በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለቤተሰብ | ትዳር

ጥሩ አድማጭ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

ጥሩ አድማጭ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?

ተፈታታኙ ነገር

“እያዳመጥከኝ አይደለም!” ትላለች ባለቤትህ። “ግን እኮ እያዳመጥኳት ነበር” ትላለህ ለራስህ። ይሁንና በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አንተ የሰማኸውና ባለቤትህ የተናገረችው ነገር የተለያየ ነው። በዚህም የተነሳ ሌላ ጭቅጭቅ ይፈጠራል።

እንዲህ ያለውን አለመግባባት ማስቀረት ትችላለህ። ይህን ለማድረግ ግን በቅድሚያ አንተ እያዳመጥካት እንዳለህ አድርገህ ብታስብም እንኳ ባለቤትህ ከተናገረችው ሐሳብ ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ አንዳንድ ዝርዝር ነገሮችን ሳትሰማ ሊያመልጡህ የሚችሉት ለምን እንደሆነ መረዳት ያስፈልግሃል።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

ትኩረትህ ስለተከፋፈለ፣ ስለደከመህ ወይም ሁለቱም ሊሆን ይችላል። ልጆቹ እየተንጫጩ ነው፤ ቴሌቪዥኑ ይጮኻል፤ አንተ ደግሞ በሥራ ቦታ ስለገጠመህ አንድ ችግር እያብሰለሰልክ ነው። በዚህ መሃል ባለቤትህ ምሽት ላይ ሊጠይቋችሁ ስለሚመጡት እንግዶች ማውራት ትጀምራለች። አንተም “በእሺታ” ራስህን ትነቀንቃለህ፤ ይሁንና ባለቤትህ የተናገረችውን ነገር በእርግጥ ሰምተሃታል? አልሰማሃት ይሆናል።

ለመገመት ትሞክራለህ። እንዲህ ዓይነቱ “ልብን ለማንበብ” የመሞከር ልማድ ጎጂ ነው። ባለቤትህ ለተናገረቻቸው ቃላት የራስህ ትርጉም እየሰጠህ ከቃላቱ በስተጀርባ አንድ የሆነ የተሰወረ መልእክት እንዳለ ትገምታለህ። ለምሳሌ ያህል ባለቤትህ “በዚህ ሳምንት ትርፍ ሰዓት መሥራት አብዝተሃል” አለችህ እንበል። አንተም እየወቀሰችህ እንዳለ ስለተሰማህ “እና ምን ላድርግ? አንቺ እንደሆነ ገንዘብ አልበቃሽ ብሏል” ትላታለህ። ባለቤትህ ሐሳቡን ያነሳችው በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አብራችሁ ዘና እንድትሉ በማሰብ ስለነበር ብስጭት ብላ “ለምን እንዲህ አደረግክ ወጣኝ?” ትልሃለች።

ቶሎ መፍትሔ ፍለጋ ትሮጣለህ። ማርሴ * እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ እኔ የምፈልገው ስሜቴን ማጋራት ብቻ ነው፤ ማይክ ግን ችግሩን መፍታት የምችልበትን መንገድ ሊነግረኝ ይሞክራል። እኔ የምፈልገው መፍትሔውን አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስሜቴን እንዲረዳልኝ ብቻ ነው።” የችግሩ መንስኤ ምንድን ነው? የማይክ አእምሮ ቶሎ ወደ መፍትሔ ፍለጋ ይሮጣል። በዚህም የተነሳ ማይክ፣ ማርሴ እየነገረችው ያለውን ነገር በተወሰነ ደረጃ ወይም ሙሉ በሙሉ ላያዳምጣት ይችላል።

የችግሩ መንስኤ ምንም ሆነ ምን ጥሩ አድማጭ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

ምን ማድረግ ትችላለህ?

በትኩረት አዳምጥ። ባለቤትህ ልትነግርህ የምትፈልገው አንድ አስፈላጊ ጉዳይ አለ፤ ይሁን እንጂ አንተ ለማዳመጥ ዝግጁ ነህ? ምናልባት ዝግጁ ላትሆን ትችላለህ። በወቅቱ አእምሮህ በሌሎች ነገሮች ተይዞ ሊሆን ይችላል። ከሆነ እያዳመጥካት እንዳለ ለማስመሰል አትሞክር። ከተቻለ እየሠራህ ያለኸውን ነገር ተወት አድርግና ለትዳር ጓደኛህ ሙሉ ትኩረት ስጣት ወይም የጀመርከውን ነገር እስክትጨርስ ድረስ እንድትጠብቅህ ልትጠይቃት ትችላለህ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ያዕቆብ 1:19

በየተራ ለመናገር ተስማሙ። ማዳመጥ የአንተ ተራ ከሆነ ተናግራ ሳትጨርስ ጣልቃ እንድትገባ ወይም በጉዳዩ አለመስማማትህን እንድትገልጽ የሚገፋፋህን ስሜት ተቆጣጠር። አንተም ተራህ ሲደርስ ትናገራለህ። ለአሁኑ ዝም ብለህ አዳምጥ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 18:13

ያልገባህን ነገር ጠይቅ። እንዲህ ማድረግህ የትዳር ጓደኛህ እየተናገረች ያለችውን ነገር በተሻለ ሁኔታ እንድትረዳ ያስችልሃል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ማርሴ እንዲህ ብላለች፦ “ማይክ ጥያቄ ሲጠይቀኝ ደስ ይለኛል። እንዲህ ማድረጉ የምናገረውን ነገር የማወቅ ፍላጎት እንዳለው ይጠቁመኛል።”

ቃላቱን ብቻ ሳይሆን መልእክቱን አዳምጥ። በአካላዊ መግለጫ፣ በዓይን እንቅስቃሴና በድምፅ ቃና የሚተላለፈውን መልእክት ልብ በል። አንድ ሰው “እሺ ይሁን” ቢል የተናገረበት መንገድ በነገሩ መስማማቱን የሚያሳይ ሳይሆን “አንተ እንዳሻህ” የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ ሊሆን ይችላል። “ልርዳሽ ብለኸኝ አታውቅም” የሚለው አነጋገር “ምንም እንደማታስብልኝ ይሰማኛል” ማለት ሊሆን ይችላል። በቃላት ባይገለጽም እንኳ ትክክለኛውን መልእክት ለመረዳት ጣር። አለበለዚያ ለማለት በተፈለገው ነገር ላይ በማተኮር ፈንታ በተባለው ነገር ላይ መከራከር ልትጀምር ትችላለህ።

በትዕግሥት አዳምጥ። እየሰማኸው ያለኸው ነገር ባያስደስትህም እንኳ አእምሮህን አትዝጋ ወይም ትተህ አትሂድ። ለምሳሌ ያህል ባለቤትህ እየወቀሰችህ ቢሆንስ? ከ60 ለሚበልጡ ዓመታት በትዳር የኖሩት ግሪጎሪ “በትዕግሥት አዳምጥ” በማለት ይመክራሉ። አክለውም “የትዳር ጓደኛህ የምትናገረውን ነገር በቁም ነገር ተመልከተው። ይህ ብስለት የሚጠይቅ ቢሆንም ይክሳል” ብለዋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 18:15

የትዳር ጓደኛህን ስሜት ለመረዳት ልባዊ ፍላጎት ይኑርህ። ከልብ ማዳመጥ እንዲሁ የጥሩ ሥነ ምግባር መለኪያ ብቻ ሳይሆን የፍቅር መግለጫም ነው። የትዳር ጓደኛህ የምትለውን ነገር የማወቅ ልባዊ ፍላጎት ካለህ ራስህን ማስገደድ ሳያስፈልግህ በደስታ ልታዳምጣት ትችላለህ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እየሠራህበት እንዳለ ታሳያለህ፦ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:4 ጉድ ኒውስ ትራንስሌሽን

^ አን.9 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።