በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | ትዳር

ይቅር ማለት የምትችሉት እንዴት ነው?

ይቅር ማለት የምትችሉት እንዴት ነው?

ተፈታታኙ ነገር

አንተና የትዳር ጓደኛህ በምትጨቃጨቁበት ጊዜ ቀደም ሲል መፍትሔ ማግኘት የነበረባቸውን ያለፉ ታሪኮች የማንሳት ልማድ አላችሁ? ከሆነ ችግሩ ምን ሊሆን ይችላል? አንዳችሁ ወይም ሁለታችሁም ይቅር ማለት ይከብዳችሁ ይሆናል።

እርግጥ ነው፣ ይቅር ማለትን መማር ትችላላችሁ። እስቲ በመጀመሪያ አንድ ባል ወይም አንዲት ሚስት ይቅር ማለት የሚከብዳቸው ለምን እንደሆነ እንመልከት።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

የበላይነት ማግኘት። አንዳንድ ባልና ሚስቶች ይቅርታ የማያደርጉት በትዳር ጓደኛቸው ላይ በሆነ መንገድ የበላይነት ማግኘት ስለሚፈልጉ ነው። በመሆኑም ሌላ ጊዜ ግጭት ሲነሳ ያለፈውን ታሪክ በትዳር ጓደኛቸው ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ይጠቀሙበታል።

ቂም መያዝ። አንድ ሰው በደል ሲፈጸምበት ቅሬታው እስኪሽር ድረስ ረጅም ጊዜ ሊወስድበት ይችላል። የትዳር ጓደኛውን ይቅር እንዳለ በአንደበቱ ይገልጽ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ በውስጡ ቂም ሊይዝ ይችላል። ምናልባትም ብድር ለመመለስ አጋጣሚ ይፈልግ ይሆናል።

የጠበቁት ሳይሆን ሲቀር። አንዳንድ ሰዎች ትዳር ውስጥ የሚገቡት በልብ ወለድ ታሪክ ውስጥ የሚቀርበው ዓይነት አስደሳች የፍቅር ሕይወት እንደሚኖራቸው ተስፋ በማድረግ ነው። ስለዚህ “ፍጹም ተስማሚ” የትዳር ጓደኛ ይሆነኛል ብለው ያሰቡት ሰው ለነገሮች ያለው አመለካከት ከእነሱ ጋር መስማማት እንዳለበት ስለሚጠብቁ አለመግባባት ሲነሳ እነሱ ሐሳባቸውን ለመቀየር ዝግጁዎች አይደሉም። በገሃዱ ዓለም ሊሆኑ የማይችሉ ነገሮችን መጠበቅ አንድን ሰው ስህተት ፈላጊ እንዲሆንና ይቅር ያለማለት ዝንባሌ እንዲያዳብር ሊያደርገው ይችላል።

አለመረዳት። ብዙ ባልና ሚስቶች ይቅር ለማለት የማይፈልጉት ይቅርታ ማድረጋቸው ሌላ መልእክት የሚያስተላልፍ ሆኖ ስለሚሰማቸው ነው። ለምሳሌ ያህል፦

ይቅር ካልኩኝ የተፈጸመውን በደል አቅልዬ እንደተመለከትኩት ያሳያል።

ይቅር ካልኩኝ የተፈጸመውን በደል መርሳት ይጠበቅብኛል።

ይቅር ካልኩኝ ሌላ ጊዜም እንደፈለገ እንዲሆን መብት ይሰጠዋል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ይቅር ማለት ከላይ የተጠቀሱትን መልእክቶች አያስተላልፍም። ያም ሆኖ ይቅርታ ማድረግ ከባድ ሊሆን ይችላል፤ በተለይ በባልና ሚስት መካከል ልዩ የሆነ ቅርርብ ስላለ ይህን ማድረግ ሊከብድ ይችላል።

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ይቅርታ ማድረግ ያለውን ትርጉም ተረዱ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ይቅርታ ማድረግ’ የሚለው ሐረግ “መተው” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍበት ጊዜ አለ። ስለዚህ ይቅርታ ማድረግ ሲባል የተፈጸመውን በደል መርሳት ወይም አቅልሎ መመልከት ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይቅርታ ማድረግ አንዳንድ ጊዜ የሚያመለክተው ለራሳችሁ ጤንነትና ለትዳራችሁ ስትሉ ጉዳዩን መተውን ነው።

ይቅር አለማለት ያሉትን መዘዞች ተረዱ። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት አንድ ሰው ቅሬታን ይዞ መቆየቱ፣ በትዳሩ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት ብንተወው እንኳ ግለሰቡን የመንፈስ ጭንቀትንና ከፍተኛ የደም ግፊትን ጨምሮ ለተለያዩ አካላዊና ስሜታዊ ችግሮች በከፍተኛ ሁኔታ ሊያጋልጠው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “አንዳችሁ ለሌላው ደጎችና ከአንጀት የምትራሩ ሁኑ፤ አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እርስ በርሳችሁ በነፃ ይቅር ተባባሉ” በማለት የሚናገረው ለዚህ ነው።—ኤፌሶን 4:32

ይቅር ማለት ያሉትን ጥቅሞች ተረዱ። ይቅር የማለት መንፈስ ማዳበር አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ በደልን እንዳትቆጥሩ እንዲሁም አንዳችሁ የሌላውን ድርጊት በመጥፎ እንዳትተረጉሙ ያስችላችኋል። ይህ ደግሞ በውስጣችሁ ቅሬታ እንዳትይዙና ፍቅራችሁ እያደገ እንዲሄድ ይረዳችኋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ቆላስይስ 3:13

እውነታውን ተቀበሉ። የትዳር ጓደኛችሁ ድክመት እንዳለበት አምናችሁ የምትቀበሉ ከሆነ ይቅር ማለት ቀላል ይሆንላችኋል። ትዳራችሁን መታደግ (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ብሏል፦ “ባላገኛችሁት ነገር ላይ የምታተኩሩ ከሆነ ያገኛችሁትን ነገር በቀላሉ ልትረሱት ትችላላችሁ። ታዲያ ማተኮር የምትፈልጉት በየትኛው ነገር ላይ ነው?” እናንተን ጨምሮ፣ ማንም ሰው ፍጹም እንዳልሆነ አስታውሱ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ያዕቆብ 3:2

ምክንያታዊ ሁኑ። ከዚህ በኋላ የትዳር ጓደኛችሁ የተናገረው ወይም ያደረገው ነገር ቅር ሲያሰኛችሁ ራሳችሁን እንደሚከተለው በማለት ጠይቁ፦ ‘ይህ ሁኔታ በእርግጥ ይህን ያህል ሊያስቀይመኝ ይገባል? ይቅርታ ልጠየቅ ይገባኛል ወይስ የተፈጸመውን ነገር ችላ ብዬ መተው እችላለሁ?’—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ 1 ጴጥሮስ 4:8

አስፈላጊ ከሆነ ጉዳዩን ተወያዩበት። ቅር የተሰኛችሁበትን ነገርና ጉዳዩ ለምን እንዳስቀየማችሁ ረጋ ብላችሁ ለትዳር ጓደኛችሁ ለማስረዳት ሞክሩ። የትዳር ጓደኛችሁን ሐሳብ በመጥፎ አትተርጉሙ፤ ወይም እኔ ያልኩት ካልሆነ ብላችሁ ድርቅ አትበሉ። እንዲህ ማድረግ የትዳር ጓደኛችሁ ራሱን ለመከላከል እንዲነሳሳ ከማድረግ ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ የትዳር ጓደኛችሁ ድርጊት ምን ስሜት እንዳሳደረባችሁ ብቻ ተናገሩ።