በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

እውነት ሲኦል አለ? የመጽሐፍ ቅዱሱ ሲኦል ምንድን ነው?

እውነት ሲኦል አለ? የመጽሐፍ ቅዱሱ ሲኦል ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ “ሲኦል” የሚለውን ቃል በአንዳንድ ጥቅሶች ላይ አስገብተውታል። (መዝሙር 16:10፤ የሐዋርያት ሥራ 2:27 የ1954 ትርጉም) በዚህ ርዕስ ላይ ያለው ሃይማኖታዊ ሥዕል እንደሚያሳየው፣ ብዙ ሰዎች ሲኦል ክፉ ሰዎች በእሳት የሚቀጡበት ዘላለማዊ መሠቃያ ቦታ እንደሆነ ያምናሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ ያስተምራል?

በዚህ ርዕስ ውስጥ፦

 ሲኦል፣ ሰዎች ለዘላለም የሚሠቃዩበት ቦታ ነው?

 አይደለም። “ሲኦል” የተባለው የዕብራይስጥ ቃልም ሆነ አቻው የሆነው “ሐዲስ” የተባለው ግሪክኛ ቃል መሠረታዊ ትርጉማቸው “መቃብር” የሚል ነው፤ የሰው ልጆች ሁሉ ሲሞቱ የሚሄዱበትን መቃብር ያመለክታል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያሳየው፣ ወደ ሲኦል ወይም ወደ “መቃብር” የሄዱ ሰዎች በሕይወት የሉም።

  •   የሞቱ ሰዎች ምንም አያውቁም፤ ስለዚህ ምንም ዓይነት ሥቃይ አይሰማቸውም። “በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና።” (መክብብ 9:10 የ1954 ትርጉም) ሲኦል የሥቃይ ድምፅ የሚሰማበት ቦታ አይደለም። በተቃራኒው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ክፉዎች ይፈሩ በሲኦልም ዝም ይበሉ።”—መዝሙር 31:17፤ 115:17 የ1954 ትርጉም

  •   አምላክ በደነገገው መሠረት የኃጢአት ቅጣት፣ ሞት እንጂ ሲኦል ውስጥ በእሳት መቃጠል አይደለም። አምላክ ለመጀመሪያው ሰው ለአዳም የነገረው የአምላክን ሕግ ቢጥስ በሞት እንደሚቀጣ ነው። (ዘፍጥረት 2:17) በሲኦል ለዘላለም እንደሚሠቃይ አልነገረውም። አዳም ኃጢአት ከሠራ በኋላ ደግሞ አምላክ ቅጣቱ ምን እንደሆነ ሲነግረው “አፈር ስለሆንክ ወደ አፈር ትመለሳለህ” ብሎታል። (ዘፍጥረት 3:19) ከመኖር ወደ አለመኖር ይሄዳል ማለት ነው። የአምላክ ሐሳብ አዳምን ሲኦል እሳት ውስጥ መክተት ቢሆን ኖሮ ይህን ይነግረው እንደነበረ ምንም ጥያቄ የለውም። አምላክ ሕጎቹን መጣስ የሚያስከትለውን ቅጣት አልቀየረውም። አዳም ኃጢአት ከሠራ ከብዙ ዓመታት በኋላ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ በአምላክ መንፈስ መሪነት “የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነው” ሲል ጽፏል። (ሮም 6:23) ከዚህ ተጨማሪ ቅጣት የሚጣልበት ምክንያት የለም፤ ምክንያቱም “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል።”—ሮም 6:7

  •   አምላክ ሰዎችን ለዘላለም ሊያሠቃይ ቀርቶ ሐሳቡ እንኳ ይዘገንነዋል። (ኤርምያስ 32:35) ይህ ሐሳብ “አምላክ ፍቅር ነው” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር ይጋጫል። (1 ዮሐንስ 4:8) አምላክ እንድናመልከው የሚፈልገው እሱን ወደነው እንጂ ለዘላለም ያሠቃየናል ብለን ፈርተን አይደለም።—ማቴዎስ 22:36-38

  •   ጥሩ ሰዎች ወደ ሲኦል ሄደዋል። “ሲኦል” የሚለውን ቃል ከተጠቀሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንደምንረዳው እንደ ያዕቆብ እና ኢዮብ ያሉ ታማኝ ሰዎች ሲኦል እንሄዳለን ብለው ይጠብቁ ነበር። (ዘፍጥረት 37:35፤ ኢዮብ 14:13) ኢየሱስ ክርስቶስም እንኳ ሞቶ እስኪነሳ ባለው ጊዜ ውስጥ በሲኦል እንደቆየ ተገልጿል። (የሐዋርያት ሥራ 2:31, 32) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው፣ በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ “ሲኦል” የሚለው ቃል የሚያመለክተው መቃብርን ነው።

 የአልዓዛር እና የሀብታሙ ሰው ምሳሌስ?

 ይህን ምሳሌ የተናገረው ኢየሱስ ሲሆን በሉቃስ 16:19-31 ላይ ይገኛል። ኢየሱስ ሥነ ምግባር ለማስተማር ወይም መንፈሳዊ እውነቶችን ለመግለጥ በምሳሌዎች ይጠቀም ነበር። የአልዓዛር እና የሀብታሙ ሰው ምሳሌ እውነተኛ ታሪክ አይደለም። (ማቴዎስ 13:34) የዚህን ምሳሌ ትርጉም ለመረዳት “ሀብታሙ ሰውና አልዓዛር እነማን ናቸው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

 ሲኦል፣ ከአምላክ መለየትን የሚያመለክት ነው?

 አይደለም። የሞቱ ሰዎች ከአምላክ መለየታቸው ይታወቃቸዋል የሚለው ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይጋጫል፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ምንም እንደማያውቁ በግልጽ ያስተምራል።—መዝሙር 146:3, 4፤ መክብብ 9:5

 ከሲኦል ወጥቶ የሚያውቅ ሰው አለ?

 አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወደ መቃብር (በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ “ሲኦል”) ከወረዱ በኋላ በትንሣኤ አማካኝነት እንደገና ሕይወት ስላገኙ ዘጠኝ ሰዎች ታሪክ ይናገራል። a እነዚህ ሰዎች ሲኦል ውስጥ የቆዩበት ጊዜ ቢታወቃቸው ኖሮ በኋላ ላይ በዚያ ስላሳለፉት ጊዜ ይናገሩ ነበር። የሚገርመው ግን፣ ከዘጠኙ መካከል አንዳቸውም እንደተሠቃዩም ሆነ ሌላ ምንም ዓይነት ስሜት እንደተሰማቸው አልተናገሩም። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ እንደሚገልጸው፣ እነዚህ ሰዎች ጭልጥ ያለ “እንቅልፍ” የወሰዳቸው ያህል ምንም ስለማያውቁ ነው።—ዮሐንስ 11:11-14፤ 1 ቆሮንቶስ 15:3-6