በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የስኳር በሽታ—በበሽታው የመያዝ አጋጣሚህን መቀነስ ትችላለህ?

የስኳር በሽታ—በበሽታው የመያዝ አጋጣሚህን መቀነስ ትችላለህ?

በስኳር በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በመሄዱ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኗል። የስኳር በሽታ በዋነኝነት በሁለት ይከፈላል። አንደኛው፣ አብዛኛውን ጊዜ ከሕፃንነት የሚጀምር ሲሆን ሐኪሞች በአሁኑ ጊዜ ይህን ዓይነቱን የስኳር በሽታ እንዴት መከላከል እንደሚቻል አያውቁም። ሁለተኛው ደግሞ በዓለም ላይ ካሉት የስኳር በሽተኞች 90 በመቶ ገደማ የሚሆኑትን የሚያጠቃ ነው፤ ይህ ርዕስ የሚያተኩረው በዚህኛው የስኳር በሽታ ዓይነት ላይ ነው።

ሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ትላልቅ ሰዎችን ብቻ የሚያጠቃ እንደሆነ ተደርጎ ይታሰብ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ልጆችም በዚህ በሽታ መያዝ ጀምረዋል። ይሁን እንጂ በዚህኛው የስኳር በሽታ የመያዝ አጋጣሚን መቀነስ እንደሚቻል ባለሙያዎች ይናገራሉ። መሠሪ ስለሆነው ስለዚህ በሽታ መጠነኛ እውቀት ማግኘትህ ሊረዳህ ይችላል። *

የስኳር በሽታ ምንድን ነው?

የስኳር በሽታ አንድ ሰው በደሙ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን እንዲበዛ የሚያደርግ ችግር ነው። ሴሎች ኃይል ለማግኘት በደም ውስጥ የሚገኘውን ስኳር ይወስዳሉ፤ በሽታው ይህን ተፈጥሯዊ ሂደት ያዛባዋል። በዚህ ምክንያት ዋና ዋናዎቹ የአካል ክፍሎች የሚጎዱ ከመሆኑም ሌላ የደም ዝውውር ሥርዓት ችግር ያጋጥመዋል፤ ይህ ደግሞ ጣትና እግር እስከ ማጣት እንዲሁም እስከ መታወር ሊያደርስ ብሎም ለኩላሊት ሕመም ሊዳርግ ይችላል። ከስኳር በሽተኞች መካከል ብዙዎቹ በልብ ድካም ወይም ወደ አንጎል የሚሄደው የደም ሥር በሚያጋጥመው እክል (ስትሮክ) ሳቢያ ይሞታሉ።

ለሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ በዋነኝነት የሚያጋልጠው በሰውነት ውስጥ ያለው ስብ መብዛቱ ነው። በሆድና በወገብ አካባቢ የሚጠራቀም ስብ በስኳር በሽታ የመያዝን አጋጣሚ ከፍ እንደሚያደርግ ባለሙያዎች ያምናሉ። በተለይ በጣፊያና በጉበት ላይ ስብ መጠራቀሙ፣ ሰውነታችን በደም ውስጥ ያለውን ስኳር የሚቆጣጠርበትን ሥርዓት የሚያዛባ እንደሆነ ይታሰባል። ታዲያ በስኳር በሽታ የመያዝ አጋጣሚህን ለመቀነስ ምን ማድረግ ትችላለህ?

 በስኳር በሽታ የመያዝ አጋጣሚን ለመቀነስ የሚረዱ ሦስት እርምጃዎች

1. ለዚህ በሽታ ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች መካከል የምትመደብ ከሆነ በደምህ ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ተመርመር። አንድ ሰው በሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ ከመያዙ በፊት አብዛኛውን ጊዜ ቅድመ የስኳር በሽታ የተባለ የጤና ችግር ይኖርበታል፤ በዚህ ጊዜ በግለሰቡ ደም ውስጥ ያለው የስኳር መጠን ከመደበኛው በትንሹ ከፍ ይላል። የስኳር በሽታም ሆነ ቅድመ የስኳር በሽታ ለጤና አስጊ ቢሆኑም በመካከላቸው ልዩነት አለ፤ የስኳር በሽታን መቆጣጠር ቢቻልም እስከ አሁን ፈዋሽ መድኃኒት አልተገኘለትም። በሌላ በኩል ግን በቅድመ ስኳር በሽታ የተያዙ አንዳንድ ሰዎች በደማቸው ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ወደ መደበኛው ማውረድ ችለዋል። ቅድመ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ግልጽ የሆነ የሕመም ምልክት ላይታይባቸው ይችላል። ስለሆነም ችግሩ መኖሩ ልብ ሳይባል ሊቆይ ይችላል። ሪፖርቶች እንዳሳዩት በዓለም ዙሪያ 316 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ቅድመ የስኳር በሽታ አለባቸው፤ ይሁንና ብዙዎቹ ሕመሙ እንዳለባቸው እንኳ አያውቁም። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ቅድመ የስኳር በሽታ ካለባቸው ሰዎች መካከል 90 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ችግሩ እንዳለባቸው አያውቁም።

ይሁን እንጂ ቅድመ የስኳር በሽታ ምንም ጉዳት አያስከትልም ማለት አይደለም። ለሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ መንስኤ ከመሆኑም በላይ በመርሳት ችግር የመያዝ አጋጣሚን ከፍ እንደሚያደርግ በቅርቡ ተደርሶበታል። ወፍራም ከሆንክ፣ ብዙ እንቅስቃሴ የማታደርግ ከሆነ ወይም በዘርህ የስኳር በሽታ ያለበት ሰው ካለ ቅድመ የስኳር በሽታ ሊኖርብህ ይችላል። የደም ምርመራ በማድረግ ይህን ማረጋገጥ ትችላለህ።

2. ለጤና ተስማሚ የሆኑ ምግቦች ምረጥ። የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግህ ሊጠቅምህ ይችላል፦ ከወትሮ ያነሰ ምግብ ብላ። ስኳርነት ያላቸውን የፍራፍሬ ጭማቂዎችና ለስላሳ መጠጦች ከመጠጣት ይልቅ ውኃ፣ ሻይ ወይም ቡና ጠጣ። በፋብሪካ የሚዘጋጁ የምግብ ምርቶችን ከመጠቀም ይልቅ ካልተፈተገ እህል የተዘጋጀ ዳቦና ፓስታ እንዲሁም ያልተፈተገ ሩዝ በልክ ተመገብ። ጮማ የሌለበት ሥጋ፣ ዓሣ፣ ለውዝና ባቄላ ተመገብ።

3. አካላዊ እንቅስቃሴ አድርግ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በደምህ ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ሊቀንስና ክብደትህን ሊያስተካክል ይችላል። ቴሌቪዥን በማየት ከምናሳልፈው ጊዜ ውስጥ የተወሰነውን ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ መጠቀም እንደሚገባ አንድ ባለሙያ ገልጿል።

በዘር የወረስከውን ነገር መለወጥ ባትችልም አኗኗርህን መለወጥ ትችላለህ። ጤንነታችንን ለማሻሻል፣ የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን የማያስቆጭ እርምጃ ነው።

^ አን.3 ንቁ! አንድን ዓይነት የአመጋገብ ልማድ ወይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለይቶ በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አያቀርብም። እያንዳንዱ ግለሰብ ከጤና ጋር የተያያዘ ውሳኔ ከማድረጉ በፊት አማራጮቹን በጥንቃቄ መመዘንና አስፈላጊ ከሆነ ሐኪም ማማከር ይኖርበታል።