ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 3:1-22

  • ለሰርዴስ (1-6)፣ ለፊላደልፊያ (7-13)፣ ለሎዶቅያ የተላከ መልእክት (14-22)

3  “በሰርዴስ ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ሰባቱ የአምላክ መናፍስት+ ያሉትና ሰባቱን ከዋክብት+ የያዘው እንዲህ ይላል፦ ‘ሥራህን አውቃለሁ፤ ሕያው ነው የሚል ስም አለህ፤ ነገር ግን ሞተሃል።+  ሥራህን በአምላኬ ፊት በተሟላ ሁኔታ ተጠናቆ ስላላገኘሁት ንቃ፤+ ሊሞቱ የተቃረቡትን የቀሩትን ነገሮችም አጠናክር።  ስለዚህ የተቀበልከውንና የሰማኸውን ምንጊዜም አስብ፤ እንዲሁም ዘወትር ጠብቀው፤ ንስሐም ግባ።+ ካልነቃህ ግን እንደ ሌባ እመጣለሁ፤+ በየትኛው ሰዓት ከተፍ እንደምልብህም ፈጽሞ አታውቅም።+  “‘ይሁን እንጂ ልብሳቸውን ያላረከሱ+ ጥቂት ሰዎች* ከአንተ ጋር በሰርዴስ አሉ፤ እነሱም የሚገባቸው ስለሆኑ ነጭ ልብስ+ ለብሰው ከእኔ ጋር ይሄዳሉ።  ድል የሚነሳም+ልክ እንዲሁ ነጭ ልብስ ይለብሳል፤+ እኔም ስሙን ከሕይወት መጽሐፍ+ በምንም ዓይነት አልደመስስም፤* ከዚህ ይልቅ በአባቴ ፊትና በመላእክቱ ፊት ለስሙ እመሠክራለሁ።+  መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።’  “በፊላደልፊያ ላለው ጉባኤ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ ቅዱስና+ እውነተኛ የሆነው፣+ የዳዊት ቁልፍ ያለው፣+ ማንም እንዳይዘጋ፣ የሚከፍተው እንዲሁም ማንም እንዳይከፍት፣ የሚዘጋው እሱ እንዲህ ይላል፦  ‘ሥራህን አውቃለሁ፤ እነሆ፣ ማንም ሊዘጋው የማይችል የተከፈተ በር በፊትህ አድርጌአለሁ።+ ደግሞም ጥቂት ኃይል እንዳለህ አውቃለሁ፤ ቃሌንም ጠብቀሃል፤ ስሜንም አልካድክም።  እነሆ፣ አይሁዳውያን ሳይሆኑ አይሁዳውያን ነን እያሉ የሚዋሹት፣+ ከሰይጣን ምኩራብ የሆኑት ወደ አንተ መጥተው በእግርህ ፊት እንዲሰግዱ* አደርጋለሁ፤ እንዲሁም እንደወደድኩህ እንዲያውቁ አደርጋለሁ። 10  ስለ ጽናቴ የተነገረውን ቃል ስለጠበቅክ*+ እኔም በምድር ላይ የሚኖሩትን ለመፈተን በመላው ምድር ላይ ከሚመጣው የፈተና ሰዓት እጠብቅሃለሁ።+ 11  ቶሎ እመጣለሁ።+ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን ምንጊዜም አጥብቀህ ያዝ።+ 12  “‘ድል የሚነሳውን በአምላኬ ቤተ መቅደስ ዓምድ አደርገዋለሁ፤ ከዚያ በኋላም በምንም ዓይነት ከዚያ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና+ ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን የአምላኬን ከተማ የአዲሲቱን ኢየሩሳሌም+ ስም እንዲሁም የእኔን አዲስ ስም በእሱ ላይ እጽፋለሁ።+ 13  መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።’ 14  “በሎዶቅያ ላለው ጉባኤ+ መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፦ አሜን የሆነው፣+ ታማኝና እውነተኛ+ ምሥክር+ እንዲሁም ከአምላክ ፍጥረት የመጀመሪያ የሆነው+ እንዲህ ይላል፦ 15  ‘ሥራህን አውቃለሁ፤ ወይ ቀዝቃዛ ወይ ትኩስ አይደለህም። ቀዝቃዛ ወይም ደግሞ ትኩስ ብትሆን ደስ ባለኝ ነበር። 16  ለብ ያልክ እንጂ ትኩስም+ ሆነ ቀዝቃዛ+ ስላልሆንክ ከአፌ አውጥቼ ልተፋህ ነው። 17  ምክንያቱም “ሀብታም ነኝ፤+ ደግሞም ብዙ ሀብት አከማችቻለሁ፤ ምንም ነገር አያስፈልገኝም” ትላለህ፤ ነገር ግን ጎስቋላ፣ ምስኪን፣ ድሃ፣ ዕውርና የተራቆትክ መሆንህን አታውቅም፤ 18  ሀብታም እንድትሆን በእሳት የነጠረ ወርቅ፣ ልብስ እንድትለብስና ለኀፍረት የሚዳርገው እርቃንህ እንዲሸፈን+ ነጭ ልብስ እንዲሁም ማየት እንድትችል+ ዓይንህን የምትኳለው ኩል+ ከእኔ እንድትገዛ እመክርሃለሁ። 19  “‘እኔ፣ የምወዳቸውን ሁሉ እወቅሳለሁ እንዲሁም እገሥጻለሁ።+ ስለዚህ ቀናተኛ ሁን፤ ንስሐም ግባ።+ 20  እነሆ፣ በር ላይ ቆሜ እያንኳኳሁ ነው። ማንም ድምፄን ሰምቶ በሩን ከከፈተልኝ ወደ ቤቱ እገባለሁ፤ ከእሱም ጋር ራት እበላለሁ፤ እሱም ከእኔ ጋር ይበላል። 21  እኔ ድል ነስቼ ከአባቴ ጋር በዙፋኑ ላይ እንደተቀመጥኩ ሁሉ+ ድል የሚነሳውንም+ ከእኔ ጋር በዙፋኔ ላይ እንዲቀመጥ አደርገዋለሁ።+ 22  መንፈስ ለጉባኤዎቹ የሚናገረውን ጆሮ ያለው ይስማ።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “ጥቂት ስሞች።”
ወይም “አልሰርዝም።”
ወይም “እጅ እንዲነሱ።”
“የተውኩትን የጽናት ምሳሌ ስለተከተልክ” ማለትም ሊሆን ይችላል።