በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቤት ውስጥ ጥቃት ለሚደርስባቸው የሚሆን እርዳታ

የቤት ውስጥ ጥቃት ለሚደርስባቸው የሚሆን እርዳታ

 “በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት ወረርሽኝ ደረጃ ላይ የደረሰ ዓለም አቀፋዊ ችግር ነው፤ አፋጣኝ እርምጃ ያሻዋል” በማለት የዓለም የጤና ድርጅት ገልጿል። ይህ ድርጅት እንደገለጸው ‘የወንድ ጓደኛ ወይም ባል ካላቸው ሴቶች መካከል ወደ 30 በመቶ የሚጠጉት በአጋራቸው አካላዊ እና/ወይም ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸው ያውቃል።’ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው በቅርቡ በአንድ ዓመት ውስጥ በየቀኑ 137 ሴቶች በአጋራቸው ወይም በሌላ የቤተሰባቸው አባል እጅ ተገድለዋል። a

 እነዚህ አኃዛዊ መረጃዎች የቤት ውስጥ ጥቃት ምን ያህል እንደተስፋፋ የሚያሳዩ ቢሆንም ጥቃት የደረሰባት እያንዳንዷ ሴት ስለሚያጋጥማት ስሜታዊና አካላዊ ሥቃይ ሊገልጹ አይችሉም።

 የቤት ውስጥ ጥቃት እየደረሰብሽ ነው? ወይም የቤት ውስጥ ጥቃት እየደረሰበት ያለ ሰው ታውቂያለሽ? ከሆነ የሚከተሉትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክሮች ጠቃሚ ሆነው ታገኛቸዋለሽ።

  ጥቃት የደረሰብሽ በአንቺ ጥፋት አይደለም

  እርዳታ ማግኘት ትችያለሽ

  ብቻሽን አይደለሽም

  የቤት ውስጥ ጥቃት የሚያቆምበት ጊዜ ይመጣል

  ጥቃት የደረሰባቸውን ሰዎች መርዳት የሚቻልበት መንገድ

 ጥቃት የደረሰብሽ በአንቺ ጥፋት አይደለም

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።”—ሮም 14:12

 ማስታወስ ያለብሽ ነገር፦ ጥፋተኛው ጥቃት ያደረሰብሽ ግለሰብ ነው።

 አጋርሽ እሱ ለሚያደርስብሽ ጥቃት ጥፋተኛው አንቺ እንደሆንሽ የሚናገር ከሆነ ተሳስቷል። ሚስቶች ሊወደዱ እንጂ ጥቃት ሊሰነዘርባቸው አይገባም።—ቆላስይስ 3:19

 አንዳንዶች በአጋራቸው ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩት የአእምሮ ችግር ስላለባቸው፣ አስተዳደጋቸው መጥፎ ስለሆነ ወይም ከመጠን በላይ አልኮል ስለሚጠጡ ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን አጋርሽ በአንቺ ላይ ጥቃት በማድረሱ አምላክ ተጠያቂ ያደርገዋል። እንዲሁም ለመስተካከል ጥረት የማድረግ ግዴታ አለበት።

 እርዳታ ማግኘት ትችያለሽ

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በብዙ አማካሪዎች . . . ይሳካል።”—ምሳሌ 15:22

 ማስታወስ ያለብሽ ነገር፦ ፍርሃት ከተሰማሽ ወይም ምን ማድረግ እንዳለብሽ ግራ ከገባሽ ሌሎች ሰዎች ሊረዱሽ ይችላሉ።

 የሌሎች እርዳታ የሚያስፈልግሽ ለምን ሊሆን ይችላል? የቤት ውስጥ ጥቃት ውስብስብ የሆነ ችግር ነው። ምን ማድረግ እንዳለብሽ ስትወስኚ እንደሚከተሉት ያሉ ነገሮችን ግምት ውስጥ ማስገባት ስላለብሽ ግራ ልትጋቢ ትችያለሽ፦

  •   ደህንነትሽ

  •   የልጆችሽ ደህንነት

  •   የኢኮኖሚ ሁኔታ

  •   ለአጋርሽ ያለሽ ፍቅር

  •   አጋርሽ ለመስተካከል ፈቃደኛ ከሆነ ግንኙነቱን ለመቀጠል ያለሽ ፍላጎት

 እነዚህ ሁሉ ነገሮች ግራ ሊያጋቡሽና ሁኔታው ከአቅምሽ በላይ እንደሆነ ሊሰማሽ እንደሚችል የታወቀ ነው። ታዲያ እርዳታ ማግኘት የምትችይው ከየት ነው?

 የምታምኛቸው ጓደኞችሽ ወይም ቤተሰቦችሽ ሊረዱሽና ሊያጽናኑሽ ይችላሉ። ለሚያስብልሽ ሰው ስሜትሽን መናገርሽ በእጅጉ ሊረዳሽ ይችላል።

 የቤት ውስጥ ጥቃት ለሚደርስባቸው ሰዎች የተዘጋጁ የስልክ መስመሮችን በመጠቀም ወዲያውኑ እርዳታ ማግኘት ትችያለሽ። እንዲህ ባሉ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች ራስሽን መጠበቅ የምትችይው እንዴት እንደሆነ ሊነግሩሽ ይችላሉ። በተጨማሪም አጋርሽ ችግሩን አምኖ ከተቀበለና መስተካከል የሚፈልግ ከሆነ እነዚህ ባለሙያዎች ለውጥ ማድረግ የሚችለው እንዴት እንደሆነ ሊጠቁሙት ይችላሉ።

 ሌሎች ባለሙያዎችም አፋጣኝ እርዳታ ሲያስፈልግሽ ሊረዱሽ ይችላሉ። ከእነዚህ መካከል ሐኪሞች፣ ነርሶችና ሌሎች የሠለጠኑ ባለሙያዎች ይገኙበታል።

 ብቻሽን አይደለሽም

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ይሖዋ b ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።”—መዝሙር 34:18

 ማስታወስ ያለብሽ ነገር፦ አምላክ እንደሚረዳሽ ቃል ገብቶልሻል።

 ይሖዋ በእጅጉ ያስብልሻል። (1 ጴጥሮስ 5:7) የውስጥሽን ሐሳብና ስሜትሽን ይረዳል። በመሆኑም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ሊያጽናናሽ ይችላል። እንዲሁም ወደ እሱ እንድትጸልዪ ግብዣ አቅርቦልሻል። ያጋጠመሽን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብና ኃይል እንዲሰጥሽ በጸሎት ልትጠይቂው ትችያለሽ።—ኢሳይያስ 41:10

 የቤት ውስጥ ጥቃት የሚያቆምበት ጊዜ ይመጣል

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እያንዳንዱም ከወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ይኖራል፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።”—ሚክያስ 4:4 የግርጌ ማስታወሻ

 ማስታወስ ያለብሽ ነገር፦ መጽሐፍ ቅዱስ በቅርቡ ሁላችንም በቤታችን ውስጥ ያለስጋት መኖር የምንችልበት ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል።

 ለችግሮቻችን በሙሉ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጠን የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል” የሚል ተስፋ ይሰጠናል። (ራእይ 21:4) ያን ጊዜ አእምሯችን በጥሩ ትዝታዎች ስለሚሞላ መጥፎ ትዝታዎቻችን በሙሉ ደብዝዘው ይጠፋሉ። (ኢሳይያስ 65:17) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ሰላም የሰፈነበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጠናል።

a ይህ ርዕስ ጥቃት ስለሚደርስባቸው ሴቶች የሚናገር ቢሆንም ብዙዎቹ ሐሳቦች ጥቃት ለሚደርስባቸው ወንዶችም ይሠራሉ።

b መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ የግል ስም ይሖዋ ነው።