በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አሊሳ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ቱርክ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ቱርክ

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ‘የመንግሥቱን ምሥራች’ በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። (ማቴ. 24:14) አንዳንዶቹ እንዲያውም ምሥራቹን ለመስበክ ወደ ሌሎች አገሮች ሄደዋል። ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ጳውሎስ ሚስዮናዊ ሆኖ ባደረጋቸው ጉዞዎች፣ በአሁኑ ጊዜ ቱርክ ተብላ የምትጠራው አገር ወዳለችበት አካባቢ በመሄድ ምሥራቹን በስፋት ሰብኳል። * ከ2,000 ዓመታት በኋላ ይኸውም በ2014 ደግሞ በቱርክ በድጋሚ ልዩ የስብከት ዘመቻ ተካሂዷል። ይህ የስብከት ዘመቻ የተዘጋጀው ለምንድን ነው? በዘመቻው እነማን ተካፍለዋል?

“ምንድን ነው የተፈጠረው?”

በቱርክ ከ2,800 የሚበልጡ አስፋፊዎች ያሉ ሲሆን የአገሪቱ ነዋሪዎች ግን 79 ሚሊዮን ናቸው። በመሆኑም 1 አስፋፊ ወደ 28,000 ለሚጠጉ ሰዎች መስበክ አለበት ማለት ነው። ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው አስፋፊዎቹ መስበክ የቻሉት ከአገሪቱ ነዋሪዎች መካከል ለተወሰኑት ብቻ ነው። የልዩ የስብከት ዘመቻው ዓላማ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች መስበክ ነበር። ወደ 550 የሚጠጉ ቱርክኛ የሚናገሩ ወንድሞችና እህቶች ከተለያዩ አገሮች ወደ ቱርክ በመሄድ በአገሪቱ ካሉት አስፋፊዎች ጋር በዘመቻው ተካፍለዋል። ዘመቻው ምን ውጤት አስገኝቷል?

ለብዙዎች ምሥክርነት ተሰጥቷል። በኢስታንቡል የሚገኝ አንድ ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ሰዎች እኛን ሲያዩ ‘እዚህ የሚካሄድ ልዩ ስብሰባ አለ እንዴ? የትም ስንሄድ የይሖዋ ምሥክሮችን እያገኘን ነው!’ ይሉን ነበር።” በኢዝሚር ከተማ የሚገኝ አንድ ጉባኤ ደግሞ የሚከተለውን ደብዳቤ ጽፏል፦ “ታክሲ መጠበቂያ ቦታ ላይ የሚሠራ አንድ ሰው ወደ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ቀርቦ ‘ምንድን ነው የተፈጠረው? ከቀድሞው የተለየ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመራችሁ እንዴ?’ ብሎ ጠየቀው።” በእርግጥም ዘመቻው የሰዎችን ቀልብ ስቧል።

ስቴፈን

ከሌላ አገር የመጡት ወንድሞች በስብከቱ ሥራ በጣም ተደስተዋል። ከዴንማርክ የመጣው ስቴፈን እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “በየዕለቱ አገልግሎት ስወጣ ስለ ይሖዋ ጨርሶ ሰምተው ለማያውቁ ሰዎች እመሠክር ነበር። የይሖዋ ስም እንዲታወቅ እያደረግኩ እንደሆነ ተሰምቶኛል።” ከፈረንሳይ የመጣው ዣን ዳቪድ ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአንድ መንገድ ላይ ብቻ ለሰዓታት መስበክ ችለን ነበር። በጣም አስደሳች ነበር! አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች አያውቁም። በእያንዳንዱ ቤት ማለት ይቻላል፣ ከቤቱ ባለቤት ጋር ውይይት መጀመር፣ ለግለሰቡ አንድ ቪዲዮ ማሳየት እንዲሁም ጽሑፍ ማበርከት ችለናል።”

ዣን ዳቪድ (መሃል)

እነዚህ 550 ወንድሞችና እህቶች በሁለት ሳምንት ውስጥ ብቻ 60,000 የሚያህሉ ጽሑፎችን አበርክተዋል! በእርግጥም ዘመቻው ምሥራቹ በስፋት እንዲሰበክ አጋጣሚ ከፍቷል።

ወንድሞች ለአገልግሎቱ ያላቸው ቅንዓት ጨምሯል። ልዩ የስብከት ዘመቻው በቱርክ የሚኖሩ ወንድሞችንም ይበልጥ እንዲሠሩ አነሳስቷቸዋል። ብዙዎች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር አስበዋል። እንዲያውም ከዘመቻው በኋላ ባሉት 12 ወራት ውስጥ በቱርክ ያሉት የዘወትር አቅኚዎች ቁጥር 24 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

ሺሪን

ከሌላ አገር መጥተው በዘመቻው የተካፈሉ ወንድሞችና እህቶች፣ ወደሚኖሩበት አገር ከተመለሱ በኋላም እንኳ ዘመቻው በአገልግሎታቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ተናግረዋል። ከጀርመን የመጣች ሺሪን የተባለች እህት እንደሚከተለው ስትል ጽፋለች፦ “በቱርክ ያሉ ወንድሞች፣ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መስበክ ምንም አይከብዳቸውም። እኔ ደግሞ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መስበክ በጣም ይጨንቀኛል። ሆኖም ልዩ የስብከት ዘመቻውና በቱርክ ያሉ ወንድሞች ምሳሌ እንዲሁም ደጋግሜ መጸለዬ፣ ከዚህ በፊት ማድረግ ያልቻልኩትን ነገር ለማድረግ ረድተውኛል። በባቡር ውስጥ እንኳ መስበክና ትራክት ማበርከት ችያለሁ! አሁን እንደ በፊቱ አይጨንቀኝም።”

ዮሐንስ

ከጀርመን የመጣው ዮሐንስ ደግሞ “አገልግሎቴን የማከናውንበትን መንገድ በተመለከተ አንዳንድ ትምህርቶችን አግኝቻለሁ” ብሏል። “በቱርክ የሚኖሩት ወንድሞች በተቻለ መጠን ለብዙዎች እውነትን የማካፈል ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይመሠክራሉ። ወደ ጀርመን ስመለስ እንደ እነሱ ለማድረግ ወሰንኩ። አሁን ከበፊቱ ይበልጥ ለብዙ ሰዎች እሰብካለሁ።”

ዘይነፕ

ከፈረንሳይ የመጣችው ዘይነፕ እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ዘመቻ በአገልግሎቴ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይበልጥ ድፍረት እንዲኖረኝ እንዲሁም በይሖዋ የበለጠ እንድታመን ረድቶኛል።”

አስፋፊዎቹ እርስ በርስ ይበልጥ ተቀራርበዋል። በተለያዩ አገሮች የሚኖሩት ወንድሞች አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅርና አንድነት የማይረሳ ትዝታ ጥሎባቸዋል። ቀደም ብለን የጠቀስነው ዣን ዳቪድ “ወንድሞች ምን ያህል እንግዳ ተቀባይ እንደሆኑ ማየት ችለናል” ብሏል። አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “እንደ ወዳጆቻቸውና እንደ ቤተሰባቸው አባል አድርገው ተቀብለውናል። በቤታቸው አስተናግደውናል። ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር እንዳለን ከዚያ በፊትም አውቃለሁ፤ ስለዚህ ጉዳይ በጽሑፎቻችን ላይ ብዙ ጊዜ አንብቤያለሁ። አሁን ግን በራሴ ሕይወት መመልከት ቻልኩ። ከይሖዋ ሕዝቦች አንዱ በመሆኔ ይበልጥ ኩራት ተሰማኝ፤ ይህን ልዩ መብት ስለሰጠኝም ይሖዋን አመሰገንኩት።”

ክሌር (መሃል)

ከፈረንሳይ የመጣችው ክሌር ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “የምንኖረው በቱርክም ይሁን በዴንማርክ፣ በጀርመን ወይም በፈረንሳይ ሁላችንም አንድ ቤተሰብ ነን። አምላክ በአገራት መካከል ያለውን ድንበር በትልቅ ላጲስ ያጠፋው ያህል ነበር።”

ስቲፈኒ (መሃል)

ከፈረንሳይ የመጣችው ስቲፈኒም እንዲህ ብላለች፦ “አንድነት እንዲኖረን የሚያደርገው ባሕል ወይም ቋንቋ ሳይሆን ሁላችንም ይሖዋን የምንወድ መሆናችን እንደሆነ ልዩ የስብከት ዘመቻው አስተምሮናል።”

ዘላቂ ጥቅም አስገኝቷል

ከሌላ አገር መጥተው በዘመቻው ከተካፈሉት ወንድሞች ብዙዎቹ፣ በቱርክ ባለው ሰፊ ሥራ እገዛ ለማበርከት ሲሉ ወደዚያ ለመዛወር እያሰቡ ነው። እንዲያውም ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል ክርስቲያኖች ወደ ቱርክ ተዛውረዋል። የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ የሄዱትን እነዚህን ክርስቲያኖች በጣም እናደንቃቸዋለን።

ርቆ በሚገኝ አካባቢ የሚኖሩ 25 አስፋፊዎች ያሉበትን አንድ ቡድን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ለበርካታ ዓመታት በዚህ ቦታ ያገለግል የነበረው አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ነው። የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ በ2015 ስድስት ክርስቲያኖች ከኔዘርላንድስና ከጀርመን ወደዚህ አካባቢ በመዛወራቸው በዚያ የነበሩት አስፋፊዎች ምን ያህል እንደተደሰቱ መገመት ይቻላል!

በዋናው ግንባር ላይ ሆኖ ማገልገል

የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ ወደ ቱርክ የመጡ ክርስቲያኖች በዚያ የተወሰነ ጊዜ ካሳለፉ በኋላ ምን ተሰምቷቸዋል? በዚያ የሚመሩት ሕይወት አንዳንድ ጊዜ ተፈታታኝ እንደሆነ ባይካድም ወደዚያ በመምጣታቸው በእጅጉ ተክሰዋል። አንዳንዶቹ የተናገሩትን እስቲ እንመልከት፦

ፌዴሪኮ

በ40ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኝና ከስፔን ወደ ቱርክ የተዛወረ ፌዴሪኮ የተባለ ባለትዳር ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የምሳሳላቸው ብዙ ቁሳዊ ነገሮች የሌሉኝ መሆኑ፣ ነፃነት እንዲኖረኝ እንዲሁም ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ላይ ትኩረት እንዳደርግ አስችሎኛል።” ፌዴሪኮ ሌሎችም በዚህ ዓይነቱ አገልግሎት እንዲሳተፉ ያበረታታ እንደሆነ ሲጠየቅ “እንዴታ!” በማለት መልሷል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ ለመርዳት ብለን ወደ ሌላ አገር ስንሄድ በይሖዋ እንክብካቤ እንደምንተማመን እናሳያለን። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይሖዋ እንደሚንከባከበን ተሰምቶናል።”

ሩዲ

ሩዲ የተባለ በ50ዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኝና ከኔዘርላንድስ የመጣ ባለትዳር ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “በምሳሌያዊ አነጋገር በዋናው ግንባር ላይ ሆኖ ማገልገል እንዲሁም እውነትን ጨርሶ ሰምተው ለማያውቁ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን መናገር ከፍተኛ እርካታ አስገኝቶልናል። ሰዎች እውነትን ሲቀበሉ ምን ያህል እንደሚደሰቱ መመልከት በጣም ያስደስተናል።”

ሳሻ

በ40ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የሚገኝና ከጀርመን የመጣ ሳሻ የተባለ ባለትዳር ደግሞ እንደሚከተለው በማለት ተናግሯል፦ “አገልግሎት በወጣሁ ቁጥር፣ እውነትን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሰሙ ሰዎች ያጋጥሙኛል። እንዲህ ያሉት ሰዎች ይሖዋን የማወቅ አጋጣሚ እንዲያገኙ መርዳት መቻሌ ታላቅ እርካታ አምጥቶልኛል።”

አትሱኮ

ከጃፓን የመጣችና በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የምትገኝ አትሱኮ የተባለች ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “ከአሁን በፊት አርማጌዶን ቶሎ እንዲመጣ እፈልግ ነበር። ወደ ቱርክ ከመጣሁ በኋላ ግን ይሖዋ እስከ አሁን በመታገሱ አመሰግነዋለሁ። ይሖዋ ከዓለም አቀፉ የስብከት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ነገሮችን እንዴት እንደሚመራ በተመለከትኩ መጠን ከቀድሞው የበለጠ ወደ እሱ ለመቅረብ እነሳሳለሁ።”

አሊሳ የተባለች በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ የምትገኝና ከሩሲያ የመጣች እህት “በዚህ ዓይነት የአገልግሎት መስክ ተሰማርቼ ይሖዋን ማገልገሌ የእሱን ጥሩነት ለመቅመስ አስችሎኛል” በማለት ተናግራለች። (መዝ. 34:8) አክላም “ይሖዋ አባቴ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ወዳጄም ነው፤ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እሱን በተሻለ ሁኔታ ማወቅ ችያለሁ። ሕይወቴ በአስደሳች ነገሮች፣ ልዩ በሆኑ ተሞክሮዎችና ይሖዋ በልግስና በሚሰጠኝ በረከቶች የተሞላ ነው!” ብላለች።

“ወደ ማሳው . . . ተመልከቱ”

በቱርክ በተካሄደው ልዩ የስብከት ዘመቻ አማካኝነት ብዙዎች ምሥራቹን መስማት ችለዋል። ያም ሆኖ፣ ገና ያልተሸፈነ ሰፊ ክልል አለ። የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ ወደ ቱርክ የመጡ ክርስቲያኖች፣ ስለ ይሖዋ ፈጽሞ ሰምተው የማያውቁ ሰዎች በየቀኑ ያገኛሉ። እንዲህ ባለው ክልል ውስጥ ማገልገል ትፈልጋላችሁ? ከሆነ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ብለን እናበረታታችኋለን። (ዮሐ. 4:35) ‘አዝመራው ወደነጣበት’ ማሳ ሄዳችሁ ማገልገል ትችሉ ይሆን? ከሆነ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችሏችሁን እርምጃዎች ከአሁኑ መውሰድ ጀምሩ። እርግጠኛ መሆን የምትችሉበት አንድ ነገር አለ፦ ምሥራቹን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” በማሰራጨቱ ሥራ የምታደርጉትን ተሳትፎ መጨመራችሁ፣ ተወዳዳሪ የሌለው በረከት ያስገኝላችኋል!—ሥራ 1:8

^ አን.2 “መልካሚቱን ምድር ተመልከቱ” (በአማርኛ አይገኝም) የተባለውን ብሮሹር ከገጽ 32-33 ተመልከት።