ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 16:1-21

  • ‘የአምላክን ቁጣ የያዙ ሰባት ሳህኖች’ (1-21)

    • መላእክት በምድር (2)፣ በባሕር (3)፣ በወንዞችና በምንጮች (4-7)፣ በፀሐይ (8, 9)፣ በአውሬው ዙፋን (10, 11)፣ በኤፍራጥስና (12-16) በአየር ላይ አፈሰሱ (17-21)

    • በአርማጌዶን የሚካሄድ የአምላክ ጦርነት (14, 16)

16  እኔም ከቅዱሱ ስፍራ*+ የወጣ ታላቅ ድምፅ ሰባቱን መላእክት “ሂዱና የአምላክን ቁጣ የያዙትን ሰባቱን ሳህኖች በምድር ላይ አፍስሱ” ሲል ሰማሁ።+  የመጀመሪያው መልአክ ሄዶ በሳህኑ ውስጥ ያለውን በምድር ላይ አፈሰሰው።+ በዚህ ጊዜም የአውሬው ምልክት በነበራቸውና+ ምስሉን ያመልኩ በነበሩት ሰዎች+ ላይ ጉዳት የሚያስከትልና አስከፊ የሆነ ቁስል+ ወጣባቸው።  ሁለተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን ወደ ባሕር አፈሰሰው።+ ባሕሩም እንደሞተ ሰው ደም ሆነ፤+ በባሕሩም+ ውስጥ ያለ ሕያው ፍጡር* ሁሉ ሞተ።  ሦስተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን ወደ ወንዞችና ወደ ውኃ ምንጮች አፈሰሰው።+ እነሱም ደም ሆኑ።+  እኔም በውኃዎች ላይ ሥልጣን ያለው መልአክ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “ያለህና የነበርክ+ ታማኝ አምላካችን፣+ እነዚህን የፍርድ ውሳኔዎች ስላስተላለፍክ አንተ ጻድቅ ነህ፤+  ምክንያቱም የቅዱሳንንና የነቢያትን ደም አፍስሰዋል፤+ አንተም ደም እንዲጠጡ ሰጥተሃቸዋል፤+ ደግሞም ይገባቸዋል።”+  መሠዊያውም “አዎ፣ ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ* አምላክ ሆይ፣+ ፍርድህ ሁሉ እውነትና ጽድቅ ነው”+ ሲል ሰማሁ።  አራተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን በፀሐይ ላይ አፈሰሰው፤+ ፀሐይም ሰዎችን በእሳት እንድትለበልብ ተፈቀደላት።  ሰዎቹም በኃይለኛ ሙቀት ተለበለቡ፤ ሆኖም እነሱ በእነዚህ መቅሰፍቶች ላይ ሥልጣን ያለውን አምላክ ስም ተሳደቡ እንጂ ንስሐ አልገቡም፤ ለእሱም ክብር አልሰጡም። 10  አምስተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን በአውሬው ዙፋን ላይ አፈሰሰው። መንግሥቱም በጨለማ ተዋጠ፤+ እነሱም ከሥቃያቸው የተነሳ ምላሳቸውን ያኝኩ ጀመር፤ 11  ይሁንና ከሥቃያቸውና ከቁስላቸው የተነሳ የሰማይን አምላክ ተሳደቡ፤ ከሥራቸውም ንስሐ አልገቡም። 12  ስድስተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን በታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ላይ አፈሰሰው፤+ ከፀሐይ መውጫ* ለሚመጡት ነገሥታት መንገድ እንዲዘጋጅላቸውም+ የወንዙ ውኃ ደረቀ።+ 13  እኔም እንቁራሪት የሚመስሉ በመንፈስ የተነገሩ ሦስት ርኩሳን ቃላት* ከዘንዶው+ አፍና ከአውሬው አፍ እንዲሁም ከሐሰተኛው ነቢይ አፍ ሲወጡ አየሁ። 14  እንዲያውም እነዚህ በአጋንንት መንፈስ የተነገሩ ቃላት ናቸው፤ ተአምራዊ ምልክቶችም ይፈጽማሉ፤+ እነሱም ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን+ ወደሚካሄደው ጦርነት ሊሰበስቧቸው+ ወደ ዓለም ነገሥታት ሁሉ ይወጣሉ። 15  “እነሆ፣ እንደ ሌባ እመጣለሁ።+ ራቁቱን እንዳይሄድና ሰዎች ኀፍረቱን እንዳያዩበት+ ነቅቶ የሚኖርና+ መደረቢያውን የሚጠብቅ ሰው ደስተኛ ነው።” 16  እነሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን*+ ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው። 17  ሰባተኛው መልአክ በሳህኑ ውስጥ ያለውን በአየር ላይ አፈሰሰው። በዚህ ጊዜ ከቅዱሱ ስፍራ፣* ከዙፋኑ “ተፈጸመ!” የሚል ታላቅ ድምፅ ወጣ።+ 18  እንዲሁም የመብረቅ ብልጭታ፣ ድምፅና ነጎድጓድ ተከሰተ፤ ሰው በምድር ላይ መኖር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ታይቶ የማያውቅ ታላቅ የምድር ነውጥም ተከሰተ፤+ የምድር ነውጡ መጠነ ሰፊና እጅግ ታላቅ ነበር። 19  ታላቂቱ ከተማ+ ለሦስት ተከፈለች፤ የብሔራት ከተሞችም ፈራረሱ፤ አምላክም የመዓቱን የቁጣ ወይን ጠጅ የያዘውን ጽዋ ይሰጣት ዘንድ+ ታላቂቱ ባቢሎንን+ አስታወሳት። 20  ደሴቶችም ሁሉ ሸሹ፤ ተራሮችም ሊገኙ አልቻሉም።+ 21  ከዚያም ታላቅ የበረዶ ድንጋይ ከሰማይ በሰዎች ላይ ወረደ፤+ እያንዳንዱ የበረዶ ድንጋይ አንድ ታላንት* ይመዝን ነበር፤ መቅሰፍቱ እጅግ ታላቅ ስለነበር ሰዎቹ ከበረዶው መቅሰፍት+ የተነሳ አምላክን ተሳደቡ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

የቤተ መቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን ያመለክታል።
ወይም “ነፍስ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ከምሥራቅ።”
ቃል በቃል “ርኩሳን መናፍስት።”
ግሪክኛ፣ ሐርማጌዶን። “የመጊዶ ተራራ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው።
የቤተ መቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን ያመለክታል።
የግሪኩ ታላንት 20.4 ኪሎ ግራም ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።