የጴጥሮስ ሁለተኛው ደብዳቤ 1:1-21

  • ሰላምታ (1)

  • መመረጣችሁን አስተማማኝ አድርጉ (2-15)

    • በእምነት ላይ የሚጨመሩ ባሕርያት (5-9)

  • “ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል” (16-21)

1  የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያና ሐዋርያ ከሆነው ከስምዖን ጴጥሮስ፣ በአምላካችን ጽድቅ እንዲሁም በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ አማካኝነት እኛ ያገኘነውን ዓይነት ክቡር እምነት ለተቀበሉ፦  ስለ አምላክና ስለ ጌታችን ኢየሱስ በምትቀስሙት ትክክለኛ እውቀት+ አማካኝነት ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።  መለኮታዊ ኃይሉ፣ በገዛ ክብሩና በጎነቱ ስለጠራን አምላክ ባገኘነው ትክክለኛ እውቀት+ ለአምላክ ያደርን ሆነን ለመኖር የሚረዱንን ነገሮች ሁሉ ሰጥቶናል።*  በእነዚህ ነገሮች አማካኝነት ክቡርና እጅግ ታላቅ የሆነ ተስፋ ሰጥቶናል፤*+ ይህን ያደረገውም የመጥፎ ምኞት* ውጤት ከሆነው ከዓለም ብልሹ ምግባር አምልጣችሁ፣ በዚህ ተስፋ አማካኝነት ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንድትሆኑ ነው።+  በመሆኑም ልባዊ ጥረት በማድረግ+ በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ጨምሩ፤+ በበጎነት ላይ እውቀትን፣+  በእውቀት ላይ ራስን መግዛትን፣+ ራስን በመግዛት ላይ ጽናትን፣ በጽናት ላይ ለአምላክ ማደርን፣+  ለአምላክ በማደር ላይ ወንድማዊ መዋደድን፣ በወንድማዊ መዋደድ ላይ ፍቅርን ጨምሩ።+  እነዚህ ነገሮች በውስጣችሁ ቢኖሩና ቢትረፈረፉ፣ ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያላችሁን ትክክለኛ እውቀት ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሥራ ፈቶችና ፍሬ ቢሶች እንዳትሆኑ ይጠብቋችኋል።+  እነዚህ ነገሮች የሚጎድሉት ማንኛውም ሰው ብርሃን ላለማየት ዓይኑን የጨፈነ ዕውር ሰው* ነው፤+ ደግሞም ከቀድሞ ኃጢአቱ መንጻቱን ረስቷል።+ 10  በመሆኑም ወንድሞች፣ መጠራታችሁንና+ መመረጣችሁን አስተማማኝ ለማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ ትጉ፤ እነዚህን ነገሮች የምታደርጉ ከሆነ ፈጽሞ አትወድቁምና።+ 11  እንዲያውም በእጅጉ ትባረካላችሁ፤ ጌታችንና አዳኛችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥትም+ ትገባላችሁ።+ 12  ስለዚህ ምንም እንኳ እነዚህን ነገሮች የምታውቁና በተማራችሁት እውነት ጸንታችሁ የቆማችሁ ብትሆኑም፣ ስለ እነዚህ ነገሮች ሁልጊዜ እናንተን ከማሳሰብ ወደኋላ አልልም። 13  በዚህ ድንኳን*+ እስካለሁ ድረስ እናንተን በማሳሰብ ማነቃቃት ተገቢ ይመስለኛል፤+ 14  ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ እንዳሳወቀኝ ይህ ድንኳን የሚወገድበት ጊዜ እንደቀረበ አውቃለሁ።+ 15  እኔ ከሄድኩ በኋላ እነዚህን ነገሮች ማስታወስ* እንድትችሉ ሁልጊዜ አቅሜ የፈቀደውን ሁሉ አደርጋለሁ። 16  የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መገኘት ያሳወቅናችሁ በብልሃት የተፈጠረ ተረት ተከትለን ሳይሆን ግርማውን በገዛ ዓይናችን አይተን ነው።+ 17  ከግርማዊው ክብር “እኔ ራሴ በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው”+ የሚል ቃል* ለእሱ በተነገረ ጊዜ ከአባታችንና ከአምላካችን ክብርና ሞገስ ተቀብሏል። 18  ከእሱ ጋር በቅዱሱ ተራራ በነበርንበት ጊዜ ይህ ቃል ከሰማይ ሲመጣ ሰምተናል። 19  በመሆኑም ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ጎህ እስኪቀድና የንጋት ኮከብ+ እስኪወጣ ድረስ በጨለማ ቦታ፣ በልባችሁ ውስጥ ለሚበራ መብራት+ የምትጠነቀቁትን ያህል ለትንቢታዊው ቃል ትኩረት መስጠታችሁ መልካም ነው። 20  በመጀመሪያ ደረጃ፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያለው ትንቢት ሁሉ በሰው ሐሳብ ላይ የተመሠረተ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። 21  መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤+ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው* ተናገሩ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “በነፃ ሰጥቶናል።”
ወይም “በነፃ ሰጥቶናል።”
ወይም “የፍትወት።”
“በቅርብ ያለውን ብቻ የሚያይ፣ ዕውር ሰው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ሥጋዊ አካሉን ያመለክታል።
ወይም “መጥቀስ።”
ቃል በቃል “ድምፅ።”
ቃል በቃል “ተነድተው።”