የማርቆስ ወንጌል 4:1-41

  • የመንግሥቱ ምሳሌዎች (1-34)

    • ዘሪው (1-9)

    • ኢየሱስ ምሳሌዎችን የተጠቀመበት ምክንያት (10-12)

    • የዘሪው ምሳሌ ትርጉም (13-20)

    • ‘መብራት አምጥቶ እንቅብ የሚደፋበት የለም’ (21-23)

    • “በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል” (24, 25)

    • ‘ዘሪው ሌሊት ይተኛል’ (26-29)

    • የሰናፍጭ ዘር (30-32)

    • ምሳሌ መጠቀም (33, 34)

  • ኢየሱስ ማዕበሉን ጸጥ አሰኘ (35-41)

4  ዳግመኛም በባሕሩ አጠገብ ሆኖ ያስተምር ጀመር፤ እጅግ ብዙ ሕዝብም ወደ እሱ መጥቶ ተሰበሰበ። በመሆኑም ጀልባ ላይ ወጥቶ ከተቀመጠ በኋላ ከባሕሩ ዳርቻ ፈቀቅ አለ፤ ሕዝቡ ሁሉ ግን በባሕሩ ዳርቻ ነበር።+  ከዚያም ብዙ ነገር በምሳሌ ያስተምራቸው ጀመር፤+ እንዲህም አላቸው፦+  “ስሙ። እነሆ፣ ዘሪው ሊዘራ ወጣ።+  በሚዘራበት ጊዜ አንዳንዶቹ ዘሮች መንገድ ዳር ወደቁ፤ ወፎችም መጥተው ለቀሟቸው።  ሌሎቹ ደግሞ ብዙ አፈር በሌለው ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቁ፤ አፈሩም ጥልቀት ስላልነበረው ወዲያውኑ በቀሉ።+  ፀሐይ በወጣ ጊዜ ግን ተቃጠሉ፤ ሥር ስላልነበራቸውም ደረቁ።  ሌሎቹ ዘሮች ደግሞ በእሾህ መካከል ወደቁ፤ እሾሁም አድጎ አነቃቸው፤ ፍሬም አልሰጡም።+  ሌሎቹ ግን ጥሩ አፈር ላይ ወድቀው ከበቀሉና ካደጉ በኋላ ፍሬ ማፍራት ጀመሩ፤ ደግሞም 30፣ 60 እና 100 እጥፍ አፈሩ።”+  ከዚያም “የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” አለ።+ 10  ብቻውን በሆነ ጊዜ አሥራ ሁለቱና በዙሪያው የነበሩት ሌሎች ሰዎች ስለ ምሳሌዎቹ ይጠይቁት ጀመር።+ 11  እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ለእናንተ የአምላክን መንግሥት ቅዱስ ሚስጥር+ የመረዳት ችሎታ ተሰጥቷችኋል፤ በውጭ ላሉት ግን የሚሰሙት ነገር ሁሉ እንዲሁ ምሳሌ ብቻ ሆኖ ይቀርባቸዋል፤+ 12  በመሆኑም ማየቱን ያያሉ ግን ልብ አይሉም፤ መስማቱን ይሰማሉ ግን ትርጉሙን አይረዱም፤ ደግሞም ሙሉ በሙሉ ስለማይመለሱ ይቅርታ አያገኙም።”+ 13  በተጨማሪም እንዲህ አላቸው፦ “ይህን ምሳሌ ካልተረዳችሁ ታዲያ ሌሎቹን ምሳሌዎች ሁሉ እንዴት ትረዳላችሁ? 14  “ዘሪው ቃሉን ይዘራል።+ 15  ቃሉ ሲዘራ መንገድ ዳር እንደወደቁት ዘሮች የሆኑት እነዚህ ናቸው፤ ቃሉን እንደሰሙ ግን ሰይጣን መጥቶ+ በውስጣቸው የተዘራውን ቃል ይወስደዋል።+ 16  በተመሳሳይም በድንጋያማ መሬት እንደተዘሩት ዘሮች የሆኑት እነዚህ ናቸው፤ ቃሉን እንደሰሙ በደስታ ይቀበሉታል።+ 17  ሆኖም ቃሉ በውስጣቸው ሥር ስለማይሰድ የሚቆዩት ለጥቂት ጊዜ ነው፤ ከዚያም በቃሉ የተነሳ መከራ ወይም ስደት ሲደርስባቸው ወዲያውኑ ይሰናከላሉ። 18  በእሾህ መካከል እንደተዘሩት ዘሮች የሆኑ ሌሎች ደግሞ አሉ። እነዚህ ቃሉን የሰሙ ናቸው፤+ 19  ይሁንና የዚህ ሥርዓት* ጭንቀትና+ ሀብት ያለው የማታለል ኃይል+ እንዲሁም የሌሎች ነገሮች ሁሉ ምኞት+ ወደ ልባቸው ሰርጎ በመግባት ቃሉን ያንቀዋል፤ የማያፈራም ይሆናል። 20  በመጨረሻም፣ ጥሩ አፈር ላይ እንደተዘሩት ዘሮች የሆኑት ቃሉን የሚሰሙና በደስታ የሚቀበሉ እንዲሁም 30፣ 60 እና 100 እጥፍ የሚያፈሩ ናቸው።”+ 21  ደግሞም እንዲህ አላቸው፦ “መብራት አምጥቶ እንቅብ* የሚደፋበት ወይም አልጋ ሥር የሚያስቀምጠው ይኖራል? የሚቀመጠው በመቅረዝ ላይ አይደለም?+ 22  ስለዚህ የተሸሸገ መገለጡ፣ የተሰወረም ይፋ መውጣቱ አይቀርም።+ 23  የሚሰማ ጆሮ ያለው ሁሉ ይስማ።”+ 24  አክሎም እንዲህ አላቸው፦ “የምትሰሙትን ነገር ልብ በሉ።+ በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል፤ እንዲያውም ከዚያ የበለጠ ይጨመርላችኋል። 25  ላለው ይጨመርለታልና፤+ የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።”+ 26  ከዚያም እንዲህ አለ፦ “የአምላክ መንግሥት መሬት ላይ ዘር የሚዘራን ሰው ይመስላል። 27  ሰውየው ሌሊት ይተኛል፤ ማለዳም ይነሳል፤ እንዴት እንደሆነም ሳያውቅ ዘሩ ይበቅልና ያድጋል። 28  መሬቱም ራሱ ቀስ በቀስ ፍሬ ያፈራል፤ በመጀመሪያ ቡቃያውን፣ ከዚያም ዛላውን በመጨረሻም በዛላው ላይ የጎመራ ፍሬ ይሰጣል። 29  ሰብሉ እንደደረሰ ግን የመከር ወቅት በመሆኑ ሰውየው ማጭዱን ይዞ ያጭዳል።” 30  ደግሞም እንዲህ አለ፦ “የአምላክን መንግሥት ከምን ጋር ልናነጻጽረው እንችላለን? ወይስ በምን ምሳሌ ልንገልጸው እንችላለን? 31  መሬት ላይ በተዘራች ጊዜ በምድር ላይ ካሉ ዘሮች ሁሉ እጅግ የምታንስን የሰናፍጭ ዘር ይመስላል።+ 32  ከተዘራች በኋላ ግን አድጋ ከሌሎች ተክሎች ሁሉ የምትበልጥ ትሆናለች፤ ትላልቅ ቅርንጫፎችም ታወጣለች፤ በመሆኑም የሰማይ ወፎች በጥላዋ ሥር መስፈሪያ ያገኛሉ።” 33  ኢየሱስ እንዲህ የመሳሰሉ በርካታ ምሳሌዎችን+ ተጠቅሞ መረዳት በሚችሉት መጠን ቃሉን ይነግራቸው ነበር። 34  እንዲያውም ያለምሳሌ አይነግራቸውም ነበር፤ ብቻቸውን በሚሆኑበት ጊዜ ግን ለደቀ መዛሙርቱ ሁሉንም ነገር ያብራራላቸው ነበር።+ 35  በዚያ ቀን፣ ምሽት ላይ “ወደ ባሕሩ ማዶ እንሻገር” አላቸው።+ 36  በመሆኑም ሕዝቡን ካሰናበቱ በኋላ እዚያው ጀልባዋ ውስጥ እንዳለ ይዘውት ሄዱ፤ ሌሎች ጀልባዎችም አብረውት ነበሩ።+ 37  በዚህ ጊዜ እጅግ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ተነሳ፤ ማዕበሉም ከጀልባዋ ጋር እየተላተመ ወደ ውስጥ ይገባ ጀመር፤ ከዚህም የተነሳ ጀልባዋ በውኃ ልትሞላ ተቃረበች።+ 38  ኢየሱስ ግን በጀልባዋ የኋለኛ ክፍል ትራስ* ተንተርሶ ተኝቶ ነበር። ስለዚህ ቀስቅሰውት “መምህር፣ ስናልቅ ዝም ብለህ ታያለህ?” አሉት። 39  በዚህ ጊዜ ተነስቶ ነፋሱን ገሠጸው፤ ባሕሩንም “ጸጥ በል! ረጭ በል!” አለው።+ ነፋሱ ቆመ፤ ታላቅ ጸጥታም ሰፈነ። 40  ከዚያም “ለምን ትሸበራላችሁ?* አሁንም እምነት የላችሁም?” አላቸው። 41  እነሱ ግን በታላቅ ፍርሃት ተውጠው እርስ በርሳቸው “ለመሆኑ ይህ ማን ነው? ነፋስና ባሕር እንኳ ይታዘዙለታል” ተባባሉ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “የዚህ ዘመን።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
እንደ ስንዴ ያሉ የእህል ዓይነቶችን ለመስፈር የሚያገለግል ዕቃ።
ወይም “መከዳ።”
ወይም “ትርበተበታላችሁ?”