ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 1:1-32

  • ሰላምታ (1-7)

  • ጳውሎስ ወደ ሮም ለመሄድ የነበረው ጉጉት (8-15)

  • ‘ጻድቅ በእምነት ይኖራል’ (16, 17)

  • አምላክን የማያከብሩ ሰዎች የሚያመካኙበት ነገር የላቸውም (18-32)

    • የአምላክ ባሕርያት በፍጥረት ሥራው ላይ ይታያሉ (20)

1  የክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ ከሆነው፣ ሐዋርያ እንዲሆን ከተጠራውና የአምላክን ምሥራች እንዲያውጅ ከተሾመው* ከጳውሎስ፤+  ይህ ምሥራች አምላክ በነቢያቱ አማካኝነት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድሞ የሰጠው የተስፋ ቃል ሲሆን  በሥጋ ከዳዊት ዘር+ ስለተወለደው ልጁ የሚገልጽ ነው፤  ይሁንና እሱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የአምላክ ልጅ+ መሆኑ እንዲታወቅ ተደርጓል። ይህም የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት በተነሳ+ ጊዜ ነው።  ለስሙ ክብር በብሔራት ሁሉ መካከል+ በእምነት የሚታዘዙ ሰዎች እንዲገኙ ሲባል በእሱ አማካኝነት ጸጋና ሐዋርያነት+ ተቀብለናል፤*  የኢየሱስ ክርስቶስ እንዲሆኑ ከአሕዛብ ከተጠሩት መካከል እናንተም ትገኙበታላችሁ።  ቅዱሳን እንድትሆኑ ለተጠራችሁና በአምላክ ለተወደዳችሁ በሮም ለምትኖሩ ሁሉ፦ አባታችን ከሆነው አምላክና ከጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን።  ከሁሉ አስቀድሜ፣ ስለ እምነታችሁ በመላው ዓለም ስለሚወራ ስለ ሁላችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለአምላኬ ምስጋና አቀርባለሁ።  ያለማቋረጥ ዘወትር በጸሎቴ እናንተን ሳልጠቅስ እንደማላልፍ፣+ ስለ ልጁ የሚገልጸውን ምሥራች በማወጅ በሙሉ ልቤ ቅዱስ አገልግሎት የማቀርብለት አምላክ ምሥክሬ ነው፤ 10  ደግሞም በአምላክ ፈቃድ አሁን በመጨረሻ እንደ ምንም ተሳክቶልኝ ወደ እናንተ መምጣት እንድችል ልመና እያቀረብኩ ነው። 11  ለመጽናት የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እጓጓለሁና፤ 12  ይህን ስል እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ+ ነው። 13  ይሁንና ወንድሞች፣ በሌሎች አሕዛብ መካከል ፍሬ እንዳፈራሁ ሁሉ በእናንተም መካከል ፍሬ አፈራ ዘንድ ወደ እናንተ ለመምጣት ብዙ ጊዜ አቅጄ እንደነበር እንድታውቁ እፈልጋለሁ። ሆኖም ለመምጣት ባሰብኩ ቁጥር የሆነ እንቅፋት ያጋጥመኛል። 14  ለግሪካውያንም ሆነ ግሪካውያን ላልሆኑ* እንዲሁም ለጠቢባንም ሆነ ላልተማሩ ዕዳ አለብኝ፤ 15  በመሆኑም በሮም ላላችሁት ለእናንተም ምሥራቹን ለማወጅ እጓጓለሁ።+ 16  እኔ በምሥራቹ አላፍርምና፤+ እንዲያውም ለሚያምን ሁሉ+ ይኸውም በመጀመሪያ ለአይሁዳዊ+ ከዚያም ለግሪካዊ+ ምሥራቹ መዳን የሚያስገኝ የአምላክ ኃይል ነው። 17  ምክንያቱም “ጻድቅ ግን በእምነት ይኖራል”+ ተብሎ እንደተጻፈ ሁሉ እምነት ያላቸው+ ሰዎች፣ አምላክ በምሥራቹ አማካኝነት ጽድቁን እንደሚገልጥ ይረዳሉ፤ ይህ ደግሞ እምነታቸውን ያጠነክርላቸዋል። 18  እውነትን ለማፈን+ የተንኮል ዘዴ የሚጠቀሙ ሰዎች በሚፈጽሙት አምላክን የሚጻረር ድርጊትና ክፋት ሁሉ ላይ የአምላክ ቁጣ+ ከሰማይ እየተገለጠ ነው፤ 19  ምክንያቱም ስለ አምላክ ሊታወቅ የሚችለው ነገር በእነሱ ዘንድ በግልጽ የታወቀ ነው፤ ይህም የሆነው አምላክ ይህን ግልጽ ስላደረገላቸው ነው።+ 20  የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና+ አምላክነቱ+ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤+ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል፤ ስለሆነም የሚያመካኙበት ነገር የላቸውም። 21  አምላክን የሚያውቁ ቢሆኑም እንኳ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም ብሎም አላመሰገኑትም፤ ከዚህ ይልቅ አስተሳሰባቸው ከንቱ ሆነ፤ የማያስተውለው ልባቸውም ጨለመ።+ 22  ጥበበኞች ነን ቢሉም ሞኞች ሆኑ፤ 23  ሊጠፋ የማይችለውን አምላክ ክብር ጠፊ በሆነው ሰው፣ በወፎች፣ አራት እግር ባላቸው እንስሳትና በምድር ላይ በሚሳቡ ፍጥረታት ምስል ለወጡት።+ 24  ስለሆነም አምላክ እንደ ልባቸው ምኞት የገዛ ራሳቸውን አካል እንዲያስነውሩ ለርኩሰት አሳልፎ ሰጣቸው። 25  እነዚህ ሰዎች የአምላክን እውነት በሐሰት ለውጠዋል፤ በፈጣሪ ፋንታ ለፍጥረት ክብር ሰጥተዋል፤* እንዲሁም ቅዱስ አገልግሎት አቅርበዋል፤ ይሁንና ለዘላለም ሊወደስ የሚገባው ፈጣሪ ብቻ ነው። አሜን። 26  አምላክ አሳፋሪ ለሆነ የፆታ ምኞት+ አሳልፎ የሰጣቸው በዚህ ምክንያት ነው፤ ሴቶቻቸውም ተፈጥሯዊ የሆነውን ግንኙነት ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ ግንኙነት ለወጡ፤+ 27  ወንዶቹም ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ከሴቶች ጋር መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው ኃይለኛ በሆነ የፆታ ስሜት ተቃጠሉ፤ ወንዶች ከወንዶች ጋር አስነዋሪ ነገር ፈጸሙ፤+ እነሱ ራሳቸውም ለጥፋታቸው የሚገባውን ቅጣት* እየተቀበሉ ነው።+ 28  ለአምላክ እውቅና መስጠት ተገቢ መስሎ ስላልታያቸው* መደረግ የማይገባውን ነገር እንዲያደርጉ አምላክ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ለሌለው አስተሳሰብ አሳልፎ ሰጣቸው።+ 29  ደግሞም እነዚህ ሰዎች በዓመፅ፣+ በኃጢአተኝነት፣ በስግብግብነት፣*+ በክፋት፣ በቅናት፣+ በነፍሰ ገዳይነት፣+ በጥል፣ በማታለልና+ በተንኮል+ የተሞሉ ናቸው፤ እንዲሁም ስም አጥፊዎች፣* 30  ሐሜተኞች፣+ አምላክን የሚጠሉ፣ ተሳዳቢዎች፣ ትዕቢተኞች፣ ጉረኞች፣ ክፋት ጠንሳሾች፣ ለወላጆች የማይታዘዙ፣+ 31  የማያስተውሉ፣+ ቃላቸውን የማይጠብቁ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸውና ምሕረት የለሾች ናቸው። 32  እነዚህ ሰዎች ‘እንዲህ ያሉ ነገሮችን የሚያደርጉ* ሁሉ ሞት ይገባቸዋል’+ የሚለውን የአምላክን የጽድቅ ሕግ በሚገባ የሚያውቁ ቢሆኑም በዚህ ድርጊታቸው መግፋት ብቻ ሳይሆን ይህን የሚያደርጉትንም ይደግፋሉ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ከተለየው።”
ወይም “ተቀብያለሁ።” እዚህ ላይ ጳውሎስ በብዙ ቁጥር የተጠቀመው ራሱን ለማመልከት ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለባዕዳን።” ቃል በቃል “ላልሠለጠኑ።”
ወይም “ፍጥረትን አምልከዋል።”
ወይም “ብድራት።”
ወይም “ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማግኘት ስላልፈለጉ።”
ወይም “አሾክሿኪዎች።”
ወይም “በመጎምጀት።”
እንዲህ ያሉ ነገሮችን የመሥራት ልማድ ያላቸውን ሰዎች ያመለክታል።