በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጥምቀት ምንድን ነው?

ጥምቀት ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 “መጠመቅ” የሚለው አገላለጽ፣ ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ መጥለቅን ያመለክታል። a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተለያዩ ሰዎች ጥምቀት የሚገልጹ ብዙ ዘገባዎች አሉ። (የሐዋርያት ሥራ 2:41) ከእነዚህ ዘገባዎች መካከል አንዱ ኢየሱስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ በመጥለቅ እንደተጠመቀ የሚገልጸው ነው። (ማቴዎስ 3:13, 16) ኢየሱስ ከተጠመቀ ከዓመታት በኋላ አንድ ኢትዮጵያዊ፣ እየተጓዘ ባለበት መንገድ አጠገብ በሚገኝ ውኃ ውስጥ በመግባት ተጠምቋል።—የሐዋርያት ሥራ 8:36-40

 ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ መጠመቅ እንዳለባቸው አስተምሯል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ሐዋርያው ጴጥሮስም ይህን ትምህርት የሚያጠናክር ሐሳብ ጽፏል።—1 ጴጥሮስ 3:21

በዚህ ርዕስ ውስጥ፦

 ጥምቀት ምን ያመለክታል?

 ጥምቀት አንድ ሰው ከኃጢአቱ ንስሐ እንደገባና በማንኛውም ሁኔታ ሥር የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ እንደተስማማ በሰዎች ፊት ይፋ ለማድረግ የሚወስደው እርምጃ ነው። ይህም በመላ ሕይወቱ አምላክንና ኢየሱስን መታዘዝን ይጨምራል። አንድ ሰው ሲጠመቅ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ መጓዝ ይጀምራል።

 ውኃ ውስጥ መጥለቅ፣ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ያደረገውን ለውጥ ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ምልክት ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ መጠመቅን ከመቀበር ጋር ያመሳስለዋል። (ሮም 6:4፤ ቆላስይስ 2:12) ግለሰቡ ውኃ ውስጥ መጥለቁ፣ ለቀድሞ አኗኗሩ እንደሞተ ያሳያል። ከውኃው መውጣቱ ደግሞ ራሱን ለአምላክ የወሰነ ክርስቲያን በመሆን አዲስ ሕይወት መጀመሩን ይጠቁማል።

 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕፃናት ጥምቀት ወይም ክርስትና ስለማስነሳት ምን ይላል?

 “ክርስትና መነሳት” ወይም “ክርስትና ማስነሳት” የሚሉት አገላለጾች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኙም። b መጽሐፍ ቅዱስ ሕፃናት መጠመቅ እንዳለባቸውም አያስተምርም።

 ሕፃናትን ማጥመቅ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ነገር ጋር አይጣጣምም። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው መጠመቅ ከፈለገ የተወሰኑ መሥፈርቶችን ማሟላት እንዳለበት ያስተምራል። ለምሳሌ ቢያንስ መሠረታዊ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መረዳትና እነዚህን ትምህርቶች በሕይወቱ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል። ከኃጢአቱ ንስሐ መግባት ይጠበቅበታል። እንዲሁም በጸሎት አማካኝነት ራሱን ለአምላክ መወሰን ያስፈልገዋል። (የሐዋርያት ሥራ 2:38, 41፤ 8:12) ሕፃናት ደግሞ እነዚህን ነገሮች ማድረግ አይችሉም።

 በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ ሲባል ምን ማለት ነው?

 ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሚከተለውን መመሪያ ሰጥቷቸዋል፦ “ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ [አስተምሯቸው]።” (ማቴዎስ 28:19, 20) “በ . . . ስም” የሚለው አገላለጽ፣ የሚጠመቀው ግለሰብ አብና ወልድ ያላቸውን ሥልጣንና ቦታ እንዲሁም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚጫወተውን ሚና መረዳትና መቀበል እንዳለበት ያመለክታል። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ ለነበረው ሰው “በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነስና ተራመድ!” ብሎታል። (የሐዋርያት ሥራ 3:6) ይህ ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ ነው፦ ጴጥሮስ የክርስቶስን ሥልጣን የተቀበለ ከመሆኑም ሌላ ሽባ የነበረው ሰው የተፈወሰው በኢየሱስ እንደሆነ እውቅና ሰጥቷል።

  •   “አብ” የተባለው ይሖዋ c አምላክ ነው። ይሖዋ ፈጣሪ፣ ሕይወት ሰጪና ሁሉን ቻይ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ከሁሉ የላቀ ሥልጣን አለው።—ዘፍጥረት 17:1፤ ራእይ 4:11

  •   “ወልድ” የተባለው ሕይወቱን ለእኛ ሲል የሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ሮም 6:23) ኢየሱስ፣ አምላክ ለሰው ልጆች ባለው ዓላማ አፈጻጸም ውስጥ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና ካልተረዳንና ካልተቀበልን መዳን ልናገኝ አንችልም።—ዮሐንስ 14:6፤ 20:31፤ የሐዋርያት ሥራ 4:8-12

  •   “መንፈስ ቅዱስ” አምላክ የተለያዩ ነገሮችን ለማከናወን የሚጠቀምበት ኃይል ነው። d አምላክ ለመፍጠር፣ ሕይወት ለመስጠት፣ ለነቢያቱና ለሌሎች መልእክቱን ለማስተላለፍ እንዲሁም ፈቃዱን ለመፈጸም የሚያስችላቸውን ኃይል ለመስጠት ቅዱስ መንፈሱን ተጠቅሞበታል። (ዘፍጥረት 1:2፤ ኢዮብ 33:4፤ ሮም 15:18, 19) አምላክ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የእሱን ሐሳብ እንዲጽፉ ለመምራትም ቅዱስ መንፈሱን ተጠቅሟል።—2 ጴጥሮስ 1:21

 ድጋሚ መጠመቅ ኃጢአት ነው?

 ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ የሚወስኑ በርካታ ሰዎች አሉ። ሆኖም እነዚህ ሰዎች ቀደም ሲል በነበሩበት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠምቀው ከነበረስ? ድጋሚ ቢጠመቁ ኃጢአት ይሆንባቸዋል? አንዳንዶች አዎ የሚል መልስ ይሰጣሉ፤ ምናልባት እንዲህ የሚሉት ኤፌሶን 4:5 ላይ የሚገኘውን “አንድ ጌታ፣ አንድ እምነት፣ አንድ ጥምቀት አለ” የሚለውን ጥቅስ መሠረት በማድረግ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ይህ ጥቅስ አንድ ሰው ድጋሚ መጠመቅ እንደሌለበት የሚጠቁም አይደለም። እንዴት?

 የጥቅሱ አውድ። የኤፌሶን 4:5⁠ን አውድ ስንመለከት ሐዋርያው ጳውሎስ እውነተኛ ክርስቲያኖች በእምነት አንድ መሆናቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ጎላ አድርጎ እየገለጸ ነበር። (ኤፌሶን 4:1-3, 16) እንዲህ ያለው አንድነት ሊኖር የሚችለው አንድ ጌታ ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስን ከተከተሉ፣ አንድ እምነት ካላቸው ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚያስተምረው ነገር ተመሳሳይ አረዳድ ካላቸው እንዲሁም ከጥምቀት ጋር በተያያዘ አንድ ዓይነት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሥፈርት ከተከተሉ ብቻ ነው።

 ሐዋርያው ጳውሎስ ቀደም ሲል የተጠመቁ አንዳንድ ሰዎች ድጋሚ እንዲጠመቁ አበረታቷል። ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች የተጠመቁት የክርስትናን ትምህርት ሙሉ በሙሉ ሳይረዱ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 19:1-5

 አምላክ የሚቀበለው ጥምቀት። ጥምቀት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ከተፈለገ በትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) አንድ ሰው የተጠመቀው ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሚጋጩ የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶች ላይ ተመሥርቶ ከሆነ ጥምቀቱ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም። (ዮሐንስ 4:23, 24) ግለሰቡ ይህን እርምጃ የወሰደው ከልቡ ተነሳስቶ ቢሆንም “በትክክለኛ እውቀት ላይ [ተመሥርቶ]” አይደለም። (ሮም 10:2) በአምላክ ፊት ተቀባይነት ለማግኘት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር፣ የተማረውን ነገር ተግባር ላይ ማዋል፣ ሕይወቱን ለአምላክ መወሰንና ድጋሚ መጠመቅ ይኖርበታል። በዚህ ሁኔታ ሥር ድጋሚ መጠመቁ ኃጢአት አይሆንበትም። እንዲያውም እንዲህ ማድረጉ ተገቢ ይሆናል።

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ስለ ጥምቀት የሚናገሩ ሌሎች ዘገባዎች

 መጽሐፍ ቅዱስ የክርስቶስ ተከታዮች ውኃ ውስጥ በመጥለቅ ከሚጠመቁት ጥምቀት፣ የተለየ ትርጉም ወይም ዓላማ ስላላቸው ሌሎች ጥምቀቶችም ይናገራል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎች ተመልከት።

 መጥምቁ ዮሐንስ ያከናወነው ጥምቀት። e አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች የሙሴን ሕግ ማለትም አምላክ በሙሴ አማካኝነት ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን ሕግ በመጣስ ለፈጸሙት ኃጢአት ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየት ወደ ዮሐንስ እየሄዱ ይጠመቁ ነበር። የዮሐንስ ጥምቀት ሕዝቡ መሲሑን ይኸውም የናዝሬቱን ኢየሱስን ማወቅና መቀበል እንዲችሉ አዘጋጅቷቸዋል።—ሉቃስ 1:13-17፤ 3:2, 3፤ የሐዋርያት ሥራ 19:4

 ኢየሱስ ራሱ የተጠመቀው ጥምቀት። ኢየሱስ በመጥምቁ ዮሐንስ የተጠመቀው ጥምቀት ለየት ያለ ነበር። ኢየሱስ ፍጹም ሰው ሲሆን ምንም ኃጢአት አልነበረበትም። (1 ጴጥሮስ 2:21, 22) ስለዚህ የእሱ ጥምቀት ንስሐ መግባትን ወይም ‘ጥሩ ሕሊና ለማግኘት ለአምላክ ልመና ማቅረብን’ አይጨምርም። (1 ጴጥሮስ 3:21) ከዚህ ይልቅ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ ወይም ክርስቶስ በመሆን የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ራሱን ማቅረቡን የሚያሳይ ነበር። አምላክ ለኢየሱስ ያለው ፈቃድ ደግሞ ለእኛ ሲል ሕይወቱን መስጠቱን ይጨምራል።—ዕብራውያን 10:7-10

 በመንፈስ ቅዱስ መጠመቅ። መጥምቁ ዮሐንስም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ስለመጠመቅ ተናግረዋል። (ማቴዎስ 3:11፤ ሉቃስ 3:16፤ የሐዋርያት ሥራ 1:1-5) ይህ ጥምቀት በመንፈስ ቅዱስ ስም ከመጠመቅ ጋር አንድ አይደለም። (ማቴዎስ 28:19) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

 በመንፈስ ቅዱስ የሚጠመቁት ከኢየሱስ ተከታዮች መካከል የተወሰኑት ብቻ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው በምድር ላይ እንዲገዙ ስለተጠሩ በመንፈስ ቅዱስ ይቀባሉ። f (1 ጴጥሮስ 1:3, 4፤ ራእይ 5:9, 10) ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኢየሱስ ተከታዮች ተገዢዎቻቸው ይሆናሉ።—ማቴዎስ 5:5፤ ሉቃስ 23:43

 በክርስቶስ ኢየሱስ እና በሞቱ ውስጥ መጠመቅ። በመንፈስ ቅዱስ የሚጠመቁ ሰዎች ‘በክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥም’ ይጠመቃሉ። (ሮም 6:3) በመሆኑም ይህን ጥምቀት የሚጠመቁት ከኢየሱስ ጋር አብረው በሰማይ የሚገዙት ቅቡዓን ተከታዮቹ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ ውስጥ በመጠመቅ፣ ቅቡዓን ተከታዮቹን ያቀፈው ጉባኤ አባል ይሆናሉ። ኢየሱስ የጉባኤው ራስ፣ እነሱ ደግሞ አካል ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 12:12, 13, 27፤ ቆላስይስ 1:18

 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘የኢየሱስ ሞት ውስጥም’ ይጠመቃሉ። (ሮም 6:3, 4) የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል አምላክን በመታዘዝ ላይ ያተኮረ የመሥዋዕትነት ሕይወት ይመራሉ እንዲሁም በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋቸውን ይተዋሉ። ከሞቱ በኋላ መንፈሳዊ ፍጡር ሆነው በሰማይ ለመኖር ትንሣኤ ሲያገኙ ይህ ምሳሌያዊ ጥምቀት ይጠናቀቃል።—ሮም 6:5፤ 1 ቆሮንቶስ 15:42-44

 በእሳት መጠመቅ። መጥምቁ ዮሐንስ እያዳመጡት ለነበሩት ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እሱ [ኢየሱስ] በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል። ላይዳውን በእጁ ይዟል፤ አውድማውንም ፈጽሞ ያጸዳል፤ ስንዴውንም ወደ ጎተራ ያስገባል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል።” (ማቴዎስ 3:11, 12) በእሳት በመጠመቅና በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅ መካከል ልዩነት እንዳለ ልብ በል። ዮሐንስ ይህን አገላለጽ የተጠቀመው ምንን ለማመልከት ነው?

 ስንዴው የሚያመለክተው ኢየሱስን ሰምተው የሚታዘዙትን ሰዎች ነው። እነዚህ ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ የመጠመቅ ተስፋ አላቸው። ገለባው፣ ኢየሱስን ለመስማት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን ያመለክታል። የእነዚህ ሰዎች መጨረሻ በእሳት መጠመቅ ነው፤ ይህም ዘላለማዊ ጥፋትን ያመለክታል።—ማቴዎስ 3:7-12፤ ሉቃስ 3:16, 17

a ቫይንስ ኮምፕሊት ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ወርድስ የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “መጠመቅ” የሚለው የግሪክኛ ቃል “መግባትን፣ መጥለቅንና መውጣትን” ያመለክታል።

b “ክርስትና ማንሳት” የሚለው አገላለጽ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ለሕፃናት ስም በማውጣት ከዚያም ራሳቸው ላይ ውኃ በመርጨት ወይም በማፍሰስ የሚፈጽሙትን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ያመለክታል።

c ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (መዝሙር 83:18) “ይሖዋ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

dመንፈስ ቅዱስ ምንድን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

eመጥምቁ ዮሐንስ ማን ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

fወደ ሰማይ የሚሄዱት እነማን ናቸው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

g መጽሐፍ ቅዱስ “ጥምቀት” የሚለውን አገላለጽ ዕቃዎችን እንደመንከር ያሉ የመንጻት ሥነ ሥርዓቶችን ለማመልከት ይጠቀምበታል። (ማርቆስ 7:4 ግርጌ፤ ዕብራውያን 9:10 ግርጌ) እርግጥ ነው፣ ይህ ዓይነቱ ጥምቀት ኢየሱስም ሆነ ተከታዮቹ ከተጠመቁበት ውኃ ውስጥ መጥለቅን የሚጠይቅ ጥምቀት የተለየ ነው።