በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በእምነታቸው ምሰሏቸው

“ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር” ዳነ

“ከሌሎች ሰባት ሰዎች ጋር” ዳነ

ኃይለኛው ዶፍ በሚወርድበት ጊዜ ኖኅና ቤተሰቡ አንድ ላይ ስብስብ ብለው ተቀምጠዋል። ጨለማ በዋጠው ክፍል ውስጥ ያለውን ይህን ቤተሰብ ጭል ጭል በሚለው ኩራዝ ተጠቅመህ ፊታቸው ላይ የሚነበበውን ስሜት ለማየት ሞክር፤ ዝናቡ እንደ ፏፏቴ በመርከቡ ጣሪያ ላይ ሲወርድ እንዲሁም እየተንደረደረ የሚመጣው ጎርፍ መርከቧን በግራና በቀኝ ሲያላጋት በድንጋጤ ዓይናቸው ፈጧል። መቼም የሚሰማው ድምፅ በጣም አስፈሪ እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም።

ኖኅ ታማኝ የሆነችውን ሚስቱንና ምንጊዜም ከጎኑ ያልተለዩትን ሦስት ልጆቹን ከነሚስቶቻቸው ሲመለከት ልቡ በአመስጋኝነት ስሜት ተሞልቶ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ኖኅ በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ ከምንም በላይ የሚወደው ቤተሰቡ አብሮት በመሆኑ ተበረታትቶ መሆን አለበት። ምክንያቱም ሁሉም ምንም የሚያሰጋቸው ነገር የለም። ኖኅ፣ ድምፁ በሁካታውና በጫጫታው እንዳይዋጥ በማሰብ ጮክ ብሎ ከቤተሰቡ ጋር የምስጋና ጸሎት ሲያቀርብ ይታይህ።

ኖኅ ጠንካራ እምነት የነበረው ሰው ነው። አምላኩ ይሖዋ እሱንና ቤተሰቡን በሕይወት እንዲጠብቃቸው ያነሳሳው ኖኅ እንዲህ ያለ እምነት ማሳየቱ ነው። (ዕብራውያን 11:7) ይሁን እንጂ ቤተሰቡ እምነት ማሳየት የሚያስፈልጋቸው ዝናቡ መጣል እስኪጀምር ድረስ ነው? አይደለም፤ እንዲያውም ከፊታቸው ፈታኝ የሆነ ጊዜ ስለሚጠብቃቸው ይህን ባሕርይ ማሳየታቸው ከመቼው ጊዜ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። እኛም ብንሆን ሁከት በነገሠበት በዚህ ዘመን እምነት ማዳበራችን አንገብጋቢ ነው። እንግዲያው ኖኅ ካሳየው እምነት ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

“አርባ ቀንና አርባ ሌሊት”

የሚወርደው ዶፍ ዝናብ “ለአርባ ቀንና አርባ ሌሊት” ቀጠለ። (ዘፍጥረት 7:4, 11, 12) የውኃው ከፍታም እያደር እየጨመረ፣ እየጨመረ፣ እየጨመረ ሄደ። በዚህ ጊዜ ኖኅ፣ አምላኩ ይሖዋ በአንድ በኩል ጻድቃንን ሲያድን በሌላ በኩል ደግሞ ክፉዎችን ሲቀጣ ማየት ችሏል።

የጥፋት ውኃው፣ መላእክት ለቆሰቆሱት ዓመፅ መቋጫ አበጅቶለታል። ብዙ መላእክት ሰይጣን ላሳደረባቸው የራስ ወዳድነት ስሜት በመሸነፋቸው በሰማይ የነበራቸውን “ትክክለኛ መኖሪያ” ትተው ሴቶችን አግብተው መኖር ጀምረው ነበር፤ በዚህም የተነሳ ኔፊሊም ተብለው የሚጠሩ ዲቃላ ልጆች ተወለዱ። (ይሁዳ 6፤ ዘፍጥረት 6:4) እንዲህ ያለው ዓመፅ በምድር ላይ በመስፋፋቱ የሰይጣን ልብ በደስታ እንደፈነደቀ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ይህ ሁኔታ የይሖዋ ምድራዊ ፍጥረት ቁንጮ የሆኑትን የሰው ልጆች ክብር የሚያዋርድ ነው።

ይሁን እንጂ የውኃው መጠን እየጨመረ ሲሄድ ዓመፀኞቹ መላእክት ሥጋዊ አካላቸውን ጥለው ወደ መንፈሳዊው ዓለም ለመሸሽ ተገደዱ፤ ከዚያ ወዲህ ዳግመኛ ሥጋ አልለበሱም። ትተዋቸው የሄዷቸው ሚስቶቻቸውና ልጆቻቸው ግን ከኅብረተሰቡ ጋር በውኃው ተጥለቅልቀው ጠፉ።

ከሄኖክ ዘመን አንስቶ ሰባት መቶ ለሚጠጉ ዓመታት ይሖዋ ክፉ የሆኑና ፈሪሃ አምላክ የሌላቸውን ሰዎች እንደሚያጠፋ ሲያስጠነቅቅ ቆይቶ ነበር። (ዘፍጥረት 5:24፤ ይሁዳ 14, 15) ከድጡ ወደ ማጡ እንደሚባለው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰዎች ክፋት እየባሰ ሄደ፤ በዚህም የተነሳ ምድር የተበላሸች ከመሆኑም ሌላ በዓመፅ ተሞልታ ነበር። አሁን ግን አልሰማ በማለታቸው ለጥፋት ተዳረጉ። ታዲያ ኖኅና ቤተሰቡ በደረሰው ጥፋት ተደስተው ይሆን?

በፍጹም! መሐሪ የሆነው አምላካቸውም ቢሆን አልተደሰተም። (ሕዝቅኤል 33:11) ይሖዋ ብዙ ሰዎች እንዲድኑ ሲል መደረግ ያለበትን ነገር ሁሉ አድርጓል። ሄኖክ የማስጠንቀቂያ መልእክት እንዲያሰማ ተልእኮ የሰጠው ሲሆን ኖኅን ደግሞ መርከብ እንዲሠራ አዝዞት ነበር። ኖኅና ቤተሰቡ ለአሥርተ ዓመታት ግዙፉን መርከብ ሲገነቡ ቆይተዋል፤ በዚህ ጊዜ ሥራቸውን ሰዎች ሁሉ ያዩት ነበር። ከዚህም በላይ ይሖዋ፣ ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” በመሆን እንዲያገለግልም መመሪያ ሰጥቶት ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) እንደ ሄኖክ ሁሉ ኖኅም ሕዝቡን በዓለም ላይ ስለሚመጣው ፍርድ አስጠንቅቋል። ታዲያ ሕዝቡ ምን ምላሽ ሰጠ? ኢየሱስ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ከሰማይ ሆኖ ተመልክቶ ስለነበር በኖኅ ዘመን የነበሩትን ሰዎች አስመልክቶ ሲናገር “የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም” ብሏል።—ማቴዎስ 24:39

ይሖዋ የመርከቧን በር ከዘጋ በኋላ በነበሩት 40 ቀናት ውስጥ የኖኅና የቤተሰቡ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። ኃይለኛው ዶፍ ዝናብ መርከቡ ላይ መውረዱን ሲቀጥል ስምንቱም በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ማለትም እርስ በርስ እንደ መረዳዳት፣ ቤታቸውን እንደ ማስተካከልና በመርከቧ ውስጥ ለነበሩት እንስሳት የሚያስፈልጋቸውን እንደ ማቅረብ ባሉ ሥራዎች ተጠምደው ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ይሁንና አንድ ቀን ያ ግዙፍ መርከብ በድንገት መናወጥ ጀመረ። ይህ የሆነው መርከቡ መንቀሳቀስ ስለጀመረ ነው! የውኃው ከፍታ እየጨመረ ሲሄድ መርከቧ ተንሳፈፈች፤ ከዚያም የውኃው መጠን ቀስ በቀስ ሲጨምር “መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሣት።” (ዘፍጥረት 7:17) ሁሉን ቻይ አምላክ የሆነውን የይሖዋን ኃይል የሚያሳይ እንዴት ያለ አስደናቂ ትዕይንት ነው!

ኖኅ፣ የእሱም ሆነ የቤተሰቡ ሕይወት በመትረፉ ብቻ ሳይሆን እነሱን ተጠቅሞ ለጠፉት ሰዎች አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ይሖዋ የምሕረት እጁን በመዘርጋቱም አመስጋኝ ሆኖ መሆን አለበት። እርግጥ ያንን ከባድ ሥራ በመሥራት ያሳለፏቸው ዓመታት በወቅቱ ትርጉም የለሽ ሊመስሉ ይችሉ ይሆናል። ሰዎች ማስጠንቀቂያውን ለመስማት እምቢተኞች ነበሩ! መቼም ኖኅ የጥፋት ውኃው በመጣበት ጊዜ በሕይወት የነበሩ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም የወንድምና የእህት ልጆች ሳይኖሩት አይቀርም፤ ሆኖም ከቅርብ የቤተሰቡ አባላት በስተቀር የሰማው አንድም ሰው አልነበረም። (ዘፍጥረት 5:30) እነዚያ ስምንት ነፍሳት መርከቡ ውስጥ በመግባት ሕይወታቸውን ማዳን ችለዋል፤ በመሆኑም ሰዎች የመዳን አጋጣሚ እንዲያገኙ ሲሉ ያጠፉትን ጊዜ መለስ ብለው ሲያስቡ ተጽናንተው እንደሚሆን ግልጽ ነው።

ይሖዋ ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም። (ሚልክያስ 3:6) ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የእኛ ዘመን “ከኖኅ ዘመን” ጋር በእጅጉ እንደሚመሳሰል ገልጾ ነበር። (ማቴዎስ 24:37) አሁን ያለንበት ዘመንም ቢሆን በመከራ የተሞላ በመሆኑ ይታወቃል፤ በመሆኑም ይህ ሥርዓት በቅርቡ ይደመሰሳል። ዛሬም በተመሳሳይ የአምላክ ሕዝቦች ለሰዎች ሁሉ የማስጠንቀቂያ መልእክት እያሰሙ ነው። ታዲያ ለዚህ መልእክት ምላሽ ትሰጥ ይሆን? ሕይወት አድን የሆነውን ይህን እውነት ቀደም ብለህ ተቀብለህ ከሆነ ደግሞ መልእክቱን ለሌሎች በማዳረሱ ሥራ ትተባበር ይሆን? ኖኅና ቤተሰቡ ለሁላችንም ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል።

‘ከውኃ ዳኑ’

መርከቧ በዚያ በሚናወጥ ውቅያኖስ ላይ በምትንሳፈፍበት ጊዜ የተሠራችበት እንጨት የሚያሰማው ሲጢጥ የሚልና የሚንቋቋ ድምፅ በውስጧ ለነበሩት ሰዎች መሰማቱ አይቀርም። ታዲያ በዚህ ጊዜ ኖኅ የሞገዱ ኃይለኛነት ወይም የመርከቧ ጥንካሬ አሳስቦት ይሆን? በፍጹም። በዘመናችን ያሉት ተጠራጣሪዎች እንዲህ ያለ ጭንቀት ይፈጠርባቸው ይሆናል፤ ኖኅ ግን እንዲህ ዓይነት ሰው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅ . . . መርከብ የሠራው በእምነት” እንደሆነ ይናገራል። (ዕብራውያን 11:7) ለመሆኑ ኖኅ እምነት ያሳየው እንዴት ነበር? ይሖዋ ኖኅንና ከእሱ ጋር የነበሩትን ሁሉ ከዚያ የጥፋት ውኃ እንደሚያድናቸው ቃል ኪዳን ገብቶ ነበር። (ዘፍጥረት 6:18, 19) አጽናፈ ዓለምን፣ ምድርንና በላይዋ ላይ ያሉትን ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ የፈጠረ አምላክ መርከቧ ምንም ጉዳት እንዳይደርስባት ሊጠብቃት ይችላል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይደለም? ምንም ጥያቄ የለውም! በእርግጥም ኖኅ፣ ይሖዋ ቃሉን እንደሚጠብቅ መተማመኑ ተገቢ ነው። ደግሞም እሱና ቤተሰቡ ‘ከውኃው ድነዋል።’—1 ጴጥሮስ 3:20

ዝናቡ ለ40 ቀንና ለ40 ሌሊት ከጣለ በኋላ በመጨረሻ አቆመ። ዝናቡ ያቆመው በዘመናችን አቆጣጠር መሠረት በ2370 ዓ.ዓ. ታኅሣሥ አካባቢ ነበር። የቤተሰቡ የመርከብ ላይ ሕይወት ግን ገና አላበቃም። ብዙ ፍጥረታትን የያዘችው ይህቺ መርከብ ተራሮች በሙሉ እስኪሸፈኑ ድረስ ምድርን ባጥለቀለቀው ባሕር ላይ ወዲያ ወዲህ ማለቷን ቀጥላለች። (ዘፍጥረት 7:19, 20) ኖኅ ሴምን፣ ካምንና ያፌትን በማስተባበር ለእንስሳቱ በሙሉ መኖ በማቅረብ እንዲሁም ንጽሕናቸውን በመጠበቅና ጤንነታቸውን በመንከባከብ አድካሚውን ሥራ ሲወጣ በዓይነ ሕሊናችን ሊታየን ይችላል። እርግጥ ነው፣ እነዚያን ሁሉ የዱር እንስሳት ታዛዥና ገራም በማድረግ በቀላሉ ወደ መርከቧ እንዲገቡ ያደረገ አምላክ ከመርከቧ እስኪወጡ ድረስ በዚሁ ሁኔታ እንዲቀጥሉ እንዳደረገላቸው ምንም ጥያቄ የለውም። a

ኖኅ የተፈጸመውን እያንዳንዱን ክንውን በደንብ ሳይመዘግብ አልቀረም። መጽሐፍ ቅዱስ ዝናቡ መዝነብ የጀመረበትንና ያቆመበትን ጊዜ ይነግረናል። በተጨማሪም ምድር ለ150 ቀናት በውኃ እንደተሸፈነች ይገልጽልናል። በመጨረሻም ውኃው መጉደል ጀመረ። አንድ ቀን የሆነው ግን ፈጽሞ የማይረሳ ነው፤ መርከቧ በአሁኗ ቱርክ ውስጥ በሚገኙት ‘የአራራት ተራሮች’ ላይ አረፈች። ይህ የሆነው ሚያዝያ 2369 ዓ.ዓ. ሳይሆን አይቀርም። የተራሮቹ አናት መታየት የጀመረው ከ73 ቀናት በኋላ ሰኔ ወር ላይ ነበር። ከሦስት ወራት በኋላ ማለትም መስከረም ላይ ኖኅ የመርከቧን ጣሪያ በከፊል ለማንሳት ወሰነ። በተከፈተው ጣራ በኩል ብርሃንና ንጹሕ አየር ሲገባ ኖኅ ያ ሁሉ ልፋታቸው እንደካሳቸው ተሰምቶት መሆን አለበት። ኖኅ አካባቢው አስተማማኝና ለመኖሪያ ተስማሚ መሆኑን ለማረጋገጥ ቀደም ብሎ ፍተሻ ማድረግ ጀምሮ ነበር። መጀመሪያ ቁራን ላከ። ቁራውም ለተወሰነ ጊዜ ያህል እየበረረና እየተመለሰ ቆየ፤ ሲመለስ የሚያርፈው መርከቧ ጣሪያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም ርግብ ላከ፤ ርግቧም ጎጆ መሥሪያ ቦታ እስክታገኝ ድረስ ወደ ኖኅ ተመልሳ ትመጣ ነበር።—ዘፍጥረት 7:24 እስከ 8:13

ኖኅ፣ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ወቅት እንኳ የቤተሰብ አምልኮ ያከናውን እንደነበር ጥርጥር የለውም

ኖኅ ከዕለታዊ ተግባሮቹ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ጉዳዮች እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። ቤተሰቡ በኅብረት ሆነው ሲጸልዩና ጠባቂያቸው ስለሆነው የሰማዩ አባታቸው ሲነጋገሩ በዓይነ ሕሊናችን ሊታየን ይችላል። ኖኅ አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎችን ከማድረጉ በፊት ምንጊዜም ይሖዋ የሚሰጠውን መመሪያ ይጠብቅ ነበር። ኖኅ በመርከቧ ውስጥ ከአንድ ዓመት በላይ ከቆየ በኋላ በመጨረሻ ‘ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ እንደደረቀች’ ማየት ቢችልም እንኳ በሩን ከፍቶ ለመውጣት አልሞከረም። (ዘፍጥረት 8:14) ከዚህ ይልቅ ይሖዋ መመሪያ እስኪሰጠው ድረስ ጠብቋል።

በዛሬው ጊዜ ያሉ የቤተሰብ ራሶች ከዚህ ታማኝ ሰው ብዙ ነገር መማር ይችላሉ። ኖኅ ሥርዓታማ፣ ታታሪ፣ ትዕግሥተኛና በእሱ ሥር ያሉትን ሁሉ ለመንከባከብ ትጉህ ነበር። ኖኅ ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግን በሚያደርገው ነገር ሁሉ የይሖዋ አምላክን ፈቃድ ግምት ውስጥ ማስገባት ነው። በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ኖኅን በእምነቱ የምንመስለው ከሆነ ለምንወዳቸው ሁሉ በረከት እንሆናለን።

“ከመርከቧ ውጡ”

በመጨረሻም ይሖዋ “አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ” በማለት ኖኅን አዘዘው። ቤተሰቡም በታዛዥነት ቀድመው ወጡ፤ ከዚያም እንስሳቱ በሙሉ ተከትለዋቸው ወጡ። ይህ የሆነው ግን እንዴት ነው? የወጡት ሥርዓት በሌለው መንገድ እየተንጋጉ ነው? በጭራሽ! ዘገባው “በየወገናቸው ከመርከቧ ወጡ” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 8:15-19) ኖኅና ቤተሰቡ ከመርከቧ ከወጡ በኋላ ነፋሻማ አየር ባለበትና አካባቢውን ለመቃኘት በሚያስችለው ተራራ ላይ ሆነው የጸዳችውን ምድር ተመለከቱ። አሁን ኔፊሊሞች፣ ተንሰራፍቶ የነበረው ዓመፅ፣ ዓመፀኞቹ መላእክትና መላው ክፉ ኅብረተሰብ ከምድር ላይ ተወግደዋል! b የሰው ዘር ሕይወቱን በአዲስ መልክ ሀ ብሎ ለመጀመር ዕድል አገኘ።

ኖኅ ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቅ ነበር። ከመርከቧ እንደወጣ መጀመሪያ ያደረገው ለይሖዋ አምልኮ ማቅረብ ነው። መሠዊያ ከሠራ በኋላ “ሰባት ሰባት” አድርጎ ወደ መርከቧ ካስገባቸው በአምላክ ፊት ንጹሕ ተደርገው ከሚታዩት እንስሳት መካከል ለይሖዋ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። (ዘፍጥረት 7:2፤ 8:20) ታዲያ አምላክ መሥዋዕቱን ተቀብሎት ይሆን?

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርም ደስ የሚያሰኘውን መዐዛ አሸተተ” በማለት መልሱን ይነግረናል። አምላክ፣ የሰው ልጆች ምድርን በዓመፅ ሲሞሏት ልቡ በጣም አዝኖ ነበር፤ አሁን ግን በምድር ላይ ፈቃዱን ለመፈጸም የቆረጡ ታማኝ አምላኪዎችን ያቀፈ አንድ ቤተሰብ በማየቱ በደስታ ተሞልቷል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ይህ ቤተሰብ ፍጹም እንዲሆን አልጠበቀበትም። ጥቅሱ ሲቀጥል “ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት” ያዘነበለ እንደሆነ ይናገራል። (ዘፍጥረት 8:21) እስቲ ይሖዋ ለሰው ዘር ርኅራኄ ያሳየበትን ሌላ አጋጣሚ ተመልከት።

አምላክ የምድርን እርግማን አነሳ። አምላክ ምድርን የረገማት አዳምና ሔዋን ባመፁበት ወቅት ሲሆን በዚህም የተነሳ የእርሻ ሥራ ከመጠን በላይ አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። የኖኅ አባት ላሜሕ ለልጁ ኖኅ የሚል ስም በመስጠት ልጁ የሰውን ዘር ከእርግማኑ እንደሚያሳርፍ ትንቢት ተናግሮ ነበር፤ የስሙ ትርጉም ‘እረፍት’ ወይም “መጽናናት” የሚል ሳይሆን አይቀርም። ኖኅ ትንቢቱ ሲፈጸም በማየቱ ብሎም ምድር ለማልማት ይበልጥ ቀላል እንደምትሆን ሲያውቅ ፊቱ በደስታ አብርቶ መሆን አለበት። ኖኅ ወዲያውኑ የግብርና ሥራ መጀመሩ ምንም አያስገርምም!—ዘፍጥረት 3:17, 18፤ 5:28, 29፤ 9:20

ኖኅና ቤተሰቡ ከመርከቧ ወደጸዳችው ምድር ሲወጡ

በዚህ ወቅት ይሖዋ ለኖኅ ዘሮች በሙሉ ነፍስ ማጥፋትንና ደምን አላግባብ መጠቀምን የሚከለክሉትን ጨምሮ ሕይወታቸውን የሚመሩባቸው ግልጽና ቀላል ሕጎች ሰጣቸው። በተጨማሪም አምላክ በምድር ላይ ያለን ሕይወት ዳግመኛ በውኃ እንደማያጠፋ በመናገር ከሰው ዘር ጋር ቃል ኪዳን ገባ። ይሖዋ የገባው ቃል ኪዳን አስተማማኝ መሆኑን ማረጋገጫ ለመስጠት ሲል ውብ የሆነ ተፈጥሯዊ ክስተት ይኸውም ቀስተ ደመና እንዲታይ አደረገ። እስከ ዘመናችን ድረስ ቀስተ ደመና ባየን ቁጥር ይሖዋ በፍቅር ተገፋፍቶ የገባውን ቃል ኪዳን እናስታውሳለን።—ዘፍጥረት 9:1-17

የኖኅ ታሪክ ልብ ወለድ ቢሆን ኖሮ ታሪኩ በቀስተ ደመናው ሊደመደም ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ኖኅ በእውን የነበረ ሰው ነው፤ ቀሪ ሕይወቱም ቢሆን አልጋ ባልጋ አልነበረም። በዚያ ዘመን ረጅም ዕድሜ መኖር የተለመደ ስለነበረ ይህ ታማኝ ሰው ከጥፋት ውኃው በኋላ ለ350 ዓመታት መጽናት ነበረበት፤ እነዚያ ዓመታትም ብዙ ሐዘን አስከትለውበታል። በአንድ ወቅት በመስከሩ ከባድ ስህተት ፈጽሟል፤ ይባስ ብሎ ደግሞ የልጅ ልጁ የሆነው ከነዓን ከዚያ የከፋ ኃጢአት የፈጸመ ሲሆን ይህም በዘሮቹ ላይ መዘዝ አስከትሏል። ኖኅ፣ በኖረበት ዘመን ዘሮቹ በናምሩድ ዘመን እንደ ጣዖት አምልኮና ዓመፅ ባሉ ኃጢአቶች ውስጥ ሲወድቁ ተመልክቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ኖኅ ረጅም ዕድሜ በመኖሩ ልጁ ሴም በእምነቱ ለዘሮቹ ጠንካራ ምሳሌ ሲሆን ለማየት በቅቷል።—ዘፍጥረት 9:21-28፤ 10:8-11፤ 11:1-11

እኛም እንደ ኖኅ ችግሮች ቢያጋጥሙንም በእምነት ጎዳና ላይ መመላለሳችንን መቀጠል ይኖርብናል። በዙሪያችን ያሉ ሰዎች እውነተኛውን አምላክ ችላ ሲሉ አልፎ ተርፎም እሱን ማገልገል ሲያቆሙ ልክ እንደ ኖኅ በጽናት መቀጠል ያስፈልገናል። ይሖዋ አገልጋዮቹ ታማኝ በመሆን ረገድ የሚያሳዩትን ጽናት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው ‘እስከ መጨረሻው የሚጸና ይድናል።’—ማቴዎስ 24:13

a አንዳንድ እንስሳት በተፈጥሯቸው ኃይላቸውን ለመቆጠብ ሲሉ ለወራት ድብን ባለ እንቅልፍ እንደሚያሳልፉ ሁሉ አምላክም በመርከቡ ውስጥ ያሉት እንስሳት የሚፈጁትን መኖ ለመቀነስ ሲል ይህን ዘዴ በእንስሳቱ ላይ ተጠቅሞ ሊሆን እንደሚችል የሚሰማቸው ሰዎች አሉ። አምላክ በዚህ ዘዴ ይጠቀም አይጠቅም የምናውቀው ነገር ባይኖርም በመርከቧ ውስጥ የነበሩትን ሁሉ በሕይወት ለማቆየት የገባውን ቃል ኪዳን እንደጠበቀ ግን ጥርጥር የለውም።

b ከምድር ላይ ከተወገዱት ነገሮች መካከል በኤደን የሚገኘው የአትክልት ሥፍራም ይገኝበታል፤ ይህ ቦታ በጎርፉ ተጠራርጎ ሳይጠፋ አይቀርም። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ደግሞ ወደ ገነት የሚያስገባውን በር የሚጠብቁት ኪሩቤል ከ1600 ዓመታት በኋላ ኃላፊነታቸውን አጠናቅቀው ወደ ሰማይ ተመልሰዋል ማለት ነው።—ዘፍጥረት 3:22-24