በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ጸሎት

ጸሎት

ጸሎታችንን የሚሰማ አካል አለ?

“ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ።”—መዝሙር 65:2

ሰዎች ምን ይላሉ?

ሰዎች ጸሎትህ ከጣሪያው አያልፍም” ሲሉ ሰምተህ ይሆናል። በተለይ በመከራ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጸሎታቸው የሚሰማላቸው ስለ መሆኑ ጥርጣሬ ሊገባቸው ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋ [አምላክ] ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ፤ ጆሮዎቹም ምልጃቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው፤ የይሖዋ ፊት ግን ክፉ ነገሮችን በሚያደርጉ ላይ ነው” ይላል። (1 ጴጥሮስ 3:12) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አምላክ ጸሎት ይሰማል። በተለይ ደግሞ መመሪያዎቹን የሚከተሉ ሰዎች የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሰማል። አንድ ሌላ ጥቅስም አምላክ ጸሎታችንን ለመስማት ፈቃደኛ መሆኑን ሲገልጽ “በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል” ይላል። (1 ዮሐንስ 5:14) በመሆኑም በቅን ልቦና ተነሳስተው ወደ አምላክ የሚጸልዩ ሰዎች ከፈቃዱ ጋር የሚስማማው ምን ዓይነት ልመና እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋቸዋል።

 መጸለይ ያለብን እንዴት ነው?

“በምትጸልዩበት ጊዜ . . . አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ።”—ማቴዎስ 6:7

ሰዎች ምን ይላሉ?

እንደ ቡድሂስት፣ ካቶሊክ፣ ሂንዱና እስልምና ያሉ አንዳንድ ሃይማኖቶች፣ ተከታዮቻቸው በመቁጠሪያዎች ተጠቅመው ጸሎታቸውን እየቆጠሩ እንዲደግሙ ያስተምራሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ጸሎት ከልብ የመነጨና የውስጥ ሐሳብን የሚገልጽ መሆን አለበት፤ ስለዚህ ተሸምድዶ በዘልማድ የሚደገም መሆን አይኖርበትም። ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ይሰጡናል፦ “በምትጸልዩበት ጊዜ አሕዛብ እንደሚያደርጉት አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ፤ እነሱ ቃላት በማብዛት ተሰሚነት የሚያገኙ ይመስላቸዋል። ስለዚህ እንደ እነሱ አትሁኑ፤ ምክንያቱም አባታችሁ የሆነው አምላክ ገና ሳትለምኑት ምን እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል።”—ማቴዎስ 6:7, 8

ይህን ማወቅ ለምን አስፈለገ?

አንድ ሰው ጸሎቱን በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት በሌለው መንገድ የሚያቀርብ ከሆነ ጊዜውን የሚያባክን ከመሆኑም በላይ አምላክን ሊያሳዝነው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ለመስማማት የማይፈልጉ ሰዎች የሚያቀርቡት ጸሎት በአምላክ ዘንድ “አስጸያፊ” እንደሆነ በመግለጽ ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 28:9

መጸለይ ያለብን ወደ ማን ነው?

“እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት።”—ኢሳይያስ 55:6

ሰዎች ምን ይላሉ?

አንዳንድ ሰዎች ወደ ማርያም ወይም “ቅዱሳን” ተደርገው ወደሚታዩ መላእክት አሊያም ሰዎች ይጸልያሉ። ከእነዚህ መካከል “በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ የሚያስፈልጉንን ነገሮች” ያሟላል ተብሎ የሚታመነው የፓጁወው “ቅዱስ” አንቶኒ እና “ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች” ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን እንደሚጠብቅ የሚታመነው “ቅዱስ” ይሁዳ ይገኙበታል። ብዙ ሰዎች፣ ከአምላክ ጋር እንደሚያማልዷቸው ተስፋ በማድረግ “ቅዱሳን” ተደርገው ወደሚታዩ እንዲህ ያሉ ሰዎችና ወደ መላእክት ይጸልያሉ።

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች መጸለይ ያለባቸው “በሰማይ [ወደሚኖረው] አባታችን” ነው። (ማቴዎስ 6:9) መጽሐፍ ቅዱስ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ” የሚል ማሳሰቢያ ይሰጣል።—ፊልጵስዩስ 4:6