ዘዳግም 4:1-49

  • ታዛዦች እንዲሆኑ የቀረበ ጥሪ (1-14)

    • አምላክ ያደረገላችሁን ነገር አትርሱ (9)

  • ይሖዋ እሱ ብቻ እንዲመለክ ይፈልጋል (15-31)

  • እንደ ይሖዋ ያለ አምላክ የለም (32-40)

  • ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያሉ የመማጸኛ ከተሞች (41-43)

  • ሙሴ ለእስራኤላውያን ሕጉን ነገራቸው (44-49)

4  “አሁንም እስራኤል ሆይ፣ በሕይወት እንድትኖሩና+ የአባቶቻችሁ አምላክ ይሖዋ የሚሰጣችሁን ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፣ ትጠብቋቸው ዘንድ የማስተምራችሁን ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች አዳምጡ።  እኔ የማዛችሁን የአምላካችሁን የይሖዋን ትእዛዛት ጠብቁ፤ በምሰጣችሁ ትእዛዝ ላይ ምንም ነገር አትጨምሩ፤ ከዚያም ላይ ምንም አትቀንሱ።+  “ይሖዋ ከፌጎር ባአል ጋር በተያያዘ ምን እንዳደረገ በገዛ ዓይናችሁ አይታችኋል፤ አምላክህ ይሖዋ የፌጎርን ባአል የተከተለውን እያንዳንዱን ሰው ከመካከልህ አጥፍቶታል።+  አምላካችሁን ይሖዋን የሙጥኝ ያላችሁት እናንተ ሁላችሁ ግን ይኸው ዛሬም በሕይወት አላችሁ።  እኔም አምላኬ ይሖዋ ባዘዘኝ መሠረት ሥርዓቶችንና ድንጋጌዎችን+ ያስተማርኳችሁ በምትወርሷት ምድር ውስጥ እንድትጠብቋቸው ነው።  እነዚህንም በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤+ ፈጽሟቸውም፤ እንዲህ ብታደርጉ ስለ እነዚህ ሥርዓቶች ሁሉ በሚሰሙ ሕዝቦች ፊት እንደ ጥበበኞችና+ እንደ አስተዋዮች+ ትቆጠራላችሁ፤ እነሱም ‘ይህ ታላቅ ብሔር በእርግጥም ጥበበኛና አስተዋይ ሕዝብ ነው’+ ይላሉ።  በምንጠራው ጊዜ ሁሉ ለእኛ ቅርብ እንደሆነው እንደ አምላካችን እንደ ይሖዋ፣ ለእሱ ቅርብ የሆኑ አማልክት ያሉት ታላቅ ብሔር የትኛው ነው?+  ዛሬ በፊታችሁ እንዳስቀመጥኩት እንደዚህ ሕግ ያለ የጽድቅ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች ያሉት የትኛው ታላቅ ብሔር ነው?+  “ዓይኖቻችሁ ያዩአቸውን ነገሮች እንዳትረሱና በሕይወት ዘመናችሁ ሁሉ ከልባችሁ እንዳይጠፉ ተጠንቀቁ፤ ራሳችሁንም ጠብቁ።* እነዚህንም ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ ንገሯቸው።+ 10  በኮሬብ በአምላካችሁ በይሖዋ ፊት በቆማችሁበት ቀን ይሖዋ ‘በምድር ላይ በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት+ ይማሩና ልጆቻቸውንም ያስተምሩ+ ዘንድ ቃሌን እንዲሰሙ+ ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ’ ብሎኝ ነበር። 11  “በመሆኑም እናንተ መጥታችሁ በተራራው ግርጌ ቆማችሁ፤ ተራራውም እስከ ሰማያት ድረስ* እየነደደ ነበር፤ ጨለማ፣ ደመናና ድቅድቅ ጨለማ ሆኖ ነበር።+ 12  ይሖዋም ከእሳቱ ውስጥ ያነጋግራችሁ ጀመር።+ እናንተም ድምፅ ከመስማት በስተቀር መልክ አላያችሁም፤+ የሰማችሁት ድምፅ ብቻ ነበር።+ 13  እሱም እንድትጠብቁት ያዘዛችሁን ቃል ኪዳኑን ይኸውም አሥርቱን ትእዛዛት* ገለጸላችሁ።+ ከዚያም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው።+ 14  በዚያን ጊዜ ይሖዋ፣ ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር የምትፈጽሟቸውን ሥርዓቶችና ደንቦች እንዳስተምራችሁ አዘዘኝ። 15  “በመሆኑም ይሖዋ በኮሬብ በእሳቱ መካከል ሆኖ ባነጋገራችሁ ቀን ምንም መልክ ስላላያችሁ ራሳችሁን ጠብቁ፤* 16  ይኸውም ምግባረ ብልሹ በመሆን በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን የትኛውንም ዓይነት ምስል፣ የወንድ ወይም የሴት ምስል፣+ 17  በምድር ላይ ያለን የማንኛውንም እንስሳ ምስል ወይም በሰማይ ላይ የሚበርን የማንኛውንም ወፍ ምስል፣+ 18  መሬት ለመሬት የሚሄድን የማንኛውንም ነገር ምስል አሊያም ከምድር በታች በውኃ ውስጥ ያለን የማንኛውንም ዓሣ ምስል ለራሳችሁ እንዳትሠሩ ነው።+ 19  እንዲሁም ዓይኖችህን ወደ ሰማይ አቅንተህ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን ይኸውም የሰማይን ሠራዊት በሙሉ በምታይበት ጊዜ ተታለህ እንዳትሰግድላቸውና እንዳታገለግላቸው።+ እነዚህ አምላክህ ይሖዋ ከሰማይ በታች ላሉ ሕዝቦች ሁሉ የሰጣቸው ናቸው። 20  እናንተን ግን ልክ እንደ ዛሬው ሁሉ ይሖዋ የእሱ የግል ንብረት*+ እንድትሆኑ የብረት ማቅለጫ ምድጃ ከሆነችው ከግብፅ አውጥቶ አመጣችሁ። 21  “ይሖዋ በእናንተ የተነሳ እኔን ተቆጣኝ፤+ ዮርዳኖስን እንደማልሻገርም ሆነ አምላካችሁ ይሖዋ ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ወደ መልካሚቱ ምድር እንደማልገባ ማለ።+ 22  እንግዲህ እኔ የምሞተው በዚህ አገር ነው፤ ዮርዳኖስን አልሻገርም፤+ እናንተ ግን ተሻግራችሁ ይህችን መልካም ምድር ትወርሳላችሁ። 23  አምላካችሁ ይሖዋ ከእናንተ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንዳትረሱ+ እንዲሁም አምላካችሁ ይሖዋ የከለከላችሁን የማንኛውንም ነገር የተቀረጸ ምስል ለራሳችሁ እንዳትሠሩ ተጠንቀቁ።+ 24  ምክንያቱም አምላካችሁ ይሖዋ የሚባላ እሳት፣+ እሱ ብቻ እንዲመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው።+ 25  “ልጆችና የልጅ ልጆች ስታፈሩ፣ በምድሪቱም ላይ ረጅም ዘመን ስትኖሩ፣ የጥፋት ጎዳና ወደመከተል ዞር ብትሉና የማንኛውንም ነገር የተቀረጸ ምስል+ ብትሠሩ እንዲሁም በአምላካችሁ በይሖዋ ፊት ክፉ ነገር በመፈጸም እሱን ብታስቆጡት+ 26  ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትወርሷት ምድር ያለጥርጥር ወዲያውኑ እንደምትደመሰሱ በዚህ ቀን ሰማይንና ምድርን በእናንተ ላይ ምሥክር አድርጌ እጠራባችኋለሁ። በምድሪቱ ላይ ረጅም ዘመን ከመኖር ይልቅ ሙሉ በሙሉ ትደመሰሳላችሁ።+ 27  ይሖዋም በሕዝቦች መካከል ይበትናችኋል፤+ ይሖዋ በሚበትናችሁ ብሔራትም መካከል ጥቂቶቻችሁ ብቻ ትተርፋላችሁ።+ 28  እዚያም ማየትም ሆነ መስማት፣ መብላትም ሆነ ማሽተት የማይችሉ በሰው እጅ የተሠሩ የእንጨትና የድንጋይ አማልክትን ታገለግላላችሁ።+ 29  “እዚያ ሆናችሁ አምላካችሁን ይሖዋን ብትፈልጉት፣ በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ*+ ብትሹት በእርግጥ ታገኙታላችሁ።+ 30  ከጊዜ በኋላ ከባድ ጭንቀት ውስጥ ስትገባና እነዚህ ሁሉ ነገሮች በአንተ ላይ ሲደርሱ ያኔ ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ትመለሳለህ፤ ድምፁንም ትሰማለህ።+ 31  ምክንያቱም አምላክህ ይሖዋ መሐሪ አምላክ ነው።+ አይተውህም፣ አያጠፋህም ወይም ለአባቶችህ በመሐላ ያጸናላቸውን ቃል ኪዳን አይረሳም።+ 32  “እንግዲህ ከአንተ ዘመን በፊት ስለነበሩት ስለ ቀደሙት ጊዜያት ይኸውም አምላክ ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረበት ቀን አንስቶ ስላለው ዘመን ጠይቅ፤ ከአንዱ የሰማይ ጥግ እስከ ሌላኛው የሰማይ ጥግ ድረስ እስቲ መርምር። እንዲህ ያለ እጅግ ታላቅ ነገር ተደርጎ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ተሰምቶ ያውቃል?+ 33  ልክ እንደ አንተ፣ አምላክ በእሳት ውስጥ ሆኖ ሲናገር የሰማና በሕይወት የኖረ ሌላ ሕዝብ አለ?+ 34  ወይስ አምላካችሁ ይሖዋ የገዛ ዓይኖቻችሁ እያዩ ለእናንተ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ በፍርድ እርምጃዎች፣* ድንቅ በሆኑ ምልክቶች፣ በተአምራት፣+ በጦርነት፣+ በብርቱ እጅ፣+ በተዘረጋ ክንድና አስፈሪ በሆኑ ሥራዎች+ ከሌላ ብሔር መካከል ለራሱ ብሔር ለመውሰድ ሞክሯል? 35  እውነተኛው አምላክ፣ ይሖዋ መሆኑን ታውቅ ዘንድ እነዚህን ነገሮች እንድታይ ተደርገሃል፤+ ከእሱ ሌላ ማንም የለም።+ 36  አንተን ለማረም ከሰማያት ድምፁን እንድትሰማ አደረገህ፤ በምድርም ላይ የእሱን ታላቅ እሳት እንድታይ አደረገህ፤ ድምፁንም ከእሳቱ ውስጥ ሰማህ።+ 37  “እሱ አባቶችህን ስለወደደና ከእነሱ በኋላ የሚመጣውን ዘራቸውን ስለመረጠ+ ከአንተ ጋር በመሆን በታላቅ ኃይሉ ከግብፅ አወጣህ። 38  እንዲሁም ዛሬ እንደሆነው ሁሉ ወደ ምድራቸው ሊያስገባህና ምድራቸውን ርስት አድርጎ ሊሰጥህ ከአንተ ይልቅ ታላቅና ኃያል የሆኑትን ብሔራት ከፊትህ አባረራቸው።+ 39  እንግዲህ በላይ በሰማይም ሆነ በታች በምድር እውነተኛው አምላክ፣ ይሖዋ እንደሆነ ዛሬ እወቅ፤ እንዲሁም ልብ በል።+ ሌላ ማንም የለም።+ 40  ለአንተም ሆነ ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ልጆችህ መልካም እንዲሆንላችሁና አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ላይ ለረጅም ዘመን እንድትኖር እኔ ዛሬ የማዝህን የእሱን ሥርዓትና ትእዛዛት ጠብቅ።”+ 41  በዚያን ጊዜ ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ሦስት ከተሞችን ለየ።+ 42  ነፍስ ያጠፋ ማንኛውም ግለሰብ ባልንጀራውን የገደለው ሆን ብሎ ካልሆነና የቆየ ጥላቻ ካልነበረው+ ከእነዚህ ከተሞች ወደ አንዱ በመሸሽ በዚያ መኖር ይችላል።+ 43  ከተሞቹም ለሮቤላውያን በአምባው ላይ ባለው ምድረ በዳ የምትገኘው ቤጼር፣+ ለጋዳውያን በጊልያድ የምትገኘው ራሞት+ እንዲሁም ለምናሴያውያን በባሳን+ ያለችው ጎላን+ ናቸው። 44  ሙሴ በእስራኤል ሕዝብ ፊት ያስቀመጠው ሕግ+ ይህ ነው። 45  እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ሙሴ የሰጣቸው ማሳሰቢያዎች፣ ሥርዓቶችና ድንጋጌዎች እነዚህ ናቸው፤+ 46  ይህን የነገራቸው በዮርዳኖስ ክልል ከቤትጰኦር+ ባሻገር በሚገኘው ሸለቆ ይኸውም ሙሴና እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ድል ባደረጉት በሃሽቦን+ ይኖር በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሲሖን ምድር ነበር።+ 47  እነሱም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው ክልል የነበሩትን የሁለቱን የአሞራውያን ነገሥታት ምድር ማለትም የሲሖንን ምድርና የባሳንን ንጉሥ የኦግን+ ምድር ወረሱ፤ 48  ይህም ምድር በአርኖን ሸለቆ* ዳርቻ ከሚገኘው ከአሮዔር+ አንስቶ እስከ ሲዎን ተራራ ይኸውም እስከ ሄርሞን+ ድረስ ያለውን አካባቢ ይሸፍናል፤ 49  እንዲሁም ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚገኘውን የአረባን ምድርና በጲስጋ+ ሸንተረር ግርጌ እስከሚገኘው እስከ አረባ ባሕር* ድረስ ያለውን አካባቢ ይጨምራል።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለነፍሳችሁም ከፍተኛ ትኩረት ስጡ።”
ቃል በቃል “እስከ ሰማያት ልብ ድረስ።”
ቃል በቃል “ቃላት።”
ወይም “ለነፍሳችሁም ከፍተኛ ትኩረት ስጡ።”
ወይም “ውርሻው።”
ወይም “በፈተናዎች።”
ወይም “ደረቅ ወንዝ።”
ጨው ባሕርን ወይም ሙት ባሕርን ያመለክታል።