በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የአምላክ መንግሥት

የአምላክ መንግሥት

የአምላክ መንግሥት የሰዎችን የልብ ሁኔታ የሚያመለክት ነገር ነው?

“አንተ ከአምላክ መንግሥት የራቅህ አይደለህም።”ማርቆስ 12:34

ሰዎች ምን ይላሉ?

አንድ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖት፣ የአምላክ መንግሥት “አምላክ በአንድ ሰው ልብና ሕይወት ላይ መንገሡን የሚያመለክት ሁኔታ” እንደሆነ ያስተምራል፤ ብዙ ሰዎች በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የአምላክ መንግሥት፣ እውን የሆነ መስተዳድር እንጂ ግለሰቦች በልባቸው ለአምላክ መገዛታቸውን የሚያሳይ ምሳሌያዊ አገላለጽ አይደለም። የአምላክ መንግሥት የሚገዛው መላዋን ምድር ነው።—መዝሙር 72:8፤ ዳንኤል 7:14

ታዲያ ኢየሱስ “የእግዚአብሔር መንግሥት በውሥጣችሁ ናት” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? (ሉቃስ 17:21 የ1879 ትርጉም) ኢየሱስ፣ መንግሥቱ በአድማጮቹ ልብ ውስጥ እንዳለ መናገሩ ሊሆን አይችልም። ለምን? ምክንያቱም በዚያ ወቅት ያዳምጡት የነበሩት ሰዎች ፈሪሳውያን ነበሩ። የእነዚህ ሰዎች አምልኮ ግብዝነት የሚንጸባረቅበት ስለሆነ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም፤ በመሆኑም ኢየሱስ ወደ አምላክ መንግሥት እንደማይገቡ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 23:13) ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት “በውሥጣችሁ ናት” ወይም አዲስ ዓለም ትርጉም እና በርካታ የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንዳስቀመጡት “በመካከላችሁ ነው” ብሎ መናገሩ ተገቢ ነው። እንዴት? የአምላክ መንግሥት የወደፊት ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ነበር።—ሉቃስ 17:21

 የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?

“መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን።” —ማቴዎስ 6:10

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የአምላክ መንግሥት አምላክ ያቋቋመው እውን መስተዳድር ሲሆን የዚህ መንግሥት ገዥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ማቴዎስ 28:18፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:14, 15) የዚህ መንግሥት ዓላማ በሰማይና በምድር የአምላክን ፈቃድ ማስፈጸም ነው። (ማቴዎስ 6:10) አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት የሰው ልጆችን ችግሮች ያስወግዳል። መንግሥቱ ሰብዓዊ መስተዳድሮች መቼም ቢሆን ሊፈጽሟቸው ያልቻሏቸውን ነገሮች ያከናውናል።

በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምድር ገነት ትሆናለች፤ የሰው ልጆችም ሰላምና ደህንነት የሚያገኙ ሲሆን ሁሉ ነገር ይሟላላቸዋል። (መዝሙር 46:9፤ ኢሳይያስ 35:1፤ ሚክያስ 4:4) በዚያ ጊዜ የሚታመምም ሆነ የሚሞት አይኖርም፤ በሽታ ከምድር ገጽ ይጠፋል። (ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:4) ያረጁ ሰዎች እንኳ እንደገና ወጣት ይሆናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሥጋው እንደ ሕፃን ልጅ ገላ ይታደሳል፤ ወደ ወጣትነቱም ዘመን ይመለሳል” የሚል ትንቢት ይዟል።—ኢዮብ 33:25

ምን ማድረግ ትችላለህ?

አምላክ የሚጠብቅብህን እስካደረግህ ድረስ የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆን ትችላለህ፤ ዘርህ ወይም የትውልድ ቦታህ በዚህ ረገድ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ እንደማያዳላ” ይገልጻል፤ “ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው” ይላል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

የአምላክ መንግሥት በሰዎች ጥረት ሊመጣ ይችላል?

“የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል።”—ዳንኤል 2:44

ሰዎች ምን ይላሉ?

አንዳንዶች፣ እምነታቸውን በማስፋፋት ወይም በዓለም ዙሪያ ሰላም እና የወንድማማችነት መንፈስ እንዲሰፍን በማድረግ የአምላክን መንግሥት በምድር ላይ ማቋቋም እንደሚችሉ ይሰማቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የአምላክን መንግሥት የሚያቋቁመው አምላክ እንጂ ሰዎች አይደሉም። (ዳንኤል 2:44) አምላክ መንግሥቱን ባቋቋመበት ወቅት “የራሴን ንጉሥ ሾምሁ” ብሏል። (መዝሙር 2:6) የአምላክ መንግሥት በሰዎች ጥረት ሊመጣ አይችልም፤ ይህ መንግሥት ምድርን የሚያስተዳድረው ከሰማይ በመሆኑ የሰው ልጆች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንቅፋት ሊፈጥርበት አይችልም።—ማቴዎስ 4:17

አንተን ሊያሳስብህ የሚገባው ለምንድን ነው?

የሰው ልጆች ሰላምና አንድነት እንዲኖራቸው መመኘት ተፈጥሯዊ ነገር ነው። እንዲያውም አንተ ራስህ እነዚህን ነገሮች ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ተካፍለህ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ያሰብከው አለመሳካቱን ስትመለከት ተስፋ ቆርጠህ ይሆናል። የአምላክ መንግሥት ሊመጣ የሚችለው በአምላክ ኃይል እንደሆነ ማወቅህ የአምላክ መንግሥት ተገዥ በመሆን ይበልጥ ጠቃሚ የሆነ ነገር ለማከናወን እንድትጥር ያነሳሳሃል።