የሐዋርያት ሥራ 10:1-48

  • ቆርኔሌዎስ ያየው ራእይ (1-8)

  • ጴጥሮስ ንጹሕ የሆኑ እንስሳት በራእይ አየ (9-16)

  • ጴጥሮስ ወደ ቆርኔሌዎስ ሄደ (17-33)

  • ጴጥሮስ ምሥራቹን ለአሕዛብ አወጀ (34-43)

    • አምላክ አያዳላም’ (34, 35)

  • አሕዛብ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ተጠመቁ (44-48)

10  በቂሳርያ “የጣሊያን ክፍለ ጦር”* ተብሎ በሚጠራ ሠራዊት ውስጥ ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ የጦር መኮንን* ነበር።  እሱም ከመላው ቤተሰቡ ጋር ለአምላክ ያደረና ፈሪሃ አምላክ የነበረው ሰው ሲሆን ለሰዎች ምጽዋት የሚሰጥና ዘወትር ወደ አምላክ የሚማልድ ሰው ነበር።  ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት+ ገደማ አንድ የአምላክ መልአክ ወደ እሱ ሲመጣ በራእይ በግልጽ አየ፤ መልአኩም “ቆርኔሌዎስ!” አለው።  ቆርኔሌዎስም በድንጋጤ ትኩር ብሎ እያየው “ጌታ ሆይ፣ ምንድን ነው?” በማለት ጠየቀው። እሱም እንዲህ አለው፦ “ጸሎትህና ምጽዋትህ በአምላክ ፊት መታሰቢያ እንዲሆን አርጓል።+  ስለዚህ አሁን ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን አስጠራው።  ይህ ሰው፣ ቤቱ በባሕሩ አጠገብ በሚገኘው በቆዳ ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት አርፏል።”  ያነጋገረው መልአክ ተለይቶት እንደሄደ ከአገልጋዮቹ ሁለቱን እንዲሁም እሱን በቅርብ ከሚያገለግሉት ወታደሮች መካከል ለአምላክ ያደረ አንድ ወታደር ጠራ፤  የሆነውንም ነገር ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ኢዮጴ ላካቸው።  በማግስቱም የተላኩት ሰዎች ተጉዘው ወደ ከተማዋ ሲቃረቡ ጴጥሮስ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ገደማ ሊጸልይ ወደ ሰገነት ወጣ። 10  ይሁን እንጂ በጣም ከመራቡ የተነሳ መብላት ፈለገ። ምግብ እየተዘጋጀ ሳለም ሰመመን ውስጥ ገባ፤+ 11  ሰማይም ተከፍቶ ትልቅ ጨርቅ የሚመስል ነገር በአራቱም ጫፍ ተይዞ ወደ ምድር ሲወርድ አየ፤ 12  በላዩም የተለያዩ በምድር ላይ የሚኖሩ አራት እግር ያላቸው እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታት እንዲሁም የሰማይ ወፎች ነበሩ። 13  ከዚያም አንድ ድምፅ “ጴጥሮስ፣ ተነሳና አርደህ ብላ!” አለው። 14  ጴጥሮስ ግን “ጌታ ሆይ፣ በጭራሽ፤ ምክንያቱም እኔ ንጹሕ ያልሆነና የረከሰ ነገር በልቼ አላውቅም” አለ።+ 15  ያም ድምፅ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ “አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው” አለው። 16  ይህም ለሦስተኛ ጊዜ ተደገመ፤ ወዲያውኑም ጨርቅ የሚመስለው ነገር ወደ ሰማይ ተወሰደ። 17  ጴጥሮስ ‘የራእዩ ትርጉም ምን ይሆን’ በማለት በጣም ግራ ተጋብቶ እያለ ቆርኔሌዎስ የላካቸው ሰዎች የስምዖንን ቤት አጠያይቀው መጡና የውጭው በር ላይ ቆሙ።+ 18  ከዚያም ተጣርተው ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራው ስምዖን በዚያ በእንግድነት አርፎ እንደሆነ ጠየቁ። 19  ጴጥሮስ ያየውን ራእይ በሐሳቡ እያወጣና እያወረደ ሳለ መንፈስ+ እንዲህ አለው፦ “እነሆ፣ ሦስት ሰዎች ይፈልጉሃል። 20  ስለዚህ ተነስተህ ወደ ታች ውረድ፤ የላክኋቸው እኔ ስለሆንኩ ምንም ሳትጠራጠር አብረሃቸው ሂድ።” 21  ጴጥሮስም ሰዎቹ ወዳሉበት ወርዶ “የምትፈልጉት ሰው እኔ ነኝ። ወደዚህ የመጣችሁት ለምንድን ነው?” አላቸው። 22  እነሱም እንዲህ አሉ፦ “በአይሁዳውያን ሁሉ የተመሠከረለት ቆርኔሌዎስ+ የተባለ ጻድቅና አምላክን የሚፈራ አንድ የጦር መኮንን፣ ወደ አንተ መልእክተኞች ልኮ ወደ ቤቱ እንዲያስመጣህና የምትለውን ነገር እንዲሰማ አንድ ቅዱስ መልአክ መለኮታዊ መመሪያ ሰጥቶታል።” 23  እሱም ወደ ቤት አስገብቶ አስተናገዳቸው። በማግስቱም ተነስቶ ከእነሱ ጋር ሄደ፤ በኢዮጴ ያሉ አንዳንድ ወንድሞችም አብረውት ሄዱ። 24  በሚቀጥለው ቀንም ወደ ቂሳርያ ገባ። ቆርኔሌዎስም ዘመዶቹንና የቅርብ ወዳጆቹን ሰብስቦ እየጠበቃቸው ነበር። 25  ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተቀበለውና እግሩ ላይ ወድቆ ሰገደለት።* 26  ጴጥሮስ ግን “ተነስ፣ እኔም እንደ አንተው ሰው ነኝ” ብሎ አስነሳው።+ 27  ከእሱ ጋር እየተነጋገረ ወደ ውስጥ ሲገባም ብዙ ሰዎች ተሰብስበው አገኘ። 28  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “አንድ አይሁዳዊ ከሌላ ዘር ጋር ይወዳጅ ወይም ይቀራረብ ዘንድ ሕጉ እንደማይፈቅድ በሚገባ ታውቃላችሁ፤+ ሆኖም አምላክ ማንንም ሰው ንጹሕ ያልሆነ ወይም ርኩስ ማለት እንደማይገባኝ ገልጦልኛል።+ 29  በመሆኑም በተጠራሁ ጊዜ ምንም ሳላንገራግር መጣሁ። ስለዚህ ለምን እንዳስጠራችሁኝ ማወቅ እፈልጋለሁ።” 30  ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለ፦ “ከአራት ቀን በፊት በዚሁ ሰዓት ይኸውም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በቤቴ ሆኜ እየጸለይኩ ሳለ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው ድንገት ፊቴ ቆሞ 31  እንዲህ አለኝ፦ ‘ቆርኔሌዎስ፣ ጸሎትህ ተሰምቶልሃል፤ ምጽዋትህም በአምላክ ፊት ታስቦልሃል። 32  ስለዚህ ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ ተብሎ የሚጠራውን ስምዖንን አስጠራው። ይህ ሰው፣ ቤቱ በባሕሩ አጠገብ በሚገኘው በቆዳ ፋቂው በስምዖን ቤት በእንግድነት አርፏል።’+ 33  እኔም ወዲያውኑ ሰዎች ላክሁብህ፤ አንተም በመምጣትህ መልካም አድርገሃል። ስለዚህ አሁን እኛ ይሖዋ* እንድትናገር ያዘዘህን ነገር ሁሉ ለመስማት ይኸው ሁላችንም በአምላክ ፊት ተገኝተናል።” 34  በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መናገር ጀመረ፦ “እነሆ፣ አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ፤+ 35  ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።+ 36  አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእስራኤል ልጆች የሰላም ምሥራች ለማወጅ ቃሉን ላከላቸው፤+ ይህም ምሥራች ኢየሱስ የሁሉ ጌታ+ እንደሆነ የሚገልጽ ነው። 37  ዮሐንስ ስለ ጥምቀት ከሰበከ በኋላ ከገሊላ አንስቶ በመላው ይሁዳ ይወራ ስለነበረው ጉዳይ ታውቃላችሁ፤+ 38  የተወራውም ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ነው። አምላክ በመንፈስ ቅዱስ ቀባው፤+ ደግሞም ኃይል ሰጠው፤ ኢየሱስም አምላክ ከእሱ ጋር ስለነበር መልካም ነገር እያደረገና+ በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር የወደቁትን እየፈወሰ+ በዚያ አገር ሁሉ ተዘዋወረ። 39  እሱ በአይሁዳውያን አገርም ሆነ በኢየሩሳሌም ላደረጋቸው ነገሮች ሁሉ እኛ ምሥክሮች ነን፤ እነሱ ግን በእንጨት* ላይ ሰቅለው ገደሉት። 40  አምላክ እሱን በሦስተኛው ቀን አስነሳው፤+ ከዚያም ለሰዎች እንዲገለጥ* አደረገው፤ 41  የተገለጠው ግን ለሁሉም ሰው ሳይሆን አምላክ አስቀድሞ ለመረጣቸው ምሥክሮች ይኸውም ከሞት ከተነሳ በኋላ አብረነው ለበላንና ለጠጣን ለእኛ ነው።+ 42  በተጨማሪም አምላክ እሱን በሕያዋንና በሙታን ላይ ፈራጅ አድርጎ እንደሾመው+ ለሰዎች እንድንሰብክና በተሟላ ሁኔታ* እንድንመሠክር አዘዘን።+ 43  በእሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአት ይቅርታ እንደሚያገኝ+ ነቢያት ሁሉ ስለ እሱ ይመሠክራሉ።”+ 44  ጴጥሮስ ስለዚህ ጉዳይ ገና እየተናገረ ሳለ ቃሉን እየሰሙ በነበሩት ሁሉ ላይ መንፈስ ቅዱስ ወረደ።+ 45  ከጴጥሮስ ጋር የመጡት የተገረዙ አማኞች* የመንፈስ ቅዱስ ነፃ ስጦታ ከአሕዛብ ወገን በሆኑ ሰዎችም ላይ በመፍሰሱ ተገረሙ። 46  ምክንያቱም በባዕድ ቋንቋዎች* ሲናገሩና አምላክን ሲያወድሱ ይሰሟቸው ነበር።+ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ እንዲህ አለ፦ 47  “እንደ እኛው መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉትን እነዚህን ሰዎች በውኃ እንዳይጠመቁ ሊከለክላቸው የሚችል አለ?”+ 48  ይህን ካለ በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እንዲጠመቁ አዘዛቸው።+ ከዚያም የተወሰነ ቀን አብሯቸው እንዲቆይ ለመኑት።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የጦር ጓድ።” ወደ 600 የሚጠጉ ወታደሮችን ያቀፈ የሮም ሠራዊት።
ወይም “መቶ አለቃ።”
ወይም “እጅ ነሳው።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “በዛፍ።”
ወይም “እንዲታይ።”
ወይም “በሚገባ።”
ወይም “ታማኝ አገልጋዮች።”
ቃል በቃል “በልሳኖች።”