በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

የትዳር ጓደኛችሁን በአክብሮት መያዝ

የትዳር ጓደኛችሁን በአክብሮት መያዝ

ዊል * እንዲህ ይላል፦ “ሬቸል ስትናደድ ያለማቋረጥ ታለቅሳለች። ለመነጋገር ከተቀመጥን ትነጫነጫለች፤ ይባስ ብላም ታኮርፈኛለች። ሁኔታው ምንም መፍትሔ ያለው አይመስልም። አሁን አሁን ተስፋ እየቆረጥኩ መጥቻለሁ።”

ሬቸል እንዲህ ትላለች፦ “ዊል ቤት ሲመጣ እያለቀስኩ ነበር። የተናደድኩበትን ምክንያት ላስረዳው ስሞክር ንግግሬን አቋረጠኝ። ያስለቀሰኝ ጉዳይ ያን ያህል የሚያሳስብ ነገር እንዳልሆነና እንድረሳው ነገረኝ። ይህ ደግሞ ይበልጥ አበሳጨኝ።”

እናንተስ፣ እንደ ዊል ወይም እንደ ሬቸል የሚሰማችሁ ጊዜ አለ? ዊልም ሆነ ሬቸል ሐሳባቸውን ለመግለጽ ቢሞክሩም ብዙውን ጊዜ እንዳሰቡት ስለማይሆንላቸው ለብስጭት ይዳረጋሉ። ለምን?

ወንዶችና ሴቶች ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መንገድ የተለያየ ነው፤ የሚፈልጉት ነገርም ቢሆን ይለያያል። ሴቶች ስሜታቸውን በግልጽ መናገር እንዲሁም ዘወትር የውስጣቸውን አውጥተው ማካፈል ይፈልጋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ ወንዶች ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ በመስጠትና በጣም አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮችን አንስቶ ለመወያየት ባለመፈለግ ሰላማቸውን ለመጠበቅ ይጥራሉ። ታዲያ እነዚህን ልዩነቶች ማስታረቅና ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? የትዳር ጓደኛችሁን በአክብሮት በመያዝ ነው።

ሰው አክባሪ የሆነ ግለሰብ ለሌሎች ከፍ ያለ ግምት ያለው ከመሆኑም ባሻገር ስሜታቸውን ለመረዳት ይጥራል። ከእናንተ የበለጠ ሥልጣን ወይም ተሞክሮ ያላቸውን ሰዎች ማክበር ተገቢ መሆኑን ከልጅነታችሁ ጀምሮ ተምራችሁ ይሆናል። ወደ ትዳር ስንመጣ ግን ሁኔታው ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም በትዳር ውስጥ አክብሮት እንድናሳይ የሚጠበቅብን በእኛ ደረጃ ላለ ሰው ማለትም ለትዳር ጓደኛችን ነው። ለስምንት ዓመታት በትዳር የቆየችው ሊንዳ “ፊል ሌሎች ሰዎች ሲያነጋግሩት በትዕግሥት እንደሚያዳምጣቸውና ስሜታቸውን እንደሚረዳላቸው አውቃለሁ” በማለት ተናግራለች። “እኔም የፈለግኩት ልክ ለሌሎቹ እንደሚያደርገው የእኔንም ስሜት እንዲረዳልኝ ብቻ ነው።” ምናልባት አንተም ጓደኞችህን ሌላው ቀርቶ ፈጽሞ የማታውቃቸውን ሰዎች በትዕግሥት የምታዳምጥ እንዲሁም እነዚህን ሰዎች በአክብሮት የምታነጋግር ልትሆን ትችላለህ። ለትዳር ጓደኛህስ የዚያኑ ያህል አሳቢ ነህ?

አክብሮት አለማሳየት በቤት ውስጥ ውጥረት እንዲነግሥ ሊያደርግና ወደ ከረረ ግጭት ሊመራ ይችላል። ጠቢብ የሆነ አንድ ንጉሥ “ጥልና ክርክር በበዛበት ቤት በታላቅ ግብዣ ላይ ከመገኘት ይልቅ፣ ሰላም ባለበት ቤት ደረቅ የዳቦ ፍርፋሪ መመገብ ይሻላል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 17:1 የ1980 ትርጉም) አንድ ባል፣ ሚስቱን በአክብሮት መያዝ እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (1 ጴጥሮስ 3:7) ሚስትም ብትሆን “ባሏን በጥልቅ ልታከብር ይገባል።”​—ኤፌሶን 5:33

ታዲያ አክብሮት በተሞላበት መንገድ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ አንዳንድ ጠቃሚ ምክሮችን እስቲ እንመልከት።

የትዳር ጓደኛችሁ መናገር ሲፈልግ

ተፈታታኙ ነገር፦

ብዙ ሰዎች ከማዳመጥ ይልቅ መናገር ይቀናቸዋል። አንተም እንደዚህ ዓይነት ሰው ነህ? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከማዳመጡ አስቀድሞ የሚመልስን’ ሰው ሞኝ እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። (ምሳሌ 18:13) ስለዚህ ከመናገርህ በፊት አዳምጥ። ለምን? በትዳር ዓለም 26 ዓመታት ያሳለፈችው ካራ “ባለቤቴ ወዲያውኑ ለችግሮቼ መፍትሔ ለመስጠት ባይሞክር እመርጣለሁ” በማለት ተናግራለች። አክላም “በተናገርኩት ነገር መስማማት ወይም የችግሩን መንስኤ ለማወቅ መጣር ላያስፈልገው ይችላል። እኔ የምፈልገው እንዲያዳምጠኝና ስሜቴን እንዲረዳልኝ ብቻ ነው” ብላለች።

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች ሐሳባቸውን ከመግለጽ ወደኋላ ሊሉ ይችላሉ፤ እንዲሁም የትዳር ጓደኞቻቸው ስሜታቸውን አውጥተው እንዲናገሩ ሲጫኗቸው ደስ ላይላቸው ይችላል። በቅርቡ ትዳር የመሠረተችው ሎሪ ባሏ ስሜቱን አውጥቶ ለመናገር ረጅም ጊዜ እንደሚወስድበት ተገንዝባለች። ሎሪ “ስሜቱን መግለጽ እስኪጀምር በትዕግሥት መጠበቅ አለብኝ” ብላለች።

መፍትሔው፦

ጭቅጭቅ ሊያስከትል ይችላል ብላችሁ ስለምታስቡት አንድ ጉዳይ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር መነጋገር በምትፈልጉበት ጊዜ ሁለታችሁም የምትረጋጉበትንና ዘና የምትሉበትን ጊዜ በመምረጥ ጉዳዩን አንስታችሁ ተወያዩ። የትዳር ጓደኛችሁ በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ፍላጎት ባያሳይስ? “የሰው ልብ ሐሳብ እንደ ጥልቅ ውሃ ነው፤ አስተዋይ ሰው ግን ከዚያ ቀድቶ ያወጣዋል” የሚለውን ጥቅስ አስታውሱ። (ምሳሌ 20:5) ከጉድጓድ ውስጥ በፍጥነት ውኃ ለመቅዳት ብትሞክሩ በጣም ብዙ ስለሚፈስባችሁ የምትፈልጉትን ያህል ውኃ ማግኘት አትችሉም። በተመሳሳይም የትዳር ጓደኛችሁ ሐሳቡን እንዲገልጽ ለማድረግ መጫን ግለሰቡ ጭራሹኑ ስሜቱን አውጥቶ እንዳይናገር ሊያደርገው ይችላል፤ ይህ ደግሞ በልቡ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ‘ቀድቶ ለማውጣት’ የነበራችሁን አጋጣሚ ያሳጣችኋል። ከዚህ ይልቅ በእርጋታና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ጥያቄዎችን አቅርቡ፤ እንዲሁም የትዳር ጓደኛችሁ እናንተ እንደምትፈልጉት ቶሎ ስሜቱን አውጥቶ ባይናገር ታጋሽ ሁኑ።

የትዳር ጓደኛችሁ በሚናገርበት ጊዜ ‘ለመስማት የፈጠናችሁ እንዲሁም ለመናገርና ለቁጣ የዘገያችሁ’ መሆን አለባችሁ። (ያዕቆብ 1:19) ጥሩ አድማጭ የሆነ ሰው ሌላው ሲናገር ጆሮውን ብቻ ሳይሆን ልቡንም ሰጥቶ ያዳምጣል። በመሆኑም የትዳር ጓደኛችሁ በሚናገርበት ጊዜ ስሜቱን ለመረዳት ጥረት አድርጉ። የትዳር ጓደኛችሁ የምታዳምጡበትን መንገድ በማየት ብቻ ምን ያህል እንደምታከብሩት ወይም እንደማታከብሩት ማስተዋል ይችላል።

ኢየሱስ እንዴት ማዳመጥ እንዳለብን አስተምሮናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የታመመ ሰው ለእርዳታ ወደ እሱ በቀረበበት ጊዜ ኢየሱስ መፍትሔ ለመስጠት አልቸኮለም። በመጀመሪያ የሰውየውን ልመና አዳመጠ። ከዚያም በሰማው ነገር ስሜቱ በጥልቅ ተነካ። በመጨረሻም ሰውየውን ፈወሰው። (ማርቆስ 1:40-42) እናንተም የትዳር ጓደኛችሁ በሚናገርበት ጊዜ ይህንኑ ምሳሌ ተከተሉ። ምናልባት የትዳር ጓደኛችሁ የሚፈልገው አፋጣኝ መፍትሔ ሳይሆን ስሜቱን ከልብ የሚረዳለት ሰው ሊሆን እንደሚችል አትዘንጉ። ስለዚህ በቅድሚያ በጥሞና አዳምጡ። ቀጥሎም ስሜቱን ለመረዳት ሞክሩ። ከዚያም ለትዳር ጓደኛችሁ የመፍትሔ ሐሳብ ለመስጠት ጥረት አድርጉ፤ አዎ፣ መፍትሔ መስጠት የመጨረሻው እርምጃ እንደሆነ አስታውሱ። እንዲህ በማድረግ የትዳር ጓደኛችሁን እንደምታከብሩ ታሳያላችሁ።

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በሚቀጥለው ጊዜ የትዳር ጓደኛችሁ እናንተን ማነጋገር ሲጀምር ወዲያውኑ ምላሽ እንድትሰጡት የሚገፋፋችሁን ውስጣዊ ስሜት ተቆጣጠሩ። የትዳር ጓደኛችሁ ተናግሮ እስኪጨርስ ጠብቁ፤ እንዲሁም ምንም ዓይነት ሐሳብ ከመስጠታችሁ በፊት ስሜቱን ተረዱ። ከዚያም የትዳር ጓደኛችሁን “ከልብ እያዳመጥኩህ እንደነበረ ተሰምቶሃል?” ብላችሁ ጠይቁት።

እናንተ መናገር ስትፈልጉ

ተፈታታኙ ነገር፦

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሊንዳ “በቴሌቪዥን የሚተላለፉ አንዳንድ አስቂኝ ፊልሞች ስለ ትዳር ጓደኛ መጥፎ ነገር ማውራት እንዲሁም የትዳር ጓደኛን መሳደብና በአሽሙር መናገር ምንም ችግር እንደሌለው አድርገው ያቀርባሉ” በማለት ተናገራለች። አንዳንዶች ያደጉት አክብሮት በጎደለው መንገድ መናገር በተለመደበት ቤት ውስጥ ነው። እነዚህ ሰዎች ከጊዜ በኋላ ሲያገቡ በራሳቸው ቤተሰብ ውስጥ ይህ ዓይነቱን ባሕርይ ማስወገድ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። በካናዳ የምትኖረው ኢቪ “ያደግኩት አሽሙር መናገር፣ መጯጯህና ክብርን ዝቅ የሚያደርጉ ቃላትን መጠቀም በተለመደበት ቤት ውስጥ ነው” ብላለች።

መፍትሔው፦

ለሌሎች ስለ ትዳር ጓደኛችሁ አንስታችሁ ስታወሩ “እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል ማንኛውም መልካም ቃል” ተናገሩ። (ኤፌሶን 4:29) ስለ ትዳር ጓደኛችሁ የምትናገሩበት መንገድ ሌሎች እሱን እንዲያከብሩት የሚያደርግ ይሁን።

ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ብቻችሁን በምትሆኑበት ጊዜም እንኳ በአሽሙር ከመናገር እንዲሁም ክብርን ዝቅ የሚያደርጉ ቃላትን ከመጠቀም ተቆጠቡ። በጥንቷ እስራኤል ትኖር የነበረችው ሜልኮል በአንድ ወቅት በባሏ በንጉሥ ዳዊት ተናዳ ነበር። “የእስራኤል ንጉሥ በመኳንንቱ ገረዶች ፊት እንደ አንድ ተራ ሰው ራቍቱን መታየቱ ክብሩ ሆኖ ነው!” በማለት በአሽሙር ተናግራው ነበር። አነጋገሯ ዳዊትን ቅር ያሰኘው ከመሆኑም በላይ አምላክን አሳዝኖታል። (2 ሳሙኤል 6:20-23) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ስትነጋገሩ ስለምትጠቀሙባቸው ቃላት በጥንቃቄ አስቡ። (ቆላስይስ 4:6) ትዳር ከመሠረተ ስምንት ዓመት የሆነው ፊል እሱና ሚስቱ አሁንም ድረስ በመካከላቸው አለመግባባት እንደሚፈጠር ሳይሸሽግ ተናግሯል። እሱ የሚናገረው ነገር አንዳንድ ጊዜ ሁኔታውን ጭራሽ እንደሚያባብሰው አስተውሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ተከራክሮ መርታት ሽንፈት እንጂ ‘ድል’ አለመሆኑን ማስተዋል ችያለሁ። ከዚህ ይልቅ ዝምድናችንን ማጠናከሩ ይበልጥ አስደሳችና ጠቃሚ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ።”

በጥንት ዘመን የኖረች አንዲት አረጋዊት መበለት ለምራቶቿ “በየባላችሁ ቤት ዕረፍት ይስጣችሁ” በማለት ምኞቷን ገልጻላቸው ነበር። (ሩት 1:9 የ1954 ትርጉም) ባልና ሚስት እርስ በርስ ሲከባበሩ ቤታቸው ‘የእረፍት’ ቦታ እንዲሆን ያደርጋሉ።

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በዚህ ንዑስ ርዕስ ሥር ባለው ሐሳብ ላይ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ለመወያየት ጊዜ መድቡ። ከዚያም የትዳር ጓደኛችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁት፦ “በሰዎች ፊት ስለ አንተ ስናገር እንዳከበርኩህ ይሰማሃል ወይስ እንዳቃለልኩህ? አነጋገሬን ለማሻሻል ምን ማስተካከያዎችን ባደርግ ጥሩ ነው?” የትዳር ጓደኛችሁ ስሜቱን አውጥቶ በሚናገርበት ጊዜ ከልባችሁ አዳምጡ። እንዲሁም የትዳር ጓደኛችሁ የሰጣችሁን ሐሳብ ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርጉ።

በመካከላችሁ የአመለካከት ልዩነት እንዳለ አምናችሁ ተቀበሉ

ተፈታታኙ ነገር፦

መጽሐፍ ቅዱስ ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” ይሆናሉ ሲል ሁለቱም አንድ ዓይነት አመለካከት ወይም ባሕርይ ሊኖራቸው ይገባል ማለቱ እንደሆነ አድርገው በተሳሳተ መንገድ የሚረዱ አዳዲስ ተጋቢዎች አሉ። (ማቴዎስ 19:5) ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ከእውነታው የራቀ እንደሆነ ወዲያውኑ ይገነዘባሉ። ከተጋቡ በኋላ በመካከላቸው ያሉት ልዩነቶች ብዙውን ጊዜ ጭቅጭቅ እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናሉ። ሊንዳ እንዲህ ትላለች፦ “በመካከላችን ያለው አንዱ ትልቅ ልዩነት ፊል የእኔን ያህል የማይጨነቅ መሆኑ ነው። አንዳንድ ጊዜ እኔ ስጨነቅ እሱ ግን ምንም ዓይነት የመረበሽ ስሜት አይታይበትም፤ በዚህ ጊዜ እኔን ያሳሰበኝ ጉዳይ ለእሱ ያን ያህል ግድ የማይሰጠው ስለሚመስለኝ እናደዳለሁ።”

መፍትሔው፦

አንዳችሁ የሌላውን ማንነት ተቀበሉ፤ እንዲሁም የትዳር ጓደኛችሁ ያለውን የተለየ አመለካከት አክብሩ። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ ዓይንና ጆሮ የሚሠሩበት መንገድ ይለያያል፤ ሆኖም ሁለቱም ተባብረው ስለሚሠሩ ምንም አደጋ ሳይደርስባችሁ የመኪና መንገድ ማቋረጥ ትችላላችሁ። በትዳር ዓለም ለሦስት አሥርተ ዓመታት ገደማ ያሳለፈችው ኤድሪን እንዲህ ትላለች፦ “አመለካከታችን ከአምላክ ቃል ጋር እስካልተጋጨ ድረስ እኔና ባለቤቴ አንዳችን ከሌላው የተለየ አመለካከት ያለን መሆኑ ቅር አያሰኘኝም። ደግሞም እኮ ተጋባን ማለት ፍጹም አንድ ዓይነት ሰው ሆነናል ማለት አይደለም።”

የትዳር ጓደኛችሁ ከእናንተ የተለየ አመለካከት በሚኖረው ወይም የተለየ ምላሽ በሚሰጥበት ጊዜ በራሳችሁ ፍላጎት ላይ ብቻ አታተኩሩ። የትዳር ጓደኛችሁን ስሜት ግምት ውስጥ አስገቡ። (ፊልጵስዩስ 2:4) የኤድሪን ባል የሆነው ካል እንደሚከተለው በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል፦ “ባለቤቴ በአንዳንድ ነገሮች ላይ ያላትን አመለካከት የማልረዳበት ወይም በሐሳቧ የማልስማማበት ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ እሷን ከራሴ አመለካከት በጣም አስበልጬ እንደምወዳት ለራሴ ደጋግሜ እነግረዋለሁ። እሷ ተደሰተች ማለት እኔም ተደሰትኩ ማለት ነው።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ የትዳር ጓደኛችሁ ያለው አመለካከት ወይም ነገሮችን የሚይዝበት መንገድ ከእናንተ የሚበልጠው በምን በምን መንገዶች እንደሆነ በዝርዝር ጻፉ።​—ፊልጵስዩስ 2:3

ትዳር ደስታ የሰፈነበትና ዘላቂ እንዲሆን ከሚያደርጉት ቁልፍ ነገሮች ውስጥ አንዱ አክብሮት ነው። “አክብሮት በትዳር ውስጥ ደስታና የደኅንነት ስሜት እንዲኖር ያደርጋል” በማለት ሊንዳ ተናግራለች። “በእርግጥም አክብሮት ልናዳብረው የሚገባ ባሕርይ ነው።”

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።

ራሳችሁን እንዲህ እያላችሁ ጠይቁ፦

  • የትዳር ጓደኛዬ ከእኔ የተለየ አመለካከት ያለው መሆኑ ቤተሰባችንን የጠቀመው እንዴት ነው?

  • የትዳር ጓደኛዬ የሚያደርገው ምርጫ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር እስካልተጋጨ ድረስ ከእሱ አመለካከት ጋር ለመስማማት ፈቃደኛ መሆኔ ጥሩ የሚሆነው ለምንድን ነው?