በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

የብልግና ምስሎች—ጎጂ ናቸው?

የብልግና ምስሎች—ጎጂ ናቸው?

በዛሬው ጊዜ የብልግና ምስሎች በዓለም ላይ እንደ አሸን ፈልተዋል። a የብልግና ምስሎች በማስታወቂያዎች፣ በፋሽኖች፣ በፊልሞች፣ በሙዚቃዎች፣ በመጽሔቶች አልፎ ተርፎም በቴሌቪዥን፣ በቪዲዮ ጨዋታዎች፣ በዘመናዊ ሞባይሎች፣ በተንቀሳቃሽ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችና በድረ ገጾች፣ አሁን አሁን ደግሞ በኢንተርኔት የፎቶ መለዋወጫዎች ጭምር ሊገኙ ይችላሉ። በዚህ ዘመን የብልግና ምስሎች በሰፊው ተቀባይነት እያገኙ የመጡ ይመስላል። የብልግና ምስሎችን የሚያዩ ሰዎች ቁጥር፣ የሚያዩት መጠንና የተስፋፉባቸው ቦታዎች በታሪክ ውስጥ የአሁኑን ያህል የጨመረበት ጊዜ የለም።— “የብልግና ምስሎችን የተመለከተ መረጃ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

የብልግና ምስሎቹ የሚዘጋጁበት መንገድም ቢሆን እየተቀየረ መጥቷል። ፕሮፌሰር ጌል ዳይንስ የተባሉ ሴት እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “በዛሬው ጊዜ ያሉ የብልግና ምስሎች አስጸያፊነታቸው እየጨመረ በመምጣቱ ቀደም ሲል በጣም አስነዋሪ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ የነበሩ ምስሎች አሁን ግን የተለመዱ ሆነዋል።”

የብልግና ምስሎች መስፋፋታቸውና አስጸያፊነታቸው መጨመሩ በአንተ ላይ ለውጥ ያመጣል? የብልግና ምስሎችን የምትመለከታቸው እንዴት ነው? ምንም ጉዳት እንደሌላቸው ጊዜ ማሳለፊያዎች? እንደ ገዳይ መርዝ? ወይስ ሁለቱም ሐሳቦች ተጋንነዋል? ኢየሱስ “ጥሩ ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያፈራል፤ የበሰበሰ ዛፍ ሁሉ ግን የማይጠቅም ፍሬ ያፈራል” ብሏል። (ማቴዎስ 7:17) ታዲያ የብልግና ምስሎች ምን ዓይነት ፍሬ እያፈሩ ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ በመጀመሪያ ስለ ብልግና ምስሎች የሚነሱ አንዳንድ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እንመልከት።

የብልግና ምስሎች በአንድ ሰው ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው?

ባለሙያዎች ምን ይላሉ? አንዳንድ ተመራማሪዎችና ሐኪሞች፣ የብልግና ምስሎች ከባድ ሱስ የሚያስይዙ በመሆናቸው ኮኬይን ከሚባለው ኃይለኛ ዕፅ ጋር ያመሳስሏቸዋል።

በኢንተርኔት የብልግና ምስሎችን የመመልከት ሱስ ተጠናውቶት የነበረው ብራየን b እንዲህ ብሏል፦ “ምስሎቹን ከማየት ሊያስቆመኝ የሚችል ምንም ነገር አልነበረም። የቅዠት ዓለም ውስጥ እንዳለሁ ይሰማኝ ነበር። ያንቀጠቅጠኝና ራሴን ያመኝ ነበር። ለማቆም ብታገልም ዓመታት ካለፉ በኋላም እንኳ ሱሱ ያስቸግረኝ ነበር።”

የብልግና ምስሎችን የመመልከት ሱስ የተጠናወታቸው ሰዎች ይህ ልማዳቸው እንዳይታወቅባቸው ለማድረግ ይሞክራሉ። ጉዳዩን በድብቅ ለመያዝ የሚሞክሩ ከመሆኑም በላይ ሌሎችን ሊያታልሉ ይችላሉ። በመሆኑም ብዙዎቹ ከሰው የመገለል፣ የኀፍረት፣ የውጥረት፣ የጭንቀትና የብስጭት ስሜት የሚሰማቸው መሆኑ ምንም አያስደንቅም። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ራሳቸውን የማጥፋት ሐሳብ ይመጣባቸዋል። የብልግና ምስሎችን በሞባይል ስልኩ ላይ በየቀኑ ይጭን የነበረ ሰርጌ የተባለ ሰው “ስለ ራሴ ብቻ አስብ የነበረ ሲሆን ተስፋ ቆርጬም ነበር” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “የዋጋ ቢስነት፣ የጥፋተኝነትና የብቸኝነት ስሜት ይሰማኝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ወጥመድ ውስጥ እንደገባሁ ሆኖ ይሰማኝ ነበር። እርዳታ ለመጠየቅ በጣም አፍሬ እንዲሁም ፈርቼ ነበር።”

የብልግና ምስሎችን ለአንድ አፍታ ወይም ድንገት ማየትም እንኳ መጥፎ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። ከብልግና ምስሎችና ጽሑፎች ጋር በተያያዘ እውቅ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጁዲት ሬይስማን በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ኮሚቴ ፊት የምሥክርነት ቃላቸውን ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል፦ “የብልግና ምስሎች በአእምሮ ላይ የሚታተሙ ከመሆኑም ባሻገር አንጎል ላይ ለውጥ ያመጣሉ። ምክንያቱም በቅጽበትና ከእኛ ቁጥጥር ውጭ በሆነ መንገድ ከአእምሮ ለመፋቅ የሚያዳግት ወይም እስከነጭራሹ ሊፋቅ የማይችል ትውስታ የሚያመጣ ባዮኬሚካላዊ ለውጥ በአንጎል ላይ እንዲከሰት ያደርጋሉ።” የብልግና ምስሎች የሚታዩባቸውን ድረ ገጾች የመመልከት ሱስ ተጠናውቷት የነበረችው የ19 ዓመቷ ሱዛን እንዲህ ብላለች፦ “ምስሎቹ በአእምሮዬ ላይ በማይጠፋ ሁኔታ ተቀርጸዋል። ሳላስበው ይመጡብኛል። ሙሉ በሙሉ ከአእምሮዬ ላጠፋቸው እንደማልችል ይሰማኛል።”

ዋናው ነጥብ፦ የብልግና ምስሎች አንድን ሰው ባሪያ እንዲሆን ብሎም ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ያደርጉታል።—2 ጴጥሮስ 2:19

የብልግና ምስሎች በቤተሰብ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት እንዴት ነው?

ባለሙያዎች ምን ይላሉ? “በብልግና ምስሎች የተነሳ ትዳሮችና ቤተሰቦች ይፈርሳሉ።”—ዘ ፖርን ትራፕ፣ በዌንዲ እና በላሪ ሞልትዝ የተዘጋጀ መጽሐፍ

የብልግና ምስሎች በትዳርና በቤተሰብ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉት በሚከተሉት መንገዶች ነው፦

  • በባልና ሚስት መካከል ያለውን መተማመን፣ ቅርርብና ፍቅር ያቀዘቅዛሉ።—ምሳሌ 2:12-17

  • ራስ ወዳድነትን፣ በስሜት መራራቅንና በትዳር ጓደኛ አለመርካትን ያስከትላሉ።—ኤፌሶን 5:28, 29

  • ተገቢ ያልሆነ የፆታ ፍላጎትና ምኞት ይቀሰቅሳሉ።—2 ጴጥሮስ 2:14

  • የብልግና ምስሎችን የሚመለከቱ ሰዎች የትዳር ጓደኛቸው ለሕሊና የሚከብዱ የፆታ ድርጊቶችን እንዲፈጽም ለማስገደድ ይፈተናሉ።—ኤፌሶን 5:3, 4

  • ከትዳር ጓደኛቸው ውጪ ላለ ሰው የፆታ ስሜት በማሳየት አልፎ ተርፎም ምንዝር በመፈጸም ታማኝነትን እንዲያጓድሉ ሊያደርጓቸው ይችላሉ።—ማቴዎስ 5:28

መጽሐፍ ቅዱስ የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው ሌላውን ‘ማታለል’ እንደማይኖርባቸው ይናገራል። (ሚልክያስ 2:16 የ1954 ትርጉም) ታማኝነት ማጉደል ከማታለል ድርጊቶች አንዱ ሲሆን እንዲህ ያለው ድርጊት ትዳርን በእጅጉ የሚጎዳ ከመሆኑም ሌላ ወደ መለያየትና ወደ ፍቺ ሊመራ ይችላል። የትዳር መፍረስ ደግሞ ልጆችን ይጎዳል።

በተጨማሪም የብልግና ምስሎች ልጆችን በቀጥታ ሊጎዱ ይችላሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ብራየን እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “ድብብቆሽ እየተጫወትኩ ሳለ ድንገት አባቴ ያስቀመጣቸውን የብልግና ምስሎች ያሉባቸው መጽሔቶች አገኘሁ፤ በወቅቱ የአሥር ዓመት ገደማ ልጅ ነበርኩ። እነዚህ ምስሎች ትኩረቴን የሳቡት ለምን እንደሆነ ባይገባኝም መጽሔቶቹን በድብቅ መመልከት ጀመርኩ። በዚህ መንገድ፣ አዋቂም ሆኜ ሊለቀኝ ያልቻለ ክፉ ልማድ ተጠናወተኝ።” ጥናቶች እንደሚያሳዩት የብልግና ምስሎች በጉርምስና ዕድሜ ላይ ያሉ ወጣቶች ገና በለጋ ዕድሜያቸው የፆታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ አልፎ ተርፎም ሴሰኞች፣ በፆታ ረገድ ጭካኔ የሚንጸባረቅበት ምግባር እንዲያሳዩ እና በስሜትም ሆነ በሥነ ልቦና ያልተረጋጉ እንዲሆኑ ተጽዕኖ ሊያሳድሩባቸው ይችላሉ።

ዋናው ነጥብ፦ የብልግና ምስሎች ትዳርንና ቤተሰብን ይጎዳሉ፤ የኋላ ኋላ ደግሞ ሐዘንና ሥቃይ ያስከትላሉ።—ምሳሌ 6:27

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ብልግና ምስሎች ምን ይላል?

የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው መጎምጀት ናቸው።”—ቆላስይስ 3:5

በአጭር አነጋገር ይሖዋ c የብልግና ምስሎችን ይጠላል። ይህ የሆነው ከፆታ ጋር የተያያዙ ነገሮችን በጥቅሉ ስለሚጠላ አይደለም። የፆታ ፍላጎትን የፈጠረው እሱ ነው፤ ይህን ያደረገበት ዓላማም የትዳር ጓደኛሞች አንዳቸው የሌላውን ፍላጎት እንዲያረኩ፣ በስሜት እንዲቀራረቡና ልጆች እንዲወልዱ በማሰብ ነው።—ያዕቆብ 1:17

ታዲያ ይሖዋ ለብልግና ምስሎች ከፍተኛ ጥላቻ አለው ብለን መናገር የምንችለው ለምንድን ነው? እስቲ ጥቂት ምክንያቶችን እንመልከት፦

  • የብልግና ምስሎች የሰዎችን ሕይወት እንደሚያመሰቃቅሉ ያውቃል።—ኤፌሶን 4:17-19

  • በጣም ይወድደናል፤ እንዲሁም ጉዳት እንዳይደርስብን ይፈልጋል።—ኢሳይያስ 48:17, 18

  • ይሖዋ በትዳርና በቤተሰብ ላይ አደጋ እንዳይደርስ ይፈልጋል።—ማቴዎስ 19:4-6

  • በሥነ ምግባር ንጹሕ እንድንሆንና የሌሎችን መብት እንድናከብር ይፈልጋል።—1 ተሰሎንቄ 4:3-6

  • የፆታ ስሜታችንን በአግባቡና ክብር ባለው መንገድ እንድናረካ ይፈልጋል።—ዕብራውያን 13:4

  • ይሖዋ የብልግና ምስሎች ስለ ፆታ የተዛባ፣ ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበትና ሰይጣናዊ የሆነ አመለካከት እንደሚያንጸባርቁ ያውቃል።—ዘፍጥረት 6:2፤ ይሁዳ 6, 7

ዋናው ነጥብ፦ የብልግና ምስሎች አንድ ሰው ከአምላክ ጋር ያለውን ወዳጅነት ያበላሹበታል።—ሮም 1:24

ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ የብልግና ምስሎችን ከመመልከት ወጥመድ መውጣት ለሚፈልጉ ሰዎች ታላቅ ርኅራኄ ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩም የበዛ ነው። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 103:8, 14) አምላክ ትሑት የሆኑ ሰዎች ‘እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ’ ወደ እሱ ዘወር በማለት “ምሕረትና ጸጋ” እንዲያገኙ ጋብዟቸዋል።—ዕብራውያን 4:16 “የብልግና ምስሎችን ከመመልከት ልማድ መላቀቅ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

በርካታ ሰዎች ከአምላክ እርዳታ አግኝተዋል። ታዲያ እሱ የሚሰጠው እርዳታ ውጤታማ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ መጥፎ ልማዶችን ስላሸነፉ ሰዎች ምን እንደሚል ልብ በል፦ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስምና በአምላካችን መንፈስ ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣ ተቀድሳችኋል እንዲሁም ጻድቃን ተብላችሁ ተጠርታችኋል።” (1 ቆሮንቶስ 6:11) እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እነዚህም ሰዎች “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አለኝ” ብለው መናገር ይችላሉ።—ፊልጵስዩስ 4:13

የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማዷን ማሸነፍ የቻለችው ሱዛን እንዲህ ብላለች፦ “ከብልግና ምስሎች ሱስ እንድትላቀቁ ሊረዳችሁ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። የእሱን እርዳታና አመራር ከጠየቃችሁ በእሱ ፊት ንጹሕ አቋም ማግኘት ትችላላችሁ። እሱ አያሳፍራችሁም።”

a የብልግና ምስሎች ተብሎ የተተረጎመው “ፖርኖግራፊ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አንድን ተመልካች፣ አንባቢ ወይም አድማጭ የፆታ ስሜቱ እንዲነሳሳ የሚያደርጉ የብልግና ሐሳቦችን በአጠቃላይ ያመለክታል። ይህም ፎቶግራፎችን አልፎ ተርፎም ጽሑፎችንና የሚደመጡ ነገሮችን ይጨምራል።

b በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።

c የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።