የሉቃስ ወንጌል 3:1-38

  • ዮሐንስ ሥራውን ጀመረ (1, 2)

  • ዮሐንስ ስለ ጥምቀት ሰበከ (3-20)

  • ኢየሱስ ተጠመቀ (21, 22)

  • የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሐረግ (23-38)

3  ጢባርዮስ ቄሳር በነገሠ በ15ኛው ዓመት፣ ጳንጥዮስ ጲላጦስ የይሁዳ አገረ ገዢ፣ ሄሮድስ*+ የገሊላ አውራጃ ገዢ፣* ወንድሙ ፊልጶስ ደግሞ የኢጡርያስና የጥራኮኒዶስ አውራጃ ገዢ፣ ሊሳኒዮስ የአቢላኒስ አውራጃ ገዢ በነበሩበት ጊዜ  እንዲሁም ቀያፋና የካህናት አለቃው ሐና በነበሩበት ዘመን+ የአምላክ ቃል በምድረ በዳ+ ወደነበረው ወደ ዘካርያስ ልጅ ወደ ዮሐንስ+ መጣ።  ዮሐንስም ለኃጢአት ይቅርታ፣ የንስሐ ምልክት የሆነውን ጥምቀት እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለው አገር ሁሉ ሄደ፤+  ይህም የሆነው በነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተብሎ በተጻፈው ቃል መሠረት ነው፦ “አንድ ሰው በምድረ በዳ ‘የይሖዋን* መንገድ አዘጋጁ! ጎዳናዎቹንም አቅኑ’ በማለት ይጮኻል።+  ‘ሸለቆው ሁሉ ይሞላ፤ ተራራውና ኮረብታው ሁሉ ይደልደል፤ ጠማማው መንገድ ቀጥ ያለ፣ ጎርበጥባጣውም መንገድ ለጥ ያለ ይሁን፤  ሥጋም* ሁሉ የአምላክን ማዳን* ያያል።’”+  በመሆኑም ዮሐንስ በእሱ እጅ ለመጠመቅ የሚመጡትን ሰዎች እንዲህ ይላቸው ነበር፦ “እናንተ የእፉኝት ልጆች፣ ከሚመጣው ቁጣ እንድትሸሹ ያስጠነቀቃችሁ ማን ነው?+  እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፍሩ። ‘እኛ እኮ አባታችን አብርሃም ነው’ እያላችሁ ራሳችሁን አታጽናኑ። አምላክ ለአብርሃም ከእነዚህ ድንጋዮች ልጆች ማስነሳት እንደማይሳነው ልነግራችሁ እወዳለሁ።  እንዲያውም መጥረቢያው ዛፎቹ ሥር ተቀምጧል። ስለዚህ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ሁሉ ተቆርጦ እሳት ውስጥ ይጣላል።”+ 10  በዚህ ጊዜ ሕዝቡ “ታዲያ ምን ብናደርግ ይሻላል?” ብለው ይጠይቁት ነበር። 11  እሱም መልሶ “ሁለት ልብስ* ያለው አንዱን ምንም ለሌለው ይስጥ፤ ምግብ ያለውም እንዲሁ ያድርግ” አላቸው።+ 12  ቀረጥ ሰብሳቢዎች እንኳ ሳይቀሩ ለመጠመቅ+ ወደ እሱ መጥተው “መምህር፣ ምን እናድርግ?” አሉት። 13  እሱም “ከተተመነው ቀረጥ በላይ አትጠይቁ”* አላቸው።+ 14  ወታደሮች ደግሞ “እኛስ ምን እናድርግ?” ብለው ይጠይቁት ነበር። እሱም “በማንም ላይ ግፍ አትሥሩ* ወይም ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፤+ ከዚህ ይልቅ ባላችሁ መተዳደሪያ* ረክታችሁ ኑሩ” አላቸው። 15  ሕዝቡ ክርስቶስን ይጠባበቁ ስለነበር “ይህ ሰው ክርስቶስ ይሆን?” እያሉ ሁሉም በልባቸው ስለ ዮሐንስ ያስቡ ነበር።+ 16  ዮሐንስ ለሁሉም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ሆኖም ከእኔ የሚበረታ የሚመጣ ሲሆን እኔ የጫማውን ማሰሪያ እንኳ ለመፍታት አልበቃም።+ እሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል።+ 17  አውድማውን ፈጽሞ ለማጥራትና ስንዴውን ወደ ጎተራ ለማስገባት ላይዳውን* በእጁ ይዟል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” 18  በተጨማሪም ዮሐንስ በተለያዩ መንገዶች ምክር በመስጠት ለሕዝቡ ምሥራች ማብሰሩን ቀጠለ። 19  ሆኖም የአውራጃ ገዢ የሆነው ሄሮድስ የወንድሙ ሚስት በሆነችው በሄሮድያዳ ምክንያትና በሠራቸው ሌሎች ክፉ ድርጊቶች የተነሳ ዮሐንስ ስለወቀሰው 20  በክፋት ላይ ክፋት በመጨመር ዮሐንስን ወህኒ ቤት አስገባው።+ 21  ሕዝቡም ሁሉ እየተጠመቁ በነበረ ጊዜ ኢየሱስም ተጠመቀ።+ እየጸለየም ሳለ ሰማይ ተከፈተ፤+ 22  መንፈስ ቅዱስም አካላዊ ቅርጽ ይዞ በርግብ መልክ በእሱ ላይ ወረደ፤ ከዚያም “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ።+ 23  ኢየሱስ+ ሥራውን ሲጀምር 30 ዓመት ገደማ ሆኖት ነበር፤+ ሕዝቡም የዮሴፍ ልጅ+ እንደሆነ አድርገው ያስቡ ነበር፤ዮሴፍ የሄሊ ልጅ፣ 24  ሄሊ የማታት ልጅ፣ማታት የሌዊ ልጅ፣ሌዊ የሚልኪ ልጅ፣ሚልኪ የያና ልጅ፣ያና የዮሴፍ ልጅ፣ 25  ዮሴፍ የማታትዩ ልጅ፣ማታትዩ የአሞጽ ልጅ፣አሞጽ የናሆም ልጅ፣ናሆም የኤስሊ ልጅ፣ኤስሊ የናጌ ልጅ፣ 26  ናጌ የማአት ልጅ፣ማአት የማታትዩ ልጅ፣ማታትዩ የሴሜይ ልጅ፣ሴሜይ የዮሴክ ልጅ፣ዮሴክ የዮዳ ልጅ፣ 27  ዮዳ የዮናን ልጅ፣ዮናን የሬስ ልጅ፣ሬስ የዘሩባቤል ልጅ፣+ዘሩባቤል የሰላትያል ልጅ፣+ሰላትያል የኔሪ ልጅ፣ 28  ኔሪ የሚልኪ ልጅ፣ሚልኪ የሐዲ ልጅ፣ሐዲ የቆሳም ልጅ፣ቆሳም የኤልሞዳም ልጅ፣ኤልሞዳም የኤር ልጅ፣ 29  ኤር የኢየሱስ* ልጅ፣ኢየሱስ የኤሊዔዘር ልጅ፣ኤሊዔዘር የዮሪም ልጅ፣ዮሪም የማታት ልጅ፣ማታት የሌዊ ልጅ፣ 30  ሌዊ የሲምዖን ልጅ፣ሲምዖን የይሁዳ ልጅ፣ይሁዳ የዮሴፍ ልጅ፣ዮሴፍ የዮናም ልጅ፣ዮናም የኤልያቄም ልጅ፣ 31  ኤልያቄም የሜልያ ልጅ፣ሜልያ የሜና ልጅ፣ሜና የማጣታ ልጅ፣ማጣታ የናታን ልጅ፣+ናታን የዳዊት ልጅ፣+ 32  ዳዊት የእሴይ ልጅ፣+እሴይ የኢዮቤድ ልጅ፣+ኢዮቤድ የቦዔዝ ልጅ፣+ቦዔዝ የሰልሞን ልጅ፣+ሰልሞን የነአሶን ልጅ፣+ 33  ነአሶን የአሚናዳብ ልጅ፣አሚናዳብ የአርናይ ልጅ፣አርናይ የኤስሮን ልጅ፣ኤስሮን የፋሬስ ልጅ፣+ፋሬስ የይሁዳ ልጅ፣+ 34  ይሁዳ የያዕቆብ ልጅ፣+ያዕቆብ የይስሐቅ ልጅ፣+ይስሐቅ የአብርሃም ልጅ፣+አብርሃም የታራ ልጅ፣+ታራ የናኮር ልጅ፣+ 35  ናኮር የሴሮህ ልጅ፣+ሴሮህ የረኡ ልጅ፣+ረኡ የፋሌቅ ልጅ፣+ፋሌቅ የኤቤር ልጅ፣+ኤቤር የሴሎም ልጅ፣+ 36  ሴሎም የቃይናን ልጅ፣ቃይናን የአርፋክስድ ልጅ፣+አርፋክስድ የሴም ልጅ፣+ሴም የኖኅ ልጅ፣+ኖኅ የላሜህ ልጅ፣+ 37  ላሜህ የማቱሳላ ልጅ፣+ማቱሳላ የሄኖክ ልጅ፣ሄኖክ የያሬድ ልጅ፣+ያሬድ የመላልኤል ልጅ፣+መላልኤል የቃይናን ልጅ፣+ 38  ቃይናን የሄኖስ ልጅ፣+ሄኖስ የሴት ልጅ፣+ሴት የአዳም ልጅ፣+አዳም የአምላክ ልጅ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “የአራተኛው ክፍል ገዢ።”
ሄሮድስ አንቲጳስን ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ሰውም።”
ወይም “አምላክ የሚያድንበትን መንገድ።”
ወይም “ትርፍ ልብስ።”
ወይም “አትሰብስቡ።”
ወይም “ማንንም አትንጠቁ።”
ወይም “ደሞዝ።”
እህልን ከገለባው ለመለየት የሚያገለግል ከእንጨት የሚሠራ እንደ አካፋ ያለ መሣሪያ ነው።
አንዳንድ በእጅ የተጻፉ ጥንታዊ ቅጂዎች “የዮሴ” ይላሉ።