በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ንድፍ አውጪ አለው?

ዲ ኤን ኤ ያለው መረጃ የመያዝ አቅም

ዲ ኤን ኤ ያለው መረጃ የመያዝ አቅም

የኮምፒውተር ተጠቃሚዎች በተፈለገ ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ከፍተኛ መጠን ያለው ዲጂታል መረጃ ያስቀምጣሉ። ሳይንቲስቶች እጅግ ብዙ መረጃ የመያዝ አቅም ያለውን በተፈጥሮ የሚገኘውን የመረጃ ማስቀመጫ ማለትም ዲ ኤን ኤን በመኮረጅ በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው የዲጂታል መረጃ ማስቀመጫ መሣሪያ ያለውን የመያዝ አቅም ይበልጥ ለማሳደግ እያሰቡ ነው።

እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ በሕያው ሴል ውስጥ የሚገኘው ዲ ኤን ኤ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ባዮሎጂያዊ መረጃዎችን ይይዛል። “ጥንታዊ ከሆኑት ፀጉራም የዝሆን ዝርያዎች ዓፅም ውስጥ ዲ ኤን ኤን ማውጣትና የያዘውን መረጃ ማየት እንችላለን” ይላሉ የአውሮፓ ባዮኢንፎርማቲክስ ተቋም ባልደረባ የሆኑት ኒክ ጎልድማን። አክለውም ዲ ኤን ኤ “ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ እጅግ አነስተኛ መጠን ያለውና ብዙ መረጃ የሚይዝ ሲሆን መረጃውን ይዞ ለማቆየት ሌላ የኃይል ምንጭ ስለማያስፈልገው ለማጓጓዝም ሆነ ለማስቀመጥ ቀላል ነው” በማለት ተናግረዋል። ዲ ኤን ኤ ሰው ሠራሽ መረጃዎችን ማስቀመጥ ይችል ይሆን? ተመራማሪዎች አዎ የሚል መልስ ይሰጣሉ።

ሳይንቲስቶች አንድ የዲጂታል መሣሪያ መረጃ የሚያስቀምጥበትን መንገድ ተጠቅመው የጽሑፍ፣ የምስልና የድምፅ ፋይሎችን ዲ ኤን ኤ ውስጥ ማስቀመጥ ችለዋል። ከጊዜ በኋላም ተመራማሪዎቹ ያስቀመጡትን መረጃ ያላንዳች መዛባት መቶ በመቶ መልሰው ማግኘት ችለዋል። ሳይንቲስቶቹ ወደፊት ይህን ዘዴ በመጠቀም 1 ግራም በሚያክል ሰው ሠራሽ ዲ ኤን ኤ ውስጥ 3,000,000 ሲዲ ሊፈጅ የሚችል መረጃ ማስቀመጥና መረጃውም በመቶዎች ምናልባትም በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሳይበላሽ እንዲቆይ ማድረግ እንደሚቻል ያምናሉ። ይህን ዘዴ በመጠቀም የመላውን ዓለም ዲጂታል መረጃ አንድ ላይ ሰብስቦ ማስቀመጥ እንደሚቻል ይገመታል። በዚህም የተነሳ ዲ ኤን ኤ “ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ሃርድ ድራይቭ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

ታዲያ ምን ይመስልሃል? የዲ ኤን ኤ መረጃ የመያዝ አቅም በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?