የሉቃስ ወንጌል 4:1-44

  • ዲያብሎስ ኢየሱስን ፈተነው (1-13)

  • ኢየሱስ በገሊላ መስበክ ጀመረ (14, 15)

  • የናዝሬት ሰዎች ኢየሱስን አልተቀበሉትም (16-30)

  • በቅፍርናሆም በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ አስተማረ (31-37)

  • የስምዖን አማትና ሌሎች ሰዎች ተፈወሱ (38-41)

  • ሕዝቡ ኢየሱስን ገለል ባለ ስፍራ አገኙት (42-44)

4  ከዚያም ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ከዮርዳኖስ ተመለሰ፤ በምድረ በዳም ሳለ መንፈስ ይመራው ነበር፤+  በዚያም 40 ቀን ቆየ፤ ዲያብሎስም ፈተነው።+ በእነዚህም ቀናት ምንም ስላልበላ መጨረሻ ላይ ተራበ።  በዚህ ጊዜ ዲያብሎስ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ይህ ድንጋይ ዳቦ እንዲሆን እዘዝ” አለው።  ኢየሱስ ግን “‘ሰው በምግብ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰለት።+  ዲያብሎስም ወደ አንድ ከፍ ያለ ቦታ አወጣውና የዓለምን መንግሥታት ሁሉ በቅጽበት አሳየው።+  ከዚያም እንዲህ አለው፦ “ይህ ሁሉ ሥልጣንና የእነዚህ መንግሥታት ክብር ተሰጥቶኛል፤+ እኔ ደግሞ ለፈለግኩት መስጠት ስለምችል ለአንተ እሰጥሃለሁ።  ስለዚህ አንድ ጊዜ በፊቴ ተደፍተህ ብታመልከኝ ይህ ሁሉ የአንተ ይሆናል።”  ኢየሱስም መልሶ “‘ይሖዋ* አምላክህን ብቻ አምልክ፤ ለእሱም ብቻ ቅዱስ አገልግሎት አቅርብ’ ተብሎ ተጽፏል” አለው።+  ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ከወሰደው በኋላ በቤተ መቅደሱ አናት* ላይ አቁሞ እንዲህ አለው፦ “የአምላክ ልጅ ከሆንክ እስቲ ራስህን ወደ ታች ወርውር፤+ 10  እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘አንተን እንዲጠብቁ መላእክቱን ስለ አንተ ያዛል።’ 11  እንዲሁም ‘እግርህን እንቅፋት እንዳይመታው በእጃቸው ያነሱሃል።’”+ 12  ኢየሱስም መልሶ “‘አምላክህን ይሖዋን* አትፈታተነው’ ተብሏል” አለው።+ 13  ዲያብሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ ሌላ አመቺ ጊዜ እስኪያገኝ ድረስ ትቶት ሄደ።+ 14  ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በመንፈስ ኃይል ወደ ገሊላ ተመለሰ።+ ዝናውም በዙሪያው ባለ አገር ሁሉ ተሰራጨ። 15  በተጨማሪም በምኩራቦቻቸው ማስተማር ጀመረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ያከብረው ነበር። 16  ከዚያም ወዳደገበት ቦታ ወደ ናዝሬት መጣ፤+ እንደ ልማዱም በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገባ፤+ ሊያነብም ተነስቶ ቆመ። 17  የነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልልም ተሰጠው፤ ጥቅልሉንም ተርትሮ እንዲህ ተብሎ የተጻፈበትን ቦታ አገኘ፦ 18  “የይሖዋ* መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ምክንያቱም ለድሆች ምሥራች እንድናገር ቀብቶኛል። ለተማረኩት ነፃነትን፣ ለታወሩትም ማየትን እንዳውጅ፣ የተጨቆኑትን ነፃ እንዳወጣ+ 19  እንዲሁም የይሖዋን* ሞገስ ስለሚያገኙበት ዓመት+ እንድሰብክ ልኮኛል።” 20  ከዚያም ጥቅልሉን ጠቅልሎ ለአገልጋዩ መልሶ ሰጠውና ተቀመጠ፤ በምኩራቡ ውስጥ ያሉት ሰዎችም ሁሉ ትኩር ብለው ይመለከቱት ነበር። 21  እሱም “ይህ አሁን የሰማችሁት የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል ዛሬ ተፈጸመ” አላቸው።+ 22  ሁሉም ስለ እሱ መልካም ነገር ይናገሩ ጀመር፤ ከአፉ በሚወጡት የሚማርኩ ቃላትም+ በመደነቅ “ይህ የዮሴፍ ልጅ አይደለም እንዴ?” ይሉ ነበር።+ 23  በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “‘አንተ ሐኪም፣ እስቲ ራስህን አድን’ የሚለውን አባባል እንደምትጠቅሱብኝ ጥርጥር የለውም። ‘በቅፍርናሆም+ እንደተደረገ የሰማነውን ነገር እዚህ በራስህ አገርም አድርግ’ ትሉኛላችሁ።” 24  እንዲህም አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ነቢይ በገዛ አገሩ ተቀባይነት አያገኝም።+ 25  እውነቱን ልንገራችሁ፦ ለምሳሌ በኤልያስ ዘመን ሰማይ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር በተዘጋና በምድሪቱ ሁሉ ላይ ጽኑ ረሃብ በተከሰተ ጊዜ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ።+ 26  ሆኖም ኤልያስ በሲዶና አገር በሰራፕታ ትኖር ወደነበረች አንዲት መበለት ተላከ እንጂ ከእነዚህ ሴቶች ወደ አንዷም አልተላከም።+ 27  በተጨማሪም በነቢዩ ኤልሳዕ ዘመን በእስራኤል ብዙ የሥጋ ደዌ በሽተኞች ነበሩ፤ ሆኖም ከሶርያዊው ከንዕማን በስተቀር ከእነሱ መካከል አንድም ሰው አልነጻም።”*+ 28  በምኩራቡ ውስጥ የነበሩት ሁሉ ይህን ሲሰሙ እጅግ ተቆጡ፤+ 29  ተነስተውም እያጣደፉ ከከተማው አስወጡት፤ ቁልቁል ገፍትረው ሊጥሉትም ፈልገው ከተማቸው ወደምትገኝበት ተራራ አፋፍ ወሰዱት። 30  እሱ ግን በመካከላቸው ሰንጥቆ ሄደ።+ 31  ከዚያም በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ወደ ቅፍርናሆም ከተማ ወረደ። እዚያም በሰንበት ሕዝቡን ያስተምር ነበር፤+ 32  በሥልጣን ይናገር ስለነበረም ሕዝቡ በትምህርት አሰጣጡ እጅግ ተደነቁ።+ 33  በምኩራቡም ውስጥ ርኩስ መንፈስ ማለትም ጋኔን ያደረበት አንድ ሰው ነበር፤ ሰውየውም በታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ጮኸ፦+ 34  “እንዴ! የናዝሬቱ ኢየሱስ፣+ እኛ ከአንተ ጋር ምን ጉዳይ አለን? የመጣኸው ልታጠፋን ነው? ማን እንደሆንክ በሚገባ አውቃለሁ፤ አንተ የአምላክ ቅዱስ አገልጋይ ነህ።”+ 35  ሆኖም ኢየሱስ “ዝም በል፤ ከእሱም ውጣ!” ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም ሰውየውን በሕዝቡ ፊት ከጣለው በኋላ ምንም ሳይጎዳው ለቆት ወጣ። 36  በዚህ ጊዜ ሁሉም በመገረም “እንዴ! ይህ ምን ዓይነት አነጋገር ነው? ርኩሳን መናፍስትን በሥልጣንና በኃይል ያዛል፤ እነሱም ታዘው ይወጣሉ!” ሲሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር። 37  ስለ ኢየሱስ የሚወራው ወሬም በዙሪያው ባለው አገር ሁሉ ተዳረሰ። 38  ኢየሱስ ከምኩራቡ ከወጣ በኋላ ወደ ስምዖን ቤት ገባ። የስምዖንም አማት ኃይለኛ ትኩሳት ይዟት እየተሠቃየች ነበር፤ እነሱም እንዲረዳት ለመኑት።+ 39  እሱም አጠገቧ ቆመና ጎንበስ ብሎ ትኩሳቱን ገሠጸው፤ ትኩሳቱም ለቀቃት። ወዲያውም ተነስታ ታገለግላቸው ጀመር። 40  ፀሐይ ስትጠልቅም ሰዎች በተለያየ በሽታ የተያዙ ሕመምተኞቻቸውን ወደ እሱ አመጡ። እሱም በእያንዳንዳቸው ላይ እጁን በመጫን ፈወሳቸው።+ 41  አጋንንትም “አንተ የአምላክ ልጅ ነህ” እያሉና እየጮኹ+ ከብዙ ሰዎች ወጡ። እሱ ግን ገሠጻቸው፤ ክርስቶስ መሆኑንም አውቀው ስለነበር+ እንዳይናገሩ ከለከላቸው።+ 42  በነጋም ጊዜ ወጥቶ ገለል ወዳለ ስፍራ ሄደ።+ ሕዝቡ ግን ፈልገው ፈላልገው * ያለበት ቦታ ድረስ መጡ፤ እንዳይሄድባቸውም ለመኑት። 43  እሱ ግን “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” አላቸው።+ 44  በመሆኑም በይሁዳ ምኩራቦች መስበኩን ቀጠለ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በጣሪያው ዙሪያ ያለ ግንብ፤ ጫፍ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “አልተፈወሰም።”
ወይም “አድነው።”