የይሁዳ ደብዳቤ 1:1-25

  • ሰላምታ (1, 2)

  • ሐሰተኛ አስተማሪዎች ፍርድ ይጠብቃቸዋል (3-16)

    • ሚካኤል ከዲያብሎስ ጋር ተከራከረ (9)

    • ሄኖክ የተናገረው ትንቢት (14, 15)

  • ከአምላክ ፍቅር አትውጡ (17-23)

  • ለአምላክ ክብር ይሁን (24, 25)

 የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና የያዕቆብ+ ወንድም ከሆነው ከይሁዳ፣ ለተጠሩትና+ አባታችን በሆነው አምላክ ለተወደዱት እንዲሁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ይሆኑ ዘንድ ጥበቃ ለተደረገላቸው፦+  ምሕረት፣ ሰላምና ፍቅር ይብዛላችሁ።  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ሁላችንም ስለምናገኘው መዳን+ ልጽፍላችሁ እጅግ ጓጉቼ የነበረ ቢሆንም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለቅዱሳን ስለተሰጠው እምነት ብርቱ ተጋድሎ እንድታደርጉ+ ለማሳሰብ ልጽፍላችሁ ተገደድኩ።  ይህን ያደረግኩት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድሞ የተነገረላቸው አንዳንድ ሰዎች ሾልከው ስለገቡ ነው፤ እነዚህ ሰዎች ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው፣ በአምላካችን ጸጋ እያሳበቡ ማንአለብኝነት የሚንጸባረቅበት ድርጊት*+ የሚፈጽሙ እንዲሁም የዋጀንንና እሱ ብቻ ጌታችን* የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን የሚክዱ ናቸው።+  ምንም እንኳ ይህን ሁሉ አስቀድማችሁ በሚገባ ታውቁ የነበረ ቢሆንም ይሖዋ* ሕዝቡን ከግብፅ ምድር እንዳዳነ፣+ በኋላም እምነት ያላሳዩትን እንዳጠፋ ላስታውሳችሁ እወዳለሁ።+  በተጨማሪም መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ ያልጠበቁትንና ተገቢ የሆነውን የመኖሪያ ስፍራቸውን የተዉትን መላእክት+ በታላቁ ቀን ለሚፈጸምባቸው ፍርድ በዘላለም እስራት በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አቆይቷቸዋል።+  በተመሳሳይም ሰዶምና ገሞራ እንዲሁም በዙሪያቸው የነበሩ ከተሞች ራሳቸውን ልቅ ለሆነ የፆታ ብልግና* አሳልፈው የሰጡ ከመሆኑም ሌላ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ የሥጋ ፍላጎታቸውን ያሳድዱ ነበር፤+ በመሆኑም በዘላለም እሳት ፍርድ ተቀጥተው ለእኛ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ሆነዋል።+  ያም ሆኖ ግን እነዚህ ሕልም አላሚዎች ሥጋን ያረክሳሉ፤ ሥልጣንን ይንቃሉ፤ የተከበሩትንም ይሳደባሉ።+  ይሁንና የመላእክት አለቃ+ ሚካኤል+ የሙሴን ሥጋ+ በተመለከተ ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ የስድብ ቃል በመናገር ሊፈርድበት አልደፈረም፤+ ከዚህ ይልቅ “ይሖዋ* ይገሥጽህ” አለው።+ 10  እነዚህ ሰዎች ግን ስለማያውቁት ነገር ሁሉ ትችት ይሰነዝራሉ።+ ደግሞም አእምሮ እንደሌላቸው እንስሳት፣+ በደመ ነፍስ የሚረዷቸውን ነገሮች ሁሉ ሲያደርጉ የራሳቸውን ሥነ ምግባር ያበላሻሉ። 11  በቃየን+ መንገድ ስለሄዱ፣ ለጥቅም ሲሉ የበለዓምን+ የተሳሳተ መንገድ በጭፍን ስለተከተሉና በቆሬ+ የዓመፅ ንግግር+ ስለጠፉ ወዮላቸው! 12  እነዚህ ሰዎች ፍቅራችሁን ለመግለጽ በምታዘጋጁት ግብዣ ላይ ተገኝተው አብረዋችሁ ሲመገቡ ልክ በባሕር ውስጥ እንደተደበቀ ዓለት+ ከመሆናቸውም ሌላ ያላንዳች ኀፍረት ለሆዳቸው ብቻ የሚያስቡ እረኞች ናቸው፤+ በነፋስ ወዲያና ወዲህ የሚነዱ ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች+ እንዲሁም በመከር ጊዜ ፍሬ የማይገኝባቸው፣ ሁለት ጊዜ የሞቱና* ከሥራቸው የተነቀሉ ዛፎች ናቸው፤ 13  አረፋ እንደሚደፍቅ ኃይለኛ የባሕር ማዕበል አሳፋሪ ድርጊታቸውን ይገልጣሉ፤+ ለዘላለም ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚጣሉ ተንከራታች ከዋክብት ናቸው።+ 14  ከአዳም ጀምሮ ሰባተኛ ትውልድ የሆነው ሄኖክ+ ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ሲል ተንብዮአል፦ “እነሆ! ይሖዋ* ከአእላፋት* ቅዱሳን መላእክቱ ጋር መጥቷል፤+ 15  የመጣውም በሁሉ ላይ ለመፍረድ፣+ ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ሰዎች ለአምላክ አክብሮት በጎደለው መንገድ የፈጸሙትን ክፉ ድርጊትና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸው ኃጢአተኞች በእሱ ላይ የተናገሩትን ክፉ ቃል ለማጋለጥ ነው።”+ 16  እነዚህ ሰዎች የሚያጉረመርሙና+ ኑሯቸውን የሚያማርሩ እንዲሁም የራሳቸውን ምኞት የሚከተሉ ናቸው፤+ ጉራ መንዛት ይወዳሉ፤ ለጥቅማቸው ሲሉም ሌሎችን ይክባሉ።+ 17  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ ግን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አስቀድመው የነገሯችሁን ቃል* አስታውሱ፤ 18  እነሱ “በመጨረሻው ዘመን መጥፎ ምኞታቸውን የሚከተሉ ዘባቾች ይነሳሉ” ይሏችሁ ነበር።+ 19  እነዚህ ሰዎች ክፍፍል የሚፈጥሩ፣+ የእንስሳ ባሕርይ ያላቸውና* መንፈሳዊ ያልሆኑ* ናቸው። 20  የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ እናንተ ግን እጅግ ቅዱስ በሆነው እምነታችሁ ላይ ራሳችሁን ገንቡ፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ጸልዩ፤+ 21  ይህን የምታደርጉት የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝላችሁን+ የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት እየተጠባበቃችሁ ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ እንድትኖሩ ነው።+ 22  በተጨማሪም ጥርጣሬ ላደረባቸው+ ምሕረት አሳዩ፤+ 23  ከእሳት ነጥቃችሁ በማውጣት አድኗቸው።+ ለሌሎች ምሕረት ማሳየታችሁንም ቀጥሉ፤ ሆኖም ይህን ስታደርጉ ለራሳችሁ መጠንቀቅና በሥጋ ሥራ ያደፈውን ልብሳቸውን መጥላት ይኖርባችኋል።+ 24  እንዳትሰናከሉ ሊጠብቃችሁና ነቀፋ የሌለባችሁ አድርጎ በታላቅ ደስታ፣ በክብሩ ፊት ሊያቆማችሁ ለሚችለው፣+ 25  አዳኛችን ለሆነው ብቸኛው አምላክ ከዘመናት ሁሉ በፊት፣ አሁንና እስከ ዘላለም በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ክብር፣ ግርማ፣ ኃይልና ሥልጣን ይሁን። አሜን።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ባለቤታችን።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ሙሉ በሙሉ የሞቱና።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ከአሥር ሺዎች።”
ወይም “አስቀድመው የተነበዩአቸውን ነገሮች።”
ወይም “ሥጋዊ ሰዎችና።”
ቃል በቃል “መንፈስ የሌላቸው።”