በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ ሃያ አንድ

ፍርሃትንና ጥርጣሬን ለማሸነፍ ታግሏል

ፍርሃትንና ጥርጣሬን ለማሸነፍ ታግሏል

1-3. ጴጥሮስ አስደናቂ ነገሮች በተከናወኑበት በዚያን ዕለት ምን ነገር ሲፈጸም ተመልክቷል? ሌሊት ላይስ ምን አጋጠመው?

ጴጥሮስ ባለ በሌለ ኃይሉ ለመቅዘፍ እየታገለ በጨለማው ውስጥ ለማየት ይጣጣራል። በስተ ምሥራቅ በኩል ከአድማሱ ባሻገር የሚታየው ደብዛዛ ብርሃን ጎህ ሊቀድ መሆኑን የሚያበስር ምልክት ይሆን? ጴጥሮስ ለረጅም ሰዓት ሲቀዝፍ ስለቆየ ጡንቻዎቹ ዝለዋል። የገሊላን ባሕር የሚያናውጠው ነፋስ ፀጉሩን እያመሰቃቀለው ነው። እየተከታተለ የሚመጣው ሞገድ ከጀልባዋ ጋር በሚላተምበት ጊዜ የሚረጨው ቀዝቃዛ ውኃ ጴጥሮስን አበስብሶታል። ያም ሆኖ ጴጥሮስ መቅዘፉን ቀጥሏል።

2 ጴጥሮስና ጓደኞቹ ወደዚህ የመጡት ኢየሱስን በባሕሩ ዳርቻ ብቻውን ትተውት ነው። ያን ዕለት ኢየሱስ፣ ተርበው የነበሩ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን በጥቂት ዳቦና ዓሣ ሲመግብ አይተዋል። ሕዝቡ ይህን ሲመለከት ኢየሱስን ሊያነግሠው አስቦ ነበር፤ እሱ ግን በፖለቲካ ውስጥ እጁን ማስገባት አልፈለገም። ተከታዮቹንም እንዲህ ማድረግ እንደሌለባቸው ሊያስተምራቸው ፈልጓል። ኢየሱስ ከሕዝቡ ገለል ካለ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ በጀልባ ተሳፍረው በተቃራኒ አቅጣጫ ወዳለው የባሕር ዳርቻ ቀድመውት እንዲሄዱ ግድ አላቸው፤ ከዚያም ለመጸለይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ።—ማር. 6:35-45፤ ዮሐንስ 6:14-17ን አንብብ።

3 ደቀ መዛሙርቱ ጉዞ ሲጀምሩ ሙሉዋ ጨረቃ በአናታቸው ትክክል ነበረች፤ አሁን ግን በስተ ምዕራብ በኩል አድማስ ውስጥ ገብታ ልትሰወር ትንሽ ቀርቷታል። ያም ሆኖ የተጓዙት ጥቂት ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር። ነፋሱና ሞገዱ የሚፈጥረው ፉጨት ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርስ እንዳይደማመጡ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በሐሳብ ነጉዶ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።

ጴጥሮስ በሁለት ዓመታት ውስጥ በርካታ ትምህርቶችን ከኢየሱስ የቀሰመ ቢሆንም ገና የሚያሻሽላቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ

4. ጴጥሮስ ግሩም ምሳሌ የሚሆነን የትኞቹን እንቅፋቶች ለመወጣት ባደረገው ትግል ነው?

4 ጴጥሮስ በአእምሮው ውስጥ ብዙ ነገሮች ሊመላለሱ ይችላሉ! ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ከተገናኘ ሁለት ዓመት አልፎታል። ብዙ አስደናቂ ነገሮች በተከናወኑባቸው በእነዚህ ሁለት ዓመታት ውስጥ በርካታ ትምህርቶችን የቀሰመ ቢሆንም ገና የሚያሻሽላቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ። ጴጥሮስ ለመሻሻል ፈቃደኛ በመሆን ይኸውም እንደ ጥርጣሬና ፍርሃት ያሉ እንቅፋቶችን ለመወጣት ትግል በማድረግ ረገድ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ይህን የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

“መሲሑን አገኘነው”!

5, 6. የጴጥሮስ ሕይወት ምን ይመስል ነበር?

5 ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር የተገናኘበትን ቀን መቼም ቢሆን አይረሳውም። “መሲሑን አገኘነው” የሚለውን አስደሳች ዜና ለመጀመሪያ ጊዜ ያበሰረው ወንድሙ እንድርያስ ነበር። ጴጥሮስ እነዚህን ቃላት ከሰማ በኋላ ሕይወቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተለወጠ።—ዮሐ. 1:41

6 ጴጥሮስ ይኖር የነበረው የገሊላ ባሕር ተብሎ በሚጠራው ሐይቅ ሰሜናዊ ዳርቻ ላይ በምትገኘው በቅፍርናሆም ነው። እሱና እንድርያስ የዘብዴዎስ ልጆች ከሆኑት ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር በጋራ ሆነው ዓሣ የማጥመድ ሥራ ይሠሩ ነበር። ጴጥሮስ የሚኖረው ከሚስቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ከአማቱና ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር ነበር። ዓሣ በማጥመድ ሥራ እንዲህ ያለውን ቤተሰብ ማስተዳደር ትጋት፣ ጉልበትና ብልሃት እንደሚጠይቅ እሙን ነው። ጴጥሮስና ጓደኞቹ በሁለት ጀልባዎች መካከል መረባቸውን ወደ ባሕሩ ከጣሉ በኋላ ያጠመዱትን ዓሣ ወደ ጀልባቸው ሲጎትቱ ይታይህ፤ ይህን ሥራ በመሥራት የሚያሳልፏቸው በርካታ ሌሊቶች ምን ያህል አድካሚ እንደሆኑ ማሰብ ትችላለህ። ቀኑንም ቢሆን የሚያሳልፉት ዓሣዎችን በመለየትና በመሸጥ እንዲሁም መረባቸውን በመጠገንና በማጽዳት ነው።

7. ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ምን ሰማ? ይህ ዜናስ አስደሳች የሆነው ለምንድን ነው?

7 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እንድርያስ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ነበር። ጴጥሮስ ወንድሙ እንድርያስ፣ ዮሐንስ ያውጀው የነበረውን መልእክት ሲነግረው በጉጉት ያዳምጥ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። አንድ ቀን ዮሐንስ ወደ ኢየሱስ እያመለከተ “የአምላክ በግ ይኸውላችሁ!” ብሎ ሲናገር እንድርያስ ሰማ። እንድርያስ ወዲያውኑ ኢየሱስን መከተል የጀመረ ሲሆን ስለ መሲሑ መምጣት የሚገልጸውን አስደሳች ዜናም ለጴጥሮስ አበሰረው! (ዮሐ. 1:35-41) ከ4,000 ዓመታት በፊት በኤደን ዓመፅ ከተፈጸመ በኋላ ይሖዋ አምላክ ለሰው ዘሮች እውነተኛ ተስፋ የሚፈነጥቅ ልዩ የሆነ አካል ወደ ምድር እንደሚልክ ቃል ገብቶ ነበር። (ዘፍ. 3:15) እንድርያስ ይህን አዳኝ ማለትም መሲሑን በአካል አግኝቶት ነበር! ጴጥሮስም ኢየሱስን ለማግኘት በፍጥነት ወደ እሱ ሄደ።

8. ኢየሱስ ለጴጥሮስ ያወጣለት ስም ትርጉም ምንድን ነው? አንዳንዶች ይህ ስም ለእሱ መሰጠቱ ተገቢ እንዳልሆነ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?

8 እስከዚያች ቀን ድረስ ጴጥሮስ ይጠራ የነበረው ስምዖን በሚለው ስም ነበር። ይሁንና ኢየሱስ ጴጥሮስን ባየው ጊዜ “አንተ የዮሐንስ ልጅ ስምዖን ነህ፤ ኬፋ (ትርጉሙ ጴጥሮስ ማለት ነው) ተብለህ ትጠራለህ” አለው። (ዮሐ. 1:42) “ኬፋ” የሚለው ቃል የወል ስም ሲሆን “ድንጋይ” ወይም “ዐለት” የሚል ትርጉም አለው። ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ትንቢታዊ ይዘት እንዳለው ግልጽ ነው። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ልክ እንደ ዐለት ጽኑ፣ ቆራጥና አስተማማኝ በመሆን በክርስቶስ ተከታዮች ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር እየተናገረ ነበር። ጴጥሮስ ስለ ራሱ እንዲህ ይሰማው ነበር? ጴጥሮስ እንዲህ የተሰማው አይመስልም። በዛሬው ጊዜ የወንጌል ዘገባዎችን የሚያነቡ አንዳንድ ሰዎችም እንኳ ጴጥሮስ እንደ ዐለት ያለ ጽኑ ባሕርይ አለው ብሎ ማሰብ ይከብዳቸዋል። አንዳንዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሰፈረው ዘገባ አንጻር ሲታይ ጴጥሮስ ወላዋይና በአቋሙ የማይጸና ሰው እንደሆነ ይናገራሉ።

9. ይሖዋና ልጁ ሰዎችን ሲመለከቱ ትኩረት የሚያደርጉት በምን ላይ ነው? እነሱ ለእኛ ያላቸውን አመለካከት አምነን መቀበል ያለብንስ ለምን ይመስልሃል?

9 ጴጥሮስ የራሱ ድክመቶች ነበሩት። ኢየሱስ የጴጥሮስን ድክመቶች ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ይሁንና ኢየሱስ እንደ አባቱ እንደ ይሖዋ ሁልጊዜም የሚመለከተው የሰዎችን በጎ ጎን ነው። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ብዙ ጥሩ ባሕርያት እንዳሉት ያስተዋለ ሲሆን እነዚህ ባሕርያቱ ይበልጥ ጎልተው እንዲወጡ ሊረዳው ፈልጓል። በዛሬው ጊዜም ይሖዋና ልጁ ትኩረት የሚያደርጉት ባለን መልካም ጎን ላይ ነው። በእኛ ውስጥ ያን ያህል ጥሩ ነገር ያገኛሉ ብሎ ማሰብ ይከብደን ይሆናል። ይሁን እንጂ እነሱ ለእኛ ያላቸውን አመለካከት አምነን መቀበልና ጴጥሮስ እንዳደረገው ሁሉ ለመሠልጠንም ሆነ ለመቀረጽ ፈቃደኛ መሆን ይገባናል።—1 ዮሐንስ 3:19, 20ን አንብብ።

“አይዞህ አትፍራ”

10. ጴጥሮስ ምን ነገር ሲፈጸም ተመልክቶ ሊሆን ይችላል? ይሁንና ወደ የትኛው ሥራው ተመለሰ?

10 ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ከዚያ በኋላ ባደረጋቸው የስብከት ጉዞዎች ሁሉ አብሮት ሳይጓዝ አይቀርም። በመሆኑም ጴጥሮስ በቃና በተደረገው የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ኢየሱስ ውኃውን ወደ ወይን በመለወጥ የመጀመሪያውን ተአምር ሲፈጽም ተመልክቶ መሆን ይኖርበታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት አስመልክቶ የተናገረውን አስደናቂና ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት ሰምቷል። ያም ሆኖ ኢየሱስን መከተሉን በማቆም ዓሣ ወደ ማጥመድ ሥራው ተመለሰ። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ግን ጴጥሮስና ኢየሱስ በድጋሚ ተገናኙ፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ለጴጥሮስ ሙሉ ጊዜውን ከእሱ ጋር አብሮት በመስበክ እንዲያሳልፍ ግብዣ አቀረበለት።

11, 12. (ሀ) ጴጥሮስ ያሳለፈው ሌሊት ምን ይመስል ነበር? (ለ) ጴጥሮስ ኢየሱስን ሲያዳምጥ በአእምሮው ውስጥ ምን ጥያቄዎች ተፈጥረው ሊሆን ይችላል?

11 ጴጥሮስ ያሳለፈው ሌሊት ተስፋ አስቆራጭ ነበር። ዓሣ አጥማጆቹ በተደጋጋሚ ጊዜ መረባቸውን ወደ ባሕሩ ቢጥሉም ምንም ዓሣ አላገኙም። ጴጥሮስ ያለውን ልምድም ሆነ የተለያዩ ዘዴዎችን እንደተጠቀመና ዓሣዎች በብዛት ሊገኙ የሚችሉባቸውን ቦታዎች ሁሉ ሲያስስ እንዳደረ ጥርጥር የለውም። ጴጥሮስ ሌሎቹ ዓሣ አጥማጆች እንደሚመኙት ሁሉ በጨለማ በተዋጠው ባሕር ውስጥ ዓሣዎቹ ያሉበትን ቦታ ማየት ወይም ደግሞ በሆነ መንገድ ተጠቅሞ ዓሣዎቹ ወደ መረቡ እንዲገቡለት ማድረግ ቢችል ደስ ባለው ነበር። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው ምኞት ብስጭቱን ከማባባስ በቀር ምንም የሚፈይድለት ነገር የለም። ጴጥሮስ ዓሣ የሚያጠምደው ለመዝናናት ሳይሆን እጁን ጠብቀው የሚያድሩ ሰዎች ስላሉ ነው። ያም ሆነ ይህ ጴጥሮስ በመጨረሻ ባዶ እጁን ወደ ባሕሩ ዳርቻ መጣ። ከዚህ በኋላ ደግሞ መረቦቹ መጽዳት ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ኢየሱስ ወደ እሱ ሲመጣ ጴጥሮስ በዚህ ሥራ ተጠምዶ ነበር።

ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ የስብከቱ ዋና ጭብጥ ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት ሰፊ ማብራሪያ ሲሰጥ በትኩረት ማዳመጥ አልታከተውም

12 በዚህ ጊዜ ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ከበው የሚያስተምረውን ትምህርት በጉጉት ያዳምጡ ነበር። ኢየሱስ ሰዎቹ መፈናፈኛ ስላሳጡት ጴጥሮስ ጀልባ ላይ ወጥቶ ጀልባዋን ከየብስ ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርግለት ጠየቀው። ኢየሱስ በባሕሩ ላይ ሆኖ ሕዝቡን ሲያስተምር ድምፁ ጥርት ብሎ ይሰማ ነበር። በባሕሩ ዳርቻ ላይ እንዳሉት ሰዎች ሁሉ ጴጥሮስም የኢየሱስን ትምህርት በንቃት ይከታተል ነበር። ኢየሱስ የስብከቱ ዋና ጭብጥ ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት ሰፊ ማብራሪያ ሲሰጥ ጴጥሮስ በትኩረት ማዳመጥ አልታከተውም። ክርስቶስ ተስፋ የሚፈነጥቀውን ይህንን መልእክት በመላው እስራኤል ለማዳረስ በሚያደርገው ጥረት እሱን መርዳት መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ታዲያ ጴጥሮስ እንደዚያ ማድረግ ይችል ይሆን? እንደዚያ ካደረገ ቤተሰቡን በምን ያስተዳድራል? በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ያለ ምንም ውጤት ያሳለፈው ረጅም ሌሊት አሁንም ትዝ ብሎት ሊሆን ይችላል።—ሉቃስ 5:1-3

13, 14. ኢየሱስ ለጴጥሮስ ምን ተአምር ፈጸመለት? ጴጥሮስስ ምን ተሰማው?

13 ኢየሱስ ንግግሩን ሲጨርስ ጴጥሮስን “ጥልቅ ወደሆነው አካባቢ ፈቀቅ በልና መረቦቻችሁን ጥላችሁ አጥምዱ” አለው። ጴጥሮስ ግን ጥርጣሬ አደረበት። በመሆኑም “መምህር፣ ሌሊቱን ሙሉ ስንደክም አድረን ምንም አልያዝንም፤ አንተ ካልክ ግን መረቦቹን እጥላለሁ” አለው። ጴጥሮስ መረቦቹን አጽድቶ አስቀምጧቸው ነበር። በተለይ ዓሣዎቹ ሊገኙ በማይችሉበት በዚህ ሰዓት መረቦቹን እንደገና ባይጥል ይመርጥ ነበር! ያም ሆኖ ኢየሱስ ያዘዘውን ከማድረግ ወደኋላ አላለም፤ በዚህ ጊዜ በሁለተኛው ጀልባ ላይ ያሉት የሥራ ባልደረቦቹ እንዲከተሉት ምልክት ሳይሰጣቸው አልቀረም።—ሉቃስ 5:4, 5

14 ጴጥሮስ መረቦቹን መጎተት ሲጀምር ክብደቱ ከጠበቀው በላይ ሆነበት። ሁኔታውን ማመን አቅቶት ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ መረቦቹን ሲጎትት ብዛት ያላቸው ዓሣዎች መረቡ ውስጥ ሲተራመሱ ተመለከተ! ወዲያውኑም በሌላኛው ጀልባ ላይ ያሉት ባልንጀሮቻቸው መጥተው እንዲረዷቸው ምልክት ሰጣቸው። ባልንጀሮቻቸው መጥተው ሲረዷቸው ዓሣዎቹ በጣም ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ አንድ ጀልባ ብቻ ሊይዛቸው እንደማይችል ተገነዘቡ። ሁለቱን ጀልባዎች ከሞሉ በኋላም እንኳ ብዙ ዓሣዎች ተርፈው ነበር፤ እንዲያውም ከዓሣው ክብደት የተነሳ ጀልባዎቹ መስመጥ ጀመሩ። ጴጥሮስ በሁኔታው በጣም ተገረመ። ጴጥሮስ፣ ክርስቶስ ከዚህ ቀደም ተአምር ሲፈጽም የተመለከተ ቢሆንም ይህ ግን ለእሱ ተብሎ እንደተደረገ ተሰማው! ለካስ ዓሣዎች ወደ መረብ ሰተት ብለው እንዲገቡ የማድረግ ችሎታ ያለው ሰው አለ! ጴጥሮስ በፍርሃት ተዋጠ። ከዚያም በጉልበቱ ተንበርክኮ “ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ሰው ስለሆንኩ ከእኔ ራቅ” አለው። ጴጥሮስ በአምላክ ኃይል እንዲህ ያሉ ተአምራትን መፈጸም ከሚችል ሰው ጋር እንዴት ወዳጅነት መመሥረት ይችላል?—ሉቃስ 5:6-9ን አንብብ።

‘ጌታ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ሰው ነኝ’

15. ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ያደረበት ጥርጣሬና ፍርሃት ምክንያታዊ አለመሆኑን ያስተማረው እንዴት ነው?

15 ኢየሱስ ጴጥሮስን ደግነት በሚንጸባረቅበት መንገድ “አይዞህ አትፍራ፤ ከአሁን ጀምሮ ሰውን በሕይወት እንዳለ የምታጠምድ ትሆናለህ” አለው። (ሉቃስ 5:10, 11) አሁን ጴጥሮስ የሚጠራጠርበትም ሆነ የሚፈራበት ጊዜ አይደለም። ጴጥሮስ ዓሣ ማስገሩን ቢያቆም ቤተሰቡን በምን ሊያስተዳድር እንደሚችል በማሰብ መጠራጠሩም ሆነ የሠራቸውን ስህተቶችና ያሉበትን ድክመቶች እያብሰለሰለ መፍራቱ ምክንያታዊ አልነበረም። ኢየሱስ የሚያከናውነው ሥራ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ነው። የሚያገለግለው አምላክም ቢሆን “ይቅርታው ብዙ” ነው። (ኢሳ. 55:7) ይሖዋ የጴጥሮስን ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎት ያሟላለታል።—ማቴ. 6:33

16. ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ኢየሱስ ላቀረበላቸው ግብዣ ምን ምላሽ ሰጡ? ይህስ በሕይወታቸው ሊያደርጉ ከሚችሉት ውሳኔ ሁሉ የላቀ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

16 ያዕቆብና ዮሐንስ እንዳደረጉት ሁሉ ጴጥሮስም አፋጣኝ እርምጃ ወሰደ። እነዚህ ሰዎች “ጀልባዎቹን መልሰው ወደ የብስ ካስጠጉ በኋላ ሁሉን ነገር ትተው ተከተሉት።” (ሉቃስ 5:11) ጴጥሮስ በኢየሱስና እሱን በላከው አምላክ ላይ እምነት እንዳለው በተግባር አሳየ። ይህ በሕይወቱ ሊያደርገው ከሚችለው ሁሉ እጅግ የላቀ ውሳኔ ነው። አምላክን ለማገልገል ሲያስቡ ይሰማቸው የነበረውን ፍርሃትና ጥርጣሬ ያሸነፉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ እምነት እያሳዩ ነው። ይሖዋ በእሱ በመታመናቸው አላሳፈራቸውም።—መዝ. 22:4, 5

“ለምን ተጠራጠርክ?”

17. ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ባሳለፋቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ስለተከናወኑት ስለየትኞቹ ነገሮች አስቦ ሊሆን ይችላል?

17 ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ከተገናኘ ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ነፋስ በበዛበት በዚያ ሌሊት በገሊላ ባሕር ላይ ጀልባውን እየቀዘፈ ነበር። በዚህ ጊዜ ስለ ምን ነገር እያሰበ እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ሆኖም ብዙ ልንጠቅሳቸው የምንችላቸው ነገሮች ይኖራሉ! ኢየሱስ የጴጥሮስን አማት ፈውሷል። የተራራውን ስብከት ሰጥቷል። ኢየሱስ ባስተማራቸው ትምህርቶችም ሆነ ባከናወናቸው ተአምራት እሱ ይሖዋ የመረጠው መሲሕ መሆኑን በተደጋጋሚ ጊዜ አስመሥክሯል። ወራት እያለፉ ሲሄዱ ጴጥሮስ በፍርሃትና በጥርጣሬ ቶሎ የመሸነፍ ዝንባሌውን ጨምሮ ያሉበትን አንዳንድ ድክመቶች በተወሰነ መጠን አሻሽሎ መሆን አለበት። ኢየሱስም ጴጥሮስን ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ አድርጎ መርጦታል! ይሁን እንጂ ጴጥሮስ ብዙም ሳይቆይ ያለበትን ፍርሃትና ጥርጣሬ ገና ሙሉ በሙሉ እንዳላሸነፈ መገንዘቡ አይቀርም።

18, 19. (ሀ) ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ላይ ምን እንደተመለከተ ግለጽ። (ለ) ኢየሱስ ጴጥሮስ የጠየቀውን ነገር እንዲያደርግ የፈቀደለት እንዴት ነው?

18 ጊዜው አራተኛው ክፍለ ሌሊት ማለትም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት እስከ ንጋት ያለው ሲሆን ጴጥሮስ ድንገት መቅዘፉን አቁሞ በተቀመጠበት ክው ብሎ ቀረ። ከሞገዱ ባሻገር አንድ የሚንቀሳቀስ ነገር ይታያል! ሞገዱ የሚረጨው ውኃ ላይ የሚያርፈው የጨረቃ ብርሃን የፈጠረው ምስል ይሆን? በፍጹም! ያየው ነገር ታይቶ ጥፍት የሚል አይደለም። ከዚህ ይልቅ በባሕሩ ላይ እየተራመደ የሚመጣ ሰው ነው! ሰውየው እየተቃረበ ሲመጣ አልፏቸው የሚሄድ ይመስል ነበር። ደቀ መዛሙርቱ በጣም ተደናግጠው ስለነበር ምትሃት የሚያዩ መሰላቸው። በዚህ ጊዜ ሰውየው “አይዟችሁ፤ እኔ ነኝ፤ አትፍሩ” አላቸው። ለካ ሰውየው ኢየሱስ ነበር!—ማቴ. 14:25-28

19 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ከሆንክ በውኃው ላይ እየተራመድኩ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” አለው። ጴጥሮስ መጀመሪያ ላይ ወኔው መጥቶ ነበር። ይህን ልዩ ተአምር ሲያይ በጣም ከመደነቁ የተነሳ እሱም ምን ያህል እምነት እንዳለው ማሳየት ፈለገ። በመሆኑም ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ጓጓ። ኢየሱስም ወደ እሱ እንዲመጣ ጋበዘው። ጴጥሮስ በጎን በኩል እንደምንም ብሎ ጀልባዋ ጠርዝ ላይ ከወጣ በኋላ ከጀልባዋ ወርዶ የሚናወጠው ባሕር ላይ ቆመ። የቆመበት ባሕር ሳይከዳው ቀጥ ብሎ መቆም በመቻሉ ምን ያህል ተደንቆ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ወደ ኢየሱስ መራመድ ሲጀምር በአግራሞት ስሜት ተውጦ መሆን አለበት። ዳሩ ምን ያደርጋል ብዙም ሳይቆይ አንድ ሌላ ስሜት ተሰማው።—ማቴዎስ 14:29ን አንብብ።

“ማዕበሉን ሲያይ ፈራ”

20. (ሀ) ጴጥሮስ ትኩረቱ የተከፋፈለው እንዴት ነው? ይህስ ምን አስከተለበት? (ለ) ኢየሱስ ለጴጥሮስ ምን ትምህርት ሰጠው?

20 ጴጥሮስ ትኩረቱን በኢየሱስ ላይ እንዳደረገ መቀጠል ነበረበት። በይሖዋ ኃይል ተጠቅሞ ጴጥሮስን በሚናወጠው ባሕር ላይ ቀጥ ብሎ እንዲራመድ ያስቻለው ኢየሱስ ነው። ኢየሱስ ደግሞ ይህን ያደረገው ጴጥሮስ በእሱ ላይ ያለውን እምነት ተመልክቶ ነው። ይሁንና ጴጥሮስ ትኩረቱ ተከፋፈለ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንደሚናገረው ጴጥሮስ “ማዕበሉን ሲያይ ፈራ።” ጴጥሮስ ሞገዱ ከጀልባዋ ጋር ሲጋጭና ውኃውን ወደ ላይ ሲረጨው ትኩር ብሎ መመልከት ጀመረ፤ በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በፍርሃት ተዋጠ። ምናልባትም ሐይቁ ውስጥ ሰምጦ ሲሞት ታይቶት ሊሆን ይችላል። ፍርሃቱ እየጨመረ ሲሄድ እምነቱ እያሽቆለቆለ ሄደ። ወደፊት በሚኖረው ጽኑ አቋም የተነሳ “ዐለት” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶት የነበረው ይህ ሰው እምነቱ በመዋዠቁ ምክንያት እንደ ድንጋይ መስጠም ጀመረ። ጴጥሮስ የተዋጣለት ዋናተኛ የነበረ ቢሆንም በዚህ ወቅት ባለው ችሎታ መተማመን አልቻለም። በመሆኑም “ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ። ከዚያም ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ ያዘውና ከውኃው አወጣው። እዚያው ውኃው ላይ እያሉም ኢየሱስ “አንተ እምነት የጎደለህ፣ ለምን ተጠራጠርክ?” በማለት ለጴጥሮስ አንድ አስፈላጊ ትምህርት ሰጠው።—ማቴ. 14:30, 31

21. ጥርጣሬ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? ይህን ስሜት መዋጋት የምንችለውስ እንዴት ነው?

21 “ለምን ተጠራጠርክ?” የሚለው አነጋገር ምንኛ ተስማሚ ነው! ጥርጣሬ አጥፊ ሊሆን ይችላል። በጥርጣሬ ከተሸነፍን እምነታችን ሊዳከምብንና በመንፈሳዊ የመስመጥ አደጋ ሊያጋጥመን ይችላል። በመሆኑም ጥርጣሬን አጥብቀን መዋጋት ይኖርብናል! እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሁልጊዜም ትኩረታችንን በትክክለኛው ነገር ላይ በማድረግ ነው። ፍርሃት በሚያሳድሩብን፣ ተስፋ በሚያስቆርጡን እንዲሁም በይሖዋና በልጁ ላይ እንዳናተኩር በሚያደርጉን ነገሮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ የሚሰማን ጥርጣሬ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይሄዳል። ከዚህ ይልቅ በይሖዋና በልጁ ላይ ትኩረት የምናደርግ እንዲሁም እነሱን ለሚወዷቸው ሰዎች ከዚህ ቀደም ባደረጉት፣ አሁን እያደረጉ ባሉትና ወደፊት በሚያደርጉት ነገር ላይ የምናሰላስል ከሆነ አጥፊ የሆነውን የጥርጣሬ ስሜት ማሸነፍ እንችላለን።

22. ጴጥሮስ እምነት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ ልንከተል ይገባል የምንለው ለምንድን ነው?

22 ጴጥሮስ ኢየሱስን ተከትሎ ጀልባው ላይ ከወጣ በኋላ ማዕበሉ እየተረጋጋ ሲመጣ ተመለከተ። በገሊላ ባሕር ላይ ፍጹም ጸጥታ ሰፈነ። እንደ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ሁሉ ጴጥሮስም ኢየሱስን “አንተ በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነህ” አለው። (ማቴ. 14:33) በሐይቁ ላይ ጎህ እየቀደደ ሲሄድ የጴጥሮስ ልብ በአድናቆት ስሜት ተሞልቶ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚያ በኋላ ጥርጣሬና ፍርሃት ሊያሸንፈው እንደማይገባ ጥሩ ትምህርት አግኝቷል። ይሁንና ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረለት እንደ ዐለት ጽኑ የሆነ ክርስቲያን እንዲሆን ገና ብዙ ለውጥ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ተስፋ ሳይቆርጥ ጥረት ለማድረግና እያደገ ለመሄድ ቆርጦ ተነስቷል። አንተስ እንዲህ ለማድረግ ቆርጠሃል? ጴጥሮስ እምነት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል ቢባል እንደምትስማማ ምንም ጥርጥር የለውም።