በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ተቃውሞ ማሰማት መፍትሔ ይሆናል?

ተቃውሞ ማሰማት መፍትሔ ይሆናል?

የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኞች ናቸው። (ዮሐንስ 17:16፤ 18:36) በመሆኑም በዚህ ርዕስ ሥር፣ ሕዝባዊ ዓመፅ የተካሄደባቸው አንዳንድ ቦታዎች እንደ ምሳሌ ቢጠቀሱም መጽሔቱ አንደኛውን አገር ከሌላው የሚያስበልጥ ወይም ማንኛውንም ፖለቲካዊ ጉዳይ የሚደግፍ ሐሳብ አይሰጥም።

ሞሐመድ ቡአዚዚ ታኅሣሥ 17 ቀን 2010 ሁሉ ነገር ከአቅሙ በላይ ሆነበት። በቱኒዝያ ጎዳናዎች ሸቀጥ እያዞረ የሚሸጠው ይህ የ26 ዓመት ወጣት የተሻለ ሥራ ለማግኘት አለመቻሉ በራሱ ሆድ አስብሶታል። በዚያ ላይ ደግሞ ምግባረ ብልሹ ባለሥልጣናት ጉቦኛ መሆናቸው አበሳጭቶታል። ይህም እንዳይበቃው በዚህ ዕለት ጠዋት ላይ ተቆጣጣሪዎች ሞሐመድ እያዞረ የሚሸጠውን ፍራፍሬ ወሰዱበት። ሞሐመድ ሚዛኑን ሊወስዱበት ሲሉ ለመከላከል ሞከረ፤ በዚህ ጊዜ አንዲት ፖሊስ በጥፊ እንደመታችው የዓይን ምሥክሮች ገልጸዋል።

በደረሰበት ሁኔታ ውርደት የተሰማውና በንዴት የተቃጠለው ሞሐመድ፣ አቅራቢያው ወደሚገኝ የመንግሥት መሥሪያ ቤት በመሄድ ቅሬታውን ቢያሰማም ጆሮ የሚሰጠው አላገኘም። በዚህ ጊዜ ሞሐመድ ከመሥሪያ ቤቱ ፊት ለፊት ሆኖ “ታዲያ ምን ሠርቼ ልብላ?” ብሎ ጮኸ። ከዚያም ሰውነቱ ላይ ተቀጣጣይ ፈሳሽ ካርከፈከፈ በኋላ ክብሪት ለኮሰ። ቃጠሎው ባደረሰበት ጉዳት የተነሳ ሦስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሕይወቱ አለፈ።

ሞሐመድ ቡአዚዚ ተስፋ በመቁረጥ የወሰደው እርምጃ ቱኒዝያንም ሆነ ሌሎች አገሮችን አናግቷል። ለአገሪቱ መንግሥት መገልበጥ ምክንያት የሆነውና በሌሎች የአረብ አገሮችም የተዛመተው ሕዝባዊ ዓመፅ የተቆሰቆሰው በሞሐመድ ድርጊት የተነሳ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። የአውሮፓ ፓርላማ ለቡአዚዚና ለሌሎች አራት ሰዎች የ2011 የሳከሮቭ የሐሳብ ነፃነት ሽልማትን ሰጠ፤ በተጨማሪም የለንደኑ ዘ ታይምስ መጽሔት ሞሐመድ ቡአዚዚን የ2011 የዓመቱ ሰው እንዲሆን መርጦታል።

ይህ ምሳሌ እንደሚያሳየው ሰዎች ተቃውሟቸውን መግለጻቸው ከፍተኛ ኃይል ሊኖረው ይችላል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራትን እንደ ማዕበል እያናወጠ ያለው ሕዝባዊ ዓመፅ መንስኤው ምንድን ነው? ተቃውሞን ከመግለጽ ሌላ ለችግሮች መፍትሔ የሚያስገኝ አማራጭ ይኖር ይሆን?

 ሕዝባዊ ተቃውሞ እየተስፋፋ የመጣው ለምንድን ነው?

ለብዙ ተቃውሞዎች መቀስቀስ ምክንያት የሆኑት የሚከተሉት ነገሮች ናቸው፦

  • በኢኮኖሚው እና በፖለቲካው ሥርዓት አለመርካት። ሰዎች፣ መንግሥት ፍላጎታቸውን እንደሚያሟላላቸውና የኢኮኖሚው ሥርዓት እንደሚፈልጉት እንደሆነ ከተሰማቸው ተቃውሞ ለማንሳት አያስቡም፤ ችግሮች ቢኖሯቸው እንኳ ሥርዓቱን ተከትለው ችግሮቻቸውን ለመፍታት ይጥራሉ። በሌላ በኩል ግን ሕዝቡ፣ ባለሥልጣናት በሙስና የተዘፈቁ እንደሆኑ፣ የፍትሕ መጓደል እንደሰፈነ እንዲሁም ሥርዓቱ ጥቂቶችን ብቻ የሚጠቅም እንደሆነ ሲሰማው ተቃውሞ የሚቀሰቀስበት ሁኔታ ይፈጠራል።

  • ተቃውሞን የሚቆሰቁሱ ነገሮች። ብዙ ጊዜ ሰዎች፣ እርምጃ ለመውሰድና ችለው የኖሩትን ነገር ለመለወጥ የሚያነሳሳቸው የሆነ ምክንያት ይኖራል። ለምሳሌ ሞሐመድ ቡአዚዚ የወሰደው እርምጃ በቱኒዝያ ሕዝባዊ ዓመፅ እንዲቀሰቀስ አድርጓል። በሕንድ አገር፣ አና ሐዛሪ የተባሉ የለውጥ አራማጅ ሙስናን በመቃወም ያደረጉት የረሃብ አድማ ደጋፊዎቻቸው በ450 ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች ለተቃውሞ እንዲወጡ አድርጓል።

መጽሐፍ ቅዱስ ከብዙ ዘመናት በፊት እንደተናገረው የምንኖረው ‘አንዱ በሌላው ላይ ገዥ በሚሆንበትና ሌላው ደግሞ ተጨቍኖ በሚኖርበት ዓለም’ ውስጥ ነው። (መክብብ 8:9 የ1980 ትርጉም) ሙስና እና የፍትሕ መጓደል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ በጣም ተስፋፍተዋል። በእርግጥም ሰዎች የፖለቲካውና የኢኮኖሚው ሥርዓት ፍላጎታቸውን እንደማያሟሉላቸው ይበልጥ እየተገነዘቡ መጥተዋል። መረጃዎች በሞባይል ስልኮች፣ በኢንተርኔት እንዲሁም የ24 ሰዓት አገልግሎት በሚሰጡ የዜና ማሰራጫዎች በፍጥነት ስለሚተላለፉ ገለልተኛ በሆኑ አካባቢዎች የተፈጸሙ ሁኔታዎች እንኳ በበርካታ ቦታዎች ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ይሆናሉ።

ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ምን ውጤት አስገኝተዋል?

የሕዝባዊ ዓመፅ ደጋፊዎች፣ ተቃውሞዎች የሚከተሉትን ውጤቶች እንዳስገኙ ይናገራሉ፦

  • ድሆች እርዳታ እንዲያገኙ አድርጓል። በ1930ዎቹ በዓለም ላይ በተከሰተው ታላቅ የኢኮኖሚ ድቀት ወቅት በቺካጎ፣ ኢሊኖይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከቤት ኪራይ ጋር በተያያዘ ዓመፅ ተነስቶ ነበር፤ በመሆኑም የከተማይቱ ባለሥልጣናት ተከራዮችን ከተከራዩት ቤት የማስወጣቱ እንቅስቃሴ እንዲቆም እንዲሁም አንዳንድ ተቃዋሚዎች ሥራ እንዲያገኙ አድርገዋል። በኒው ዮርክ ሲቲ የተቀሰቀሰ ተመሳሳይ ተቃውሞ ደግሞ ከቤታቸው የተባረሩ 77,000 ቤተሰቦች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ አስተዋጽኦ አድርጓል።

  • የፍትሕ መጓደል እንዲወገድ አድርጓል። በ1955/1956 በሞንትጎመሪ፣ አላባማ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደው የከተማ አውቶቡሶችን ያለመሳፈር አድማ፣ ጥቁሮችና ነጮች ተለያይተው እንዲቀመጡ ያዝዝ የነበረው ሕግ እንዲለወጥ አድርጓል።

  • የግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ አድርጓል። በሆንግ ኮንግ አቅራቢያ ሊሠራ የታቀደ የድንጋይ ከሰል የኃይል ማመንጫ፣ የአካባቢ ብክለት እንደሚያስከትል በመግለጽ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በታኅሣሥ 2011  ተቃውሟቸውን በማሰማታቸው ፕሮጀክቱ ተሰርዟል።

አንዳንዶች ተቃውሞ በማሰማት ዓላማቸውን ማሳካት ቢችሉም የተሻለ መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው

እርግጥ ነው፣ ተቃዋሚዎች ያሰቡት የሚሳካላቸው ሁልጊዜ አይደለም። ለምሳሌ፣ አንዳንድ መሪዎች የሕዝቡን ጥያቄ ከመቀበል ይልቅ ተቃዋሚዎቹን ለመቅጣት እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። በመካከለኛው ምሥራቅ የምትገኝ አንዲት አገር ፕሬዚዳንት፣ በአገራቸው ያለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ አስመልክተው በቅርቡ በሰጡት ሐሳብ ላይ “እንደ ብረት በጠነከረ ክንድ ሊደመሰስ ይገባዋል” ብለዋል፤ ደግሞም በዚሁ ዓመፅ የተነሳ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።

ተቃዋሚዎች ዓላማቸውን ማሳካት በሚችሉበት ጊዜም እንኳ በኋላ ላይ አዳዲስ ችግሮች ብቅ ማለታቸው አይቀርም። አንድን የአፍሪካ አገር መሪ ከሥልጣን በማውረድ ረገድ ድርሻ የነበረው አንድ ሰው አዲስ ስለተቋቋመው መንግሥት ለታይም መጽሔት በሰጠው መግለጫ ላይ “እንደ ገነት ያለ ሁኔታ የሰፈነ ቢመስልም ብዙም ሳይቆይ ሁሉም ነገር ቀውስ ውስጥ ገባ” ብሏል።

የተሻለ አማራጭ ይኖር ይሆን?

እውቅ የሆኑ በርካታ ግለሰቦች፣ የሰው ልጆች ጨቋኝ ሥርዓቶችን የመቃወም የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ለምሳሌ፣ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ባደረጉት እንቅስቃሴ ምክንያት ለበርካታ ዓመታት በእስራት የቆዩትና የቼክ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሟቹ ቫትስላፍ ሃቨል በ1985 እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “[ተቃዋሚው] ሊሰጥ የሚችለው ግፋ ቢል ሕይወቱን ነው፤ ይህንንም የሚያደርገው የቆመለት ነገር እውነት መሆኑን የሚያስረግጥበት ሌላ መንገድ ስለሌለው ነው።”

ሃቨል የተናገሩት ነገር እንደሚጠቁመው ሞሐመድ ቡአዚዚ እና እንደ እሱ ያሉ ሌሎች ሰዎች እንዲህ ያለ እርምጃ  የሚወስዱት ድምፃቸውን ለማሰማት የሚያስችል የተሻለ አማራጭ እንደሌላቸው ስለሚሰማቸው ነው። በቅርቡ በአንድ የእስያ አገር በርካታ ሰዎች ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ጭቆናን በመቃወም ራሳቸውን አቃጥለዋል። ሰዎች እንዲህ ያለውን አሰቃቂ እርምጃ ለመውሰድ የሚያነሳሳቸው ምን እንደሆነ አንድ ሰው ለኒውስዊክ መጽሔት ሲገልጽ “ጠመንጃ የለንም። በሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት ለማድረስ አንፈልግም። ታዲያ ሌላ ምን ማድረግ እንችላለን?” ብሏል።

መጽሐፍ ቅዱስ የፍትሕ መጓደል፣ ሙስና እና ጭቆና መፍትሔ የሚያገኙበትን መንገድ ይናገራል። ለሰው ልጆች ችግሮች መፍትሔ ማምጣት ያልቻለውንና ሕዝቡ ለተቃውሞ እንዲነሳ የሚያደርገውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት የሚተካ መንግሥት አምላክ በሰማይ እንዳቋቋመ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። የዚህን መንግሥት ገዥ በተመለከተ የተነገረ አንድ ትንቢት “ችግረኛው በጮኸ ጊዜ፣ ምስኪኑንና ረዳት የሌለውን ይታደገዋል። ሕይወታቸውን ከጭቈናና ከግፍ ያድናል” ይላል።—መዝ. 72:12, 14

የይሖዋ ምሥክሮች፣ ለሰው ልጅ ሰላም የሰፈነበት ዓለም የሚያመጣው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ ያምናሉ። (ማቴዎስ 6:9, 10) በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች በተቃውሞ እንቅስቃሴዎች አይካፈሉም። ይሁን እንጂ፣ በአምላክ የሚመራ መንግሥት ሰዎች ተቃውሞ እንዲያነሱ ምክንያት የሚሆኗቸውን ነገሮች በሙሉ ያስወግዳል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው? እንደዚያ ይመስል ይሆናል። ቢሆንም ብዙዎች የአምላክ መንግሥት ይህን ማድረግ እንደሚችል ይተማመናሉ። አንተም በአምላክ መንግሥት ላይ እምነት መጣል ይቻል እንደሆነ ራስህ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።