በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኤሪክ እና ኤሚ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ጋና

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ጋና

የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር ሄደው የሚያገለግሉ ወንድሞችን ወይም እህቶችን ታውቃለህ? ‘እነዚህ ወንድሞች ወደ ሌላ አገር ሄደው እንዲያገለግሉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? እንዲህ ላለው አገልግሎት የሚዘጋጁት እንዴት ነው? እኔስ እንደዚህ ባለው አገልግሎት መካፈል እችላለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቀህ ታውቅ ይሆናል። እንደነዚህ ላሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የተሻለው መንገድ እነዚህን ወንድሞችና እህቶች መጠየቅ እንደሆነ ግልጽ ነው። እስቲ አንዳንድ ጥያቄዎችን እንጠይቃቸው።

ምን አነሳሳቸው?

ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር ሄዳችሁ ለማገልገል ያነሳሳችሁ ምንድን ነው? ኤሚ የመጣችው ከዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን አሁን በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ ትገኛለች። እንዲህ ብላለች፦ “ወደ ሌላ አገር ሄጄ ለማገልገል ሳስብ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም እዚህ ግብ ላይ ልደርስ እንደማልችል ይሰማኝ ነበር።” ታዲያ አመለካከቷን የለወጠው ምንድን ነው? “በ2004 በቤሊዝ የሚያገለግሉ አንድ ባልና ሚስት እነሱ ወዳሉበት ሄጄ አብሬያቸው ለአንድ ወር በአቅኚነት እንዳገለግል ጋበዙኝ። እኔም ግብዣቸውን የተቀበልኩ ሲሆን አገልግሎቱን በጣም ወደድኩት! ከአንድ ዓመት በኋላ፣ በአቅኚነት ለማገልገል ወደ ጋና ሄድኩ።”

አሮን እና ስቴፋኒ

በአሁኑ ጊዜ በ20ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የምትገኘውና ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣችው ስቴፋኒ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሁኔታዋን ቆም ብላ ገምግማ ነበር፤ በመሆኑም እንዲህ ብላ አሰበች፦ ‘ጥሩ ጤንነት ያለኝ ሲሆን የቤተሰብ ኃላፊነትም የለብኝም። በእርግጥም በይሖዋ አገልግሎት አሁን ከማደርገው የበለጠ ብዙ መሥራት እችላለሁ።’ በዚህ መንገድ ራሷን በሐቀኝነት መመርመሯ አገልግሎቷን ለማስፋት ወደ ጋና እንድትሄድ አነሳሳት። ከዴንማርክ የመጡትና በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ፊሊፕ እና አይዳ የተባሉ አቅኚዎች፣ ሰባኪዎች ወደሚያስፈልጉበት ክልል ሄደው ለማገልገል ሁልጊዜ ይመኙ ነበር። በመሆኑም ምኞታቸውን ለማሳካት የሚያስችሏቸውን አጋጣሚዎች ይፈልጉ ነበር። ፊሊፕ “አጋጣሚውን ስናገኝ፣ ይሖዋ ‘ሂዱ’ እንዳለን ተሰማን” ብሏል። በ2008 ወደ ጋና የሄዱ ሲሆን በዚያም ከሦስት ዓመት በላይ አገልግለዋል።

ብሩክ እና ሀንዝ

በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት ሀንዝ እና ብሩክ የሚባሉ አቅኚ ባልና ሚስት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያገለግላሉ። እነዚህ ባልና ሚስት፣ ካትሪና የተባለችው አውሎ ነፋስ በ2005 ካደረሰችው ውድመት በኋላ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች እርዳታ በመስጠቱ ሥራ ተሳትፈዋል። ከዚያም በዓለም አቀፍ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ ለመካፈል አመለከቱ፤ ሆኖም አልተጋበዙም። ሀንዝ እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “ንጉሥ ዳዊት ቤተ መቅደሱን እንዲሠራ ስላልተፈቀደለት ግቡን እንደለወጠ የሚገልጽ ንግግር በአንድ የክልል ስብሰባ ላይ አዳመጥን። ይህ ትምህርት እኛም ቲኦክራሲያዊ ግቦቻችንን መቀየር እንደምንችል እንድንገነዘብ ረዳን።” (1 ዜና 17:1-4, 11, 12፤ 22:5-11) ብሩክም አክላ “ይሖዋ ሌላ በር እንድናንኳኳ ፈልጎ ነበር” በማለት ተናግራለች።

ሀንዝና ብሩክ በሌሎች አገሮች ያገለገሉ ጓደኞቻቸውን ግሩም ተሞክሮዎች ከሰሙ በኋላ ሌላ አገር ሄደው በአቅኚነት ለማገልገል ተነሳሱ። በ2012 ወደ ጋና የሄዱ ሲሆን በዚያም ለአራት ወራት በአንድ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ አገለገሉ። ከዚያ በኋላ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መመለስ ግድ ቢሆንባቸውም በጋና ማገልገላቸው ከአምላክ መንግሥት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ ለመስጠት ያላቸውን ፍላጎት አጠናክሮታል። ከዚያ ወዲህ በማይክሮኔዥያ በተከናወነው የቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ላይ እገዛ አበርክተዋል።

ግባቸው ላይ ለመድረስ የወሰዱት እርምጃ

ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር ሄዳችሁ ለማገልገል ዝግጅት ያደረጋችሁት እንዴት ነው? ስቴፋኒ እንዲህ ብላለች፦ “ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አገር ሄዶ ከማገልገል ጋር በተያያዘ መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡ ርዕሶችን አነበብኩ። * በተጨማሪም ሌላ አገር ሄጄ ለማገልገል ስላለኝ ግብ የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንዲሁም የወረዳ የበላይ ተመልካቹንና ባለቤቱን አማከርኳቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ግቤን በተመለከተ ወደ ይሖዋ ብዙ ጊዜ እጸልይ ነበር።” ከዚህም በተጨማሪ ስቴፋኒ ኑሮዋን ቀላል አድርጋ የነበረ ሲሆን ወጪዋን መቀነሷ ሌላ አገር ሄዳ በምታገለግልበት ጊዜ የሚያስፈልጋትን ገንዘብ ለማጠራቀም አስችሏታል።

ሀንዝ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ወደሚመራን ቦታ መሄድ ስለፈለግን አመራሩን ለማግኘት ወደ እሱ ጸለይን። በተጨማሪም ዕቅዳችንን ተግባራዊ የምናደርግበትን ቀን በመጥቀስ እንጸልይ ነበር።” እነዚህ ባልና ሚስት ወደ አራት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ደብዳቤዎች ላኩ። በጋና ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ አዎንታዊ ምላሽ ካገኙ በኋላ ለሁለት ወራት ለመቆየት አስበው ወደዚያ ተጓዙ። ሀንዝ “ከጉባኤው ጋር ማገልገል በጣም ስላስደሰተን ቆይታችንን አራዘምነው” በማለት ተናግሯል።

ኤድሪያ እና ጆርጅ

በ30ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኙትና በካናዳ የሚኖሩት ጆርጅ እና ኤድሪያ የሚባሉ ባልና ሚስት፣ የይሖዋን በረከት ለማግኘት መልካም ማሰብ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ውሳኔ ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን ለማስታወስ ይጥሩ ነበር። ስለዚህ ግባቸው ላይ ለመድረስ ቁርጥ ያለ እርምጃ ወሰዱ። ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አገር ለማገልገል ስትል ወደ ጋና ከሄደች እህት ጋር ተገናኙና ብዙ ጥያቄዎች ጠየቋት። ከዚህም ሌላ በካናዳና በጋና ወደሚገኙት ቅርንጫፍ ቢሮዎች ጻፉ። ኤድሪያ እንዲህ ብላለች፦ “በተጨማሪም ቀደም ሲል ካደረግነው ይበልጥ ኑሯችንን ቀላል የምናደርግባቸውን መንገዶች መፈለግ ጀመርን።” እንዲህ ያሉ ውሳኔዎች ማድረጋቸው በ2004 ወደ ጋና ለመዛወር አስቻላቸው።

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም

ወደ ሌላ አገር ከሄዳችሁ በኋላ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጠሟችሁ? እንዴትስ ተቋቋማችኋቸው? ኤሚ መጀመሪያ ላይ የከበዳት ናፍቆት ነበር። “ሁሉም ነገር እኔ ከለመድኩት በጣም የተለየ ነበር” ብላለች። ታዲያ በዚህ ረገድ የረዳት ምንድን ነው? ኤሚ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “የቤተሰቤ አባላት ስልክ እየደወሉ አገልግሎቴን በጣም እንደሚያደንቁ ይነግሩኝ ነበር፤ ይህም ወደዚህ ለመምጣት የወሰንኩት ለምን እንደሆነ እንዳልረሳ ረድቶኛል። ቆየት ብሎም እኔና ቤተሰቤ በኢንተርኔት አማካኝነት በቪዲዮ እየተያየን ማውራት ጀመርን። በዚህ መንገድ አንዳችን ሌላውን ማየት ስለምንችል ቤተሰቤ በጣም ሩቅ እንደሆኑ አይሰማኝም ነበር።” ኤሚ፣ ተሞክሮ ካካበተች አንዲት የአገሩ ተወላጅ የሆነች እህት ጋር ጓደኝነት መመሥረቷ የአካባቢውን የተለያዩ ባሕሎች ለመረዳት እንዳስቻላት ተናግራለች። “ሰዎች አንድ ነገር ያደረጉበት ምክንያት ግራ ሲገባኝ ጓደኛዬን ሄጄ እጠይቃታለሁ። እሷም ማድረግ ያለብኝንና የሌለብኝን ነገር እንዳውቅ የረዳችኝ ሲሆን ይህም አገልግሎቴን በደስታ ለማከናወን በጣም ጠቅሞኛል።”

ጆርጅና ኤድሪያ መጀመሪያ ወደ ጋና እንደሄዱ፣ ወደ ድሮ ዘመን የተመለሱ ያህል ሆኖ ተሰምቷቸው እንደነበረ ይናገራሉ። ኤድሪያ “ልብሳችንን ለማጠብ በማሽን ፋንታ በባልዲዎች መጠቀም ጀመርን” ብላለች። አክላም ምግብ ማዘጋጀት፣ ከለመዱት አንጻር በጣም ረጅም ጊዜ ይወስድባቸው እንደነበር ተናግራለች። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን አስቸጋሪውን ሁኔታ፣ ከለመዱት የተለየ ነገር እንደሆነ ብቻ አድርገው መመልከት ጀመሩ። ብሩክ፣ አቅኚዎች እንቅፋቶች ቢያጋጥሟቸውም ሕይወታቸው የሚያረካ እንደሆነ ገልጻለች። እንዲሁም ያገኟቸውን የሚያንጹ ተሞክሮዎች በሙሉ ሲያስቡ፣ የማይረሳ ትዝታ ጥለውባቸው እንዳለፉ ይሰማቸዋል።

የሚክስ አገልግሎት

እንዲህ ያለውን አገልግሎት ሌሎችም እንዲቀምሱት የምታበረታቱት ለምንድን ነው? ስቴፋኒ እንዲህ ብላለች፦ “እውነትን ለመማር በጣም ከመጓጓታቸው የተነሳ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ እንድታስጠኗቸው የሚፈልጉ ግለሰቦችን በምታገኙበት ክልል መስበክ በጣም ያስደስታል። በሕይወቴ ውስጥ ካደረግኳቸው ጥሩ ውሳኔዎች አንዱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ማገልገል ነው!” ስቴፋኒ በ2014 አሮን የተባለ ወንድም ያገባች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በጋና በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ያገለግላሉ።

አሁን በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ክሪስቲን የተባለች ከጀርመን የመጣች አቅኚ “በዚህ ዓይነቱ አገልግሎት በመካፈሌ ብዙ ተምሬያለሁ” በማለት ተናግራለች። ክሪስቲን ወደ ጋና ከመሄዷ በፊት በቦሊቪያ አገልግላለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “የምኖረው ከቤተሰቤ ርቄ ስለሆነ እርዳታ ሲያስፈልገኝ ምንጊዜም የምጠይቀው ይሖዋን ነው። ይሖዋ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እውን ሆኖልኛል። በተጨማሪም በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን ተወዳዳሪ የሌለው አንድነት መመልከት ችያለሁ። ይህ አገልግሎት አስደሳች ሕይወት እንድመራ አስተዋጽኦ አድርጓል።” ክሪስቲን በቅርቡ ጌድዮን የተባለ ወንድም ያገባች ሲሆን አሁን አብረው በጋና እያገለገሉ ነው።

ክሪስቲን እና ጌድዮን

ፊሊፕና አይዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸው እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ምን እርምጃ እንደሚወስዱ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፦ “ከ15 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ነበሩን፤ ይሁንና ጥናቶቻችንን በደንብ ለማስተማር ስንል ከ10 በላይ ሰዎችን ላለማስጠናት ወሰንን።” ታዲያ እንዲህ ማድረጋቸው ተማሪዎቹን ጠቅሟቸዋል? ፊሊፕ እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ማይክል የሚባልን አንድ ወጣት አስጠና ነበር። ማይክል በየቀኑ ያጠና የነበረ ከመሆኑም ሌላ በደንብ ተዘጋጅቶ ይመጣ ነበር፤ በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተሰኘውን መጽሐፍ በአንድ ወር ውስጥ ጨረስን። ከዚያም ማይክል ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆነ። አገልግሎት በወጣበት በመጀመሪያው ቀን ‘የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼን ሳስጠና ልትረዳኝ ትችላለህ?’ ብሎ ጠየቀኝ። እኔም በመገረም ሳየው፣ ሦስት ሰዎችን ጥናት እንዳስጀመረና እነሱን ለማስጠናት እርዳታ እንደሚፈልግ ነገረኝ።” እስቲ አስቡት፦ አስተማሪዎች በጣም ከማስፈለጋቸው የተነሳ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች ናቸው!

አይዳ እና ፊሊፕ

ኤሚ፣ ሰባኪዎች በጣም እንደሚያስፈልጉ የተገነዘበችው ወዲያውኑ እንደሆነ ትናገራለች፦ “ጋና ከደረስኩ ብዙም ሳልቆይ በአንዲት አነስተኛ መንደር እየሰበክን መስማት የተሳናቸውን ግለሰቦች መፈለግ ጀመርን። በዚያች መንደር ውስጥ ብቻ ስምንት መስማት የተሳናቸው ሰዎች አገኘን!” ኤሚ ከጊዜ በኋላ ኤሪክ የተባለ ወንድም ያገባች ሲሆን በልዩ አቅኚነት እያገለገሉ ነው። እነዚህ ባልና ሚስት፣ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ከ300 በላይ መስማት የተሳናቸው አስፋፊዎችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ለመርዳት ሲሉ በምልክት ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ያገለግላሉ። ጆርጅና ኤድሪያ በጋና ማገልገላቸው፣ ሚስዮናዊ መሆን ምን ማለት እንደሆነ በገዛ ዓይናቸው ለመመልከት አስችሏቸዋል። በመሆኑም በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በ126ኛው ክፍል እንዲሠለጥኑ ሲጠሩ በጣም ተደሰቱ! በዛሬው ጊዜ ሞዛምቢክ ውስጥ በሚስዮናዊነት እያገለገሉ ነው።

ያነሳሳቸው ፍቅር ነው

ከሌሎች አገሮች የመጡ ብዙ ወንድሞችና እህቶች አዝመራውን ለመሰብሰብ በአካባቢው ካሉት ክርስቲያኖች ጎን ተሰልፈው በትጋት ሲሠሩ ማየት በጣም ያስደስታል። (ዮሐ. 4:35) በጋና በየሳምንቱ በአማካይ 120 ግለሰቦች ይጠመቃሉ። ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ ወደ ጋና እንደሄዱት 17 የይሖዋ ምሥክሮች ሁሉ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንጌላውያን ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ተገፋፍተው ‘በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን አቅርበዋል።’ እነዚህ ክርስቲያኖች የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ሄደው ያገለግላሉ። ይሖዋ እንደነዚህ ባሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች ልቡ ምንኛ ይደሰት ይሆን!—መዝ. 110:3፤ ምሳሌ 27:11

^ አን.9የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደህ ማገልገል ትችላለህ?” እና “ወደ መቄዶንያ መሻገር ትችላለህ?” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።—መጠበቂያ ግንብ ሚያዝያ 15 እና ታኅሣሥ 15, 2009