በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

በትዳር ጓደኛ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት መፍትሔው ምን ይሆን?

በትዳር ጓደኛ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት መፍትሔው ምን ይሆን?

የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። የኢዛቤል * ወላጆች ልጃቸውን ለመጠየቅ መጥተዋል። ከሴት ልጃቸውና ከባለቤቷ ጋር በመጫወት ጥሩ ምሽት አሳለፉ። ሴት ልጁ እንዲህ ያለ ጥሩ ባል በማግባቷ የማይኮራ ማን ነው? ባልየው ሚስቱን አሳቢነት በተሞላበት ሁኔታ ይይዛታል።

እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ ደግሞ ተመልከት። ፍራንክ በንዴት ጨሷል። አሁንም እንደተለመደው ሚስቱን በጥፊና በርግጫ በመምታት፣ ፀጉሯን ይዞ በመጎተት እንዲሁም ራሷን ከግድግዳ ጋር በማጋጨት ንዴቱን ይወጣባታል።

ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱም ሁኔታዎች የሚገልጹት ስለ አንድ ባልና ሚስት መሆኑን ስታውቅ ትገረም ይሆናል።

ፍራንክ እንደ ብዙዎቹ ተደባዳቢ ባሎች ሰው ፊት ወይም የሚስቱ ወላጆች ባሉበት “ጨዋና ደግ ሰው” ሆኖ መታየት ያውቅበታል። ከሚስቱ ጋር ብቻውን በሚሆንበት ጊዜ ግን በጣም ጨካኝ ነው።

እንደ ፍራንክ ያሉ ብዙ ወንዶች፣ ተደባዳቢ ወላጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ ስለሚያድጉ እነሱ ራሳቸው ትልቅ ሰው በሚሆኑበት ጊዜ ባሕርያቸው ተቀባይነት  ያለው አልፎ ተርፎም ትክክል እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛን መደብደብ ትክክልና ተቀባይነት ያለው ነገር ሊሆን የሚችልበት ምንም ምክንያት የለም። አብዛኞቹ ሰዎች አንድ ሰው ሚስቱን እንደደበደበ ሲሰሙ የሚደነግጡት ለዚህ ነው።

ያም ሆኖ በትዳር ጓደኛ የሚሰነዘር ጥቃት በጣም የተለመደ ነገር ሆኗል። ለምሳሌ፣ በዩናይትድ ስቴትስ በቤት ውስጥ ከሚፈጠር አምባጓሮ ጋር በተያያዘ አንድ ጥናት ተካሂዶ ነበር፤ በዚህ ጥናት መሠረት በመላ አገሪቱ ለዚሁ ተብለው የተዘጋጁ የጥሪ ማዕከሎች በአንድ ቀን ውስጥ ብቻ በየደቂቃው በአማካይ ከ16 የሚበልጡ የስልክ ጥሪዎች ይደርሳቸዋል። በትዳር ጓደኛ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት የትኛውም ባሕል፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ኑሮ የማይገድበው በመላው ዓለም የተዛመተ ችግር ሆኗል። ሪፖርት የማይደረጉ በርካታ አምባጓሮዎች ስለሚኖሩ ሁኔታው አኃዛዊ መረጃዎች ከሚያሳዩት በላይ አስከፊ እንደሚሆን አያጠራጥርም። *

በትዳር ጓደኛ የሚሰነዘርን ጥቃት የሚገልጹ ሪፖርቶች የሚከተሉትን ጥያቄዎች ያስነሳሉ፦ አንድ ሰው ሚስቱን ይቅርና ማንኛውንም ሰው ቢሆን እንዴት በጭካኔ ይደበድባል? ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ባሎች እርዳታ ማግኘት ይችላሉ?

የዚህ መጽሔት አዘጋጆች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ጠቃሚ ምክር ተደባዳቢ የሆኑ የትዳር ጓደኞችን ባሕርይ ሊለወጥ እንደሚችል ያምናሉ። እንዲህ ያለ ለውጥ ማድረግ ቀላል ነው? አይደለም። ይሁንና ለውጥ ማድረግ ይቻላል? አዎ፣ ይቻላል! የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጠበኛ የነበሩ ብዙ ሰዎች ተለውጠው አሳቢዎችና ሰው አክባሪዎች እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። (ቆላስይስ 3:8-10) እስቲ የትሮይንና የቫለሪን ሁኔታ እንመልከት።

መጀመሪያ ላይ ግንኙነታችሁ ምን ይመስል ነበር?

ቫለሪ፦ በተጫጨንበት ምሽት ትሮይ፣ ፊቴ ለአንድ ሳምንት ያህል እስኪበልዝ ድረስ በጥፊ መታኝ።  አጥብቆ ይቅርታ ጠየቀኝና ሁለተኛ እንደማይለምደው ቃል ገባልኝ። በቀጣዮቹ ዓመታት እነዚህን ቃላት በተደጋጋሚ ጊዜያት ሰምቻቸዋለሁ።

ትሮይ፦ ትናንሹ ነገር ሁሉ ያበሳጨኝ ነበር፤ ለምሳሌ ምግብ ቶሎ ሳይቀርብልኝ ሲቀር በጣም እናደድ ነበር። አንድ ጊዜ ቫለሪን በሽጉጥ ሰደፍ መታኋት። በሌላ ጊዜ ደግሞ ክፉኛ ስለደበደብኳት የሞተች መስሎኝ ነበር። ከዚህም ሌላ ልጃችን አንገት ላይ ቢላ አጋድሜ ‘እገድለዋለሁ’ በማለት ላስፈራራት ሞከርኩ።

ቫለሪ፦ ሁልጊዜ የምኖረው በፍርሃት ነበር። ትሮይ ቁጣው እስኪበርድለት ድረስ ከቤት ሸሽቼ የምወጣባቸው ጊዜያት ነበሩ። ያም ሆኖ ከዱላው ይበልጥ መቋቋም የሚከብደኝ ስድቡን ነበር።

ትሮይ፣ ድሮም ተደባዳቢ ነበርክ?

ትሮይ፦ አዎ፣ ከልጅነቴ ጀምሮ ተደባዳቢ ነበርኩ። ያደግኩት ጠበኛ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቴ በእኔም ሆነ በወንድሞቼና በእህቶቼ ፊት እናቴን ብዙ ጊዜ ይደበድባት ነበር። አባታችን ትቶን ከሄደ በኋላ እናቴ ከሌላ ሰው ጋር መኖር ጀመረች፤ እሱም ቢሆን ይደበድባት ነበር። ይህ ሳይበቃው ደግሞ እህቴንና እኔን አስገድዶ አስነወረን። በዚህም የተነሳ እስር ቤት ገባ። እርግጥ ይህ ለእኔ ባሕርይ ሰበብ ሊሆን እንደማይችል እገነዘባለሁ።

ቫለሪ፣ ይህ ሁሉ እየደረሰብሽ ባልሽን ጥለሽ ያልሄድሽው ለምንድን ነው?

ቫለሪ፦ ፈርቼ ስለነበረ ነው። ‘የገባሁበት ገብቶ ቢገድለኝስ? ወላጆቼን ቢገድልስ? ብከሰውና ሁኔታው ቢባባስስ?’ እያልኩ አስብ ነበር።

ሁኔታዎች መለወጥ የጀመሩት መቼ ነው?

ትሮይ፦ ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረች። መጀመሪያ ላይ በእነዚህ አዳዲስ ወዳጆቿ ቀንቼ የነበረ ሲሆን ከዚህ “የመናፍቃን ሃይማኖት” ላድናት ይገባል ብዬ አስቤ ነበር። ስለሆነም ቫለሪን ብቻ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክሮችንም ሰላም እነሳቸው ጀመር። አንድ ቀን ግን የሚጥል በሽታ የነበረበት የአራት ዓመት ልጃችን ዳንኤል ሆስፒታል ገባና ለሦስት ሳምንት ያህል በዚያ ቆየ። በዚህ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ነገር አደረጉልን፤ የስድስት ዓመት ልጃችንን ዴዚሬን ሳይቀር ይንከባከቡ ነበር። አንድ የይሖዋ ምሥክር ሥራ አድሮ ከወጣ በኋላ ቫለሪ እንድታርፍ ቀኑን ሙሉ ዳንኤልን ሲጠብቅ ዋለ። በክፉ ዓይን እመለከታቸው የነበሩት እነዚህ ሰዎች ያሳዩን ደግነት በጥልቅ ነካኝ። እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን በተግባር ስላየሁ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኑኝ ጠየቅኳቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ  እየገፋሁ ስሄድ አንድ ሰው ሚስቱን እንዴት መያዝ እንዳለበትና እንደሌለበት ተማርኩ። ጠበኝነትንና ስድብን እርግፍ አድርጌ ተውኩ። በመጨረሻም የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

እንድትለወጥ የረዱህ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ናቸው?

ትሮይ፦ በጣም ብዙ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ በ1 ጴጥሮስ 3:7 ላይ ለባለቤቴ “ክብር” ማሳየት እንደሚገባኝ ይናገራል። ገላትያ 5:23 “ገርነት” እንድናሳይና ‘ራሳችንን እንድንገዛ’ ያበረታታናል። ኤፌሶን 4:31 ‘ስድብን’ ያወግዛል። ዕብራውያን 4:13 ደግሞ በአምላክ “ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ” እንደሆነ ይናገራል። ስለዚህ የማደርገውን ነገር ሌሎች ሰዎች ባያዩ እንኳ አምላክ ይመለከተዋል። በተጨማሪም “መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል” ስለሚያበላሽ ጓደኞቼን መተው እንደሚኖርብኝ ተገነዘብኩ። (1 ቆሮንቶስ 15:33) ምክንያቱም የቀድሞ ጓደኞቼ ጠበኛ እንድሆን ያበረታቱኝ ነበር። ሴትን “በቁጥጥር ሥር” ለማድረግ መደብደብ እንደሚገባ ይሰማቸው ነበር።

አሁን ስለ ትዳራችሁ ምን ይሰማችኋል?

ቫለሪ፦ ትሮይ የይሖዋ ምሥክር ከሆነ 25 ዓመታት አልፈዋል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከልቡ አፍቃሪ፣ ደግና አሳቢ ሆኖልኛል።

ትሮይ፦ በቤተሰቤ ላይ ያደረስኩትን በደል መለወጥ አልችልም፤ ሚስቴም ብትሆን ያ ሁሉ ግፍ ሊደርስባት አይገባም ነበር። በታሪካችን ውስጥ ጥቁር ነጥብ ጥሎ ያለፈው ይህ ሁኔታ ፈጽሞ የሚረሳበትን ይኸውም ኢሳይያስ 65:17 ፍጻሜውን የሚያገኝበትን ዘመን በጉጉት እጠባበቃለሁ።

በትዳር ጓደኛቸው ጥቃት እየተሰነዘረባቸው ላሉ ሰዎች ምን ምክር ትሰጣላችሁ?

ትሮይ፦ በመሳደብም ሆነ በመማታት በቤተሰባችሁ አባላት ላይ ጥቃት የምትሰነዝሩ ከሆነ እርዳታ እንደሚያስፈልጋችሁ በማመን እርዳታ ለማግኘት ጥረት አድርጉ። በብዙ መንገድ እርዳታ ማግኘት ይቻላል። እኔ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴና ከእነሱ ጋር መቀራረቤ ሥር ሰድዶ የነበረውን የጠበኝነት ባሕርዬን እንዳስወግድ ረድቶኛል።

ቫለሪ፦ ያላችሁበትን ሁኔታ ከሌላ ከማንም ሰው ጋር ለማወዳደር ወይም የሚበጃችሁን ነገር እንደሚያውቁላችሁ የሚያስቡ ሰዎች የሚሰጧችሁን ምክር ለመስማት አትቸኩሉ። ሁሉም ሰው ተመሳሳይ ውጤት ባይገጥመውም እኔ ግን አሁን ያለንን ጥሩ ግንኙነት ስመለከት ትዳሬን አሽቀንጥሬ ባለመጣሌ ደስ ብሎኛል።

በትዳር ጓደኛ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ሊወገድ ይችላል

በርካታ ወንዶች መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታቸው አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ እንዲችሉ ረድቷቸዋል

መጽሐፍ ቅዱስ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ እንዲሁም ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ነገሮችን ለማቅናት . . . ይጠቅማል” ይላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ከላይ እንደተጠቀሰው እንደ ትሮይ ሁሉ ጠበኛ የነበሩ ብዙ ባለትዳሮች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ሥራ ላይ በማዋል አስተሳሰባቸውንና ምግባራቸውን መለወጥ ችለዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ለትዳራችሁ ጠቃሚ የሆነ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችለው እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋላችሁ? ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በአካባቢያችሁ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች አነጋግሩ ወይም www.pr418.com የተባለውን ድረ ገጽ ተመልከቱ።

^ စာပိုဒ်၊ 3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ စာပိုဒ်၊ 8 በሚስቶቻቸው የሚደበደቡ በርካታ ወንዶች እንዳሉ አይካድም። ይሁን እንጂ ሪፖርት ከሚደረጉት አምባጓሮዎች መካከል አብዛኞቹ ወንዶች ሚስቶቻቸውን እንደደበደቡ የሚገልጹ ናቸው።