በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ | ትዳር

መደራደር የሚቻለው እንዴት ነው?

መደራደር የሚቻለው እንዴት ነው?

ተፈታታኙ ነገር

አንተና የትዳር ጓደኛህ በአንድ ጉዳይ ላይ የተለያየ ፍላጎት አላችሁ እንበል። በዚህ ጊዜ ቢያንስ ሦስት አማራጮች አሏችሁ፦

  1. የምትፈልጉትን ነገር እስክታገኙ ድረስ በድርቅና ችክ ልትሉ ትችላላችሁ።

  2. ምንም ሳትከራከሩ የትዳር ጓደኛችሁን ፍላጎት ልትቀበሉ ትችላላችሁ።

  3. ሁለታችሁም ልትደራደሩ ትችላላችሁ።

‘እኔ ግን መደራደር አልፈልግም’ ትል ይሆናል። ‘ምክንያቱም ከተደራደርን ሁለታችንም የምንፈልገውን አናገኝም!’

በትክክለኛው መንገድ ከተደራደራችሁ ምርጫው ሁለታችሁንም የሚጎዳ አይሆንም። መደራደር የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ከማየታችን በፊት ግን ይህን አስፈላጊ ክህሎት በተመለከተ ማወቅ የሚኖርባችሁን የተወሰኑ ነገሮች እንመልከት።

ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

መደራደር ተባብሮ መሥራትን ይጠይቃል። ከመጋባታችሁ በፊት ውሳኔ የምታደርጉት በግላችሁ ነበር። አሁን ግን ሁኔታዎች ተለውጠዋል፤ በመሆኑም ሁለታችሁም ትዳራችሁን ከግል ምርጫዎቻችሁ ማስቀደም ይጠበቅባችኋል። ይህ ሁኔታ እንደሚጎዳችሁ ከማሰብ ይልቅ ጥቅሙ ላይ አተኩሩ። አሌክሳንድራ የተባለች አንዲት ባለትዳር “የሁለት ሰዎች ሐሳብ ሲዋሃድ ግለሰቦቹ ለየብቻ ሊያመጡ ከሚችሉት የተሻለ መፍትሔ ሊያስገኝ ይችላል” ብላለች።

መደራደር የሌላውን ሰው ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል። የትዳር አማካሪ የሆኑት ጆን ጎትመን እንዲህ ብለዋል፦ “የትዳር ጓደኛህ በምትናገረው ወይም በምታምነው ነገር ሁሉ መስማማት ባይጠበቅብህም የእሷን ሐሳብ ግምት ውስጥ ለማስገባት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆን ያስፈልግሃል። የትዳር ጓደኛህ ስለ አንድ ችግር ከአንተ ጋር ለመነጋገር ስትሞክር እጅህን አጣጥፈህ ራስህን በመነቅነቅ እምቢታህን የምትገልጽ (ወይም እምቢ ለማለት እያሰብክ) ከሆነ ውይይታችሁ የትም አይደርስም።” *

መደራደር የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን ይጠይቃል። “እኔ ያልኩት ካልሆነ” ብሎ ድርቅ ከሚል የትዳር ጓደኛ ጋር መኖር የሚፈልግ ሰው የለም። ሁለቱም የትዳር ጓደኛሞች የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ሊኖራቸው ይገባል። ጁን የተባለች አንዲት ባለትዳር እንዲህ ብላለች፦ “ባለቤቴን ለማስደሰት ስል እሱ የሚፈልገውን ነገር የማደርግበት ጊዜ አለ፤ እሱም አንዳንድ ጊዜ ለእኔ እንዲሁ ያደርግልኛል። ትዳር ማለት ይህ ነው፤ መቀበል ብቻ ሳይሆን መስጠትም ጭምር ነው።”

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ውይይት የምትጀምሩበትን መንገድ አሳምሩ። ብዙውን ጊዜ ውይይቱ ሲደመደም የሚኖራችሁ ስሜት ውይይቱን ስትጀምሩ በነበራችሁ ስሜት ላይ የተመካ ነው። ውይይቱን ሸካራ ቃላት በመናገር የምትጀምሩ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ሰላማዊ በሆነ መንገድ መደራደር አትችሉም። በመሆኑም “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ አድርጉ። (ቆላስይስ 3:12) እንደነዚህ ያሉትን ባሕርያት ማንጸባረቃችሁ ሳትጨቃጨቁ ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት ያስችላችኋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ቆላስይስ 4:6

በሚያስማሟችሁ ነጥቦች ላይ አተኩሩ። ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ስትነጋገሩ ትኩረታችሁ ያረፈው በአመለካከት ልዩነታችሁ ላይ ከሆነ ለመደራደር የምታደርጉት ጥረት ወደ ጦፈ ጭቅጭቅ ሊያመራ ይችላል። ከዚህ ይልቅ በሚያስማሟችሁ ነጥቦች ላይ አተኩሩ። የሚያስማሟችሁን ነጥቦች ማግኘት እንድትችሉ የሚከተለውን ዘዴ ተጠቀሙ፦

ሁለታችሁም ሁለት ዝርዝሮችን አዘጋጁ። በመጀመሪያው ዝርዝር ላይ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በጣም የምትፈልጓቸውን ነገሮች ጻፉ። በሁለተኛው ዝርዝር ላይ ደግሞ ለመደራደር ዝግጁ የሆናችሁባቸውን ጉዳዮች ጻፉ። ከዚያም በጻፋችኋቸው ዝርዝሮች ላይ ተወያዩ። እንዲህ ስታደርጉ ሁለታችሁም ከጠበቃችሁት በላይ በብዙ ነገሮች ላይ እንደምትስማሙ ትገነዘቡ ይሆናል። ይህ ከሆነ ደግሞ መደራደር ከባድ አይሆንባችሁም። ሐሳባችሁ በጣም ቢራራቅም እንኳ ምርጫችሁን በወረቀት ላይ ማስፈራችሁ ሁለታችሁም ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ እንድታዩት ይረዳችኋል።

በጋራ በመመካከር መፍትሔ ፈልጉ። አንዳንድ ጉዳዮችን ተወያይቶ መፍታት በአንጻራዊ ሁኔታ ቀላል ሊሆን ይችላል። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ግን ባልና ሚስቱ በጋራ መመካከራቸው አንደኛው ብቻውን ሊያመጣ የማይችለውን መፍትሔ ሊያስገኝ ይችላል፤ ይህም ትስስራቸውን ይበልጥ ያጠናክረዋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ መክብብ 4:9

አመለካከታችሁን ለማስተካከል ፈቃደኞች ሁኑ። መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ልታከብር ይገባል” ይላል። (ኤፌሶን 5:33) በትዳር ውስጥ ፍቅርና አክብሮት ካለ ሁለቱም አንዳቸው የሌላውን አመለካከት ግምት ውስጥ ለማስገባትና የሌላውን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኞች ይሆናሉ። ካሜሮን የተባለ አንድ ባለትዳር እንዲህ ብሏል፦ “ማድረግ የማትፈልጉትን ነገር ለትዳር ጓደኛችሁ ስትሉ ለማድረግ ፈቃደኞች ከሆናችሁ፣ በኋላ ላይ ይህን ነገር እየወደዳችሁት ልትሄዱ ትችላላችሁ።”—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ ዘፍጥረት 2:18

^ አን.12 ትዳርን ስኬታማ የሚያደርጉ ሰባት ደንቦች (እንግሊዝኛ) ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።