የሐዋርያት ሥራ 7:1-60

  • እስጢፋኖስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት ያቀረበው ንግግር (1-53)

    • የቤተሰብ ራሶች ዘመን (2-16)

    • የሙሴ አመራር፤ የእስራኤል የጣዖት አምልኮ (17-43)

    • “አምላክ የሰው እጅ በሠራው ቤት አይኖርም” (44-50)

  • እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወገረ (54-60)

7  ሊቀ ካህናቱም “ይህ የተባለው ነገር ልክ ነው?” አለው።  እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፣ ስሙ። አባታችን አብርሃም በካራን መኖር ከመጀመሩ በፊት በሜሶጶጣሚያ ሳለ የክብር አምላክ ተገለጠለት፤+  እንዲህም አለው፦ ‘ከአገርህ ወጥተህ፣ ከዘመዶችህም ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ።’+  እሱም ከከለዳውያን አገር ወጥቶ በካራን መኖር ጀመረ። አባቱ ከሞተ+ በኋላ ደግሞ አምላክ ከዚያ ተነስቶ አሁን እናንተ ወደምትኖሩበት ወደዚህ ምድር እንዲዛወር አደረገው።+  ሆኖም በወቅቱ በዚህ ምድር ምንም ርስት፣ ሌላው ቀርቶ እግሩን ሊያሳርፍ የሚችልበት መሬት እንኳ አልሰጠውም፤ ይሁንና ገና ልጅ ሳይኖረው ለእሱም ሆነ ከእሱ በኋላ ለዘሮቹ ምድሪቱን ርስት አድርጎ እንደሚሰጣቸው ቃል ገባለት።+  ከዚህም በላይ አምላክ፣ ዘሮቹ በሰው አገር ባዕዳን ሆነው እንደሚኖሩ እንዲሁም የአገሩ ሰዎች ለ400 ዓመት በባርነት እንደሚገዟቸውና እንደሚያጎሳቁሏቸው* ነገረው።+  ደግሞም አምላክ ‘በባርነት የሚገዛቸውን ብሔር እፈርድበታለሁ፤+ ከዚያም በኋላ ከነበሩበት አገር ወጥተው በዚህ ስፍራ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርቡልኛል’ ሲል ተናግሯል።+  “በተጨማሪም አምላክ ከእሱ ጋር የግርዘት ቃል ኪዳን አደረገ፤+ አብርሃምም ይስሐቅን ወለደ፤+ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው።+ ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤* ያዕቆብም 12ቱን የቤተሰብ ራሶች* ወለደ።  የቤተሰብ ራሶቹም በዮሴፍ ቀንተው+ ወደ ግብፅ ሸጡት።+ ሆኖም አምላክ ከእሱ ጋር ነበር፤+ 10  ከመከራውም ሁሉ ታደገው፤ በግብፅ ንጉሥ በፈርዖንም ፊት ሞገስና ጥበብ አጎናጸፈው። ፈርዖንም በግብፅና በቤቱ ሁሉ ላይ ገዢ አድርጎ ሾመው።+ 11  ይሁንና በግብፅና በከነአን አገር ሁሉ ታላቅ መከራ ያስከተለ ረሃብ ተከሰተ፤ አባቶቻችንም የሚበሉት ነገር አጡ።+ 12  ሆኖም ያዕቆብ በግብፅ እህል መኖሩን ሲሰማ አባቶቻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደዚያ ላካቸው።+ 13  ለሁለተኛ ጊዜ ሲሄዱ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ነገራቸው፤ ፈርዖንም ስለ ዮሴፍ ቤተሰብ ሰማ።+ 14  ስለዚህ ዮሴፍ መልእክት ልኮ አባቱን ያዕቆብንና ዘመዶቹን ሁሉ ከዚያ አገር አስጠራ፤+ እነሱም በአጠቃላይ 75 ሰዎች* ነበሩ።+ 15  ያዕቆብም ወደ ግብፅ ወረደ፤+ በዚያም ሞተ፤+ አባቶቻችንም በዚያ ሞቱ።+ 16  አፅማቸውም ወደ ሴኬም ተወስዶ አብርሃም በሴኬም ከኤሞር ልጆች በብር ገንዘብ* በገዛው መቃብር ውስጥ ተቀበረ።+ 17  “አምላክ ለአብርሃም የተናገረው የተስፋ ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ሲቃረብ ሕዝባችን በግብፅ እየበዛና እየተበራከተ ሄደ፤ 18  ይህም የሆነው ዮሴፍን የማያውቅ ሌላ ንጉሥ በግብፅ እስከተነሳበት ጊዜ ድረስ ነው።+ 19  ይህ ንጉሥ በወገኖቻችን ላይ ተንኮል በመሸረብ ሕፃናት ልጆቻቸውን ለሞት አሳልፈው እንዲሰጡ አባቶቻችንን አስገደዳቸው።+ 20  በዚህ ወቅት በአምላክ ፊት እንኳ ሳይቀር እጅግ ውብ የነበረው ሙሴ ተወለደ። በአባቱም ቤት ሦስት ወር በእንክብካቤ ኖረ።*+ 21  በተጣለ ጊዜ+ ግን የፈርዖን ልጅ ወስዳ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋ አሳደገችው።+ 22  ሙሴም የግብፃውያንን ጥበብ ሁሉ ተማረ። በንግግሩና በተግባሩም ብርቱ ሆነ።+ 23  “ሙሴ 40 ዓመት በሞላው ጊዜ ወንድሞቹ የሆኑት የእስራኤል ልጆች ያሉበትን ሁኔታ ለማየት* በልቡ አሰበ።*+ 24  እሱም አንድ ግብፃዊ በአንድ እስራኤላዊ ላይ በደል ሲፈጽም አየ፤ ለእስራኤላዊውም አግዞ ግብፃዊውን በመግደል ተበቀለለት። 25  ወንድሞቹ አምላክ በእሱ አማካኝነት እንደሚያድናቸው የሚያስተውሉ መስሎት ነበር፤ እነሱ ግን ይህን አላስተዋሉም። 26  በማግስቱም እርስ በርሳቸው ሲጣሉ አገኛቸው፤ እሱም ‘ሰዎች፣ እናንተ እኮ ወንድማማቾች ናችሁ። ለምን እርስ በርሳችሁ ትጣላላችሁ?’ በማለት ሊያስታርቃቸው ሞከረ። 27  ይሁንና በባልንጀራው ላይ ጥቃት እየፈጸመ የነበረው ሰው ገፈተረውና እንዲህ አለው፦ ‘አንተን በእኛ ላይ ማን ገዢና ፈራጅ አደረገህ? 28  ትናንት ግብፃዊውን እንደገደልከው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋለህ እንዴ?’ 29  ሙሴ ይህን ሲሰማ ሸሽቶ በምድያም አገር ባዕድ ሆኖ ኖረ፤ በዚያም ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ።+ 30  “ከ40 ዓመትም በኋላ በሲና ተራራ አቅራቢያ በሚገኝ ምድረ በዳ፣ በሚነድ ቁጥቋጦ ነበልባል ውስጥ አንድ መልአክ ተገለጠለት።+ 31  ሙሴም ባየው ነገር ተደነቀ። ሆኖም ሁኔታውን ለማጣራት ወደዚያ ሲቀርብ የይሖዋ* ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማ፦ 32  ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነኝ።’+ በዚህ ጊዜ ሙሴ ይንቀጠቀጥ ጀመር፤ ሁኔታውን ይበልጥ ለማጣራትም አልደፈረም። 33  ይሖዋም* እንዲህ አለው፦ ‘የቆምክበት ስፍራ ቅዱስ መሬት ስለሆነ ጫማህን አውልቅ። 34  በግብፅ ባለው ሕዝቤ ላይ እየደረሰ ያለውን ጭቆና በእርግጥ አይቻለሁ፤ የጭንቅ ጩኸታቸውንም ሰምቻለሁ፤+ ልታደጋቸውም ወርጃለሁ። አሁንም ና፣ ወደ ግብፅ እልክሃለሁ።’ 35  ‘አንተን ማን ገዢና ፈራጅ አደረገህ?’ ብለው የተቃወሙትን ይህንኑ ሙሴን+ አምላክ በቁጥቋጦው ውስጥ በተገለጠለት መልአክ አማካኝነት ገዢና ነፃ አውጪ አድርጎ ላከው።+ 36  ይህ ሰው በግብፅ፣ በቀይ ባሕርና+ በምድረ በዳ ለ40 ዓመት+ ድንቅ ነገሮችንና ተአምራዊ ምልክቶችን በመፈጸም+ ከግብፅ እየመራ አወጣቸው።+ 37  “‘አምላክ ከወንድሞቻችሁ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳላችኋል’ ብሎ ለእስራኤል ልጆች የተናገረው ይኸው ሙሴ ነው።+ 38  በሲና ተራራ ካነጋገረው መልአክና+ ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በጉባኤው መካከል የነበረው እሱ ነው፤+ ደግሞም ለእኛ ይሰጠን ዘንድ ሕያው የሆነውን ቅዱስ ቃል ተቀበለ።+ 39  አባቶቻችን ለእሱ ለመታዘዝ ፈቃደኞች አልሆኑም፤ ከዚህ ይልቅ እሱን በመቃወም በልባቸው ወደ ግብፅ ተመለሱ፤+ 40  አሮንንም ‘ፊት ፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን። ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት አናውቅምና’ አሉት።+ 41  ስለሆነም በዚያን ጊዜ ጥጃ ሠርተው ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ይደሰቱ ጀመር።+ 42  በዚህ ጊዜ አምላክ ፊቱን ከእነሱ አዞረ፤ በነቢያትም መጻሕፍት እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት የሰማይ ሠራዊትን እንዲያመልኩ ተዋቸው፦+ ‘የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ለ40 ዓመት በምድረ በዳ መባና መሥዋዕት ያቀረባችሁት ለእኔ ነበር? 43  ይልቁንም ልታመልኳቸው የሠራችኋቸውን ምስሎች ይኸውም የሞሎክን+ ድንኳንና ሮምፋ የሚባለውን አምላክ ኮከብ ተሸክማችሁ ተጓዛችሁ። ስለዚህ ከባቢሎን ወዲያ እንድትሰደዱ አደርጋችኋለሁ።’+ 44  “አባቶቻችን በምድረ በዳ የምሥክሩ ድንኳን ነበራቸው፤ ይህ ድንኳን የተሠራው አምላክ ሙሴን ባነጋገረው ወቅት በሰጠው ትእዛዝና ባሳየው ንድፍ መሠረት ነበር።+ 45  አባቶቻችንም ይህን ድንኳን በመረከብ ከኢያሱ ጋር ሆነው አምላክ ከአባቶቻችን ፊት ያባረራቸው ብሔራት ይኖሩበት ወደነበረው ምድር+ ይዘውት ገቡ።+ እስከ ዳዊት ዘመን ድረስም በዚህ ምድር ቆየ። 46  ዳዊትም በአምላክ ፊት ሞገስ አገኘ፤ ለያዕቆብ አምላክም መኖሪያ ስፍራ የማዘጋጀት መብት እንዲሰጠው ጠየቀ።+ 47  ይሁን እንጂ ቤት የሠራለት ሰለሞን ነበር።+ 48  ሆኖም ልዑሉ አምላክ የሰው እጅ በሠራው ቤት አይኖርም፤+ ይህም ነቢዩ እንዲህ ሲል በተናገረው መሠረት ነው፦ 49  ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤+ ምድር ደግሞ የእግሬ ማሳረፊያ ናት።+ ለእኔ የምትሠሩልኝ ምን ዓይነት ቤት ነው? ይላል ይሖዋ።* ወይስ የማርፍበት ቦታ የት ነው? 50  እነዚህን ነገሮች ሁሉ የሠራው እጄ አይደለም?’+ 51  “እናንተ ግትሮች፣ ልባችሁና ጆሯችሁ ያልተገረዘ፣ ሁልጊዜ መንፈስ ቅዱስን እንደተቃወማችሁ ነው፤ አባቶቻችሁ እንዳደረጉት እናንተም እንዲሁ ታደርጋላችሁ።+ 52  ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ስደት ያላደረሱበት ማን አለ?+ አዎ፣ እነሱ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገድለዋቸዋል፤+ እናንተም አሁን ይህን ጻድቁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ደግሞም ገደላችሁት፤+ 53   በመላእክት አማካኝነት የተላለፈውን ሕግ ተቀበላችሁ፤+ ነገር ግን አልጠበቃችሁትም።” 54  እነሱም ይህን ሲሰሙ ልባቸው በንዴት በገነ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጩበት ጀመር። 55  እሱ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ትኩር ብሎ ወደ ሰማይ ሲመለከት የአምላክን ክብር እንዲሁም ኢየሱስ በአምላክ ቀኝ ቆሞ አየ፤+ 56  ከዚያም “እነሆ፣ ሰማያት ተከፍተው የሰው ልጅም+ በአምላክ ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።+ 57   በዚህ ጊዜ በኃይል እየጮኹ ጆሯቸውን በእጃቸው ደፍነው በአንድነት ወደ እሱ ሮጡ። 58  ይዘውት ከከተማው ውጭ ካስወጡት በኋላ በድንጋይ ይወግሩት ጀመር።+ ምሥክሮቹም+ መደረቢያቸውን ሳኦል በተባለ ወጣት እግር አጠገብ አስቀመጡ።+ 59  እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ መንፈሴን ተቀበል” ብሎ ተማጸነ። 60  ከዚያም ተንበርክኮ በታላቅ ድምፅ “ይሖዋ* ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው” ብሎ ጮኸ።+ ይህን ከተናገረም በኋላ በሞት አንቀላፋ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “እንደሚያንገላቷቸው።”
“ይስሐቅም በያዕቆብ ላይ እንዲሁ አደረገ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ፓትሪያርኮች።”
ወይም “ነፍሳት።” ዘፍ 46:20, 27 ላይ የሚገኙትን የግርጌ ማስታወሻዎች ተመልከት።
ብር ከተባለው ማዕድን የተሠራ ገንዘብ።
ወይም “ሦስት ወር አደገ።”
ወይም “ለማጣራት።”
ወይም “ለማየት ወሰነ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።