በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ማዳጋስካር

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ማዳጋስካር

“አቅኚዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ያገለገሉ ጓደኞቼን ተሞክሮ ስሰማ እኔም እነሱ ያገኙትን ዓይነት ደስታ ለማጣጣም ተመኘሁ” በማለት ሲልቭያና የምትባል በ20ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ አቅኚ ተናግራለች። ሲልቭያና አክላም “ይሁን እንጂ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄዶ ማገልገል ከአቅሜ በላይ ነው የሚል ፍራቻ ነበረኝ” ብላለች።

አንተስ የሲልቭያናን ስሜት ትጋራለህ? የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ክልል ሄደህ ለማገልገል የምትመኝ ቢሆንም እዚህ ግብ ላይ መድረስ እንደማትችል ሆኖ ይሰማሃል? ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ! በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች አገልግሎታቸውን እንዳያሰፉ ጋሬጣ የሆኑባቸውን ነገሮች በይሖዋ እርዳታ ማሸነፍ ችለዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን ይሖዋ እንዴት እንደረዳቸው ለማየት በዓለም ላይ ካሉ ደሴቶች መካከል በስፋቷ አራተኛ የሆነችውን ማዳጋስካርን እንጎብኝ።

ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከ70 የሚበልጡ ቀናተኛ አስፋፊዎችና አቅኚዎች በዚህ ፍሬያማ መስክ ለማገልገል ሲሉ ከ11 አገሮች * መጥተዋል፤ አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በዚህች አገር ብዙ ሰዎች ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት አላቸው። በተጨማሪም የደሴቲቱ ተወላጅ የሆኑ በርካታ አስፋፊዎች በዚህች ሰፊ ደሴት ላይ የመንግሥቱን መልእክት ለማሠራጨት ሲሉ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለመዛወር ፈቃደኞች ሆነዋል። እስቲ ከአንዳንዶቹ ጋር እንተዋወቅ።

ፍርሃትንና ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎችን መቋቋም

ፐሪንና ሉዊ

ሉዊ እና ፐሪን የሚባሉ በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ባልና ሚስት ከፈረንሳይ ወደ ማዳጋስካር ተዛውረዋል። ወደ ሌላ አገር ሄደው አገልግሎታቸውን ለማስፋት ለዓመታት ሲያስቡ የቆዩ ቢሆንም ፐሪን ይህን ለማድረግ ፈራ ተባ ትል ነበር። እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ወደማላውቀው ቦታ መሄድ ያስፈራኝ ነበር። ቤተሰባችንን፣ ጉባኤያችንን፣ አፓርታማችንን፣ የምናውቃቸውን ቦታዎችና የለመድነውን አኗኗር ትቶ ስለመሄድ ሳስብ ጭንቅ ይለኝ ነበር። በእርግጥም ላሸንፈው የሚገባኝ ትልቁ እንቅፋት የራሴ ጭንቀት ነበር።” በ2012 ፐሪን እንደምንም ራሷን አደፋፈረችና ከሉዊ ጋር ወደ ማዳጋስካር ተዛወሩ። ታዲያ ስለ ውሳኔያቸው ምን ይሰማታል? “አሁን መለስ ብዬ ሳስበው በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን እጅ ማየታችን እምነታችንን እንዳጠናከረልን ይሰማኛል” ብላለች። ሉዊም በማከል እንዲህ ብሏል፦ “እስቲ አስቡት፣ ማዳጋስካር ውስጥ ባከበርነው የመጀመሪያው የመታሰቢያ በዓል ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን መካከል አሥሩ ተገኝተው ነበር!”

ሉዊና ፐሪን ችግሮች ሲያጋጥሟቸው በአገልግሎት ምድባቸው ላይ ለመቆየት ብርታት የሰጣቸው ምንድን ነው? ለመጽናት የሚያስፈልጋቸውን ኃይል እንዲሰጣቸው ይሖዋን በጸሎት ተማጸኑት። (ፊልጵ. 4:13) ሉዊ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ ጸሎታችንን እንደመለሰልንና ‘የአምላክን ሰላም’ እንደሰጠን በሕይወታችን ተመልክተናል። አገልግሎታችን በሚያስገኘው ደስታ ላይ ማተኮር ችለናል። በተጨማሪም አገር ቤት ያሉ ጓደኞቻችን ተስፋ እንዳንቆርጥ ለማበረታታት ኢ-ሜይልና ደብዳቤ ይልኩልን ነበር።”—ፊልጵ. 4:6, 7፤ 2 ቆሮ. 4:7

ሉዊና ፐሪን በመጽናታቸው ይሖዋ አትረፍርፎ ባርኳቸዋል። ሉዊ እንዲህ ብሏል፦ “በጥቅምት ወር 2014 ፈረንሳይ ውስጥ፣ ለባለትዳሮች በተዘጋጀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት * የመካፈል መብት አግኝተናል። በዚያ ትምህርት ቤት መካፈል መቻላችን ከይሖዋ ያገኘነው የማይረሳ ስጦታ ነው።” ባልና ሚስቱ ከትምህርት ቤቱ ሲመረቁ በድጋሚ በማዳጋስካር መመደባቸው በጣም አስደስቷቸዋል።

“እንኮራባችኋለን!”

ናዲንና ዲድዬ

ዲድዬ እና ናዲን የተባሉት ባልና ሚስት በ2010 ከፈረንሳይ ወደ ማዳጋስካር ሲዛወሩ በ50ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ነበሩ። ዲድዬ እንዲህ ይላል፦ “ወጣት ሳለን በአቅኚነት እናገለግል ነበር፤ ከዚያም ሦስት ልጆቻችንን አሳደግን። ልጆቻችን ለአካለ መጠን ሲደርሱ በውጭ አገር ለማገልገል አሰብን።” ናዲንም እንዲህ ብላለች፦ “ከልጆቻችን የመለየቱ ሐሳብ እንዳመነታ አድርጎኝ ነበር፤ እነሱ ግን ‘ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ወደ ሌላ አገር ብትሄዱ እንኮራባችኋለን!’ አሉን። ልጆቻችን የተናገሩት ነገር ወደ ሌላ አገር ሄደን ለማገልገል አበረታታን። አሁን የምንኖረው ከልጆቻችን በጣም ርቀን ቢሆንም ከእነሱ ጋር አዘውትረን መነጋገር መቻላችን ያስደስተናል።”

ዲድዬና ናዲን የማላጋሲን ቋንቋ መማር ተፈታታኝ ሆኖባቸው ነበር። ናዲን ፈገግ እያለች “አሁን የ20 ዓመት ወጣት አይደለንም” ብላለች። ታዲያ እንዴት ተሳካላቸው? መጀመሪያ በፈረንሳይኛ በሚካሄድ ጉባኤ ላይ መገኘት ጀመሩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ የአካባቢውን ቋንቋ ለመማር ዝግጁ እንደሆኑ ሲሰማቸው በማላጋሲ ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ ተዛወሩ። ናዲን እንዲህ ብላለች፦ “ምሥራቹን ስንሰብክ የምናገኛቸው ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ያስደስታቸዋል። ቤታቸው ድረስ ሄደን ስላነጋገርናቸው ብዙ ጊዜ ያመሰግኑናል። መጀመሪያ ላይ ሁኔታው ሕልም እንጂ እውን አልመስል ብሎኝ ነበር። በዚህ ክልል በአቅኚነት በማገልገሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ‘ደስ ሲል፣ ዛሬም ልሰብክ እሄዳለሁ!’ ብዬ አስባለሁ።”

ዲድዬ የማላጋሲን ቋንቋ መማር በጀመረበት ጊዜ ያጋጠመውን ሁኔታ ሲያስታውስ ፈገግ አለ። እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ወቅት የጉባኤ ስብሰባ እየመራሁ ነበር፤ ሆኖም ወንድሞችና እህቶች ከሚሰጡት መልስ አንዱም አልገባኝም። ‘አመሰግናለሁ’ ከማለት ውጭ ምንም ማለት አልቻልኩም። አንዲትን እህት ለሰጠችው መልስ ሳመሰግናት ከኋላዋ የተቀመጡት ወንድሞችና እህቶች መልሷ ትክክል እንዳልሆነ በምልክት ጠቆሙኝ። እኔም ጥያቄውን እንዲመልስ ቶሎ ብዬ ሌላ ወንድም ጋበዝኩ፤ መቼም እሱ የሰጠው መልስ ትክክለኛ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ።”

ግብዣውን በደስታ ተቀብለዋል

በ2005 በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ትዬሪ እና ባለቤቱ ናድያ “አምላክን የሚያስከብር ግብ ላይ ለመድረስ ተጣጣሩ” የሚለውን ድራማ ተመለከቱ። ስለ ጢሞቴዎስ የሚገልጸው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ልባቸውን ስለነካው ተጨማሪ የምሥራቹ ሰባኪዎች ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው ለማገልገል ይበልጥ ተነሳሱ። ትዬሪ እንዲህ ይላል፦ “ድራማው አልቆ እያጨበጨብን ሳለ ወደ ባለቤቴ ጠጋ ብዬ ‘የት ብንሄድ ይሻላል?’ ብዬ ጠየቅኳት። እሷም ይህንኑ እያሰበች እንደነበር ነገረችኝ።” ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ግባቸው ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ጀመሩ። ናድያ “በአራት ሻንጣዎች ውስጥ ሊሸከፍ የሚችል ጓዝ ብቻ እስኪቀረን ድረስ ንብረታችንን ቀስ በቀስ ቀነስን!” ብላለች።

በስተ ግራ፦ ናድያና ማሪ ማደሌን በስተ ቀኝ፦ ትዬሪ

በ2006 ወደ ማዳጋስካር የሄዱ ሲሆን ገና ከመጀመሪያው አንስቶ በአገልግሎታቸው ደስተኞች ነበሩ። ናድያ “የምንሰብክላቸው ሰዎች ለመልእክቱ የሚሰጡት ምላሽ በጣም ያስደስተናል” ብላለች።

ከስድስት ዓመታት በኋላ ግን ባልና ሚስቱ አንድ ተፈታታኝ ሁኔታ ገጠማቸው። በፈረንሳይ ይኖሩ የነበሩት የናድያ እናት ማሪ ማደሌን ወደቁና እጃቸው ተሰበረ፤ እንዲሁም በጭንቅላታቸው ላይ ጉዳት ደረሰባቸው። ባልና ሚስቱ ከሐኪም ጋር ከተማከሩ በኋላ ወደ ማዳጋስካር መጥተው ከእነሱ ጋር እንዲኖሩ ማሪ ማደሌንን ጠየቋቸው። እሳቸውም በወቅቱ 80 ዓመታቸው የነበረ ቢሆንም ግብዣውን በደስታ ተቀበሉ። ታዲያ ማሪ ማደሌን በውጭ አገር ስለ መኖር ምን ይሰማቸዋል? እንዲህ ብለዋል፦ “አንዳንዶቹን ነገሮች መልመድ ተፈታታኝ የሚሆንብኝ ጊዜ አለ፤ አቅሜ ውስን ቢሆንም በጉባኤ ውስጥ ጠቃሚ አስተዋጽኦ እንደማበረክት ይሰማኛል። ይበልጥ የሚያስደስተኝ ደግሞ እኔ እዚህ መኖሬ ልጆቼ በዚህ አገር በሚያከናውኑት ፍሬያማ አገልግሎት እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸው መሆኑ ነው።”

“ይሖዋ እጁን ዘርግቶልኛል”

ሪን በታንድሩይ ቋንቋ ንግግር ሲያቀርብ

ሪን በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ወንድም ነው። ሪን ያደገው በምሥራቃዊ ማዳጋስካር በሚገኝ አላኦትራ ማንጉሩ የሚባል ለም አካባቢ ነው። በትምህርቱ ጥሩ ውጤት ያመጣ ስለነበር ከፍተኛ ትምህርት ለመከታተል አስቦ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ ግን ሐሳቡን ቀየረ። እንዲህ ይላል፦ “የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስጨርስ ‘ፈተናውን ካለፍኩ አቅኚነት እጀምራለሁ’ ብዬ ለይሖዋ ቃል ገብቼ ነበር።” ሪን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ ለይሖዋ የገባውን ቃል ጠብቋል። የተወሰነ ሰዓት ብቻ እየሠራ አቅኚ ሆኖ ማገልገል ጀመረ፤ የሚኖረውም ከአንድ አቅኚ ወንድም ጋር ነበር። ሪን “እስከ ዛሬ ካደረግኳቸው ውሳኔዎች ሁሉ የተሻለው ይሄ ነው” ብሏል።

ይሁን እንጂ ቤተሰቦቹ ትምህርቱን ቀጥሎ በአንድ ጥሩ የሥራ መስክ ለመሰማራት ያልፈለገበት ምክንያት አልገባቸውም። እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ፣ አጎቴና የአባቴ አክስት ከፍተኛ ትምህርት እንድከታተል አበረታተውኝ ነበር። እኔ ግን አቅኚነቴን ማቆም ፈጽሞ አልፈለግኩም።” ብዙም ሳይቆይ ሪን የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዶ ለማገልገል አሰበ። እንዲህ ዓይነት ምኞት እንዲያድርበት ካደረጉት ነገሮች አንዱን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሌቦች ቤታችን ገብተው ብዙ ንብረት ወሰዱብኝ። ይህም ‘በሰማይ ሀብት ስለማከማቸት’ ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ቆም ብዬ እንዳስብበት አደረገኝ። በመሆኑም መንፈሳዊ ሀብት ለማከማቸት በትጋት ለመሥራት ቆርጬ ተነሳሁ።” (ማቴ. 6:19, 20) ስለዚህ ሪን ይኖርበት ከነበረው ቦታ 1,300 ኪሎ ሜትር ርቆ በአገሪቱ ደቡባዊ ጫፍ ወደሚገኝ ድርቅ የሚያጠቃው አካባቢ ተዛወረ። በዚያ አካባቢ የሚኖሩት አንታንድሩይ የሚባሉት ሕዝቦች ናቸው። ይሁንና ሪን ወደዚያ የሄደው ለምንድን ነው?

ሪን ንብረቱ ከመሰረቁ ከአንድ ወር በፊት ሁለት የአንታንድሩይ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀምሮ ነበር። በመሆኑም በእነሱ ቋንቋ አንዳንድ አገላለጾችን ተማረ፤ በተጨማሪም የመንግሥቱ መልእክት ገና ስላልደረሳቸው በርካታ የአንታንድሩይ ሰዎች ማሰብ ጀመረ። ሪን “ይሖዋ የታንድሩይ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወዳሉበት ክልል ለመዛወር እንዲረዳኝ ጸለይኩ” ብሏል።

ሪን ወደዚያ አካባቢ እንደሄደ አንድ እንቅፋት ገጠመው። በዚያ አካባቢ ሥራ ማግኘት አልቻለም። እንዲያውም አንድ ሰው “ወደዚህ የመጣኸው ለምንድን ነው? እዚህ ያሉ ሰዎች እኮ ሥራ ለማግኘት የሚሄዱት አንተ ወደነበርክበት ቦታ ነው!” አለው። ከሁለት ሳምንት በኋላ ሪን የክልል ስብሰባ ላይ ለመገኘት አካባቢውን ለቅቆ ሲሄድ በእጁ የነበረው ገንዘብ ሊያልቅ ምንም አልቀረውም ነበር፤ በመሆኑም ምን ማድረግ እንደሚሻለው ግራ ተጋብቶ ነበር። በስብሰባው የመጨረሻ ቀን ላይ አንድ ወንድም የኮቱ ኪስ ውስጥ ገንዘብ ከተተለት። ገንዘቡ፣ ሪን ወደ አንታንድሩይ አካባቢ ተመልሶ ለመሄድና እርጎ እየሸጠ ለመተዳደር የሚበቃው ነበር። ሪን እንዲህ ብሏል፦ “ልክ በሚያስፈልገኝ ጊዜ ይሖዋ እጁን ዘርግቶልኛል። አሁን ስለ ይሖዋ ለመማር አጋጣሚ ያላገኙትን ሰዎች መርዳቴን መቀጠል እችላለሁ!” በጉባኤው ውስጥም ሊያከናውነው የሚችለው ብዙ ሥራ ነበረ። ሪን አክሎም “በየሁለት ሳምንቱ የሕዝብ ንግግር አቀርባለሁ። ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት እያሠለጠነኝ ነው” ብሏል። ሪን ስለ ይሖዋ መማር ለሚፈልጉ ብዙ የታንድሩይ ተናጋሪ ሰዎች አሁንም የመንግሥቱን መልእክት እያካፈለ ነው።

“በእውነት አምላክ ይባረካል”

ይሖዋ “በምድር ላይ በረከትን የሚሻ ሁሉ በእውነት አምላክ [እንደሚባረክ]” ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ኢሳ. 65:16) አገልግሎታችንን ለማስፋት ስንጥር የሚገጥሙንን እንቅፋቶች ለማሸነፍ ተግተን ከሠራን የይሖዋን በረከት እናገኛለን። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰችውን ሲልቭያናን እንውሰድ። ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄዳ ማገልገል ከአቅሟ በላይ እንደሆነ በማሰብ ፈርታ ነበር። እንዲህ ብላ ያሰበችው ለምንድን ነው? “የግራ እግሬ ከቀኝ እግሬ በ9 ሴንቲ ሜትር ያህል ያጥራል። ስለዚህ የምራመደው እያነከስኩ ሲሆን ቶሎ ይደክመኛል” ብላለች።

ዶራቲን በተጠመቀችበት ዕለት ከሲልቭያና (በስተ ግራ) እና ከሲልቪ አን (በስተ ቀኝ) ጋር

ያም ቢሆን በ2014 ሲልቭያና በጉባኤዋ ውስጥ ከነበረች ሲልቪ አን የምትባል ወጣት አቅኚ ጋር በመሆን ወደ አንዲት አነስተኛ መንደር ተዛወረች፤ መንደሯ የምትገኘው ከትውልድ ከተማቸው 85 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው። ሲልቭያና እንቅፋቶች ቢኖሩባትም ምኞቷ ተሳክቷል፤ ደግሞም ግሩም በረከት አግኝታለች! “በአዲሱ ምድቤ ላይ ማገልገል ከጀመርኩ ገና በዓመቴ ዶራቲን የተባለች መጽሐፍ ቅዱስ የማስጠናት ወጣት በወረዳ ስብሰባችን ላይ ተጠመቀች” በማለት ተናግራለች።

“እረዳሃለሁ”

ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ሄደው የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች ከተናገሩት ነገር የምናገኘው ትምህርት አለ፦ አገልግሎታችንን ለማስፋት ስንፈልግ የሚገጥመንን እንቅፋት ለማሸነፍ በምንጣጣርበት ጊዜ ይሖዋ “አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ” በማለት ለአገልጋዮቹ የገባውን ቃል እውነተኝነት በራሳችን ሕይወት እንመለከታለን። (ኢሳ. 41:10) በውጤቱም ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ይጠናከራል። በተጨማሪም በምንኖርበት አካባቢም ሆነ በውጭ አገር ለማገልገል ራሳችንን በፈቃደኝነት ማቅረባችን በአዲሱ ዓለም ለሚጠብቁን ቲኦክራሲያዊ ሥራዎች ያዘጋጀናል። ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ዲድዬ እንደገለጸው “ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል ለወደፊቱ ጊዜ ጥሩ ሥልጠና ነው!” ሌሎች በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞችም ይህንን ሥልጠና አሁኑኑ እንዲጀምሩ እንመኛለን!

^ አን.4 በርካታ ክርስቲያኖች፣ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ ከሉክሰምበርግ፣ ከስዊዘርላንድ፣ ከስዊድን፣ ከቼክ ሪፑብሊክ፣ ከኒው ካሊዶኒያ፣ ከካናዳ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከጀርመን፣ ከጓዴሎፕና ከፈረንሳይ ወደ ማዳጋስካር መጥተዋል።

^ አን.8 ይህ ትምህርት ቤት አሁን በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ተተክቷል። ብቃቱን የሚያሟሉ በውጭ አገር የሚያገለግሉ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በትውልድ አገራቸው በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል ሊያመለክቱ ይችላሉ፤ አሊያም ደግሞ ትምህርት ቤቱ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ወይም ጥሩ አድርገው በሚናገሩት ቋንቋ በሚካሄድበት ሌላ አገር ለመካፈል ማመልከት ይችላሉ።