በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አራት

“ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ”

“ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ”

1, 2. (ሀ) የሩትና የኑኃሚን ጉዞ ምን ይመስል እንደነበር እንዲሁም የደረሰባቸውን አሳዛኝ ሁኔታ ግለጽ። (ለ) የሩት ጉዞ ከኑኃሚን የሚለየው እንዴት ነው?

ሩት የሞዓብን አምባ አቋርጦ በሚያልፈው ነፋስ በበዛበት ገላጣ መንገድ ላይ ከኑኃሚን ጋር እየተጓዘች ነው። በተንጣለለው ሜዳ ላይ ከርቀት ሲታዩ ነጥብ መስለው የሚታዩት እነዚህ ሁለት ሴቶች ብቻቸውን እየተጓዙ ነው። ሩት ጀምበሯ እያዘቀዘቀች መሆኗን ስላስተዋለች የሚያድሩበት ቦታ መፈለጉ ሳይሻላቸው እንደማይቀር በማሰብ አማቷን ቀና ብላ ተመለከተቻት። ኑኃሚንን ከልብ ስለምትወዳት እሷን ለመንከባከብ ስትል ማንኛውንም መሥዋዕትነት ከመክፈል ወደኋላ አትልም።

2 ሁለቱም ሴቶች በከባድ ሐዘን ተደቁሰዋል። ኑኃሚን ባሏን በሞት ከተነጠቀች ዓመታት አልፈዋል፤ አሁን ደግሞ ሁለቱ ወንዶች ልጆቿ መሐሎንና ኬሌዎን በመሞታቸው በሐዘን ላይ ሐዘን ተደርቦባታል። ሩትም ብትሆን ባሏን መሐሎንን በሞት በማጣቷ አዝናለች። እሷም ሆነች ኑኃሚን የሚጓዙት ወደ አንድ ስፍራ ይኸውም ወደ ቤተልሔም ነው። ይሁን እንጂ ጉዞው ለሁለቱ ሴቶች የተለያየ ትርጉም ነበረው። ኑኃሚን ወደ አገሯ እየተመለሰች ነው። ሩት ግን ወዳጅ ዘመዶቿን፣ የትውልድ አገሯን እንዲሁም የአገሯን አማልክት፣ ባሕልና ወግ ትታ ወደ ባዕድ አገር እየሄደች ነው።—ሩት 1:3-6ን አንብብ።

3. ሩት እምነት በማሳየት ረገድ የተወችውን ምሳሌ እንድንከተል የሚረዳን ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን ነው?

3 ይህች ወጣት እንዲህ ዓይነቱን ከባድ ለውጥ እንድታደርግ ያነሳሳት ምን ይሆን? ሩት አዲሱን ሕይወት ለመልመድና ኑኃሚንን ለመንከባከብ የሚያስችል ብርታት የምታገኘው እንዴት ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘታችን ሞዓባዊቷ ሩት እምነት በማሳየት ረገድ ከተወችው ምሳሌ ብዙ የምንማረው ነገር እንዳለ ይጠቁመናል። (በተጨማሪም  “እጥር ምጥን ያለ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ” የሚል ርዕስ ያለውን ሣጥን ተመልከት።) እስቲ በመጀመሪያ፣ እነዚህ ሁለት ሴቶች ወደ ቤተልሔም የሚደረገውን ረጅም ጉዞ ለመጀመር ያነሳሳቸው ምን እንደሆነ እንመልከት።

መከራ ያለያየው ቤተሰብ

4, 5. (ሀ) የኑኃሚን ቤተሰብ ወደ ሞዓብ የሄደው ለምንድን ነው? (ለ) ኑኃሚን በሞዓብ ምን ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጠሟት?

4 ሩት ያደገችው ከሙት ባሕር በስተ ምሥራቅ በምትገኝ ሞዓብ በምትባል አንዲት ትንሽ አገር ውስጥ ነው። አብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ጥልቅ ሸለቆዎች አቋርጠዋቸው የሚያልፉ አልፎ አልፎ ዛፎች የበቀሉባቸው አምባዎች ይታዩበታል። የእስራኤል ምድር በድርቅ በሚጠቃበት ጊዜም እንኳ ‘የሞዓብ’ ምድር አብዛኛውን ጊዜ ለም ነበር። ሩት ከመሐሎንና ከቤተሰቡ ጋር እንድትገናኝ ምክንያት የሆነውም ይህ ነው።—ሩት 1:1

5 በእስራኤል የተከሰተው ረሃብ፣ የኑኃሚን ባል አቤሜሌክ ሚስቱንና ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ይዞ በመጻተኝነት ለመኖር ወደ ሞዓብ እንዲሄድ አስገደደው። እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ወደመረጠው ቅዱስ ስፍራ እየሄዱ ዘወትር አምልኳቸውን ማከናወን ያስፈልጋቸው ስለነበር ይህ ቤተሰብ ወደ ሞዓብ መሄዱ የሁሉንም የቤተሰቡን አባላት እምነት ፈትኖት መሆን አለበት። (ዘዳ. 16:16, 17) የሆነ ሆኖ ኑኃሚን እምነቷን ጠብቃ መኖር ችላለች። እርግጥ ነው፣ የባሏ ሞት በሐዘን እንድትደቆስ አድርጓታል።—ሩት 1:2, 3

6, 7. (ሀ) ኑኃሚን ልጆቿ ሞዓባውያን ሴቶችን ማግባታቸው አሳስቧት ሊሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) ኑኃሚን ምራቶቿን የያዘችበት መንገድ ሊያስመሰግናት የሚገባው ለምንድን ነው?

6 ኑኃሚን፣ ሁለቱ ወንዶች ልጆቿ ሞዓባውያን ሴቶችን ማግባታቸውም ሐዘኗን እጥፍ ድርብ አድርጎት መሆን አለበት። (ሩት 1:4) ኑኃሚን የእስራኤላውያን ቅድመ አያት የሆነው አብርሃም ለልጁ ለይስሐቅ ይሖዋን ከሚያመልኩ ወገኖቹ መካከል ሚስት ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገ ታውቃለች። (ዘፍ. 24:3, 4) ከጊዜ በኋላ ደግሞ የሙሴ ሕግ እስራኤላውያንን ከጣዖት አምልኮ ለመጠበቅ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ከባዕድ ሰዎች ጋር እንዳይጋቡ የሚያዝዝ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።—ዘዳ. 7:3, 4

7 ያም ቢሆን ግን መሐሎንና ኬሌዎን ሞዓባውያን ሴቶችን አገቡ። ኑኃሚን ይህ ሁኔታ አሳስቧት ወይም አሳዝኗት ሊሆን ቢችልም ለምራቶቿ ለሩትና ለዖርፋ ከልብ የመነጨ ደግነትና ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ እንዳላለች ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። ምናልባት እነሱም አንድ ቀን እንደ እሷ ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተስፋ አድርጋ ይሆናል። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ሩትና ዖርፋ ኑኃሚንን ይወዷት ነበር። በመካከላቸው የነበረው ይህ ጠንካራ ወዳጅነት የደረሰባቸውን ሐዘን እንዲቋቋሙ ረድቷቸዋል። እነዚህ ሁለት ወጣቶች ባሎቻቸውን በሞት ያጡት ገና ልጅ ሳይወልዱ ነበር።—ሩት 1:5

8. ሩት ወደ ይሖዋ እንድትሳብ ያደረጋት ምን ሊሆን ይችላል?

8 ሩት ትከተለው የነበረው ሃይማኖት እንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁኔታ ባጋጠማት ወቅት ማጽናኛ እንድታገኝ ሊረዳት ይችል ነበር? እንዲህ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ሞዓባውያን ብዙ አማልክትን ያመልኩ የነበሩ ሲሆን ከእነሱም መካከል ዋነኛው ከሞስ ነበር። (ዘኍ. 21:29) የሞዓባውያን አምልኮ ሕፃናትን መሥዋዕት ማድረግን ጨምሮ በዚያ ዘመን ይፈጸሙ ከነበሩ የተለመዱ አሰቃቂ የጭካኔ ድርጊቶች የጸዳ አልነበረም። ሩት፣ አፍቃሪና መሐሪ ስለሆነው ስለ እስራኤል አምላክ ስለ ይሖዋ አንዳንድ ነገሮችን ከመሐሎን ወይም ከኑኃሚን ሳትማር አትቀርም፤ ይህ ደግሞ በይሖዋ እና በሞዓባውያን አማልክት መካከል ያለው ልዩነት ቁልጭ ብሎ እንዲታያት እንደሚያደርግ ጥርጥር የለውም። ይሖዋ ሕዝቦቹን የሚገዛው በማስፈራራት ሳይሆን በፍቅር ነው! (ዘዳግም 6:5ን አንብብ።) ሩት በባሏ ሞት ምክንያት የደረሰባት ከባድ ሐዘን ወደ ኑኃሚን ይበልጥ እንድትቀርብና ይህች አረጋዊት ሁሉን ቻይ ስለሆነው አምላክ ስለ ይሖዋና ስለ ድንቅ ሥራዎቹ እንዲሁም ሕዝቡን በፍቅርና በምሕረት ስለያዘበት መንገድ ስትናገር ልቧን ከፍታ እንድታዳምጥ አነሳስቷት ሊሆን ይችላል።

ሩት ሐዘን በደረሰባት ወቅት ይበልጥ ወደ ኑኃሚን በመቅረብ የጥበብ እርምጃ ወስዳለች

9-11. (ሀ) ኑኃሚን፣ ሩትና ዖርፋ ምን ለማድረግ ወሰኑ? (ለ) እነዚህ ሴቶች ከደረሰባቸው አሳዛኝ ሁኔታ ምን መገንዘብ እንችላለን?

9 ኑኃሚን ደግሞ ከትውልድ ቀዬዋ የመጣ ወሬ ለመስማት ትጓጓ ነበር። አንድ ቀን፣ በእስራኤል የነበረው ረሃብ እንደተወገደ የሚገልጽ ወሬ ደረሳት፤ ምናልባትም ይህን የሰማችው ከአንድ ተጓዥ ነጋዴ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ትኩረቱን ወደ ሕዝቡ መልሶ ነበር። ቤተልሔም ልክ እንደ ስሟ “የዳቦ ቤት” ሆና ነበር። በመሆኑም ኑኃሚን ወደ አገሯ ለመመለስ ወሰነች።—ሩት 1:6

10 ታዲያ ሩትና ዖርፋ ምን ያደርጉ ይሆን? (ሩት 1:7) የደረሰባቸው ሐዘን ከኑኃሚን ጋር ይበልጥ አቀራርቧቸዋል። በተለይም ሩት፣ በኑኃሚን ደግነትና በይሖዋ ላይ ባላት ጽኑ እምነት የተማረከች ይመስላል። ሦስቱም መበለቶች አብረው ወደ ይሁዳ ለመሄድ ተነሱ።

11 የሩት ታሪክ፣ ክፉ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ጥሩና ታማኝ የሆኑ ሰዎችም አሳዛኝ ነገር ሊያጋጥማቸው እንዲሁም የሚወዱትን ሰው በሞት ሊያጡ እንደሚችሉ ያስገነዝበናል። (መክ. 9:2, 11) በተጨማሪም ይህ ታሪክ የምንወደውን ሰው በሞት ስንነጠቅ ከሚሰማን መሪር ሐዘን መጽናናት እና ብርታት ማግኘት እንድንችል ከሌሎች፣ በተለይም እንደ ኑኃሚን ይሖዋን መጠጊያቸው ካደረጉ ሰዎች ጋር መቀራረባችን ብልህነት መሆኑን እንድንረዳ ያስችለናል።—ምሳሌ 17:17

ሩት ያሳየችው ጽኑ ፍቅር

12, 13. ኑኃሚን ምራቶቿ የሆኑት ሩትና ዖርፋ አብረዋት እንዲሄዱ ከመፍቀድ ይልቅ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የፈለገችው ለምንድን ነው? ሁለቱ ወጣት ሴቶችስ መጀመሪያ ላይ ምን ምላሽ ሰጧት?

12 ሦስቱ መበለቶች በጉዟቸው እየገፉ ሲሄዱ ኑኃሚንን አንድ ነገር ያሳስባት ጀመር። አብረዋት ስላሉት ሁለት ወጣት ሴቶችና ለእሷም ሆነ ለወንዶች ልጆቿ ስላሳዩት ፍቅር አሰበች። የገጠማቸው አሳዛኝ ሁኔታ አልበቃ ብሎ እሷ ደግሞ ሌላ ሸክም እንዳትሆንባቸው ሰጋች። አገራቸውን ጥለው ከእሷ ጋር ወደ ቤተልሔም ከሄዱ በዚያ ምን ልታደርግላቸው ትችላለች?

13 በመጨረሻም ኑኃሚን ሲያብሰለስላት የነበረውን ሐሳብ አውጥታ ተናገረች፤ እንዲህ አለቻቸው፦ “እያንዳንዳችሁ ወደ እናቶቻችሁ ቤት ተመለሱ፤ ለሞቱ ባሎቻችሁና ለእኔ በጎ ነገር እንዳደረጋችሁ፣ ለእናንተም እግዚአብሔር እንደዚሁ ያድርግላችሁ።” በተጨማሪም ይሖዋ ባልና የሞቀ ትዳር በመስጠት እንዲባርካቸው ያላትን ምኞች ገለጸችላቸው። አክሎም ዘገባው “ከዚያም ሳመቻቸው፤ እነርሱም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው አለቀሱ” ይላል። ሩትና ዖርፋ ይህችን ደግና አሳቢ ሴት ይህን ያህል የወደዷት ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። በመሆኑም ሁለቱም “አይሆንም! ከአንቺ ጋር ተመልሰን ወደ ወገኖችሽ እንሄዳለን” በማለት ተማጸኗት።—ሩት 1:8-10

14, 15. (ሀ) ዖርፋ የተመለሰችው ወዴት ነበር? (ለ) ኑኃሚን፣ ሩት ትታት እንድትመለስ ለማሳመን የሞከረችው እንዴት ነበር?

14 ይሁንና ኑኃሚን በቀላሉ የምትረታ አልሆነችም። የሚያስተዳድራት ባልም ሆነ ለእነሱ ባሎች የሚሆኑ ወንዶች ልጆች እንደሌሏትና ወደፊትም ቢሆን ሁኔታው ይለወጣል ብላ ተስፋ እንደማታደርግ በመግለጽ እስራኤል ሲደርሱ ለእነሱ ምንም ልታደርግላቸው እንደማትችል ልታሳምናቸው ሞከረች። ልታደርግላቸው የምትችለው ነገር አለመኖሩም ሐዘኗን ይበልጥ እንደሚያከብደው ነገረቻቸው። ዖርፋ፣ ኑኃሚን የተናገረችው ነገር አሳማኝ እንደሆነ ተሰማት። ዖርፋ ወደ ሞዓብ ብትመለስ እናቷ እጇን ዘርግታ የምትቀበላት ከመሆኑም ሌላ የምትገባበት ቤት አለላት። በእርግጥም ወደ ሞዓብ መመለሱ ይበልጥ ምክንያታዊ ይመስላል። ስለዚህ እያዘነች ኑኃሚንን ስማ ተሰናበተቻት፤ ወደ ኋላም ተመለሰች።—ሩት 1:11-14

15 ሩትስ ምን ታደርግ ይሆን? ኑኃሚን ያቀረበችው ሐሳብ ለእሷም ቢሆን ይሠራል። ሆኖም ዘገባው “ሩት ግን ልትለያት [አልፈለገችም]” ይላል። ምናልባት ኑኃሚን መንገዷን ስትቀጥል ሩት እየተከተለቻት እንደሆነ አስተውላ ሊሆን ይችላል። ኑኃሚን ጠንከር ባለ አነጋገር “እነሆ የባልሽ ወንድም ሚስት ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች፤ አብረሻት ተመለሽ” አለቻት። (ሩት 1:15) ኑኃሚን የተናገረችው ሐሳብ አንድ ወሳኝ ነገር እንድንገነዘብ ያስችለናል። ዖርፋ የተመለሰችው ወደ ሕዝቧ ብቻ ሳይሆን ወደ ‘አማልክቷም’ ነበር። ዖርፋ፣ ከሞስንና ሌሎች የሐሰት አማልክትን እያመለከች ብትኖርም ደስተኛ ነበረች። ሩትስ እንደዚህ ይሰማት ይሆን?

16-18. (ሀ) ሩት ጽኑ ፍቅር እንደነበራት ያሳየችው እንዴት ነው? (ለ) ጽኑ ፍቅር ማሳየትን በተመለከተ ከሩት ምን ልንማር እንችላለን? (በተጨማሪም የሁለቱን ሴቶች ሥዕል ተመልከት።)

16 ሩት በዚያ ጭር ያለ መንገድ ላይ ኑኃሚንን ስትመለከታት ትታት ላለመሄድ በልቧ ወስና ነበር። ሩት ለኑኃሚንም ሆነ ኑኃሚን ለምታመልከው አምላክ በውስጧ ከፍተኛ ፍቅር ተተክሏል። ስለዚህ እንዲህ አለቻት፦ “ተለይቼሽ እንድቀር ወይም እንድመለስ አትለማመጭኝ፤ ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ በምትኖሪበትም እኖራለሁ፤ ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል። በምትሞቺበት እሞታለሁ፤ እዚያው እቀበራለሁ። ከእንግዲህ ሞት ከሚለየን በቀር ብለይሽ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ይፍረድብኝ፤ ከዚህም የከፋ ያድርግብኝ።”—ሩት 1:16, 17

“ሕዝብሽ ሕዝቤ፤ አምላክሽ አምላኬ ይሆናል”

17 ሩት ከሞተች 3,000 የሚያህሉ ዓመታት ቢያልፉም የተናገረቻቸው ቃላት በጣም አስደናቂ ከመሆናቸው የተነሳ ዛሬም ድረስ ይታወሳሉ። እነዚህ ቃላት አንድን ግሩም ባሕርይ ይኸውም ጽኑ ፍቅርን ጥሩ አድርገው ይገልጻሉ። ሩት እጅግ ጥልቅና ጽኑ ፍቅር ስለነበራት ኑኃሚን በሄደችበት ሁሉ ከእሷ ላለመለየት ቆርጣ ነበር። ከሞት በቀር ምንም ነገር ሊለያቸው አይችልም። ሩት የሞዓባውያንን አማልክት ጨምሮ በሞዓብ የነበራትን ሁሉ ትታ ለመሄድ ዝግጁ ስለነበረች የኑኃሚን ሕዝቦች የእሷም ሕዝቦች ይሆናሉ። በመሆኑም ከዖርፋ በተለየ መልኩ ሩት የኑኃሚን አምላክ የሆነው ይሖዋ ለእሷም አምላኳ እንዲሆንላት እንደምትፈልግ በሙሉ ልብ መናገር ትችላለች። *

18 በመሆኑም ሁለቱ ብቻቸውን ወደ ቤተልሔም የሚወስደውን ረጅም መንገድ ተያያዙት። አንድ መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ጉዞው አንድ ሳምንት ያህል ሊፈጅ ይችላል። አብረው መሆናቸው በተወሰነ መጠንም ቢሆን ከሐዘናቸው እንዳጽናናቸው ጥርጥር የለውም።

19. በትዳር ውስጥ፣ በቤተሰብ አባላትና በጓደኛሞች መካከል እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሩት ጽኑ ፍቅር በማሳየት ረገድ የተወችውን አርዓያ መከተል የምንችለው በምን መንገድ ነው?

19 የምንኖረው አሳዛኝ ነገሮች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” በማለት በሚጠራው በእኛ ዘመን የምንወዳቸውን ሰዎች በሞት ማጣትን ጨምሮ በሐዘን እንድንዋጥ የሚያደርጉ የተለያዩ ነገሮች ያጋጥሙናል። (2 ጢሞ. 3:1) ስለዚህ ሩት ያሳየችው ባሕርይ ከምንጊዜውም ይበልጥ ዛሬ አስፈላጊ ነው። ጽኑ ፍቅር ከሚወዱት አካል ጋር መጣበቅንና እሱን የሙጥኝ ማለትን የሚያመለክት ሲሆን በጨለማ በተዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ለመልካም ተግባር እንድንነሳሳ የሚያደርግ ከፍተኛ ኃይል አለው። ይህ ባሕርይ በትዳር ውስጥ፣ በቤተሰብ አባላትና በጓደኛሞች መካከል እንዲሁም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በጣም ያስፈልጋል። (1 ዮሐንስ 4:7, 8, 20ን አንብብ።) እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር እያዳበርን ስንሄድ ሩት የተወችውን ግሩም አርዓያ እየተከተልን መሆናችንን እናሳያለን።

ሩትና ኑኃሚን በቤተልሔም

20-22. (ሀ) ኑኃሚን በሞዓብ ያሳለፈችው ሕይወት ምን ስሜት አሳድሮባታል? (ለ) ኑኃሚን የደረሰባትን መከራ በተመለከተ ምን የተሳሳተ አመለካከት ነበራት? (በተጨማሪም ያዕቆብ 1:13⁠ን ተመልከት።)

20 ጽኑ ፍቅር እንዳለን መናገር አንድ ነገር ሲሆን እንዲህ ያለውን ፍቅር በተግባር ማሳየት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ሩት ለኑኃሚን ብቻ ሳይሆን አምላኳ እንዲሆን ለመረጠችው ለይሖዋም ጽኑ ፍቅር እንዳላት የምታሳይበት አጋጣሚ ተከፍቶላታል።

21 በመጨረሻም ሁለቱ ሴቶች ከኢየሩሳሌም በስተ ደቡብ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ቤተልሔም ከተማ ደረሱ። የኑኃሚን መመለስ በከተማዋ ውስጥ ትልቅ የመነጋገሪያ ርዕስ መሆኑ የኑኃሚን ቤተሰብ በአንድ ወቅት በዚህች ትንሽ ከተማ ውስጥ ታዋቂ እንደነበር ይጠቁማል። በዚያ የነበሩት ሴቶች ኑኃሚንን ትኩር ብለው እያዩዋት “ይህች ኑኃሚን ናትን?” ይባባሉ ነበር። ኑኃሚን በሞዓብ ያሳለፈችው ሕይወት በጣም ሳይለውጣት አይቀርም፤ ገጽታዋና የተጎሳቆለው ሰውነቷ ለዓመታት መከራና ሐዘን እንደተፈራረቀባት ይጠቁማል።—ሩት 1:19

22 ኑኃሚን ከዓመታት በፊት ለተለየቻቸው ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ ሕይወት ምን ያህል መራራ እንደሆነባት ገለጸችላቸው። እንዲያውም “ደስታዬ” የሚል ትርጉም ያለው ኑኃሚን የሚለው ስሟ “መራራ” የሚል ትርጉም ባለው ማራ በሚለው ስም ሊተካ እንደሚገባ ተሰምቷት ነበር። ምስኪን ኑኃሚን! ከእሷ በፊት እንደኖረው እንደ ኢዮብ ሁሉ መከራ እንዲደርስባት ያደረገው ይሖዋ እንደሆነ ተሰምቷታል።—ሩት 1:20, 21፤ ኢዮብ 2:10፤ 13:24-26

23. ሩት ስለ ምን ነገር ማሰብ ጀመረች? የሙሴ ሕግ ድሆች ከየትኛው ዝግጅት እንዲጠቀሙ ይፈቅድ ነበር? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

23 ሁለቱ ሴቶች በቤተልሔም ኑሯቸውን ሲመሠርቱ ሩት ራሷንም ሆነ ኑኃሚንን እንዴት በተሻለ ሁኔታ ማስተዳደር እንደምትችል ማሰብ ጀመረች። ይሖዋ በእስራኤል ለሚኖሩ ሕዝቦቹ በሰጠው ሕግ ውስጥ ድሆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያገኙ የሚያስችል ፍቅራዊ ዝግጅት እንዳለ አወቀች። አዝመራ በሚሰበሰብበት ወቅት ድሆች ወደ ሌሎች ማሳ በመሄድ አጫጆቹን እየተከተሉ ከኋላ የወዳደቀውንና ከማሳው ዳርና ዳር የበቀለውን እንዲቃርሙ ይፈቀድላቸው ነበር። *ዘሌ. 19:9, 10፤ ዘዳ. 24:19-21

24, 25. ሩት በአጋጣሚ ወደ ቦዔዝ እርሻ በሄደች ጊዜ ምን አደረገች? የመቃረሙ ሥራስ ምን ይመስል ነበር?

24 ጊዜው ገብስ የሚታጨድበት ወቅት ሲሆን በዘመናችን የቀን አቆጣጠር መሠረት ወሩ ሚያዝያ ሳይሆን አይቀርም፤ ሩት በሕጉ ውስጥ በሰፈረው ዝግጅት መሠረት በማሳው ላይ እንድትቃርም የሚፈቅድላት ሰው ለማግኘት ወደ እርሻ ቦታዎች ሄደች። እንዳጋጣሚ ሆኖ የሄደችበት እርሻ ባለቤት ቦዔዝ የተባለ ሀብታም ባለርስት ሲሆን እሱም የኑኃሚን ባል የሆነው የሟቹ የአቤሜሌክ ዘመድ ነበር። ምንም እንኳ ሩት በሕጉ መሠረት የመቃረም መብት ቢኖራትም ፈቃድ ሳትጠይቅ ሥራዋን አልጀመረችም፤ ከዚህ ይልቅ ወደ አጫጆቹ አለቃ ቀርባ መቃረም ትችል እንደሆነ ጠየቀችው። እሱም እንድትቃርም ፈቀደላት፤ በመሆኑም ሩት ወዲያውኑ ሥራዋን ጀመረች።—ሩት 1:22 እስከ 2:3, 7

25 ሩት አጫጆቹን እየተከተለች ስትቃርም በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አጫጆቹ ገብሱን ከባልጩት በተሠራ ማጭዳቸው ሲያጭዱ የወዳደቀውን ወይም ትተውት የሄዱትን እየለቀመች በየነዶው ካሰረች በኋላ እህሉን ወደምትወቃበት ቦታ እየወሰደች ታስቀምጣለች። ሥራው ጊዜ የሚወስድና አድካሚ ከመሆኑም ሌላ ፀሐዩ እየበረታ ሲሄድ ደግሞ የባሰውን እየከበደ ይሄዳል። ያም ቢሆን ሩት መቃረሟን አላቋረጠችም፤ እንዲያውም አልፎ አልፎ ላቧን ከግንባሯ ላይ ለመጥረግ ቆም ከማለቷና ለሠራተኞቹ ታስቦ በተዘጋጀው “መጠለያ” ውስጥ ምሳዋን ለመብላት ጥቂት ከማረፏ ውጭ ያለ ፋታ ትሠራ ነበር።

ሩት ራሷንም ሆነ ኑኃሚንን ለማስተዳደር ስትል አድካሚና የሚናቅ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ነበረች

26, 27. ቦዔዝ ምን ዓይነት ሰው ነበር? ለሩትስ ምን አደረገላት?

26 ሩት የሌሎች ዓይን ውስጥ እገባለሁ ብላ አላሰበች ይሆናል፤ ሆኖም ያስተዋላት ሰው ነበር። ቦዔዝ፣ ሩትን ሲያያት የአጫጆቹን አለቃ ስለ እሷ ጠየቀው። አስደናቂ የእምነት ሰው የሆነው ቦዔዝ፣ ለሠራተኞቹ ሰላምታ ያቀረበላቸው ‘ይሖዋ ከእናንተ ጋር ይሁን’ በማለት ነበር፤ ከአጫጆቹ መካከል አንዳንዶቹ የቀን ሠራተኞች ወይም የባዕድ አገር ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። እነሱም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ሰላም አሉት። መንፈሳዊ አመለካከት ያለው ይህ በዕድሜ ጠና ያለ ሰው ሩትን እንደ ልጁ አድርጎ በመመልከት አነጋገራት።—ሩት 2:4-7

27 ቦዔዝ ሩትን “ልጄ ሆይ” ብሎ የጠራት ሲሆን ወደ እርሻው እየመጣች እንድትቃርም ሐሳብ አቀረበላት እንዲሁም ወንዶቹ አጫጆች እንዳይተናኮሏት የቤተሰቡ አባላት ከሆኑ ወጣት ሴቶች ጋር እንድትሆን መከራት። በምሳ ሰዓትም የምትበላው ምግብ ሰጣት። (ሩት 2:8, 9, 14ን አንብብ።) ከሁሉ በላይ ደግሞ ላደረገችው ነገር አመሰገናት እንዲሁም አበረታታት። ይህን ያደረገው እንዴት ነው?

28, 29. (ሀ) ሩት ምን ዓይነት ስም አትርፋ ነበር? (ለ) አንተስ ልክ እንደ ሩት በይሖዋ ክንፍ ሥር መጠለል የምትችለው እንዴት ነው?

28 ሩት የባዕድ አገር ሰው ሆና ሳለ ለእሷ ይህን ያህል ደግነትና ሞገስ ለማሳየት ያነሳሳው ምን እንደሆነ ቦዔዝን ስትጠይቀው ለአማቷ ለኑኃሚን ያደረገችውን ነገር በሙሉ እንደሰማ ገለጸላት። ኑኃሚን፣ በቤተልሔም ላሉት ሴቶች የምትወዳት ሩት ስላላት መልካም ባሕርይ ሳትነግራቸው አትቀርም፤ ይህም ቦዔዝ ጆሮ ደርሷል። በተጨማሪም ቦዔዝ “ስላደረግሽው ሁሉ እግዚአብሔር ዋጋሽን ይክፈልሽ፤ በክንፉ ጥላ ሥር ለመጠለል የመጣሽበት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ብድራትሽን አትረፍርፎ ይመልስልሽ” በማለት መናገሩ ሩት ጣዖት ማምለኳን ትታ ይሖዋን ማምለክ መጀመሯን እንደሚያውቅ ያሳያል።—ሩት 2:12

29 እነዚህ ቃላት ሩትን ምንኛ አበረታተዋት ይሆን! በእርግጥም አንዲት የወፍ ጫጩት ከአደጋ በምትጠብቃት ወላጇ ክንፍ ሥር ያለ ስጋት እንደምትቀመጥ ሁሉ ሩትም በይሖዋ አምላክ ክንፎች ሥር ለመጠለል ወስና ነበር። ሩት በሚያጽናና መንገድ ስላናገራት ቦዔዝን አመሰገነችው። ከዚያም እስኪመሽ ድረስ ስትሠራ ቆየች።—ሩት 2:13, 17

30, 31. የሥራ ልማድን፣ አመስጋኝነትንና ጽኑ ፍቅርን በተመለከተ ከሩት ምን ልንማር እንችላለን?

30 ሩት ያሳየችው በተግባር የተደገፈ እምነት በዛሬው ጊዜ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር ለምንታገል ሁሉ ግሩም ምሳሌ ነው። ሩት ሌሎች ድጋፍ ሊያደርጉልኝ ይገባል የሚል ስሜት አልነበራትም፤ በዚህም ምክንያት ለተደረገላት ነገር ሁሉ አመስጋኝ ነበረች። ሩት ትሠራው የነበረው ሥራ የሚናቅ ቢሆንም የምትወዳትን አማቷን ለመንከባከብ ስትል ስትለፋ መዋሏ አላሳፈራትም። ለደህንነቷ በማያሰጋት ሁኔታ ጥሩ ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጋር ሆና መሥራት ስለምትችልበት መንገድ የተሰጣትን ጥበብ ያዘለ ምክር በአመስጋኝነት ተቀብላ ሥራ ላይ አውላለች። ከሁሉ በላይ ደግሞ አስተማማኝ መጠጊያ የሚሆናት ከክፉ ነገሮች ሊጠብቃት የሚችለው አባቷ ይሖዋ አምላክ መሆኑን ፈጽሞ አልዘነጋችም።

31 እኛም እንደ ሩት ጽኑ ፍቅር የምናሳይ እንዲሁም ትሑት፣ ታታሪና አመስጋኝ በመሆን ረገድ ምሳሌነቷን የምንከተል ከሆነ በእምነታችን ለሌሎች ግሩም አርዓያ እንሆናለን። ይሁንና ይሖዋ ለሩትና ለኑኃሚን የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያሟላላቸው እንዴት ነበር? የዚህ ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ ይብራራል።

^ አን.17 እስራኤላውያን ያልሆኑ አብዛኞቹ ሰዎች እንደሚያደርጉት ሩት “አምላክ” የሚለውን የማዕረግ ስም ብቻ አለመጠቀሟ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ይሖዋ የሚለውን የአምላክን የግል ስም ተጠቅማለች። ዚ ኢንተርፕሪተርስ ባይብል እንደሚከተለው የሚል አስተያየት ሰጥቷል፦ “ጸሐፊው በዚህ መንገድ ይህች የባዕድ አገር ሴት እውነተኛውን አምላክ የምታመልክ መሆኗን ጎላ አድርጎ ገልጿል።”

^ አን.23 በዚህ ሕግ ውስጥ የተካተተው አስደናቂ ዝግጅት ሩት በትውልድ አገሯ ከምታውቀው ፈጽሞ የተለየ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። በዚያ ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ መበለቶች በደል ይደርስባቸው ነበር። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “አንዲት ሴት ባሏ ከሞተ በኋላ በአብዛኛው ደጋፊና ጧሪ የሚሆኗት ወንዶች ልጆቿ ነበሩ፤ ወንዶች ልጆች ከሌሏት ግን ያላት አማራጭ ራሷን ለባርነት መሸጥ፣ ዝሙት አዳሪ መሆን አለዚያም መሞት ነበር።”