በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ንድፍ አውጪ አለው?

አንበጦች እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠሩበት የነርቭ ሴል

አንበጦች እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠሩበት የነርቭ ሴል

አንበጦች የሚጓዙት በመንጋ ነው፤ “በአንድ ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ውስጥ 80 ሚሊዮን” አንበጦች አብረው ሊበርሩ ይችላሉ። ያም ሆኖ አንዳቸው ከሌላው ጋር አይጋጩም። ሚስጥሩ ምንድን ነው?

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ከዓይኖቻቸው በስተ ጀርባ ሎቡላ ጃይንት ሙቭመንት ዲቴክተር ተብሎ የሚጠራ እንቅስቃሴን የሚቆጣጠር የነርቭ ሴል አለ። አንበጦቹ ሊጋጩ ሲቃረቡ እነዚህ ሴሎች ለክንፎቻቸውና ለእግሮቻቸው መልእክት በማስተላለፍ ፈጣን እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጋሉ። እንዲያውም እርምጃ የሚወስዱበት ፍጥነት ዓይን ከሚርገበገብበት በአምስት እጥፍ ይበልጣል።

የሳይንስ ሊቃውንት የአንበጦችን ዓይንና የነርቭ ሴሎች በመኮረጅ ራዳር ወይም ጨረር የሚጠቀም የተወሳሰበ መሣሪያ ሳያስፈልግ ከፊቱ የመጣበትን ነገር መለየትና መሸሽ የሚችል በኮምፒውተር የሚመራ ተንቀሳቃሽ ሮቦት መሥራት ችለዋል። ተመራማሪዎች ይህን ቴክኖሎጂ ተሽከርካሪዎችም ላይ እየተጠቀሙበት ነው፤ መሣሪያው ፈጣንና አስተማማኝ ማስጠንቀቂያ ስለሚሰጥ ግጭትን በእጅጉ መቀነስ ያስችላል። በዩናይትድ ኪንግደም የሊንከን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ሺጋንግ ዩዌ “እንደ አንበጣ ካለች አነስተኛ ፍጡር እንኳ ብዙ መማር ይቻላል” ብለዋል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? አንበጦች እንቅስቃሴያቸውን የሚቆጣጠሩበት የነርቭ ሴል በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?