በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ ናቸው? ሁሉም ወደ አምላክ ያደርሳሉ?

ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ ናቸው? ሁሉም ወደ አምላክ ያደርሳሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የማይደሰትባቸው በርካታ ሃይማኖቶች እንዳሉ ይጠቅሳል። አምላክ የማይደሰትባቸውን ሃይማኖቶች በሁለት ዋና ዋና ምድቦች ልንከፍላቸው እንችላለን።

አንደኛው ምድብ፦ የሐሰት አማልክትን ማምለክ

 መጽሐፍ ቅዱስ የሐሰት አማልክትን ማምለክ “ከንቱ፣” “ዋጋ ቢስ” እና ‘ምንም ጥቅም የሌለው’ እንደሆነ ይገልጻል። (ኤርምያስ 10:3-5፤ 16:19, 20) ይሖዋ a አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ” የሚል ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። (ዘፀአት 20:3, 23፤ 23:24) እስራኤላውያን ሌሎች አማልክትን ባመለኩ ጊዜ ‘ይሖዋ እጅግ ተቆጥቶ’ ነበር።—ዘኁልቁ 25:3፤ ዘሌዋውያን 20:2፤ መሳፍንት 2:13, 14

 አምላክ ‘አማልክት ተብለው ለሚጠሩት’ ጣዖታት የሚቀርበውን አምልኮ በተመለከተ ዛሬም ተመሳሳይ አመለካከት አለው። (1 ቆሮንቶስ 8:5, 6ገላትያ 4:8) እሱን ማምለክ የሚፈልጉትን “ከመካከላቸው ውጡና ራሳችሁን ለዩ” በማለት የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች ከሆኑ ሰዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቋርጡ አዟቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:14-17) ሁሉም ሃይማኖቶች አንድ ከሆኑና ወደ አምላክ የሚያደርሱ ከሆኑ አምላክ እንዲህ ያለ ትእዛዝ የሰጠው ለምንድን ነው?

ሁለተኛው ምድብ፦ እውነተኛውን አምላክ እሱ በማይፈልገው መንገድ ማምለክ

 እስራኤላውያን እውነተኛውን አምላክ የሐሰት አማልክት በሚመለኩበት መንገድ ለማምለክ የሞከሩበት ጊዜ ነበር፤ ይሁንና ይሖዋ እውነተኛውን አምልኮ ከሐሰት አምልኮ ጋር ለመቀላቀል በመሞከራቸው ተቃውሟቸዋል። (ዘፀአት 32:8፤ ዘዳግም 12:2-4) ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች አምላክን ያመልኩበት የነበረውን መንገድ በተመለከተ አውግዟቸዋል፤ ሃይማኖተኛ መስለው ለመታየት ቢሞክሩም “በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ችላ” ስላሉ ግብዝ መሆናቸውን አስመሥክረዋል።—ማቴዎስ 23:23

 ዛሬም በተመሳሳይ ሰዎችን ወደ አምላክ የሚያደርሰው በእውነት ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት ብቻ ነው። ይህ እውነት የሚገኘው ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ዮሐንስ 4:24፤ 17:17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ትምህርቶችን የሚያስተምሩ ሃይማኖቶች ሰዎችን ከአምላክ ያርቃሉ። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እንደሆኑ አድርገው የሚያስቧቸው እንደ ሥላሴነፍስ አትሞትም እንዲሁም ዘላለማዊ ሥቃይ ያሉ ትምህርቶች የሐሰት አማልክትን ከሚያመልኩ ሰዎች የተወረሱ ናቸው። እንዲህ ያሉ ትምህርቶችን የሚያስፋፋ ሃይማኖት አምላክ ያወጣውን መመሪያ በሃይማኖታዊ ወጎች ስለሚተካ “ከንቱ” ወይም ዋጋ ቢስ ነው።—ማርቆስ 7:7, 8

 አምላክ ሃይማኖታዊ ግብዝነትን ይጠላል። (ቲቶ 1:16) አንድ ሃይማኖት፣ ሰዎች ወደ አምላክ እንዲቀርቡ ለማድረግ አንድን የአምልኮ ሥርዓት በዘልማድ ከመከተል ይልቅ ሰዎች በአኗኗራቸው ላይ ለውጥ እንዲያደርጉ ሊረዳቸው ይገባዋል። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ሃይማኖተኛ እንደሆነ ቢያስብም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን ያታልላል፤ አምልኮውም ከንቱ ነው። በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ ሃይማኖት ‘ወላጅ አልባ የሆኑ ልጆችንና መበለቶችን በመከራቸው መርዳት እንዲሁም ከዓለም እድፍ ራስን መጠበቅ’ ነው።”—ያዕቆብ 1:26, 27 የግርጌ ማስታወሻ

a መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የእውነተኛው አምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው