ዘዳግም 18:1-22

  • የካህናቱና የሌዋውያኑ ድርሻ (1-8)

  • መናፍስታዊ ድርጊቶች የተከለከሉ ናቸው (9-14)

  • እንደ ሙሴ ያለ ነቢይ (15-19)

  • ሐሰተኛ ነቢያትን ለይቶ ማወቅ (20-22)

18  “ሌዋውያኑ ካህናት አልፎ ተርፎም መላው የሌዊ ነገድ ከእስራኤል ጋር ድርሻም ሆነ ውርሻ አይሰጣቸውም። የእሱ ድርሻ የሆኑትን ለይሖዋ በእሳት የሚቀርቡትን መባዎች ይበላሉ።+  በመሆኑም በወንድሞቻቸው መካከል ውርሻ ሊኖራቸው አይገባም። አስቀድሞ በነገራቸው መሠረት ውርሻቸው ይሖዋ ነው።  “ካህናት ከሕዝቡ ሊያገኙ የሚገባቸው ድርሻ የሚከተለው ይሆናል፦ በሬም ሆነ በግ መሥዋዕት አድርጎ የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው የእንስሳውን ወርች፣ መንገጭላውንና ሆድ ዕቃውን ለካህኑ ይስጥ።  የእህልህን በኩር፣ አዲስ የወይን ጠጅህንና ዘይትህን እንዲሁም ከመንጋህ በመጀመሪያ የተሸለተውን ፀጉር ስጠው።+  አምላክህ ይሖዋ ከነገዶችህ ሁሉ መካከል በይሖዋ ስም ሁልጊዜ እንዲያገለግል የመረጠው እሱንና ወንዶች ልጆቹን ነው።+  “ሆኖም አንድ ሌዋዊ ከሚኖርበት በእስራኤል ከሚገኙ ከተሞችህ+ ከአንዱ ወጥቶ ይሖዋ ወደሚመርጠው ስፍራ*+ መሄድ ቢፈልግ*  በይሖዋ ፊት ቆመው እንደሚያገለግሉት ሌዋውያን ወንድሞቹ ሁሉ እሱም በዚያ በአምላኩ በይሖዋ ስም ሊያገለግል ይችላል።+  የአባቶቹን ርስት በመሸጥ ከሚያገኘው ገንዘብ በተጨማሪ ከእነሱ እኩል ምግብ ይሰጠዋል።+  “አምላክህ ይሖዋ ወደሚሰጥህ ምድር በምትገባበት ጊዜ በዚያ የሚገኙ ብሔራት የሚፈጽሟቸውን አስጸያፊ ነገሮች አታድርግ።+ 10  ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን በእሳት የሚያሳልፍ፣+ ሟርተኛ፣+ አስማተኛ፣+ ሞራ ገላጭ፣+ ምትሃተኛ፣+ 11  ድግምተኛ፣ መናፍስት ጠሪ፣+ ጠንቋይ+ ወይም ሙታን አነጋጋሪ+ በመካከልህ አይገኝ። 12  ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ሁሉ በይሖዋ ፊት አስጸያፊ ነው፤ አምላክህ ይሖዋም እነሱን ከፊትህ የሚያባርራቸው በእነዚህ አስጸያፊ ነገሮች የተነሳ ነው። 13  በአምላክህ በይሖዋ ፊት እንከን የለሽ ሆነህ መገኘት አለብህ።+ 14  “አንተ ከምድራቸው የምታስለቅቃቸው እነዚህ ብሔራት አስማተኞችንና+ ሟርተኞችን+ ይሰማሉ፤ አንተ ግን እንዲህ እንድታደርግ አምላክህ ይሖዋ አልፈቀደልህም። 15  አምላክህ ይሖዋ ከወንድሞችህ መካከል እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሳልሃል። እናንተም እሱን ማዳመጥ ይኖርባችኋል።+ 16  ይህም የሚሆነው በኮሬብ ተሰብስባችሁ+ በነበረበት ዕለት ‘እንዳልሞት የአምላኬን የይሖዋን ድምፅ ከእንግዲህ አልስማ ወይም ይህን ታላቅ እሳት ከእንግዲህ አልይ’+ በማለት አምላካችሁን ይሖዋን በጠየቃችሁት መሠረት ነው። 17  ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለኝ፦ ‘የተናገሩት ነገር መልካም ነው። 18  ከወንድሞቻቸው መካከል እንደ አንተ ያለ ነቢይ አስነሳላቸዋለሁ፤+ ቃሌንም በአፉ ላይ አደርጋለሁ፤+ እሱም እኔ የማዘውን ሁሉ ይነግራቸዋል።+ 19  በእኔ ስም የሚናገረውን ቃሌን የማይሰማውን ሰው በእርግጥ ተጠያቂ አደርገዋለሁ።+ 20  “‘እኔ እንዲናገር ያላዘዝኩትን ቃል በእብሪት ተነሳስቶ በስሜ የሚናገር ወይም በሌሎች አማልክት ስም የሚናገር ነቢይ ካለ ያ ነቢይ ይገደል።+ 21  ሆኖም አንተ በልብህ “ታዲያ ቃሉን ይሖዋ እንዳልተናገረው እንዴት እናውቃለን?” ብለህ ታስብ ይሆናል። 22  ነቢዩ በይሖዋ ስም ቢናገርና የተናገረው ቃል ባይፈጸም ወይም እውነት ሆኖ ባይገኝ ይህን ቃል የተናገረው ይሖዋ አይደለም። ይህ ቃል ነቢዩ በእብሪት ተነሳስቶ የተናገረው ነው። እሱን ልትፈራው አይገባም።’

የግርጌ ማስታወሻዎች

ይሖዋ የአምልኮ ማዕከል አድርጎ የሚመርጠውን ስፍራ ያመለክታል።
ወይም “ነፍሱ መሄድ ብትፈልግ።”