በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበረሃዋን ድመት ተዋወቁ

የበረሃዋን ድመት ተዋወቁ

የዚህች ድመት የእርግዝና ጊዜ ሁለት ወር ገደማ ሲሆን በአማካይ ሦስት ግልገሎችን ትወልዳለች

የበረሃዋ ድመት (ሳንድ ካት) ጭው ባለው በረሃ ጨለማውን ተገን አድርጋ ከጉድጓዷ ትወጣና ቆም ብላ ዙሪያ ገባውን ትቃኛለች። እንዲሁም ጆሮዋን ቀስራ ታዳምጣለች። ከዚያም ድምጿን አጥፍታ እያደባች በአሸዋማው መሬት ላይ በቀስታ መሄድ ትጀምራለች።

በድንገት ድመቷ ዘለለችና አደጋ ይመጣል ብላ ያልጠረጠረችውን የአይጥ ዝርያ እንቅ አደረገቻት። አደኑ በዚህ አያቆምም፤ ሌሊቱን ሙሉ በዚሁ መንገድ ስታድን ታድራለች። በልታ ልትጨርሰው ከምትችለው በላይ ካደነች የተረፋትን አሸዋ ውስጥ ትቀብራለች። የበረሃዋ ድመት ወደ ጉድጓዷ የምትመለሰው ሊነጋጋ ሲል ነው፤ ቀን ላይ ጨርሶ ብቅ አትልም ማለት ይቻላል። ስለዚህች በቀላሉ የማትታይ እንስሳ አንዳንድ አስደናቂ መረጃዎችን እስቲ እንመልከት።

  • ጆሯቸው ከሩቅ ስለሚሰማ የሚያድኑት እንስሳ ከመሬት በታች ቢሆንም እንኳ ሊያገኙት ይችላሉ

  • ተባዕቱ ድመት ተጓዳኝ ለማግኘት ቀጭን የሆነ ኃይለኛ ጩኸት ያሰማል። እንስቷም ይህንን ድምፅ ከረጅም ርቀት መስማት ትችላለች

  • መዳፎቻቸው በፀጉር የተሸፈኑ ናቸው፤ ይህም በሚሄዱበት ጊዜ አሸዋ ውስጥ እንዳይሰምጡ የሚረዳቸው ከመሆኑም ሌላ መዳፋቸውን ቅዝቃዜም ሆነ ሙቀት እንዳይጎዳው ይከላከልላቸዋል

  •  የጆሮዎቻቸው ውስጠኛ ክፍል ጥቅጥቅ ባለ ነጭ ፀጉር የተሸፈነ መሆኑ ነፋስ በሚኖርበት ጊዜ አሸዋ ጆሯቸው ውስጥ እንዳይገባ ይከላከልላቸዋል

  • የእነዚህ ድመቶች መዳፍ ጥቅጥቅ ባለ ፀጉር የተሸፈነ በመሆኑ ዱካቸውን ተከታትሎ ማግኘት አስቸጋሪ ነው

  • እነዚህ ድመቶች ከሚበሉት እንስሳ በሚያገኙት ውኃ ብቻ መኖር ይችላሉ

  • የካራኩም በረሃ አሸዋ እስከ 80 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚደርስ ሙቀት ሊኖረው ይችላል። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ የሙቀቱ መጠን ከዜሮ በታች እስከ 25 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሊወርድ ይችላል