በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ሩሲያ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ሩሲያ

በ1991 በሩሲያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ለረጅም ጊዜ በሥራቸው ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነስቶ ሕጋዊ እውቅና ባገኙ ጊዜ ደስታቸው ወሰን አልነበረውም። በዚያን ጊዜ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በአሥር እጥፍ አድጎ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ይኸውም ከ170,000 በላይ እንደሚሆን ማንም አላሰበም! ከእነዚህ ታታሪ የመንግሥቱ ሰባኪዎች መካከል በሩሲያ ያለውን መንፈሳዊ የመከር ሥራ ለመደገፍ ከውጭ አገር ወደ ሩሲያ የተዛወሩ የይሖዋ ምሥክሮች ይገኙበታል። (ማቴ. 9:37, 38) እስቲ አንዳንዶቹ የሚሉትን እንስማ።

ፈቃደኛ የሆኑ ወንድሞች ጉባኤዎችን አጠናክረዋል

ከታላቋ ብሪታንያ የመጣው ማቲው በሩሲያ እገዳው ሲነሳ 28 ዓመቱ ነበር። በዚያ ዓመት በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ የቀረበ አንድ ንግግር በምሥራቅ አውሮፓ ባሉት ጉባኤዎች እገዛ እንደሚያስፈልግ የሚያጎላ ነበር። ለአብነት ያህል፣ ተናጋሪው በሴይንት ፒተርስበርግ፣ ሩሲያ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ አንድ አገልጋይ ብቻ እንጂ ምንም ሽማግሌ እንደሌለ ጠቀሰ። ያም ሆኖ በዚያ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉት አስፋፊዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ነበሯቸው! ማቲው እንዲህ ብሏል፦ “ከዚያ ንግግር በኋላ የማስበው ስለ ሩሲያ ብቻ ነበር፤ በመሆኑም እዚያ ሄጄ ለማገልገል ያለኝን ፍላጎት ጠቅሼ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ።” ማቲው የተወሰነ ገንዘብ ካጠራቀመና አብዛኞቹን ንብረቶቹን ከሸጠ በኋላ በ1992 ወደ ሩሲያ ተዛወረ። ለመሆኑ ምን አጋጥሞት ይሆን?

ማቲው

ማቲው “ቋንቋውን መማር ተፈታታኝ ነበር። ከሰዎች ጋር ጥሩ መንፈሳዊ ውይይት ማድረግ አልቻልኩም” ብሏል። ሌላው ተፈታታኝ ነገር ደግሞ ማረፊያ ማግኘት ነበር። ማቲው እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤቱን ለቅቄ እንድወጣ እየተነገረኝ ከአንዱ አፓርተማ ወደ ሌላው ስንቴ እንደቀየርኩ ቁጥሩ እንኳ ጠፍቶኛል።” ማቲው መጀመሪያ ላይ እንዲህ ያሉ ችግሮች ቢያጋጥሙትም እንደሚከተለው ብሏል፦ “ወደ ሩሲያ መዛወሬ በጣም ጥሩ ውሳኔ እንደሆነ ይሰማኛል። እዚህ በማገልገሌ ከምንጊዜውም የበለጠ በይሖዋ መታመንን ተምሬያለሁ፤ እንዲሁም በብዙ መንገዶች የእሱን አመራር አግኝቻለሁ።” ከጊዜ በኋላ ማቲው የጉባኤ ሽማግሌና ልዩ አቅኚ ሆኖ የተሾመ ሲሆን አሁን በሴይንት ፒተርስበርግ አቅራቢያ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ያገለግላል።

በ1999 ሄሩ በ25 ዓመቱ በጃፓን ከሚገኘው የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተመረቀ፤ ከአስተማሪዎቹ አንዱም ወደ ሌላ አገር ሄዶ እንዲያገለግል አበረታታው። ሄሩ በሩሲያ ሰባኪዎች በጣም እንደሚያስፈልጉ ሰምቶ ስለነበር ሩሲያኛ መማር ጀመረ። በተጨማሪም አንድ ሌላ እርምጃ ወሰደ። ሄሩ እንዲህ ብሏል፦ “ለስድስት ወር ወደ ሩሲያ ሄድኩ። በሩሲያ ክረምቱ በጣም ከባድ ስለሆነ ቅዝቃዜውን መቋቋም እችል እንደሆነ ለማየት ስለፈለግኩ ወደዚያ የሄድኩት በኅዳር ወር ነበር።” ሄሩ የክረምቱን ወቅት ካሳለፈ በኋላ ወደ ጃፓን ተመለሰ፤ በዚያም ሩሲያ ሲመለስ በቋሚነት መኖር የሚያስችለውን ገንዘብ ለማጠራቀም ሲል ቀላል ሕይወት መምራት ጀመረ።

ሄሩ እና ስቬትላና

ሄሩ በሩሲያ መኖር ከጀመረ 12 ዓመት ሆኖታል፤ በብዙ ጉባኤዎች ውስጥም አገልግሏል። ከ100 በላይ አስፋፊዎች ባሉበት ጉባኤ ውስጥ ብቻውን ሽማግሌ ሆኖ የሠራበት ጊዜ ነበር። በአንድ ጉባኤ ውስጥ ሲያገለግል በየሳምንቱ አብዛኞቹን የአገልግሎት ስብሰባ ክፍሎች ያቀርብ እንዲሁም ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤቱን፣ የመጠበቂያ ግንብ ጥናቱን እና በአምስት ቡድኖች ውስጥ የጉባኤ መጽሐፍ ጥናቱን ይመራ ነበር። በተጨማሪም ብዙ የእረኝነት ጉብኝቶችን ያደርግ ነበር። ሄሩ እነዚያን ዓመታት መለስ ብሎ ሲያስብ “ወንድሞችና እህቶች በመንፈሳዊ ጠንካራ እንዲሆኑ መርዳት በጣም አስደሳች ነበር” ብሏል። ታዲያ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገሉ በእሱ ላይ ምን ለውጥ አምጥቷል? እንዲህ ይላል፦ “ወደ ሩሲያ ከመሄዴም በፊት ሽማግሌና አቅኚ ሆኜ አገለግል ነበር፤ ይሁን እንጂ እዚህ ከመጣሁ በኋላ ከይሖዋ ጋር ፍጹም አዲስ የሆነ ዝምድና እንደመሠረትኩ ይሰማኛል። በሁሉም የሕይወቴ ዘርፎች ይበልጥ በይሖዋ መታመንን ተምሬያለሁ።” በ2005 ሄሩ ስቬትላና የምትባል እህት አግብቶ በአቅኚነት አብረው ማገልገላቸውን ቀጥለዋል።

ማይክል እና ኦልጋ ከማሪና እና ከማቲው ጋር

የ34 ዓመቱ ማቲው እና 28 ዓመት የሆነው ወንድሙ ማይክል የመጡት ከካናዳ ነው። ሁለቱም ሩሲያን ከጎበኙ በኋላ፣ ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች በስብሰባዎች ላይ እንደሚገኙ ሆኖም ጥናት ሊመሩላቸው የሚችሉ ወንድሞች ጥቂት መሆናቸውን ሲያዩ ተገረሙ። ማቲው እንዲህ ይላል፦ “የሄድኩበት ጉባኤ 200 ተሰብሳቢዎች ነበሩት፤ ሆኖም ስብሰባዎቹ በሙሉ የሚመሩት በአንድ አረጋዊ የጉባኤ ሽማግሌና በአንድ ወጣት የጉባኤ አገልጋይ ነበር። ይህን ሁኔታ ማየቴ ወደዚያ ተዛውሬ በዚያ ያሉትን ወንድሞች ለመርዳት አነሳሳኝ።” ማቲው በ2002 ወደ ሩሲያ ሄደ።

ከአራት ዓመታት በኋላ ማይክልም ወደ ሩሲያ ሄደ፤ እሱም ቢሆን አሁንም ወንድሞች በጣም እንደሚያስፈልጉ ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀበትም። የጉባኤ አገልጋይ ስለነበረ በሒሳብ፣ በጽሑፍና በክልል አገልጋይነት እንዲሠራ ተመደበ። በተጨማሪም የጉባኤ ጸሐፊ የሚሠራውን ሥራ እንዲያከናውን፣ የሕዝብ ንግግር እንዲሰጥ፣ ትላልቅ ስብሰባዎችን በማደራጀት እንዲረዳና የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባት ሥራ እንዲካፈል ተጠየቀ። በአሁኑ ጊዜም ጭምር በጉባኤዎች ውስጥ ብዙ እርዳታ ያስፈልጋል። በርካታ የሥራ ምድቦችን ተቀብሎ መሥራት የሚያለፋ ቢሆንም አሁን በሽምግልና እያገለገለ ያለው ማይክል “ወንድሞችን ማገዝ ከፍተኛ እርካታ ይሰጠኛል። ከዚህ የተሻለ ሕይወቴን ልጠቀምበት የምችልበት መንገድ የለም” ብሏል።

ማቲው ከማሪና ጋር ትዳር የመሠረተ ሲሆን ማይክል ደግሞ ኦልጋን አግብቷል። ሁለቱ ወንድማማቾችና ሚስቶቻቸው ከሌሎች በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች ጋር በመሆን በማደግ ላይ ያሉትን ጉባኤዎች እየረዱ ነው።

ቀናተኛ እህቶች በመከሩ ሥራ እየተካፈሉ ነው

ታቲያና

በ1994 ታቲያና የ16 ዓመት ወጣት ሳለች ከስሎቫኪያ፣ ከቼክ ሪፑብሊክና ከፖላንድ የመጡ ስድስት ልዩ አቅኚዎች ዩክሬን ውስጥ እሷ በነበረችበት ጉባኤ እያገለገሉ ነበር። ከእነሱ ጋር ያሳለፈችውን አስደሳች ጊዜ በተመለከተ ስትናገር “ተግባቢና ደግ የሆኑ ቀናተኛ አቅኚዎች ነበሩ፤ ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ያውቁታል” ብላለች። ያላቸውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ይሖዋ እንደባረከው ስትመለከት ‘እኔም እንደነሱ መሆን እፈልጋለሁ’ ብላ አሰበች።

ታቲያና አቅኚዎቹ ባሳዩት ምሳሌነት ስለተበረታታች ዩክሬንና ቤላሩስ ውስጥ ወደሚገኙ ምሥራቹ ወዳልተሰበከባቸው ራቅ ያሉ የአገልግሎት ክልሎች ትምህርት ቤት ሲዘጋ ከጓደኞቿ ጋር ትሄድ ነበር። ለስብከት በተጓዘችበት ጊዜ በጣም ስለተደሰተች ወደ ሩሲያ በመዛወር አገልግሎቷን ለማስፋት አቀደች። በመጀመሪያ የቆየችው ለአጭር ጊዜ ነበር፤ ጊዜውን፣ ከሌላ አገር ወደ ሩሲያ ተዛውራ የነበረችን አንዲት እህት ለመጠየቅና ለአቅኚነት አገልግሎቷ ምቹ የሆነ ሥራ ለመፈለግ ተጠቅማበታለች። በኋላም በ2000 ወደ ሩሲያ ተዛወረች። ታዲያ ለውጡ ከብዷት ነበር?

ታቲያና እንደሚከተለው በማለት ትናገራለች፦ “ብቻዬን አፓርታማ ለመከራየት አቅሜ ስለማይፈቅድ በሌሎች ሰዎች ቤት ውስጥ አንድ ክፍል መከራየት ግድ ሆኖብኝ ነበር። በዚህ ሁኔታ መኖር ቀላል አልነበረም። ወደ ቤቴ ለመመለስ የፈለግሁባቸው ጊዜያት ነበሩ። ያም ቢሆን በአገልግሎቴ ብቀጥል እንደምጠቀም መገንዘብ እንድችል ይሖዋ ምንጊዜም ረድቶኛል።” በአሁኑ ጊዜ ታቲያና ሩሲያ ውስጥ ሚስዮናዊት ሆና እያገለገለች ነው። ታቲያና ሐሳቧን ስታጠቃልል እንዲህ ብላለች፦ “ከአገሬ ርቄ ባሳለፍኳቸው በእነዚያ ዓመታት በዋጋ ሊተመን የማይችል ተሞክሮና ብዙ ወዳጆች አግኝቻለሁ። ከሁሉ በላይ ደግሞ በእነዚህ ዓመታት እምነቴ ተጠናክሯል።”

ማሳኮ

በአሁኑ ጊዜ በ50ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የምትገኘውና በጃፓን ትኖር የነበረችው ማሳኮ ዕድሜዋን ሙሉ በሚስዮናዊነት የማገልገል ምኞት ነበራት፤ ሆኖም ባሉባት የጤና ችግሮች የተነሳ በዚህ የአገልግሎት መብት መካፈል እንደማትችል ይሰማት ነበር። ያም ሆኖ ጤንነቷ ትንሽ ሲሻሻል በሩሲያ ባለው የመከር ሥራ ለመካፈል በማሰብ ወደዚያ ለመዛወር ወሰነች። በዚያ ተስማሚ የሆነ ማረፊያና ቋሚ ሥራ ማግኘት አዳጋች የነበረ ቢሆንም ጃፓንኛ በማስተማርና የጽዳት ሥራ በመሥራት ራሷን እየደጎመች በአቅኚነት መካፈል ችላለች። ለመሆኑ በአገልግሎቷ ለመቀጠል የረዳት ምንድን ነው?

ማሳኮ ሩሲያ ውስጥ በአገልግሎት ያሳለፈቻቸውን 14 ዓመታት መለስ ብላ በማሰብ እንዲህ ብላለች፦ “በአገልግሎቱ ያገኘሁት ደስታ ያጋጠመኝን ማንኛውንም ችግር የሚያካክስ ነው። የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች መስበክ፣ የማይሰለችና አስደሳች ሕይወት ለመምራት ያስችላል።” አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የሚያስፈልገኝን ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንደሰጠኝ ሳስብ ይህ በራሴ ሕይወት ያየሁት ዘመናዊ ተአምር እንደሆነ ይሰማኛል።” ማሳኮ በሩሲያ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ ከማገልገሏም በተጨማሪ በኪርጊስታን ባለው የመከር ሥራም ተካፍላለች። በተጨማሪም በእንግሊዝኛ፣ በቻይንኛና በዊጉር ቋንቋ በሚመሩ ቡድኖች ውስጥ እርዳታ ማበርከት ችላለች። በአሁኑ ጊዜ በሴይንት ፒተርስበርግ በአቅኚነት እያገለገለች ነው።

እርዳታ በመስጠት በረከት ያገኙ ቤተሰቦች

ኢንገ እና ሚካኢል

በኢኮኖሚ አለመረጋጋት የተነሳ ቤተሰቦች ብዙውን ጊዜ ኑሯቸውን ለማሻሻል ወደ ሌሎች አገሮች ይዛወራሉ። ይሁን እንጂ በጥንት ዘመን እንደነበሩት እንደ አብርሃምና እንደ ሣራ ሁሉ አንዳንድ ቤተሰቦች ወደ ውጭ አገር የሚዛወሩት መንፈሳዊ ግቦችን ለመከታተል ነው። (ዘፍ. 12:1-9) በ2003 ከዩክሬን ወደ ሩሲያ የተዛወሩትን ሚካኢል እና ኢንገ የሚባሉ ባልና ሚስት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እዚያ ከሄዱ ብዙም ሳይቆይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተጠሙ ሰዎችን አገኙ።

ሚካኢል እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ ወቅት ማንም የይሖዋ ምሥክር ሰብኮ በማያውቅበት አካባቢ ሰበክን። አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ሰው በራቸውን ከፍተው ‘ሰባኪዎች ናችሁ?’ ብለው ጠየቁን። እኛም ‘አዎ’ ስንላቸው እንዲህ አሉን፦ ‘አንድ ቀን እንደምትመጡ አውቅ ነበር። ምክንያቱም ኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት መፈጸማቸው ግድ ነው።’ ከዚያም ሰውየው ማቴዎስ 24:14ን ጠቀሱልን።” ሚካኢል አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በተጨማሪም በዚያ አካባቢ ወደ አሥር ገደማ የሚሆኑ የባፕቲስት እምነት ተከታይ ሴቶችን አገኘን፤ እነዚህ ሴቶች እውነትን የተጠሙ ከመሆናቸውም ሌላ ቅኖች ናቸው። ዘላለም መኖር የተባለው መጽሐፍ የነበራቸው ሲሆን ሁልጊዜ ቅዳሜና እሁድ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ይጠቀሙበት ነበር። ብዙ ሰዓት ተወያይተን ጥያቄዎቻቸውን መለስንላቸው፤ የመንግሥቱን መዝሙሮች አብረናቸው ዘመርን፤ እንዲሁም አብረን ራት በላን። ስለዚያ ጊዜ ካሉኝ ግሩም ትዝታዎች አንዱ ይህ ነው።” ሚካኢልና ኢንገ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገላቸው ከይሖዋ ጋር ይበልጥ እንዳቀራረባቸው፣ ለሰዎች ያላቸውን ፍቅር እንዳጠነከረላቸው እንዲሁም እጅግ አርኪ ሕይወት እንዳጎናጸፋቸው ይናገራሉ። በአሁኑ ጊዜ በወረዳ ሥራ እየተካፈሉ ነው።

ኦክሳና፣ አሌክሲ እና ዩሪ

በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙት ዩሪ እና ኦክሳና የሚባሉ ከዩክሬን የመጡ ባልና ሚስት አሌክሲ ከሚባለው አሁን 13 ዓመት ከሆነው ወንድ ልጃቸው ጋር ሆነው በሩሲያ ያለውን ቅርንጫፍ ቢሮ በ2007 ጎበኙ። እዚያም የሩሲያን ካርታ ሲመለከቱ ሰባኪዎች ያልተመደቡባቸው ብዙ ቦታዎች እንዳሉ አስተዋሉ። ኦክሳና እንዲህ ብላለች፦ “ያንን ካርታ ካየን በኋላ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ከምንጊዜውም የበለጠ እንደሚያስፈልጉ ተገነዘብን። ይህም ወደ ሩሲያ ለመሄድ እንድንወስን ረዳን።” ይህን ውሳኔ እንዲያደርጉ የረዳቸው ሌላው ነገርስ ምንድን ነው? ዩሪ እንዲህ ይላል፦ “በጽሑፎቻችን ላይ የወጡ ‘በባዕድ አገር ማገልገል ትችላለህን?’ እንደሚለው ያሉ ርዕሶችን ማንበባችን ጠቅሞናል። * ቅርንጫፍ ቢሮው እንድንረዳ ሐሳብ ያቀረበልንን አንድ አካባቢ ሄደን የጎበኘን ሲሆን በዚያ ቤትና ሥራ ፈለግን።” በ2008 ወደ ሩሲያ ሄዱ።

ዩሪና ኦክሳና መጀመሪያ አካባቢ ሥራ ማግኘት አዳጋች ሆኖባቸው ነበር፤ እንዲሁም ከአንድ አፓርተማ ወደ ሌላው ብዙ ጊዜ ተዛውረዋል። ዩሪ እንዲህ ብሏል፦ “ተስፋ እንዳንቆርጥ ብዙ ጊዜ እንጸልያለን፤ እንዲሁም ይሖዋ እንደሚደግፈን በመተማመን በስብከቱ ሥራችን እንቀጥላለን። ይሖዋ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ቅድሚያ ስንሰጥ ምን ያህል እንደሚንከባከበን በሕይወታችን ተመልክተናል። በዚህ አገልግሎት መካፈላችን ቤተሰባችንን አጠናክሮታል።” (ማቴ. 6:22, 33) ለመሆኑ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል በታዳጊው አሌክሲ ላይ ምን ውጤት አምጥቷል? ኦክሳና እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “እሱንም በጣም ጠቅሞታል። ሕይወቱን ለይሖዋ ወስኖ የተጠመቀው በዘጠኝ ዓመቱ ነው። የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ እንደሚያስፈልጉ መመልከቱ ትምህርት ቤት በተዘጋ ቁጥር ረዳት አቅኚ ሆኖ እንዲያገለግል አነሳስቶታል። ለአገልግሎቱ ያለውን ፍቅርና ቅንዓት ስንመለከት በጣም እንደሰታለን።” በአሁኑ ጊዜ ዩሪና ኦክሳና በልዩ አቅኚነት እያገለገሉ ነው።

“የሚቆጨኝ ነገር”

እነዚህ የመከር ሠራተኞች ከተናገሩት ነገር በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተዛውረህ አገልግሎትህን ለማስፋት በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን ይኖርብሃል። እርግጥ ነው፣ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ የሚያገለግሉ ሁሉ በአዲሱ የአገልግሎት ክልላቸው ውስጥ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል፤ ይሁን እንጂ ለመንግሥቱ መልእክት ቀና ምላሽ ለሚሰጡ ሰዎች ምሥራቹን በማካፈል የሚገኘውን ጥልቅ ደስታ ያጣጥማሉ። አንተስ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት አካባቢ በመከሩ ሥራ መካፈል ትችል ይሆን? እንዲህ ለማድረግ ከወሰንክ ዩሪ፣ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውሮ ለማገልገል ስላደረገው ውሳኔ የተሰማው ዓይነት ስሜት ይኖርሃል፤ “የሚቆጨኝ ነገር ቢኖር ቀደም ብዬ አለመጀመሬ ነው” ብሏል።

^ አን.20 የጥቅምት 15, 1999 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 23-27 ተመልከት።