በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ | ትዳር

ቂምን መተው የሚቻልበት መንገድ

ቂምን መተው የሚቻልበት መንገድ

ተፈታታኙ ነገር

የትዳር ጓደኛሽ * የተናገረውን ወይም ያደረገውን መጥፎ ነገር መርሳት አልቻልሽም፤ የተናገራቸው ሸካራ ቃላትና የፈጸመው አሳቢነት የጎደለው ድርጊት ከአእምሮሽ ሊፋቁ አልቻሉም። በዚህም የተነሳ በአንድ ወቅት የነበረሽ ፍቅር በቂም ተተክቷል። ፍቅር አልባ የሆነውን ትዳርሽን ችለሽ ከመኖር ሌላ አማራጭ እንደሌለሽ ይሰማሻል። በዚህም ጭምር በትዳር ጓደኛሽ ላይ ቂም ይዘሻል።

ነገሮች ሊሻሻሉ እንደሚችሉ እርግጠኛ ሁኚ። በመጀመሪያ ግን ስለ ቂም ጥቂት እውነታዎችን እንመልከት።

ማወቅ የሚኖርብሽ ነገር

ቂም መያዝ ከባድ ሸክም ስለሚሆንባችሁ ትዳራችሁን መምራት እንዲከብዳችሁ ያደርጋል

ቂም ትዳርን ሊያፈርስ ይችላል። ለምን? ምክንያቱም ፍቅርን፣ ሐቀኝነትንና ታማኝነትን ጨምሮ ለትዳር መሠረት የሆኑት ባሕርያት እየከሰሙ እንዲሄዱ ያደርጋል። ከዚህ አንጻር ቂም በትዳር ውስጥ በተፈጠረ ችግር ሳቢያ የሚመጣ ነገር ሳይሆን ራሱ በትዳር ውስጥ የሚፈጠር ችግር ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ “የመረረ ጥላቻ . . . ከእናንተ መካከል ይወገድ” ማለቱ ተገቢ ነው።—ኤፌሶን 4:31

ቂም የምትይዢ ከሆነ የምትጎጂው ራስሽን ነው። ቂም መያዝ ራስን በጥፊ እየመቱ ሕመሙን ሌላ ሰው እንዲሰማው ከመጠበቅ ተለይቶ አይታይም። ማርክ ዚከል፣ ሂሊንግ ፍሮም ፋሚሊ ሪፍትስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “ቂም የያዛችሁበት የቤተሰብ አባል ስለ ጉዳዩ ምንም ስለማያውቅ በደስታ ሕይወቱን መምራቱን ቀጥሎ ይሆናል፤ ምናልባትም እናንተ የምታሳዩት ስሜት ምንም አልረበሸው ይሆናል።” ዋናው ነጥብ ምንድን ነው? ዚከል “ቂም የሚያደርስባችሁ ጉዳት ያስቀየማችሁ ሰው ካደረሰባችሁ ጉዳት ይበልጣል” ብለዋል።

^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ በአንስታይ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

ቂም መያዝ ወይም አለመያዝ በአንቺ ላይ የተመካ ነው። አንዳንድ ሰዎች ይህን ሐሳብ መቀበል ይከብዳቸው ይሆናል። ቂም እንዲይዙ ያደረጋቸው የትዳር ጓደኛቸው እንደሆነ ይገልጻሉ። ችግሩ፣ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ትኩረታችን ከቁጥጥራችን ውጪ በሆነ ነገር ላይ ማለትም በሌላ ሰው ድርጊት ላይ እንድናደርግ ያስገድደናል። መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ አማራጭ ያቀርባል። ‘እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሥራ ይፈትን’ ይላል። (ገላትያ 6:4) ሌላ ሰው የሚናገረውን ወይም የሚያደርገውን ነገር መቆጣጠር ባንችልም ጉዳዩን የምንይዝበትን መንገድ ግን መቆጣጠር እንችላለን። ቂም መያዝ ብቸኛው አማራጭ አይደለም።

 ምን ማድረግ ትችያለሽ?

ቂምን ለመተው ፈቃደኛ ሁኚ። እርግጥ ነው፣ የትዳር ጓደኛሽን ተጠያቂ ማድረግ ሊቀናሽ ይችላል። ይሁን እንጂ ቂም መያዝ በአንቺ ላይ የተመካ እንደሆነ አትርሺ። ይቅር ማለትም እንዲሁ። “ተቆጥታችሁ እያለ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ መምረጥ ትችያለሽ። (ኤፌሶን 4:26) ይቅር ባይ መሆን በትዳራችሁ ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በሰከነ መንፈስ እንድትመለከቺው ይረዳሻል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ቆላስይስ 3:13

ራስሽን በሐቀኝነት መርምሪ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንዳንድ ሰዎች “ቍጡ” እና “ግልፍተኛ” መሆን እንደሚቀናቸው ይገልጻል። (ምሳሌ 29:22) አንቺስ እንዲህ ዓይነት ችግር አለብሽ? እንደሚከተለው በማለት ራስሽን ጠይቂ፦ ‘ቁጣው የማይበርድለት ሰው ነኝ? በቀላሉ የምቀየም ነኝ? በጥቃቅን ነገሮች የመጨቃጨቅ ዝንባሌ አለኝ?’ መጽሐፍ ቅዱስ “ነገርን የሚደጋግም . . . የልብ ወዳጆችን ይለያያል” ይላል። (ምሳሌ 17:9፤ መክብብ 7:9) ይህ ሁኔታ በትዳር ውስጥም ሊያጋጥም ይችላል። በመሆኑም ቂም የመያዝ ዝንባሌ ካለሽ ‘የትዳር ጓደኛዬን ይበልጥ መታገሥ እችል ነበር?’ ብለሽ ራስሽን ጠይቂ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ጴጥሮስ 4:8

በእርግጥ መነጋገር የሚጠይቁ ጉዳዮችን ለዪ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:7) ጥፋት በተሠራ ቁጥር መነጋገር አያስፈልግም፤ አንዳንድ ጊዜ “በመኝታችሁ ሳላችሁ በልባችሁ አስቡ፤ ዝም በሉ” የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጉ በቂ ሊሆን ይችላል። (መዝሙር 4:4 የ1954 ትርጉም) ቅር በተሰኘሽበት ነገር ላይ መወያየት አስፈላጊ እንደሆነ ከተሰማሽ ደግሞ ቁጣሽ እስኪበርድ ጠብቂ። ቢያትሪስ የምትባል አንዲት ሚስት እንዲህ ብላለች፦ “እንደተጎዳሁ በሚሰማኝ ጊዜ በመጀመሪያ ለመረጋጋት ጥረት አደርጋለሁ። አንዳንድ ጊዜ በኋላ ላይ ሳስበው በደሉ ያን ያህል ከባድ እንዳልሆነ ስለምገነዘብ በአክብሮት መናገር ይበልጥ ቀላል ይሆንልኛል።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ምሳሌ 19:11

‘ይቅር ማለት’ ምን ትርጉም እንዳለው ተረጂ። መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ አንዳንድ ጊዜ ‘ይቅር ማለት’ ተብሎ የሚተረጎመው ቃል ‘አንድን ነገር መተው’ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ስለዚህ ይቅር ማለት ሲባል በደሉን አቅልለሽ መመልከት ወይም ምንም እንዳልተፈጠረ መሆን ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ቂም መያዝ ከበደሉ የበለጠ ጤንነትሽንና ትዳርሽን እንደሚጎዳው በመገንዘብ ጉዳዩን ትተዪዋለሽ ማለት ነው።

ቂም መያዝ ራስን በጥፊ እየመቱ ሕመሙን ሌላ ሰው እንዲሰማው ከመጠበቅ ተለይቶ አይታይም