ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ ሁለተኛው ደብዳቤ 9:1-15

  • ለጋሶች እንዲሆኑ የተሰጠ ማበረታቻ (1-15)

    • ‘አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል’ (7)

9  ለቅዱሳን የሚደረገውን አገልግሎት* በተመለከተ+ ልጽፍላችሁ አያስፈልግም፤  እርዳታ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆናችሁን አውቃለሁና፤ በመሆኑም “የአካይያ ወንድሞች ሌሎችን ለመርዳት ለአንድ ዓመት ያህል ዝግጁ ሆነው ሲጠባበቁ ቆይተዋል” ብዬ ለመቄዶንያ ወንድሞች በኩራት ተናግሬአለሁ፤ የእናንተ ቅንዓት ደግሞ አብዛኞቹን አነሳስቷል።  ይሁንና በዚህ ረገድ በእናንተ ላይ ያለን ትምክህት ከንቱ ሆኖ እንዳይቀር አስቀድሞ ስለ እናንተ እንደተናገርኩት ተዘጋጅታችሁ እንድትጠብቁ ወንድሞችን እልካለሁ።  አለዚያ የመቄዶንያ ወንድሞች ከእኔ ጋር መጥተው ዝግጁ ሳትሆኑ ቢያገኟችሁ፣ እናንተ ብቻ ሳትሆኑ እኛም በእናንተ በመተማመናችን እናፍራለን።  ስለዚህ ቀደም ሲል ልትሰጡ ቃል የገባችሁትን የልግስና ስጦታ አስቀድመው ያዘጋጁ ዘንድ ወንድሞች ቀደም ብለው ወደ እናንተ እንዲመጡ ማበረታታት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እንዲህ ከሆነ ስጦታው ተዘጋጅቶ ይጠብቀናል፤ ይህ ደግሞ ስጦታ የሰጣችሁት አስገድደናችሁ ሳይሆን በልግስና እንደሆነ ያሳያል።  ይሁንና ጥቂት የሚዘራ ሁሉ ጥቂት ያጭዳል፤ በብዛት የሚዘራ ሁሉ ደግሞ በብዛት ያጭዳል።+  አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ+ እያንዳንዱ ሰው ቅር እያለው* ወይም ተገዶ ሳይሆን በልቡ ያሰበውን ይስጥ።+  በተጨማሪም ምንጊዜም የሚያስፈልጋችሁ ነገር በበቂ ሁኔታ እንዲኖራችሁ እንዲሁም መልካም ሥራን ሁሉ ለመሥራት የሚያስችላችሁን ነገር በብዛት እንድታገኙ አምላክ ጸጋውን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል።+  (ይህም “በብዛት* አከፋፈለ፤ ለድሆችም ሰጠ። ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+ 10  እንግዲህ ለዘሪ ዘርን፣ ለመብል እህልን አትረፍርፎ የሚሰጠው እሱ የምትዘሩትን ዘር አትረፍርፎ ይሰጣችኋል፤ እንዲሁም የጽድቃችሁን ፍሬ ያበዛላችኋል።) 11  በሁሉም መንገድ በልግስና መስጠት እንድትችሉ አምላክ አትረፍርፎ ይባርካችኋል፤ እኛ በምናከናውነው ሥራ የተነሳ እንዲህ ያለው ልግስና ሰዎች ለአምላክ ምስጋና እንዲያቀርቡ ያነሳሳቸዋል፤ 12  ምክንያቱም ይህ የምታከናውኑት ሕዝባዊ አገልግሎት* ቅዱሳን የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በሚገባ እንዲሟሉላቸው+ ከማድረጉም በተጨማሪ በርካታ ሰዎች ለአምላክ ብዙ ምስጋና እንዲያቀርቡ ያደርጋል። 13  በዚህ የእርዳታ አገልግሎት አማካኝነት የሚያዩት ማስረጃ አምላክን እንዲያከብሩ ያደርጋቸዋል፤ ምክንያቱም እናንተ በይፋ ለምታውጁት ስለ ክርስቶስ ለሚገልጸው ምሥራች ተገዢዎች ናችሁ፤ እንዲሁም ለእነሱም ሆነ ለሁሉም በምታደርጉት መዋጮ ለጋሶች ናችሁ።+ 14  ደግሞም አምላክ ከሰጣችሁ የላቀ ጸጋ የተነሳ ስለ እናንተ ምልጃ እያቀረቡ ለእናንተ ያላቸውን ፍቅር ይገልጻሉ። 15  በቃላት ሊገለጽ ለማይችለው ነፃ ስጦታው አምላክ የተመሰገነ ይሁን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እርዳታ።”
ወይም “ያለፍላጎቱ።”
ወይም “በልግስና።”
ወይም “እርዳታ።”