የሉቃስ ወንጌል 22:1-71

  • ካህናት ኢየሱስን ለመግደል አሴሩ (1-6)

  • የመጨረሻውን ፋሲካ ለማክበር የተደረገ ዝግጅት (7-13)

  • የጌታ ራት ተቋቋመ (14-20)

  • ‘አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው ከእኔ ጋር በማዕድ ነው’ (21-23)

  • ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሚሆን ተከራከሩ (24-27)

  • ‘የመንግሥት ቃል ኪዳን’ (28-30)

  • ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ እንደሚክደው ተናገረ (31-34)

  • ዝግጁ የመሆን አስፈላጊነት፤ ሁለት ሰይፎች (35-38)

  • ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ያቀረበው ጸሎት (39-46)

  • ኢየሱስ ተያዘ (47-53)

  • ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደው (54-62)

  • ሰዎች በኢየሱስ ላይ አፌዙ (63-65)

  • በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ለፍርድ ቀረበ (66-71)

22  ፋሲካ የሚባለው የቂጣ* በዓል+ የሚከበርበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር።+  የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም ሕዝቡን ይፈሩ+ ስለነበር እሱን የሚገድሉበትን+ ከሁሉ የተሻለ መንገድ እየፈለጉ ነበር።  ከዚያም ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ሆኖ በተቆጠረውና አስቆሮቱ ተብሎ በሚጠራው በይሁዳ ሰይጣን ገባበት፤+  ይሁዳም ወደ ካህናት አለቆችና ወደ ቤተ መቅደሱ ሹሞች ሄዶ ኢየሱስን ለእነሱ አሳልፎ መስጠት ስለሚችልበት መንገድ ተነጋገረ።+  እነሱም በጉዳዩ ተደስተው የብር ገንዘብ* ሊሰጡት ተስማሙ።+  እሱም በዚህ ተስማምቶ ሕዝብ በሌለበት እሱን አሳልፎ መስጠት የሚችልበትን ምቹ አጋጣሚ ይፈልግ ጀመር።  የቂጣ በዓል የሚከበርበት ቀን ደረሰ፤ በዚህ ዕለት የፋሲካ መሥዋዕት ይቀርብ ነበር፤+  ስለዚህ ኢየሱስ “ሄዳችሁ ፋሲካን እንድንበላ አዘጋጁልን”+ ብሎ ጴጥሮስንና ዮሐንስን ላካቸው።  እነሱም “የት እንድናዘጋጅ ትፈልጋለህ?” አሉት። 10  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ወደ ከተማው ስትገቡ የውኃ እንስራ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ። እሱን ተከትላችሁ ወደሚገባበት ቤት ሂዱ።+ 11  የቤቱንም ባለቤት ‘መምህሩ “ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ፋሲካን የምበላበት የእንግዳ ማረፊያ የት ነው?” ብሎሃል’ በሉት። 12  ሰውየውም የተሰናዳ ሰፊ ሰገነት ያሳያችኋል፤ በዚያ አዘጋጁ።” 13  እነሱም ሄዱ፤ እንዳላቸውም ሆኖ አገኙት፤ ለፋሲካ በዓሉም ዝግጅት አደረጉ። 14  ሰዓቱ በደረሰ ጊዜም ከሐዋርያቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።+ 15  እንዲህም አላቸው፦ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር፤ 16  እላችኋለሁና፣ የዚህ ፋሲካ ትርጉም በአምላክ መንግሥት ፍጻሜውን እስኪያገኝ ድረስ ፋሲካን ዳግመኛ አልበላም።” 17  ከዚያም ጽዋ ተቀብሎ አምላክን ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንኩ፣ ይህን ጽዋ እየተቀባበላችሁ ጠጡ፤ 18  እላችኋለሁና፣ ከአሁን ጀምሮ የአምላክ መንግሥት እስኪመጣ ድረስ ከዚህ ወይን ዳግመኛ አልጠጣም።” 19  በተጨማሪም ቂጣ+ አንስቶ አመሰገነ፣ ከቆረሰውም በኋላ ሰጣቸውና “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠውን+ ሥጋዬን ያመለክታል።+ ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት”+ አላቸው። 20  በተጨማሪም ራት ከበሉ በኋላ ጽዋውን አንስቶ ልክ እንደዚሁ አደረገ፤ እንዲህም አለ፦ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ+ በሚፈሰው ደሜ+ አማካኝነት የሚመሠረተውን አዲሱን ቃል ኪዳን+ ያመለክታል። 21  “ነገር ግን አሳልፎ የሚሰጠኝ ሰው እጅ ከእኔ ጋር በማዕድ ነው።+ 22  እርግጥ የሰው ልጅ አስቀድሞ በተወሰነው መሠረት ይሄዳል፤+ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ግን ወዮለት!”+ 23  ስለዚህ ከመካከላቸው በእርግጥ ይህን የሚያደርገው ማን ሊሆን እንደሚችል እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ጀመር።+ 24  ደግሞም ‘ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?’ በሚል በመካከላቸው የጦፈ ክርክር ተነሳ።+ 25  እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “የአሕዛብ ነገሥታት በእነሱ ላይ ሥልጣናቸውን ያሳያሉ፤ እንዲሁም በሕዝባቸው ላይ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ።+ 26  እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ።+ ከዚህ ይልቅ ከእናንተ መካከል ታላቅ የሆነ እንደ ታናሽ ይሁን፤+ አመራር የሚሰጥም እንደ አገልጋይ ይሁን። 27  ለመሆኑ በማዕድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያገለግል ማን ይበልጣል? በማዕድ የተቀመጠው አይደለም? እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አገልጋይ ሆኜ ነው።+ 28  “ይሁን እንጂ እናንተ በፈተናዎቼ+ ከጎኔ ሳትለዩ ቆይታችኋል፤+ 29  አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ ሁሉ እኔም ከእናንተ ጋር ለመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤+ 30  ይኸውም በመንግሥቴ ከማዕዴ እንድትበሉና እንድትጠጡ+ እንዲሁም በዙፋን ተቀምጣችሁ+ በ12ቱ የእስራኤል ነገዶች ላይ እንድትፈርዱ ነው።+ 31  “ስምዖን፣ ስምዖን፣ ሰይጣን ሁላችሁንም እንደ ስንዴ ያበጥራችሁ ዘንድ ጥያቄ አቅርቧል።+ 32  እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ምልጃ አቀረብኩ፤+ አንተም በተመለስክ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።”+ 33  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ከአንተ ጋር ወደ ወህኒ ለመውረድም ሆነ ለመሞት ዝግጁ ነኝ” አለው።+ 34  እሱ ግን “ጴጥሮስ ሆይ፣ እውነት እልሃለሁ፣ ዛሬ ዶሮ ከመጮኹ በፊት፣ አላውቀውም ብለህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” አለው።+ 35  በተጨማሪም እንዲህ አላቸው፦ “ያለገንዘብ ኮሮጆ፣ ያለምግብ ከረጢትና ያለትርፍ ጫማ በላክኋችሁ ጊዜ+ የጎደለባችሁ ነገር ነበር?” እነሱም “ምንም አልጎደለብንም” አሉ። 36  በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “አሁን ግን የገንዘብ ኮሮጆ ያለው ኮሮጆውን ይያዝ፤ የምግብ ከረጢት ያለውም እንዲሁ፤ ሰይፍ የሌለው ደግሞ መደረቢያውን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። 37  ይህን የምላችሁ ‘ከዓመፀኞች ጋር ተቆጠረ’+ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ላይ መፈጸም ስላለበት ነው። ስለ እኔ የተነገረው ነገር ፍጻሜውን እያገኘ ነውና።”+ 38  እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ይኸው ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉት። እሱም “በቂ ነው” አላቸው። 39  ከዚያ ወጥቶም እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ተከተሉት።+ 40  እዚያም በደረሱ ጊዜ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” አላቸው።+ 41  እሱም የድንጋይ ውርወራ ያህል ከእነሱ በመራቅ ተንበርክኮ መጸለይ ጀመረ፤ 42  እንዲህም አለ፦ “አባት ሆይ፣ ፈቃድህ ከሆነ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ይሁንና የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።”+ 43  ከዚያም አንድ መልአክ ከሰማይ ተገልጦለት አበረታታው።+ 44  ሆኖም በከፍተኛ ጭንቀት ተውጦ ከበፊቱ ይበልጥ አጥብቆ መጸለዩን ቀጠለ፤+ ላቡም መሬት ላይ እንደሚንጠባጠብ ደም ሆኖ ነበር። 45  ከጸለየም በኋላ ወደ ደቀ መዛሙርቱ ሲሄድ ከሐዘን የተነሳ ደክሟቸው ስለነበር ሲያንቀላፉ አገኛቸው።+ 46  እሱም “ለምን ትተኛላችሁ? ተነሱ፤ ደግሞም ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” አላቸው።+ 47  ገና እየተናገረ ሳለ ብዙ ሰዎች መጡ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱ የሆነው ይሁዳ የተባለውም ሰው ይመራቸው ነበር፤ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ተጠጋ።+ 48  ኢየሱስ ግን “ይሁዳ፣ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህ?” አለው። 49  በዙሪያው የነበሩትም አዝማሚያውን ሲያዩ “ጌታ ሆይ፣ በሰይፍ እንምታቸው?” አሉት። 50  እንዲያውም ከመካከላቸው አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቆረጠው።+ 51  ኢየሱስ ግን መልሶ “ተዉ!” አለ። ጆሮውንም ዳሶ ፈወሰው። 52  ከዚያም ኢየሱስ እሱን ለመያዝ የመጡትን የካህናት አለቆች፣ የቤተ መቅደሱን ሹሞችና ሽማግሌዎች እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ መጣችሁ?+ 53   በየዕለቱ በቤተ መቅደስ አብሬያችሁ ሳለሁ+ እኔን ለመያዝ እጃችሁን አላነሳችሁብኝም።+ ይሁንና ይህ የእናንተ ሰዓትና ጨለማ የሚነግሥበት ሰዓት ነው።”+ 54  ከዚያም ሰዎቹ ይዘው ወሰዱትና+ ወደ ሊቀ ካህናቱ ቤት አመጡት፤ ጴጥሮስም በርቀት ይከተል ነበር።+ 55  በግቢው መካከል እሳት አንድደው አንድ ላይ ተቀምጠው ሳለ ጴጥሮስም ከእነሱ ጋር ተቀመጠ።+ 56  ይሁንና አንዲት አገልጋይ እሳቱ አጠገብ ተቀምጦ ሲሞቅ አየችውና ትኩር ብላ ከተመለከተችው በኋላ “ይህ ሰውም ከእሱ ጋር ነበር” አለች። 57   እሱ ግን “አንቺ ሴት፣ እኔ አላውቀውም” ሲል ካደ። 58  ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንድ ሌላ ሰው አየውና “አንተም ከእነሱ አንዱ ነህ” አለው። ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው፣ አይደለሁም” አለ።+ 59  አንድ ሰዓት ያህል ካለፈ በኋላ ደግሞ አንድ ሌላ ሰው “ይህ ሰው፣ የገሊላ ሰው ስለሆነ በእርግጥ ከእሱ ጋር ነበር!” በማለት አጥብቆ ይናገር ጀመር። 60  ጴጥሮስ ግን “አንተ ሰው፣ ምን እንደምታወራ አላውቅም” አለ። ገና እየተናገረም ሳለ ዶሮ ጮኸ። 61  በዚህ ጊዜ ጌታ ዞር ብሎ ጴጥሮስን ትክ ብሎ አየው፤ ጴጥሮስም “ዛሬ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ” በማለት ጌታ የተናገረውን ቃል አስታወሰ።+ 62  ከዚያም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ። 63  ኢየሱስን የያዙት ሰዎችም እየመቱት+ ያሾፉበት+ ጀመር፤ 64  ፊቱንም ከሸፈኑት በኋላ “እስቲ ትንቢት ተናገር! የመታህ ማን ነው?” እያሉ ይጠይቁት ነበር። 65  በእሱም ላይ ሌላ ብዙ የስድብ ቃል ይሰነዝሩ ነበር። 66  በነጋም ጊዜ የካህናት አለቆችንና ጸሐፍትን ጨምሮ የሕዝቡ ሽማግሌዎች ጉባኤ አንድ ላይ ተሰበሰበ፤+ ኢየሱስንም ወደ ሳንሄድሪን ሸንጎ አዳራሻቸው አምጥተው እንዲህ አሉት፦ 67  “አንተ ክርስቶስ ከሆንክ ንገረን።”+ እሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ብነግራችሁም እንኳ ፈጽሞ አታምኑም። 68  ብጠይቃችሁም አትመልሱም። 69  ያም ሆነ ይህ ከአሁን ጀምሮ የሰው ልጅ+ በኃያሉ አምላክ ቀኝ ይቀመጣል።”+ 70  በዚህ ጊዜ ሁሉም “ስለዚህ የአምላክ ልጅ ነህ ማለት ነው?” አሉት። እሱም “የአምላክ ልጅ መሆኔን እናንተው ራሳችሁ እየተናገራችሁ ነው” አላቸው። 71  እነሱም “ከዚህ በላይ ምን ማስረጃ ያስፈልገናል? እኛ ራሳችን ከገዛ አፉ ሰምተነዋል” አሉ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ገንዘብ።