በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በርኔት፣ ሲሞን፣ ኢስተን እና ካሌብ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ኦሺያንያ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ኦሺያንያ

ረኔ በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ በአውስትራሊያ የምትኖር እህት ስትሆን ያደገችው እውነት ውስጥ ነው፤ ቤተሰቦቿ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ረኔ “የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ስንል ብዙ ጊዜ ወደተለያዩ አካባቢዎች ሄደናል” ብላለች። “አባዬና እማዬ ሕይወታችን አስደሳች እንዲሆን ጥረት ያደርጉ ነበር! አሁን እኔ ራሴ ሁለት ልጆች አሉኝ፤ ልጆቼም እኔ ከወላጆቼ ጋር ያሳለፍኩት ዓይነት ሕይወት እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ።”

የረኔ ባል ሼን በ30ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን እሱም ተመሳሳይ መንፈሳዊ ግቦች አሉት። እንዲህ ይላል፦ “ሁለተኛዋ ልጃችን ከተወለደች በኋላ፣ በቶንጋ ደሴቶች ለማገልገል በጀልባ ወደ ደቡባዊ ምዕራብ ፓስፊክ ስለሄደ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ መጠበቂያ ግንብ ላይ አነበብን። * ያነበብነው ርዕስ በአውስትራሊያና በኒው ዚላንድ ወዳሉት የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች ደብዳቤ ጽፈን የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ የሚያስፈልጉበትን ቦታ እንድንጠይቅ አነሳሳን። * በምላሹም መጠበቂያ ግንቡ ላይ ወዳነበብነው ወደ ቶንጋ እንድንዛወር ተጋበዝን!”

ጄከብ፣ ረኔ፣ ስካይ እና ሼን

ሼንና ረኔ እንዲሁም ጄከብ እና ስካይ የተባሉት ልጆቻቸው ቶንጋ ውስጥ ለአንድ ዓመት ያህል ከቆዩ በኋላ በደሴቷ ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ የሕዝብ ዓመፅ በመቀስቀሱ ወደ አውስትራሊያ ለመመለስ ተገደዱ፤ ያም ቢሆን አገልግሎታቸውን የማስፋት ግባቸውን ከሐሳባቸው አላወጡትም። በ2011 ከአውስትራሊያ በስተ ምሥራቅ 1,500 ኪሎ ሜትር ርቃ በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ ወደምትገኘው ኖርፎክ ደሴት ተዛወሩ። ታዲያ ወደዚች ትንሽ ደሴት መሄዳቸው ምን ውጤት አስገኘ? በአሁኑ ጊዜ 14 ዓመት የሆነው ጄከብ “ይሖዋ እኛን ከመንከባከብም ባሻገር አገልግሎቱ አስደሳች እንዲሆንልን አድርጓል!” ይላል።

በቤተሰብ ሆኖ ለማገልገል ጥረት ማድረግ

እንደ ሼን፣ ረኔና ልጆቻቸው ሁሉ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሌሎች በርካታ ቤተሰቦችም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደው ለማገልገል ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። ይህን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው?

“ብዙ ሰዎች ምሥራቹን መስማት ይፈልጋሉ። በመሆኑም በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት አጋጣሚ እንዲያገኙ ማድረግ ፈለግን።”—በርኔት

በርኔት እና ሲሞን የሚባሉ በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙ ባልና ሚስት፣ አሁን 12 እና 9 ዓመት ከሆናቸው ኢስተን እና ካሌብ የሚባሉ ወንዶች ልጆቻቸው ጋር በኩዊንስላንድ፣ አውስትራሊያ ወደምትገኝ በርክታውን የምትባል ራቅ ያለች ከተማ ተዛወሩ። “የይሖዋ ምሥክሮች በዚች ከተማ የሚሰብኩት በሦስት ወይም በአራት ዓመት አንዴ ብቻ ነበር” በማለት በርኔት ተናግሯል። “ብዙ ሰዎች ምሥራቹን መስማት ይፈልጋሉ። በመሆኑም በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት አጋጣሚ እንዲያገኙ ማድረግ ፈለግን።”

ጂም፣ ጃክ፣ ማርክ እና ካረን

አሁን በ50ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኙት ማርክ እና ካረን በሲድኒ፣ አውስትራሊያ አቅራቢያ በሚገኙ የተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ አገልግለዋል፤ ከዚያም ጄሲካ፣ ጂም እና ጃክ ከተባሉት ሦስት ልጆቻቸው ጋር በመሆን በኖርዘርን ቴሪቶሪ ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ነለንቦይ የተባለ ማዕድን አውጪዎች የሚኖሩበት አካባቢ ተዛወሩ። ማርክ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎችን ስለምወድ በጉባኤም ሆነ በአገልግሎት ብዙ መሥራት በምችልበት ቦታ መሆን ፈልጌ ነበር።” ይሁን እንጂ ካረን ወደዚያ አካባቢ ለመዛወር አመንትታ ነበር። ካረን “ማርክና ሌሎች ካበረታቱኝ በኋላ ግን ለመሞከር ፈቃደኛ ሆንኩ። እንዲህ በማድረጌ አሁን ደስተኛ ነኝ!” ብላለች።

ቤንጃሚን፣ ጄድ፣ ብሪያ እና ካሮሊን

በ2011 ቤንጃሚን እና ካሮሊን፣ ጄድ እና ብሪያ የሚባሉ ለትምህርት ያልደረሱ ሁለት ሴቶች ልጆቻቸውን ይዘው ከኩዊንስላንድ፣ አውስትራሊያ በመነሳት ከኢንዶኔዢያ ተጎራባች ደሴቶች መካከል አንዷ በሆነችው በቲሞር ደሴት ላይ ወደምትገኘው ቲሞር ሌስተ የምትባል ትንሽ አገር ተመልሰው ሄዱ። ቤን እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ካሮሊን ቀደም ሲል በቲሞር ሌስተ ልዩ አቅኚዎች ሆነን አገልግለን ነበር። አገልግሎቱ እጅግ ደስ የሚል ሲሆን ወንድሞችም በጣም ይደግፉን ነበር። ከዚያ ለቀን ስንሄድ በጣም ያዘንን ሲሆን ተመልሰን ለመምጣትም ቆርጠን ነበር። ልጆቻችን ሲወለዱ፣ ወደዚያ የመመለስ ዕቅዳችንን ለጊዜው ብናስተላልፈውም ሐሳባችንን አልቀየርንም።” ካሮሊንም በማከል “ልጆቻችን በሚስዮናውያን፣ በቤቴላውያንና በልዩ አቅኚዎች ተከበው እንዲያድጉና ይሖዋን በማገልገል እንዲደሰቱ ፈለግን” ብላለች።

ወደ ሌላ አካባቢ ለመዛወር መዘጋጀት

ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ከእናንተ መካከል፣ ግንብ ለመገንባት ፈልጎ ለመጨረስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንዳለው ለማወቅ በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን የማያሰላ ማን ነው?” ብሏቸዋል። (ሉቃስ 14:28) በተመሳሳይም አንድ ቤተሰብ ወደ ሌላ አካባቢ ለመዛወር ሲያስብ ጥሩ ዕቅድ ማውጣቱ አስፈላጊ ነው። ታዲያ በየትኞቹ አቅጣጫዎች መዘጋጀት ያስፈልጋል?

በመንፈሳዊ፦ ቤን “ሌሎችን ማገልገል እንጂ ለእነሱ ሸክም መሆን አልፈለግንም” ብሏል። “በመሆኑም ከመዛወራችን በፊት ራሳችንን በመንፈሳዊ ለማጠናከር ጥረት አደረግን። በተጨማሪም በአገልግሎትና በሌሎች የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ያለንን ተሳትፎ ከፍ አደረግን።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጄከብ እንዲህ ይላል፦ “ወደ ኖርፎክ ደሴት ከመዛወራችን በፊት የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደው ስላገለገሉ ቤተሰቦች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! ላይ የወጡ ብዙ የሕይወት ታሪኮችን አነበብን። እነዚህ ቤተሰቦች ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎችና ይሖዋ እንዴት እንደተንከባከባቸው ተወያየን።” አሥራ አንድ ዓመት የሆናት እህቱ ስካይም “ለብቻዬ ሆኜም ሆነ ከእማዬና ከአባዬ ጋር ብዙ ጸልያለሁ” በማለት ተናግራለች።

በስሜት፦ ረኔ እንዲህ ትላለች፦ “በምወደው አካባቢ፣ በቤተሰብና በቅርብ ወዳጆቻችን ተከብበን እንኖር ስለነበር እዚያው መቆየት ቀላል ይሆንልን ነበር። ይሁን እንጂ ትተናቸው ስለምንሄዳቸው ነገሮች ከማብሰልሰል ይልቅ መሄዳችን ለቤተሰባችን ስለሚያመጣው ጥቅም አሰብኩ።”

ባሕሉ፦ ብዙ ቤተሰቦች በአዲሱ አካባቢ ለሚጠብቃቸው ሁኔታ ራሳቸውን ለማዘጋጀት ሲሉ ምርምር ያደርጋሉ። “ስለ ነለንቦይ ለማወቅ የቻልነውን ያህል ብዙ አነበብን” ይላል ማርክ። “እዚያ የሚኖሩ ወንድሞች፣ ስለ አካባቢው ሕዝብና ስለ ባሕሉ ፍንጭ እንዲሰጠን ሲሉ በከተማው የሚታተመውን ጋዜጣ በደግነት ይልኩልን ነበር።”

ወደ ኖርፎክ ደሴት የተዛወረው ሼን አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ከሁሉ በላይ ትኩረት ያደረግኩት ክርስቲያናዊ ባሕርያትን በማሳየት ላይ ነው። ቅን፣ ገር፣ ሐቀኛና ታታሪ ከሆንኩ በዓለም ላይ በየትኛውም ቦታ ከአካባቢው ሰው ጋር ተስማምቼ መኖር እንደምችል አውቃለሁ።”

ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መወጣት

የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደው ስኬታማ የሆኑ ክርስቲያኖች፣ ያልተጠበቁ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሊያጋጥሟቸው ይችላሉ፤ በዚህ ወቅት ከሁኔታዎች ጋር ራስን ማስማማትና አዎንታዊ መሆን አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦

ረኔ እንዲህ ትላለች፦ “አንድን ነገር መሥራት የሚቻልባቸው የተለያዩ መንገዶች እንዳሉ መቀበልን ተምሬያለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ በኖርፎክ ደሴት ላይ ከባድ ማዕበል በሚነሳበት ጊዜ አስፈላጊ አቅርቦት የጫኑ መርከቦች ጭነታቸውን ማራገፍ አይችሉም፤ በመሆኑም የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦች እጥረት ከመኖሩም ሌላ ዋጋቸው ይወደዳል። ስለዚህ ምግብ በማዘጋጅበት ጊዜ ዘዴኛ መሆንን ተምሬያለሁ።” ባሏ ሼንም “ወጪያችን ለሳምንት ከመደብነው ባጀት እንዳያልፍ እንጠነቀቃለን” በማለት ተናግሯል።

ልጃቸው ጄከብ ደግሞ ከዚህ የተለየ ተፈታታኝ ሁኔታ እንደገጠመው ይገልጻል። “አዲሱ ጉባኤያችን ከእኛ ቤተሰብ ሌላ ሰባት አባላት ብቻ የነበሩት ሲሆን ሁሉም አዋቂዎች ናቸው። ስለዚህ እኩዮቼ የሆኑ ጓደኞች ማግኘት አልቻልኩም ነበር! ከአዋቂዎቹ ጋር አብሬ ማገልገል ስጀምር ግን ብዙም ሳይቆይ ጓደኛሞች ሆንን።”

አሁን 21 ዓመት የሆነው ጂምም ተመሳሳይ ሁኔታ ገጥሞት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ለነለንቦይ በጣም ቅርብ የሆነው ጉባኤ ከ725 ኪሎ ሜትር የሚበልጥ ርቀት ላይ የሚገኝ ስለሆነ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ከወንድሞች ጋር ለመገናኘት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ቀደም ብለን በመድረስ ከወንድሞችና እህቶች ጋር ጥሩ ጊዜ እናሳልፋለን። እነዚህ ወቅቶች በዓመቱ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የምንሰጣቸው ናቸው!”

“እዚህ በመምጣታችን በጣም ደስ ብሎኛል!”

መጽሐፍ ቅዱስ “የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች” ይላል። (ምሳሌ 10:22) የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ የሄዱ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖች በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የዚህን ሐሳብ እውነተኝነት በሕይወታቸው ቀምሰውታል።

ማርክ “ከሁሉም የሚበልጠው በረከት ወደ ሌላ አካባቢ መዛወራችን በልጆቻችን ላይ ያመጣው ውጤት ነው” ይላል። “ትላልቆቹ ልጆቻችን ይሖዋ መንግሥቱን የሚያስቀድሙ ሰዎችን እንደሚንከባከብ ፍጹም እምነት አላቸው። እንዲህ ያለውን እምነት በገንዘብ መግዛት አይቻልም።”

ሼን እንዲህ ይላል፦ “ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር በጣም ተቀራርበናል። ይሖዋ ምን እንዳደረገላቸው ሲያወሩ ስሰማቸው እውነተኛ እርካታ ይሰማኛል።” ልጁ ጄከብም በአባቱ ሐሳብ ይስማማል፦ “ግሩም ጊዜ አሳልፌያለሁ። እዚህ በመምጣታችን በጣም ደስ ብሎኛል!”

^ አን.3 በታኅሣሥ 15, 2004 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 8-11 ላይ የወጣውን “‘ሰው ወዳድ ደሴቶች’ ላይ የሚኖሩ የአምላክ ወዳጆች” የሚል ርዕስ ተመልከት።

^ አን.3 በ2012 የአውስትራሊያና የኒው ዚላንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ተዋህደው አውስትራሌዢያ የሚባል ቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቁሟል።