ዘሌዋውያን 20:1-27

  • የሞሎክ አምልኮ፤ መናፍስታዊ ድርጊት (1-6)

  • ቅዱሳን ሁኑ፤ ወላጆቻችሁን አክብሩ (7-9)

  • ተገቢ ያልሆነ የፆታ ግንኙነት የፈጸሙ በሞት ይቀጣሉ (10-21)

  • በምድሪቱ ለመኖር ቅዱሳን ሁኑ (22-26)

  • መናፍስታዊ ድርጊት የሚፈጽሙ በሞት ይቀጣሉ (27)

20  ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦  “እስራኤላውያንን እንዲህ በላቸው፦ ‘ልጁን ለሞሎክ የሚሰጥ ማንኛውም እስራኤላዊ ወይም እስራኤል ውስጥ የሚኖር ማንኛውም የባዕድ አገር ሰው ይገደል።+ የአገሩ ሰዎች በድንጋይ ወግረው ይግደሉት።  ልጆቹን ለሞሎክ ስለሰጠ እንዲሁም ቅዱሱን ስፍራዬን ስላረከሰና+ ቅዱሱን ስሜን ስላቃለለ እኔ ራሴ በዚያ ሰው ላይ ፊቴን አጠቁርበታለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ።  የአገሩ ሰዎች ሰውየው ልጁን ለሞሎክ በመስጠት የፈጸመውን ድርጊት አይተው እንዳላዩ ቢሆኑና ሳይገድሉት ቢቀሩ+  እኔ ራሴ በዚህ ሰውና በቤተሰቡ ላይ እነሳባቸዋለሁ።+ ያንን ሰውም ሆነ ከሞሎክ ጋር ምንዝር በመፈጸም የእሱን ፈለግ የተከተሉትን ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ለይቼ አጠፋቸዋለሁ።  “‘አንድ ሰው* ከመናፍስት ጠሪዎችና+ ከጠንቋዮች+ ጋር መንፈሳዊ ምንዝር ለመፈጸም ወደ እነሱ ቢሄድ እኔ በዚያ ሰው* ላይ በእርግጥ እነሳበታለሁ፤ ከሕዝቡም መካከል ለይቼ አጠፋዋለሁ።+  “‘እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ስለሆንኩ ራሳችሁን ቀድሱ፤ ቅዱሳንም ሁኑ።+  ደንቦቼን ጠብቁ፤ እንዲሁም ፈጽሟቸው።+ የምቀድሳችሁ እኔ ይሖዋ ነኝ።+  “‘አባቱን ወይም እናቱን የሚረግም ማንኛውም ሰው ይገደል።+ አባቱን ወይም እናቱን ስለረገመ ደሙ በራሱ ላይ ነው። 10  “‘ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ምንዝር የሚፈጽምን ሰው በተመለከተ እንዲህ ይደረግ፦ ከባልንጀራው ሚስት ጋር ምንዝር የሚፈጽም ሰው ይገደል፤ አመንዝራውም ሆነ አመንዝራይቱ ይገደሉ።+ 11  ከአባቱ ሚስት ጋር የተኛ ሰው አባቱን ለኀፍረት ዳርጎታል።*+ ሁለቱም ይገደሉ። ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። 12  አንድ ሰው ከልጁ ሚስት ጋር ቢተኛ ሁለቱም ይገደሉ። ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ድርጊት ፈጽመዋል። ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።+ 13  “‘አንድ ሰው ከሴት ጋር እንደሚተኛ ከወንድ ጋር ቢተኛ ሁለቱም አስጸያፊ ድርጊት ፈጽመዋል።+ ስለዚህ ይገደሉ። ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። 14  “‘አንድ ሰው አንዲትን ሴትና እናቷን ቢያገባ፣ ይህ ጸያፍ ድርጊት* ነው።+ ይህ ጸያፍ ምግባር በመካከላችሁ እንዳይቀጥል እሱንም ሆነ እነሱን በእሳት ያቃጥሏቸው።+ 15  “‘አንድ ሰው ከእንስሳ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም ይገደል፤ እንስሳውንም ግደሉት።+ 16  አንዲት ሴት የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ወደ ማንኛውም እንስሳ ብትቀርብ+ ሴትየዋንም ሆነ እንስሳውን ግደል፤ ሁለቱም ይገደሉ። ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው። 17  “‘አንድ ሰው ከእህቱ ማለትም ከአባቱ ሴት ልጅ ወይም ከእናቱ ሴት ልጅ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽምና እርቃኗን ቢያይ፣ እሷም የእሱን እርቃን ብታይ ይህ አሳፋሪ ድርጊት ነው።+ በሕዝቦቻቸው ልጆች ፊት እንዲጠፉ ይደረጉ። እህቱን ለኀፍረት ዳርጓል።* ለፈጸመው ጥፋት ይጠየቅበታል። 18  “‘አንድ ሰው በወር አበባዋ ወቅት ከአንዲት ሴት ጋር ቢተኛና ከእሷ ጋር የፆታ ግንኙነት ቢፈጽም እሱም ሆነ እሷ የሚፈሰውን ደሟን ገልጠዋል።+ ስለሆነም ሁለቱም ከሕዝቦቻቸው መካከል ተለይተው እንዲጠፉ ይደረጉ። 19  “‘ከእናትህ እህት ወይም ከአባትህ እህት ጋር የፆታ ግንኙነት አትፈጽም፤ ምክንያቱም ይህ የሥጋ ዘመድን ለኀፍረት መዳረግ ነው።+ ለፈጸሙት ጥፋት ይጠየቁበታል። 20  ከአጎቱ ሚስት ጋር የተኛ ሰው አጎቱን ለኀፍረት ዳርጓል።*+ ለፈጸሙት ኃጢአት ይጠየቁበታል። ልጅ ሳይኖራቸው ይሙቱ። 21  አንድ ሰው የወንድሙን ሚስት ቢወስድ ይህ አስጸያፊ ድርጊት ነው።+ ወንድሙን ለኀፍረት ዳርጓል።* ያለልጅም ይቅሩ። 22  “‘ትኖሩባት ዘንድ እናንተን የማስገባባት ምድር እንዳትተፋችሁ+ ደንቦቼንና ድንጋጌዎቼን ሁሉ ጠብቁ፤+ እንዲሁም ፈጽሟቸው።+ 23  ከፊታችሁ አባርሬ የማስወጣቸው ብሔራት በሚመሩባቸው ደንቦች አትሂዱ፤+ ምክንያቱም እነሱ እነዚህን ነገሮች ሁሉ አድርገዋል፤ እኔም እጸየፋቸዋለሁ።+ 24  በመሆኑም እንዲህ አልኳችሁ፦ “ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ እኔ ደግሞ ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር+ እንድትወርሷት እሰጣችኋለሁ። ከሕዝቦች የለየኋችሁ አምላካችሁ ይሖዋ እኔ ነኝ።”+ 25  ንጹሕ በሆነውና ርኩስ በሆነው እንስሳ እንዲሁም ርኩስ በሆነውና ንጹሕ በሆነው ወፍ መካከል ልዩነት አድርጉ፤+ እኔ ርኩስ ነው ብዬ በለየሁላችሁ እንስሳ ወይም ወፍ አሊያም መሬት ለመሬት በሚሄድ ማንኛውም ነገር ራሳችሁን* አታርክሱ።+ 26  እኔ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ለእኔ ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል፤+ የእኔ ትሆኑ ዘንድ ከሌሎች ሕዝቦች ለየኋችሁ።+ 27  “‘መናፍስት ጠሪ ወይም ጠንቋይ የሆነ ወንድ ወይም የሆነች ሴት ካሉ ይገደሉ።+ ሕዝቡ በድንጋይ ወግሮ ይግደላቸው። ደማቸው በራሳቸው ላይ ነው።’”

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ነፍስ።”
ወይም “ነፍስ።”
ቃል በቃል “የአባቱን እርቃን ገልጧል።”
ወይም “አሳፋሪ ምግባር፤ ሴሰኝነት።”
ቃል በቃል “የእህቱን እርቃን ገልጧል።”
ቃል በቃል “የአጎቱን እርቃን ገልጧል።”
ቃል በቃል “የወንድሙን እርቃን ገልጧል።”
ወይም “ነፍሳችሁን።”