ዘፀአት 23:1-33

  • ለእስራኤላውያን የተሰጡ ድንጋጌዎች (1-19)

    • ከሐቀኝነትና ፍትሐዊ ከመሆን ጋር በተያያዘ (1-9)

    • ከሰንበትና ከበዓላት ጋር በተያያዘ (10-19)

  • እስራኤላውያንን የሚመራቸው መልአክ (20-26)

  • ምድሩን መውረስና ወሰን መከለል (27-33)

23  “የሐሰት ወሬ አትንዛ።*+ ተንኮል የሚሸርብ ምሥክር በመሆን ከክፉ ሰው ጋር አትተባበር።+  ብዙኃኑን ተከትለህ ክፉ ነገር አታድርግ፤ ከብዙኃኑ ጋር ለመስማማት ስትል የተዛባ* ምሥክርነት በመስጠት ፍትሕን አታጣም።  ችግረኛው ሙግት ሲኖረው አታድላለት።+  “የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ሲባዝን ብታገኘው ወደ እሱ ልትመልሰው ይገባል።+  የሚጠላህ ሰው አህያ ጭነቱ ከብዶት ወድቆ ብታይ ዝም ብለህ አትለፈው። ከዚህ ይልቅ ጭነቱን ከእንስሳው ላይ ለማውረድ እርዳው።+  “በመካከልህ ያለ ድሃ ሙግት ሲኖረው ፍርድ አታጣምበት።+  “ከሐሰት ክስ* ራቅ፤ እኔ ክፉውን ሰው ጻድቅ እንደሆነ አድርጌ ስለማልቆጥር*+ ንጹሑንና ጻድቁን ሰው አትግደል።  “ጉቦ አትቀበል፤ ምክንያቱም ጉቦ አጥርተው የሚያዩ ሰዎችን ዓይን ያሳውራል፤ እንዲሁም የጻድቅ ሰዎችን ቃል ሊያዛባ ይችላል።+  “የባዕድ አገር ሰውን አትጨቁን። እናንተ ራሳችሁ በግብፅ ምድር ሳላችሁ የባዕድ አገር ሰው ስለነበራችሁ የባዕድ አገር ሰው መሆን ምን ስሜት እንደሚያሳድር* ታውቃላችሁ።+ 10  “ለስድስት ዓመት መሬትህ ላይ ዘር ዝራ፤ አዝመራውንም ሰብስብ።+ 11  በሰባተኛው ዓመት ግን መሬትህን አትረሰው፤ እንዲሁ ተወው። በሕዝብህ መካከል ያሉ ድሆች ከዚያ ይበላሉ፤ ከእነሱ የተረፈውንም የዱር አራዊት ይበሉታል። በወይን እርሻህም ሆነ በወይራ ዛፍ እርሻህ እንደዚሁ ታደርጋለህ። 12  “ለስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ ሆኖም በሬህና አህያህ እንዲያርፉ እንዲሁም የሴት ባሪያህ ልጅና የባዕድ አገሩ ሰው ጉልበታቸውን እንዲያድሱ በሰባተኛው ቀን ሥራ አትሥራ።+ 13  “የነገርኳችሁን ነገሮች በሙሉ በጥንቃቄ ፈጽሙ፤+ እንዲሁም የሌሎች አማልክትን ስም አታንሱ፤ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ከአፍህ ሲወጣ ሊሰማ አይገባም።+ 14  “በዓመት ሦስት ጊዜ ለእኔ በዓል ታከብርልኛለህ።+ 15  የቂጣን በዓል ታከብራለህ።+ በአቢብ* ወር+ በተወሰነው ጊዜ፣ ባዘዝኩህ መሠረት ለሰባት ቀናት ቂጣ ትበላለህ፤ ምክንያቱም ከግብፅ የወጣኸው በዚህ ጊዜ ነው። ማንም ባዶ እጁን ፊቴ አይቅረብ።+ 16  በተጨማሪም በእርሻህ ላይ በዘራኸው መጀመሪያ በሚደርሰው የድካምህ ፍሬ የመከርን በዓል* አክብር፤+ ከእርሻህ ላይ የድካምህን ፍሬ በምትሰበስብበት በዓመቱ ማብቂያ ላይ የአዝመራ መክተቻን በዓል* አክብር።+ 17  የአንተ የሆኑ ሰዎች* ሁሉ በዓመት ሦስት ጊዜ በእውነተኛው ጌታ በይሖዋ ፊት ይቅረቡ።+ 18  “የመሥዋዕቴን ደም እርሾ ከገባበት ከማንኛውም ነገር ጋር አብረህ አታቅርብ። በበዓሎቼም ላይ የሚቀርቡት የስብ መሥዋዕቶች እስከ ጠዋት ድረስ ማደር የለባቸውም። 19  “በምድርህ ላይ የሚገኘውን መጀመሪያ የደረሰውን ምርጥ ፍሬ ወደ አምላክህ ወደ ይሖዋ ቤት አምጣ።+ “የፍየል ጠቦትን በእናቱ ወተት አትቀቅል።+ 20  “በመንገድ ላይ እንዲጠብቅህና ወዳዘጋጀሁት ስፍራ እንዲያመጣህ በፊትህ መልአክ እልካለሁ።+ 21  የሚልህን ስማ፤ ቃሉንም ታዘዝ። መተላለፋችሁን ይቅር ስለማይል+ በእሱ ላይ አታምፁ፤ ምክንያቱም እሱ ስሜን ተሸክሟል። 22  ይሁን እንጂ ቃሉን በጥንቃቄ ብትታዘዝና የምልህን ሁሉ ብታደርግ ለጠላቶችህ ጠላት እሆናለሁ፤ የሚቃወሙህንም እቃወማለሁ። 23  ምክንያቱም መልአኬ በፊትህ ይሄዳል፤ እንዲሁም ወደ አሞራውያን፣ ሂታውያን፣ ፈሪዛውያን፣ ከነአናውያን፣ ሂዋውያንና ኢያቡሳውያን ያመጣሃል፤ እኔም ጠራርጌ አጠፋቸዋለሁ።+ 24  ለአማልክታቸው አትስገድ፤ ወይም ተታለህ እነሱን አታገልግል፤ የሚያደርጉትን ነገር አታድርግ።+ ከዚህ ይልቅ አውድማቸው፤ የማምለኪያ ዓምዶቻቸውንም ሰባብር።+ 25  አምላካችሁን ይሖዋን አገልግሉ፤+ እሱም ምግብህንና ውኃህን ይባርክልሃል።+ እኔም ከመካከልህ በሽታን አስወግዳለሁ።+ 26  በምድርህ ላይ የሚኖሩ ሴቶች አያስወርዳቸውም ወይም መሃን አይሆኑም፤+ ረጅም ዕድሜ እሰጥሃለሁ። 27  “አንተ ከመድረስህ በፊት ስለ እኔ ሰምተው ይፈራሉ፤+ የምታገኛቸውም ሕዝቦች ሁሉ ግራ እንዲጋቡ አደርጋለሁ። ጠላቶችህም ሁሉ ድል ተመተው ከፊትህ እንዲሸሹ* አደርጋለሁ።+ 28  ከአንተ አስቀድሜ ጭንቀት* እልካለሁ፤+ ሂዋውያንን፣ ከነአናውያንንና ሂታውያንን ከፊትህ አባሮ ያስወጣቸዋል።+ 29  ምድሩ ባድማ እንዳይሆንና የዱር አራዊት በዝተው እንዳያስቸግሩህ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከፊትህ አባርሬ አላስወጣቸውም።+ 30  ቁጥርህ እስኪበዛና ምድሩን እስክትቆጣጠር ድረስ ጥቂት በጥቂት ከፊትህ አባርሬ አስወጣቸዋለሁ።+ 31  “ወሰንህንም ከቀይ ባሕር አንስቶ እስከ ፍልስጤማውያን ባሕር እንዲሁም ከምድረ በዳው አንስቶ እስከ ወንዙ* ድረስ አደርገዋለሁ።+ ምክንያቱም የምድሩን ነዋሪዎች በእጃችሁ አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ አንተም ከፊትህ አባረህ ታስወጣቸዋለህ።+ 32  ከእነሱም ሆነ ከአማልክታቸው ጋር ቃል ኪዳን መግባት የለብህም።+ 33  በእኔ ላይ ኃጢአት እንድትሠራ እንዳያደርጉህ በምድርህ ላይ መኖር የለባቸውም። አማልክታቸውን ብታገለግል ወጥመድ ይሆንብሃል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ቃል በቃል “አታንሳ።”
ወይም “በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያለው።”
ቃል በቃል “ቃል።”
ወይም “ክፉውን ሰው በነፃ ስለማልለቅ።”
ወይም “የባዕድ አገር ሰውን ሕይወት (ነፍስ)።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
የዳስ (የማደሪያ ድንኳን) በዓል በመባልም ይታወቃል።
የሳምንታት በዓል ወይም ጴንጤቆስጤ በመባልም ይታወቃል።
ወይም “ወንዶች።”
ወይም “ጠላቶችህ ሁሉ ጀርባቸውን ወደ አንተ እንዲያዞሩ።”
“ድንጋጤ፤ ሽብር” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ኤፍራጥስን ያመለክታል።