በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ | ትዳር

ጎጂ ንግግርን ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው?

ጎጂ ንግግርን ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው?

ተፈታታኙ ነገር

በአንተና በትዳር ጓደኛህ መካከል ግጭት በተፈጠረ ቁጥር አንዳችሁ በሌላው ላይ የትችት ናዳ ታወርዳላችሁ። በትዳራችሁ ውስጥ ጎጂ የሆኑ ቃላት መሰንዘር በጣም የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ በዕለት ተዕለት ሕይወታችሁ የሐሳብ ልውውጥ የምታደርጉት በዚህ መንገድ ሆኗል።

በትዳራችሁ ውስጥ እንዲህ ያለ ሁኔታ ተፈጥሮ ከሆነ ይህን መጥፎ ልማድ ማስወገድ ትችላላችሁ። መጀመሪያ ግን መንስኤው ምን እንደሆነ እንዲሁም ለውጥ ማድረጋችሁ ምን ጥቅም እንዳለው መገንዘባችሁ አስፈላጊ ነው።

ምክንያቱ ምንድን ነው?

አስተዳደግ። በርካታ ባሎችና ሚስቶች ያደጉት ጎጂ የሆኑ ቃላት መናገር በጣም የተለመደ በሆነበት ቤተሰብ ውስጥ ነው። ከትዳር ጓደኛሞቹ መካከል አንዳቸው ወይም ሁለቱም ከወላጆቻቸው የኮረጁትን አነጋገር ይጠቀሙ ይሆናል።

መዝናኛ የሚያሳድረው ተጽዕኖ። ፊልሞችና በቴሌቪዥን የሚታዩት ኮሜዲዎች አክብሮት የጎደላቸውን አነጋገሮች እንደ ቀልድ ስለሚጠቀሙባቸው ተመልካቾች እንዲህ ዓይነቱ ንግግር ጎጂ እንዳልሆነ አልፎ ተርፎም በጣም አስቂኝ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

ባሕል። አንዳንድ ማኅበረሰቦች አምባገነን መሆን “የወንድነት” መገለጫ እንደሆነ ወይም ሴቶች ደካማ መስለው እንዳይታዩ ሞገደኛ መሆን እንዳለባቸው ያስተምራሉ። እንዲህ ያለ አመለካከት ያላቸው የትዳር ጓደኛሞች ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ እንደ ትዳር አጋር ሳይሆን እንደ ባላንጣ የሚተያዩ ሲሆን የሚጠቀሙባቸው ቃላትም ከመፈወስ ይልቅ የሚጎዱ ናቸው።

መንስኤው ምንም ይሁን ምን ጎጂ ንግግር ለፍቺ እንዲሁም ለተለያዩ የጤና ችግሮች ሊዳርግ ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ቃላት ከአካላዊ ጥቃት የበለጠ እንደሚጎዱ ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ባሏ ይሰድባትና ይደበድባት የነበረች አንዲት ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ከዱላው ይልቅ ስድቡን መቋቋም ከብዶኝ ነበር። ጎጂ ቃላትን ከሚሰነዝርብኝ ቢመታኝ እመርጥ ነበር።”

አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ የምትሰነዝሯቸው ጎጂ ቃላት ትዳራችሁን እየሸረሸሩት ከሆነ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

 ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

ራስን በሌላው ቦታ ማስቀመጥ። ራስህን በትዳር ጓደኛህ ቦታ በማስቀመጥ የምትናገራቸው ቃላት በእሷ ላይ ምን ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል ለማሰብ ሞክር። ከቻልክ የትዳር ጓደኛህ ስሜት የተጎዳበትን በአንድ ወቅት የተናገርከውን ጎጂ ንግግር አስብ። ሊታሰብበት የሚገባው ዋናው ጉዳይ የተናገርከው ነገር ሳይሆን የሰነዘርከው ቃል በትዳር ጓደኛህ ላይ ያሳደረው ስሜት ነው። በዚያ ወቅት ጎጂ ቃላት ከመሰንዘር ይልቅ አሳቢነት በተሞላበት መንገድ ምን ልትል ትችል እንደነበር ማሰብ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቍጣን ይጭራል” ይላል።—ምሳሌ 15:1

የሚከባበሩ ሌሎች ባለትዳሮችን ምሳሌ መከተል። ምሳሌ አድርጋችሁ የምትመለከቷቸው ሰዎች በምታደርጉት የሐሳብ ልውውጥ ረገድ መጥፎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩባችሁ ከሆነ ጥሩ ምሳሌ ሊሆኗችሁ የሚችሉ ባለትዳሮችን ለማግኘት ጥረት አድርጉ። የእነሱን ምሳሌ መከተል እንድትችሉ የሚነጋገሩበትን መንገድ በጥሞና አዳምጡ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ፊልጵስዩስ 3:17

በፊት የነበራችሁ ዓይነት ስሜት እንዲሰማችሁ ጥረት አድርጉ። ብዙውን ጊዜ ጎጂ ንግግር የሚመነጨው ከአፍ ሳይሆን ከልብ ነው። ስለሆነም ስለ ትዳር ጓደኛችሁ አዎንታዊ አመለካከትና ስሜት ለማዳበር ጥረት አድርጉ። ቀደም ሲል አንድ ላይ ያሳለፋችኋቸውን አስደሳች ጊዜያት አስታውሱ። በፊት የተነሳችኋቸውን ፎቶግራፎች ተመልከቱ። ከዚህ ቀደም ያስቋችሁ የነበሩት ነገሮች ምንድን ናቸው? እርስ በርስ እንድትቀራረቡ ያደረጓችሁ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው?—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ሉቃስ 6:45

የራሳችሁን ስሜት ለመግለጽ ሞክሩ። በትዳር ጓደኛህ ላይ ጎጂ ቃላት ከመሰንዘር ይልቅ አንድን ጉዳይ በተመለከተ ምን እንደተሰማህ ግለጽ። ለምሳሌ ያህል “ድሮም አንቺ ማንኛውንም ነገር የምታደርጊው እኔን ሳታማክሪ ነው!” ከማለት ይልቅ “እኔን ሳታማክሪ አንዳንድ ነገሮችን ስታደርጊ እኔ የማቀርበው ሐሳብ ምንም ቦታ እንደማይሰጠው ሆኖ ይሰማኛል” ብትል የተሻለ ምላሽ ልታገኝ ትችላለህ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ቆላስይስ 4:6

ውይይቱን መቼ ማቆም እንዳለባችሁ እወቁ። ንግግራችሁ ወደ ቁጣ እያመራ እንደሆነ ካስተዋላችሁ ውይይቱን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፉ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ውይይቱ ወዲያውኑ ወደ ጭቅጭቅ ከተቀየረ ሌላ ጊዜ በረጋ መንፈስ መወያየት እንዲቻል ለጊዜው ክርክሩን አቋርጦ መሄዱ ምንም ስህተት የለውም።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 17:14

ብዙውን ጊዜ ጎጂ ንግግር የሚመነጨው ከአፍ ሳይሆን ከልብ ነው