በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ኖርዌይ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ኖርዌይ

ከጥቂት ዓመታት በፊት፣ ሮአል እና ኤልሳቤት የተባሉ በወቅቱ በ40ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ ይገኙ የነበሩ አንድ ባልና ሚስት የኖርዌይ ሁለተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው በበርገን ውስጥ የተመቻቸ ሕይወት ይመሩ ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት ከልጆቻቸው ከኢዛቤል እና ከፌይቢየን ጋር ጉባኤያቸው በሚያደርገው እንቅስቃሴ በታማኝነት ይካፈሉ ነበር። ሮአል በሽምግልና፣ ኤልሳቤት በአቅኚነት ልጆቻቸው ደግሞ ቀናተኛ አስፋፊዎች በመሆን ያገለግሉ ነበር።

ይሁንና መስከረም 2009 ይህ ቤተሰብ አንድ የተለየ ነገር ለማድረግ ይኸውም ለአንድ ሳምንት ያህል ገለልተኛ በሆነ ክልል ውስጥ ለመስበክ ወሰነ። በመሆኑም ሮአልና ኤልሳቤት ከፌይቢየን (በወቅቱ 18 ዓመት ይሆነዋል) ጋር በመሆን ከአርክቲክ መስመር በላይ ወደምትገኘውና የፊንማርክ ባሕረ ገብ መሬት ወደሆነችው ወደ ኖርድኪን ተጓዙ። እዚያም እንደደረሱ ከልፍዮር በተባለ ገለልተኛ ክልል ሊሰብኩ ከመጡ ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ጋር በመሆን ማገልገል ጀመሩ። ሮአል በዚያን ጊዜ የነበረውን ሁኔታ አስታውሶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ለአንድ ሳምንት በዚህ ልዩ የስብከት እንቅስቃሴ ለመካፈል ስል ሰብዓዊ ጉዳዮቼን ማስተካከል በመቻሌ መጀመሪያ ላይ ልዩ የእርካታ ስሜት ነበረኝ።”  ይሁንና ሳምንቱ መቆጠር ሲጀምር ሮአል መረበሽ ጀመረ። ምን አጋጥሞት ይሆን?

ያልተጠበቀ ጥያቄ

ሮአል እንዲህ ብሏል፦ “በፊንማርክ የሚያገለግል ማርዮ የተባለ አንድ አቅኚ፣ ላክስኤልቭ በተባለ ከተማ የሚገኝን 23 አስፋፊዎች ያሉትን አንድ ጉባኤ ሄደን መርዳት እንችል እንደሆነ በድንገት ጠየቀን።” ሮአል ጥያቄው ያልጠበቀው ስለነበረ በጣም ተገረመ። ሮአል እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “እኔና ኤልሳቤት እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ሄደን የማገልገል ሐሳቡ ነበረን፤ ይህን ለማድረግ ያሰብነው ግን ወደፊት ልጆቹ ራሳቸውን ችለው ከቤት ከወጡ በኋላ ነበር።” ይሁንና ሮአል፣ በዚህ ገለልተኛ ክልል ባገለገሉባቸው አጭር ቀናት ውስጥ ሰዎች ስለ ይሖዋ ለመማር ያላቸውን ፍላጎት አስተዋለ። ሰዎቹ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው አሁን እንጂ ወደፊት እንዳልሆነ ተረዳ። “ወንድም ያቀረበልኝ ጥያቄ ሕሊናዬን በጣም የረበሸኝ ከመሆኑም በላይ ለተወሰኑ ቀናት እንቅልፍ አሳጣኝ” በማለት ሁኔታውን አስታውሶ ተናግሯል። ማሪዮ፣ የሮአልን ቤተሰብ ይዞ ከከልፍዮር በስተ ደቡብ 240 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ላክስኤልቭ በመኪና ወሰዳቸው። የቤተሰቡ አባላት በዚያ የሚገኘውን ትንሽ ጉባኤ በገዛ ዓይናቸው እንዲመለከቱ ፈልጎ ነበር።

ላክስኤልቭ እንደደረሱ በዚያ ጉባኤ ካሉት ሁለት ሽማግሌዎች አንዱ የሆነው አንድሪያስ አካባቢውንና የመንግሥት አዳራሹን አስጎበኛቸው። ጉባኤው ሞቅ ያለ አቀባበል ያደረገላቸው ከመሆኑም ሌላ የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ ወደዚህ ቦታ ተዛውረው ቢኖሩ ደስ እንደሚላቸው ወንድሞች ለሮአል እና ለኤልሳቤት ነገሯቸው። አንድሪያስ ለሮአል እና ለፌይቢየን ሥራ እንዳገኘላቸውና ለቃለ መጠየቁ ቀጠሮ እንደያዘላቸው በቀልድ መልክ ተናገረ! ታዲያ ቤተሰቡ ምን ያደርግ ይሆን?

ምን ውሳኔ ያደርጉ ይሆን?

ፌይቢየን መጀመሪያ ላይ የሰጠው ምላሽ “ወደዚህ ተዘዋውሮ የመኖር ፍላጎት የለኝም” የሚል ነበር። አብሮ አደጎቹ ከሆኑት በጉባኤው ውስጥ ከሚገኙ የቅርብ ጓደኞቹ ተለይቶ በዚህች ትንሽ ከተማ ውስጥ መኖር የሚለው ሐሳብ አልተዋጠለትም ነበር። በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ሠራተኛ ለመሆን እየወሰደ ያለውን ሥልጠና አልጨረሰም ነበር። ኢዛቤል ግን (በወቅቱ 21 ዓመት ይሆናታል) ወደዚህ አካባቢ ተዛውሮ ስለመኖር ምን እንደሚሰማት ስትጠየቅ “ሁሌም የምመኘው እንዲህ ማድረግ ነበር!” በማለት በደስታ መልሳለች። ኢዛቤል አክላ እንዲህ ብላለች፦ “በኋላ ላይ ግን ‘ውሳኔው በእርግጥ ጥሩ ነው? ጓደኞቼ ይናፍቁኝ ይሆን? በለመድኩት ጉባኤ ውስጥ መቆየት ይሻለኝ ይሆን?’ እያልኩ ማሰብ ጀመርኩ።” ኤልሳቤትስ ለቀረበላት ግብዣ ምን ምላሽ ሰጠች? “ይሖዋ ለቤተሰባችን አንድ ኃላፊነት እንደሰጠው ተሰማኝ። በሌላ በኩል ደግሞ በቅርቡ ስለታደሰው ቤታችንና ባለፉት 25 ዓመታት ስላፈራናቸው ንብረቶች አሰብኩ።”

ኤልሳቤት እና ኢዛቤል

አንድ ሳምንቱ ሲያልቅ ሮአል እና ቤተሰቡ ወደ በርገን ተመለሱ፤ ሆኖም 2,100 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በላክስኤልቭ ስለሚኖሩት ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ማሰባቸውን አላቆሙም ነበር። ኤልሳቤት እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ጊዜ ለይሖዋ እጸልይ ነበር፤ እንዲሁም በዚያ ከተዋወቅኳቸው ወዳጆቻችን ጋር ፎቶግራፍና ተሞክሮዎችን እንለዋወጥ ስለነበረ ከእነሱ ጋር ያለን ግንኙነት ቀጥሎ ነበር።” ሮአል ደግሞ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ወደ ሌላ አካባቢ መዛወር የሚለውን ሐሳብ ውስጤ እንዲቀበለው ጊዜ ያስፈልገኝ ነበር። በተጨማሪም ከቁሳዊ ነገር አንጻር ነገሩን ማሰብ ነበረብኝ። ‘ራሳችንን ማስተዳደር የምንችለው እንዴት ነው?’ የሚለው ነገር ያሳስበኝ ነበር። ጉዳዩን በተመለከተ ብዙ ጊዜ ወደ ይሖዋ የጸለይኩ ሲሆን ከቤተሰቤና ተሞክሮ ካላቸው ወንድሞች ጋር ተወያይቻለሁ።” ፌይቢየንም ቢሆን እንዲህ ብሏል፦ “ነገሩን ይበልጥ ባሰብኩበት ቁጥር ግብዣውን ላለመቀበል ምንም አጥጋቢ ምክንያት እንደሌለኝ ተገነዘብኩ። ለይሖዋ በተደጋጋሚ ስጸልይ ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውሮ የመሄድ ፍላጎቴም እያደገ መጣ።” ኢዛቤልስ? ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውራ ማገልገሏ እንደማይቀር ስለተሰማት ከወዲሁ ራሷን ለማዘጋጀት ስትል ባለችበት ጉባኤ ውስጥ አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። ለስድስት ወራት በአቅኚነት ካገለገለችና አብዛኛው ጊዜዋን በግል ጥናት ካሳለፈች በኋላ ወደ ሌላ አካባቢ ተዛውራ ለመኖር ዝግጁ እንደሆነች ተሰማት።

ግባቸው ላይ ለመድረስ የወሰዷቸው እርምጃዎች

የቤተሰቡ አባላት፣ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ የማገልገል ፍላጎታቸው እያደገ ሲመጣ ግባቸው ላይ ለመድረስ አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ጀመሩ። ሮአል በጣም የሚወደውና ጥሩ ክፍያ የሚያገኝበት ሥራ ቢኖረውም ለአንድ ዓመት እረፍት ለመውጣት ጠየቀ። ይሁንና አሠሪው ዓመቱን ሙሉ እረፍት ከሚወጣ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ብቻ ማለትም ሁለት ሳምንት ሠርቶ ስድስት ሳምንት እረፍት እንዲወጣ ጠየቀው። ሮአል “ደሞዜ በጣም ቢቀነስም በዚህ መንገድ መሥራቴ አስደስቶኛል” ብሏል።

ኤልሳቤትም በበኩሏ እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴ በርገን ያለውን ቤታችንን እንዳከራይና በላክስኤልቭ ደግሞ የሚከራይ ቤት እንድፈልግ ነገረኝ። እንዲህ ማድረግ ብዙ ጊዜና ጥረት ቢጠይቅብኝም በመጨረሻ ተሳካ። ከጊዜ በኋላም ልጆቹ በሳምንት ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት የሚሠሩት ሥራ ስላገኙ የአስቤዛና የትራንስፖርት ወጪ በመሸፈን ረድተውናል።”

 ኢዛቤል እንዲህ ብላለች፦ “የተዛወርንባት ከተማ ትንሽ በመሆኗ ከባድ ፈተና የሆነብኝ ራሴን ችዬ በአቅኚነት ለመቀጠል የሚያስችለኝን ሥራ ማግኘት ነበር። አንዳንድ ጊዜ ምንም ተስፋ ያለው አይመስልም ነበር።” ያም ቢሆን በሳምንት ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት ብቻ አነስተኛ ሥራዎችን ሳታማርጥ በመሥራት ወጪዋን መሸፈን ችላለች፤ እንዲያውም በመጀመሪያው ዓመት ዘጠኝ የተለያዩ ቦታዎች ሠርታለች። ፌይቢየንስ እንዴት ሆኖ ይሆን? እንዲህ ብሏል፦ “በኤሌትሪክ ሙያ ለመመረቅ አፓረንት መውጣት ነበረብኝ። ይህን ደግሞ በላክስኤልቭ ማድረግ ችያለሁ። ከጊዜ በኋላም ፈተናውን አልፌ በኤሌትሪክ ሙያ በሳምንት ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት ብቻ የምሠራበት ሥራ አገኘሁ።”

ሌሎች አገልግሎታቸውን ያሰፉት እንዴት ነው?

ማሬልያስ እና ኬስኢያ በኖርዌይ ለሴሚ ተወላጅ ሲሰብኩ

ማሬልያስ እና ባለቤቱ ኬስኢያ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ማገልገል ይፈልጉ ነበር። አሁን 29 ዓመት የሆነው ማሬልያስ እንዲህ ብሏል፦ “አቅኚነትን በተመለከተ አውራጃ ስብሰባ ላይ የሚቀርቡ ንግግሮችና ቃል ምልልሶች አገልግሎቴን ስለማስፋት እንዳስብ አድርገውኛል።” አሁን 26 ዓመት የሆናት ኬስኢያ ግን ከቤተሰብ ርቆ የመሄዱ ጉዳይ እንቅፋት ሆኖባት ነበር፤ “ከምወዳቸው ሰዎች ርቆ መኖር የሚለው ሐሳብ በጣም ያስፈራኝ ነበር” ብላለች። በተጨማሪም ማሬልያስ የቤታቸውን ብድር ለመክፈል ሙሉ ጊዜ ይሠራ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ማስተካከያ ማድረግ እንድንችል ይሖዋን በጸሎት ጠይቀነው ነበር፤ እሱም ስለረዳን ተሳክቶልናል።” እነዚህ ባልና ሚስት መጀመሪያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ረዘም ያለ ጊዜ ማሳለፍ ጀመሩ። ከዚያም ቤታቸውን በመሸጥና ሥራቸውን በማቆም ነሐሴ 2011 በሰሜናዊ ኖርዌይ ወደምትገኘው አልታ ወደተባለች ከተማ ሄዱ። በአቅኚነት ለማገልገል የሚያስችላቸውን ገቢ ለማግኘት ማሬልያስ የሒሳብ ሥራ፣ ኬስኢያ ደግሞ መደብር ውስጥ መሥራት ጀመሩ።

ክኑት እና ሊስቤት የተባሉ በአሁኑ ጊዜ በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙ አንድ ባልና ሚስት፣ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደው ስላገለገሉ ክርስቲያኖች የሚናገሩ ተሞክሮዎችን ከዓመት መጽሐፍ ላይ ሲያነብቡ ልባቸው ተነካ። ሊስቤት እንዲህ ብላለች፦ “እነዚህ ተሞክሮዎች ወደ ሌላ አገር ሄዶ ስለማገልገል እንድናስብ አደረጉን። ያም ቢሆን እንደ እኔ ያለ ሰው እዚህ ግብ ላይ መድረስ አይችልም የሚል ስሜት ስለነበረኝ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል አመነታ ነበር።” ያም ሆኖ እነዚህ ባልና ሚስት ግባቸው ላይ ለመድረስ አንዳንድ እርምጃዎችን ወሰዱ። ክኑት እንዲህ ብሏል፦ “የምንኖርበትን አፓርታማ ቤት ከሸጥን በኋላ ገንዘብ ለማጠራቀም ስንል ከእናቴ ጋር መኖር ጀመርን። ከጊዜ በኋላ በሌላ አገር ማገልገል ምን እንደሚመስል ለመቅመስ እንድንችል በበርገን ውስጥ ወደሚገኝ አንድ የእንግሊዝኛ ጉባኤ ተዘዋውረን ለአንድ ዓመት አገለገልን፤ እዚያ እያለን የባለቤቴ እናት ቤት እንኖር ነበር።” ብዙም ሳይቆይ ክኑት እና ሊስቤት ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ዝግጁ እንደሆኑ ሲሰማቸው በጣም ትልቅ ለውጥ ማድረግ ወደሚጠይቅ አካባቢ ለመሄድ ይኸውም ወደ ኡጋንዳ ለመጓዝ ወሰኑ። በየዓመቱ ለሁለት ወር ወደ ኖርዌይ በመመለስ ሰብዓዊ ሥራ ይሠራሉ። እንደዚህ በማድረግ በቀሪዎቹ ወራት ራሳቸውን እየረዱ ሙሉ ጊዜያቸውን በስብከቱ ሥራ ማሳለፍ ችለዋል።

ይሖዋ “ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እዩ”

“ቤተሰባችን ይበልጥ መቀራረብ ችሏል።”—ሮአል

ታዲያ እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ምን በረከት አገኙ? ሮአል እንዲህ ብሏል፦ “ከበርገን በተሻለ በዚህ ገለልተኛ ቦታ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነን ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፍ ችለናል። አሁን ቤተሰባችን  ይበልጥ መቀራረብ ችሏል። ልጆቻችን በመንፈሳዊ እድገት ሲያደርጉ መመልከት ትልቅ በረከት ነው።” አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ቁሳዊ ነገሮችም ይበልጥ ሚዛናዊ አመለካከት አዳብረናል። አሁን ለቁሳዊ ነገር የቀድሞው ዓይነት አመለካከት የለንም።”

ኤልሳቤት ሌላ ቋንቋ መማር ጥቅም እንዳለው ተገንዝባለች። ለምን? የላክስኤልቭ ጉባኤ ክልል የካረስዮክን ገጠራማ አካባቢ ያካትታል፤ ይህ ቦታ ደግሞ በኖርዌይ፣ በስዊድን፣ በፊንላንድና በሩሲያ ሰሜናዊ ክልል የሚኖሩት የሴሚ ሕዝቦች መናኸሪያ ነው። በመሆኑም ከእነዚህ የአገሬው ሕዝቦች ጋር ለመግባባት ኤልሳቤት የሴሚን ቋንቋ መማር ጀመረች። አሁን በዚህ ቋንቋ ለመግባባት ያህል ማውራት ትችላለች። ታዲያ አዲሱን ክልል ወደደችው? በደስታ ፈክታ እንዲህ ብላለች፦ “ስድስት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አሉኝ። ታዲያ ከዚህ የተሻለ ቦታ የት አለ?”

በአሁኑ ጊዜ አቅኚና የጉባኤ አገልጋይ የሆነው ፌይቢየን ከኢዛቤል ጋር በመሆን በአዲሱ ጉባኤ ውስጥ ሦስት ወጣቶችን እንደረዱ ተናግሯል፤ እነዚህ ወጣቶች በጉባኤው ውስጥ ይበልጥ እንዲንቀሳቀሱ ማበረታቻ ያስፈልጋቸው ነበር። በአሁኑ ጊዜ ሦስቱም በአገልግሎት ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ። እንዲያውም ሁለቱ የተጠመቁ ሲሆን መጋቢት 2012 ላይም በረዳት አቅኚነት አገልግለዋል። ከእውነት ሸርተት እያሉ ከነበሩት ወጣቶች አንዷ ማንሰራራት እንድትችል ስለረዷት ፌይቢየንንና ኢዛቤልን አመስግናቸዋለች። “የተናገረችው ነገር በጣም ነው ያስደሰተኝ። ሰዎችን መርዳት እንዴት ደስ ይላል!” በማለት ፌይቢየን ተናግሯል። ኢዛቤልም “እዚህ ቦታ በመምጣቴ በእርግጥም ይሖዋ ‘ቸር እንደ ሆነ ቀምሼ ለማየት’ ችያለሁ” ብላለች። (መዝ. 34:8) “በዚያ ላይ እዚህ ማገልገል በራሱ በጣም ደስ የሚል ነው!” በማለት ጨምራ ተናግራለች።

ማሬልያስ እና ኬስኢያ አኗኗራቸው ቀላል ቢሆንም ሕይወታቸው ግን ይበልጥ ትርጉም ያለው ሆኗል። አሁን የሚያገለግሉበት በአልታ የሚገኘው ጉባኤ 41 አስፋፊዎች አሉት። ማሬልያስ እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወታችን ምን ያህል እንደተቀየረ መለስ ብዬ ሳስብ በጣም እበረታታለሁ። እዚህ በአቅኚነት ማገልገል በመቻላችን ይሖዋን እናመሰግነዋለን። ከዚህ በላይ የሚያረካ ነገር የለም።” ኬስኢያ አክላ እንዲህ ብላለች፦ “በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመንን የተማርኩ ሲሆን እሱም ተንከባክቦናል። ከዘመዶቼ ርቄ መኖሬ ከእነሱ ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜ ይበልጥ እንዳደንቅ አድርጎኛል። በውሳኔያችን በፍጹም ተቆጭቼ አላውቅም።”

ክኑት እና ሊስቤት በኡጋንዳ አንድን ቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያስጠኑ

በኡጋንዳ የሚያገለግሉት ክኑት እና ሊስቤትስ እንዴት ሆነው ይሆን? ክኑት እንዲህ ብሏል፦ “ከአዲሱ አካባቢና ባሕል ጋር መላመድ ጊዜ ይወስዳል። የውኃና የኤሌክትሪክ ችግር እንዲሁም የሆድ ሕመም የተለመዱ ነገሮች ናቸው፤ ያም ሆኖ የፈለግነውን ያህል ጥናት መምራት እንችላለን!” ሊስቤት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ከምንኖርበት አካባቢ የግማሽ ሰዓት ርቀት ላይ ምሥራቹ ያልደረሰባቸው ክልሎች አሉ። እዚያ ስንሄድ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ሲያነቡ የምናገኛቸው ሰዎች እንድናስተምራቸው ይጠይቁናል። እንዲህ ላሉ ትሑት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማር ወደር የሌለው ደስታ ያስገኛል!”

መሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ የጀመረው የስብከት ሥራ በብዙ የምድር ክፍሎች እየተሠራ እንዳለ ከሰማይ ሆኖ በሚመለከትበት ጊዜ በጣም እንደሚደሰት ምንም ጥርጥር የለውም! በእርግጥም ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች፣ ኢየሱስ ‘ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንድናደርግ’ የሰጠንን ተልእኮ ለመፈጸም ራሳቸውን በፈቃደኝነት ማቅረባቸው ልባዊ ደስታ ያስገኝላቸዋል።—ማቴ. 28:19, 20