* ሁሉ ለበላይ ባለሥልጣናት ይገዛ፤+ ሥልጣን ሁሉ የሚገኘው ከአምላክ ነውና፤+ ያሉት ባለሥልጣናት አንጻራዊ ቦታቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው።+  ስለዚህ ባለሥልጣንን የሚቃወም ሁሉ አምላክ ያደረገውን ዝግጅት ይቃወማል፤ ይህን ዝግጅት የሚቃወሙ በራሳቸው ላይ ፍርድ ያመጣሉ።  ገዢዎች የሚያስፈሩት ክፉ ለሚያደርጉ እንጂ መልካም ለሚያደርጉ አይደለምና።+ እንግዲያው ባለሥልጣንን መፍራት የማትፈልግ ከሆነ መልካም ማድረግህን ቀጥል፤+ ከእሱም ምስጋና ታገኛለህ፤  ለአንተ ጥቅም ሲባል የተሾመ የአምላክ አገልጋይ ነውና። ክፉ የምታደርግ ከሆነ ግን ልትፈራ ይገባሃል፤ ምክንያቱም ሰይፍ የሚታጠቀው እንዲያው በከንቱ አይደለም። ክፉ የሚሠራን በመቅጣት* የሚበቀል የአምላክ አገልጋይ ነው።  ስለዚህ ቁጣውን በመፍራት ብቻ ሳይሆን ስለ ሕሊናችሁ ስትሉም መገዛታችሁ አስፈላጊ ነው።+  ቀረጥ የምትከፍሉትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም እነሱ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚያከናውኑ የአምላክ አገልጋዮች ናቸው፤ የዘወትር ተግባራቸውም ይኸው ነው።  ለሁሉም የሚገባውን አስረክቡ፤ ቀረጥ ለሚጠይቅ ቀረጥ፣+ ግብር ለሚጠይቅ ግብር ስጡ፤ መፈራት የሚፈልገውን ፍሩ፤+ መከበር የሚፈልገውን አክብሩ።+  እርስ በርስ ከመዋደድ በቀር በማንም ላይ ምንም ዕዳ አይኑርባችሁ፤+ ሰውን የሚወድ ሁሉ ሕጉን ፈጽሟልና።+  ምክንያቱም “አታመንዝር፣+ አትግደል፣+ አትስረቅ፣+ አትጎምጅ”+ የሚሉት ሕጎችና ሌሎች ትእዛዛት በሙሉ “ባልንጀራህን* እንደ ራስህ ውደድ”+ በሚለው በዚህ ቃል ተጠቃለዋል። 10  ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም፤+ ስለዚህ ፍቅር የሕግ ፍጻሜ ነው።+ 11  ምን ዓይነት ዘመን ላይ እንደምንገኝ ስለምታውቁም ይህን አድርጉ፤ አማኞች ከሆንበት ጊዜ ይልቅ አሁን መዳናችን ይበልጥ ስለቀረበ ከእንቅልፍ የምትነቁበት ሰዓት አሁን ነው።+ 12  ሌሊቱ እየተገባደደ ነው፤ ቀኑም ቀርቧል። ስለዚህ ከጨለማ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አውልቀን+ የብርሃንን የጦር ዕቃዎች እንልበስ።+ 13  መረን በለቀቀ ፈንጠዝያና በስካር፣ ልቅ በሆነ የፆታ ግንኙነትና ማንአለብኝነት በሚንጸባረቅበት ድርጊት*+ እንዲሁም በጠብና በቅናት+ ሳይሆን በቀን ብርሃን እንደምንመላለስ በጨዋነት እንመላለስ።+ 14  ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤+ የሥጋ ፍላጎታችሁን ለማርካት ዕቅድ አታውጡ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ክፉ በሚሠራ ላይ የአምላክን ቁጣ በመግለጽ።”
“ባልንጀራ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል የአንድን ሰው የቅርብ ጓደኛ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሰው ሊያመለክት ይችላል።
ወይም “እፍረተ ቢስነት በሚንጸባረቅበት ምግባር።” እዚህ ላይ የገባው አሴልጊያ የሚለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።