በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ከሙስና የጸዳ መንግሥት

የአምላክ መንግሥት—ከሙስና የጸዳ መስተዳድር

የአምላክ መንግሥት—ከሙስና የጸዳ መስተዳድር

የኒካራጉዋ መንግሥት ዋና ኦዲተር፣ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚፈጸመውን ሙስና ማስወገድ እንደማይቻል የሚሰማቸው ለምን እንደሆነ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ “ምንም ተባለ ምን የሕዝብ ባለሥልጣናት ያው የአገሩ ዜጎች ናቸው፤ ሁላችንም የማኅበረሰቡ ውጤት ነን።”

‘የማኅበረሰቡ ሥነ ምግባር የተበላሸ ከሆነ ከዚህ ማኅበረሰብ የሚወጣ ማንኛውም መንግሥት የሥነ ምግባር ችግር ይኖርበታል’ ቢባል አትስማማም? ሁኔታው ይህ ከሆነ ደግሞ ከሙስና የጸዳ መንግሥት ሊኖር የሚችለው ከማኅበረሰቡ ውጭ በሆነ አካል ከተቋቋመ ብቻ ነው ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ስላለው መንግሥት ማለትም ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገር ሲሆን ኢየሱስ ተከታዮቹን ስለዚህ መንግሥት እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል።—ማቴዎስ 6:9, 10

የአምላክ መንግሥት፣ በሰማይ ሆኖ የሚገዛ እውነተኛ መስተዳድር ነው። ይህ መንግሥት ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት አጥፍቶ በምትካቸው ይገዛል። (መዝሙር 2:8, 9፤ ራእይ 16:14፤ 19:19-21) መንግሥቱ ለሰው ልጆች ከሚያመጣቸው በረከቶች መካከል አንዱ ሙስናን ማስወገድ ነው። የአምላክ መንግሥት ይህን እንደሚፈጽም እንድንተማመን የሚያደርጉ ስድስት ነጥቦችን እስቲ እንመልከት።

1. ሥልጣን

ችግሩ፦ ሰብዓዊ መንግሥታት የሚተዳደሩት በአብዛኛው በግብርና በቀረጥ መልክ ከዜጎቻቸው በሚሰበሰበው ገንዘብ ነው። ይህም አንዳንድ ባለሥልጣናት ከሕዝብ የሚገኘውን ገንዘብ ለመስረቅ እንዲፈተኑ ያደርጋል፤ ሌሎቹ ደግሞ ለመንግሥት የሚከፍሉት ግብር ወይም ሌላ ክፍያ እንዲቀነስላቸው ከሚፈልጉ ግለሰቦች ጉቦ ለመቀበል ይፈተናሉ። መንግሥት በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን የገንዘብ ኪሳራ ለማካካስ ሲል ግብር ይጨምራል፤ ይህ ደግሞ ሙስና ይበልጥ እንዲስፋፋ በር ይከፍታል፤ በመሆኑም ማቆሚያ የሌለው ሽክርክሪት ይፈጠራል። በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የሚጎዱት ሐቀኛ የሆኑ ሰዎች ናቸው።

መፍትሔው፦ የአምላክ መንግሥት ሥልጣኑን ያገኘው ሁሉን ቻይ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ነው። * (ራእይ 11:15) የአምላክ መንግሥት ለሚያከናውናቸው ሥራዎች ማስኬጃ እንዲሆን  ከዜጎቹ ግብር መሰብሰብ አያስፈልገውም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ‘ታላቅ ኃይል’ ያለው ከመሆኑም ሌላ ለጋስ ነው፤ በመሆኑም ለመንግሥቱ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር በሙሉ ማቅረብ ይችላል።—ኢሳይያስ 40:26፤ መዝሙር 145:16

2. መሪ

ችግሩ፦ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ሱዛን ሮዝአከርማን ሙስናን ለማስወገድ የሚደረገው ጥረት “ከላይ መጀመር አለበት” በማለት ገልጸዋል። መንግሥታት የጉምሩክ ባለሥልጣናት ወይም ፖሊሶች ሙስና እንዳይፈጽሙ ለማድረግ እየጣሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚፈጸሙትን ሙስና ግን ቸል ስለሚሉ ተደማጭነት ያጣሉ። ደግሞም በጣም ሐቀኛ ነው የሚባለው መሪም እንኳ ፍጹም አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግ . . . ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም።”—መክብብ 7:20

ኢየሱስ፣ እስከ ዛሬ ለሰዎች ከቀረቡት ሁሉ የሚበልጠውን ጉቦ ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነም

መፍትሔው፦ ፍጹም ካልሆኑት የሰው ልጆች በተለየ መልኩ አምላክ የመንግሥቱ መሪ እንዲሆን የመረጠው ኢየሱስ ክርስቶስ መጥፎ ነገር ለመሥራት አይፈተንም። ኢየሱስ እስከ ዛሬ ለሰዎች ከቀረቡት ሁሉ የሚበልጠውን ጉቦ ይኸውም “የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን” ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆን ይህን አሳይቷል። የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ዲያብሎስ፣ ኢየሱስ አንድ ጊዜ ብቻ ተደፍቶ ቢሰግድለት ይህን ጉቦ እንደሚሰጠው ቃል ገብቶ ነበር። (ማቴዎስ 4:8-10፤ ዮሐንስ 14:30) ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት ከፍተኛ ሥቃይ ቢደርስበትም እንኳ ታማኝነቱን ለመጠበቅ ቆርጦ ነበር፤ በመሆኑም የሚያደነዝዝ መድኃኒት በሰጡት ጊዜ ሥቃዩን ሊቀንስለት እንደሚችል ቢያውቅም ስሜቱን መቆጣጠር እንዳይሳነው ሲል መድኃኒቱን ለመጠጣት ፈቃደኛ አልሆነም። (ማቴዎስ 27:34) አምላክ ከሞት አስነስቶ ሰማያዊ ሕይወት የሰጠው ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት መሪ የመሆን ብቃት እንዳለው አስመሥክሯል።—ፊልጵስዩስ 2:8-11

3. መረጋጋት

ችግሩ፦ ብዙ አገሮች በየጊዜው ምርጫ የሚያካሂዱ ሲሆን ይህም ሕዝቡ ሙሰኛ ባለሥልጣናትን ከሥልጣን ለማውረድ አጋጣሚ እንደሚሰጠው ይታሰባል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ ያደጉ ናቸው በሚባሉት አገሮች ውስጥ የሚካሄዱት የምረጡኝ ቅስቀሳዎችና ምርጫዎችም እንኳ ለሙስና የተጋለጡ ናቸው። ሀብታሞች ለምረጡኝ ቅስቀሳዎችና ለሌሎች ነገሮች የገንዘብ እርዳታ በመስጠት በሥልጣን ላይ ባሉትም ሆነ ወደፊት ሥልጣን በሚይዙት ባለሥልጣናት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራሉ።

የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ጆን ፖል ስቲቨንስ እንዲህ ዓይነቱ ተጽዕኖ “በመንግሥት ሕጋዊነትና ጥራት ላይ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ በመንግሥት ላይ በሚኖረው እምነት ላይም” ስጋት እንደሚፈጥር ጽፈዋል። ከዚህ አንጻር ሲታይ በመላው ዓለም የሚኖሩ ብዙ ሰዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከየትኛውም ተቋም የበለጠ ሙሰኛ እንደሆኑ ማሰባቸው አያስደንቅም።

መፍትሔው፦ የአምላክ መንግሥት ቋሚና ዘላቂ አገዛዝ ስለሆነ ከምርጫ ቅስቀሳም ሆነ ከምርጫ ጋር የተያያዙ የሙስና ድርጊቶች አይኖሩም። (ዳንኤል 7:13, 14) እንዲሁም መሪው የተመረጠው በአምላክ ስለሆነ በዜጎች ድምፅ ከሥልጣን ሊወርድ አይችልም። የአምላክ መንግሥት ቋሚ ስለሆነ የሚወስዳቸው እርምጃዎች  ለተገዢዎቹ ዘላቂ ጥቅም የሚያመጡ ናቸው።

4. ሕጎች

የአምላክ መንግሥት፣ በሰማይ ሆኖ የሚገዛ እውነተኛ መስተዳድር ነው

ችግሩ፦ አዳዲስ ሕጎችን ማውጣት ችግሩን ሊያሻሽል እንደሚችል ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ሕጎችን ማብዛት ለሙስና ተጨማሪ አጋጣሚዎችን እንደሚከፍት ባለሙያዎች ደርሰውበታል። ከዚህም ሌላ ሙስናን ለመቀነስ ታስበው የሚወጡ ሕጎችን ማስፈጸም በአብዛኛው ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል፤ ያም ቢሆን ግን ያን ያህል ውጤታማ አይደለም።

መፍትሔው፦ የአምላክ መንግሥት ሕጎች ሰብዓዊ መንግሥታት ከሚያወጧቸው ሕጎች እጅግ የላቁ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ አድርግ እና አታድርግ የሚሉ ብዙ ደንቦችን ከመዘርዘር ይልቅ ወርቃማው ሕግ እየተባለ የሚጠራውን ትእዛዝ ሰጥቷል። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል።” (ማቴዎስ 7:12) የአምላክ መንግሥት ሕጎች ያላቸው አንዱ ጥሩ ገጽታ በሰዎች ድርጊት ላይ ብቻ ሳይሆን አንድን ነገር እንዲፈጽሙ በሚያነሳሳቸው ውስጣዊ ዝንባሌም ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸው ነው። ኢየሱስ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል። (ማቴዎስ 22:39) እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነቶቹን ትእዛዛት በትክክል ማስፈጸም የሚችለው ልብን ማንበብ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።—1 ሳሙኤል 16:7

5. የሰዎች ዝንባሌ

ችግሩ፦ ሰዎች ሙስናን እንዲፈጽሙ የሚገፋፏቸው ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት ናቸው። የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆኑ ሌሎች ዜጎች ብዙውን ጊዜ እነዚህ አሉታዊ ባሕርያት አሏቸው። ለምሳሌ፣ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው በሶል ከተማ ውስጥ የነበረው የገበያ አዳራሽ እንዲደረመስ ምክንያት የሆነው ባለሥልጣናቱ ከሕንፃ ተቋራጮቹ ጉቦ መቀበላቸው ነበር፤ የሕንፃ ተቋራጮቹ ይህን ያደረጉት ተገቢውን የግንባታ ቁሳቁስ ተጠቅመው ደረጃውን የጠበቀ ሕንፃ መገንባት የበለጠ ወጪ እንደሚጠይቅባቸው ስለተሰማቸው ነበር።

እንግዲያውስ ሙስናን ለማጥፋት ከተፈለገ ሰዎች እንደ ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት ያሉ ሥር የሰደዱ አሉታዊ ባሕርያትን እንዴት ማስወገድ እንደሚችሉ መማር አለባቸው። ይሁን እንጂ ሰብዓዊ መንግሥታት እንዲህ ዓይነቱን የትምህርት መርሐ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው የላቸውም።

 መፍትሔው፦ የአምላክ መንግሥት ሰዎች ለሙስና መንስኤ የሆኑ መጥፎ ዝንባሌዎችን እንዴት ማስወገድ እንደሚችሉ በማስተማር ሙስናን ከሥሩ ነቅሎ ያስወግደዋል። * ሰዎች ይህን ትምህርት ማግኘታቸው ‘አእምሯቸውን በሚያሠራው ኃይል እንዲታደሱ’ ይረዳቸዋል። (ኤፌሶን 4:23) በስግብግብነትና በራስ ወዳድነት ፈንታ ያለኝ ይበቃኛል ማለትንና ለሌሎች አሳቢነት ማሳየትን ይማራሉ።—ፊልጵስዩስ 2:4፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6

6. ዜጎች

ችግሩ፦ ጥሩ የሥነ ምግባር ትምህርት በሚሰጥበትና ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ በሚነገርለት አካባቢም እንኳ አንዳንዶች ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ሊፈጽሙ እንዲሁም ሙሰኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ባለሙያዎች፣ መንግሥታት ሙስናን ማጥፋት የማይችሉበት አንዱ ምክንያት ይህ እንደሆነ ይገልጻሉ። በመሆኑም መንግሥታት ሙስናንና የሚያስከትለውን ጎጂ ውጤት ለመቀነስ ከመጣር ባለፈ ምንም ማድረግ አይችሉም።

መፍትሔው፦ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት ፀረ ሙስናን በተመለከተ ባደረጉት ስምምነት ላይ እንደተገለጸው መንግሥታት ሙስናን ለመዋጋት በአገራቸው የሚገኙ የሕዝብ ባለሥልጣናት “ታማኞች፣ ሐቀኞችና ኃላፊነት የሚሰማቸው” እንዲሆኑ ማበረታታት ይኖርባቸዋል። ይህ ክቡር ዓላማ ቢሆንም የአምላክ መንግሥት፣ ዜጎቹ እነዚህ ባሕርያት እንዲኖሯቸው ከማበረታታት ያለፈ ነገር ያደርጋል፤ የአምላክ መንግሥት፣ ዜጎቹ እነዚህን ባሕርያት እንዲያሳዩ ይጠብቅባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ስግብግቦች” እና “ውሸታሞች” የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11፤ ራእይ 21:8

የጥንቶቹ ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ሁሉ ሰዎች እነዚህን ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር ደንቦች በጥብቅ መከተል ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ስምዖን የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ለሐዋርያት ጉቦ በመስጠት አንድ ዓይነት መንፈሳዊ ስጦታ ለማግኘት በሞከረበት ወቅት ሐዋርያቱ ጉቦውን ከመቀበል ይልቅ “ከዚህ ክፋትህ ንስሐ ግባ” ብለውት ነበር። ስምዖን፣ በልቡ ያለው መጥፎ ዝንባሌ አደጋ ሊያስከትልበት እንደሚችል ሲገነዘብ ይህን መጥፎ ምኞቱን ማሸነፍ ይችል ዘንድ እንዲጸልዩለት ሐዋርያቱን ለመናቸው።—የሐዋርያት ሥራ 8:18-24

የአምላክ መንግሥት ዜጋ መሆን—እንዴት?

የየትኛውም አገር ዜጋ ብትሆን የአምላክ መንግሥት ዜጋ የመሆን አጋጣሚ አለህ። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) የአምላክ መንግሥት በመላው ዓለም እያካሄደ ያለው የትምህርት መርሐ ግብር የዚህ መንግሥት ዜጋ መሆን የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንድትገነዘብ ይረዳሃል። የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ሊያስተምሩህ ፈቃደኞች ናቸው፤ በሳምንት አሥር ደቂቃ ያህል እንኳ በመመደብ ይህን ትምህርት መቅሰም ትችላለህ። በዚህ የትምህርት ፕሮግራም ላይ ስለ ‘አምላክ መንግሥት ምሥራች’ እና ይህ መንግሥት ሙስናን የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነ ትማራለህ። (ሉቃስ 4:43) በመሆኑም በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች እንድታነጋግራቸው ወይም ደግሞ jw.org የተሰኘውን ድረ ገጻችንን እንድትጎበኝ እንጋብዝሃለን።

መጽሐፍ ቅዱስን ያለ ክፍያ መማር ትፈልጋለህ?

^ አን.8 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።

^ አን.22 ለምሳሌ ያህል፣ በጥቅምት 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ሙስና በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ሐቀኛ መሆን ይቻላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።