በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ ሃያ

“አምናለሁ”

“አምናለሁ”

1. ማርታ የደረሰባትን ሐዘንና ያሳደረባትን ስሜት ግለጽ።

ማርታ ወንድሟ የተቀበረበት ዋሻ በአንድ ትልቅ ድንጋይ ተከርችሞ በዓይነ ሕሊናዋ እየታያት ሳይሆን አይቀርም። ሐዘኗ የድንጋዩን ያህል ከብዷታል። የምትወደውን ወንድሟን ሞት መቀበል በጣም ተቸግራለች። ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ባሉት አራት ቀናት ውስጥ ስለነበረው ሐዘንና ሊያስተዛዝኗቸው ስለመጡት እንግዶች ስታስብ ሕልም ውስጥ እንዳለች ሆኖ ይሰማታል።

2, 3. (ሀ) ማርታ ከኢየሱስ ጋር መገናኘቷ ምን ስሜት አሳደረባት? (ለ) ማርታ የተናገረችው ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ሐሳብ ስለ እሷ ምን ይጠቁማል?

2 የአልዓዛር የቅርብ ወዳጅ የሆነው ሰው ማርታ አጠገብ ቆሟል። ማርታ ኢየሱስን ስታየው ሐዘኗ እንደ አዲስ ሳይቀሰቀስባት አይቀርም፤ ምክንያቱም በምድር ላይ ወንድሟን ከሞት መታደግ ይችል የነበረው ብቸኛ ሰው እሱ እንደሆነ ታውቃለች። ያም ሆኖ በኮረብታ ላይ ከተቆረቆረችው ቢታንያ ከምትባለው ትንሽ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ ከኢየሱስ ጋር አብራ በመሆኗ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተጽናንታለች። ከእሱ ጋር በቆየችባቸው ጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ፊቱ ላይ የሚነበበውን ደግነትና አዘኔታ ስትመለከት እፎይታ የተሰማት ከመሆኑም ሌላ ብርታት አግኝታለች። ኢየሱስ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ባላት እምነትና አመለካከት ላይ እንድታተኩር የሚረዷትን ጥያቄዎች ጠየቃት። ያደረጉት ውይይት ማርታ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠውን የሚከተለውን ሐሳብ እንድትናገር አነሳስቷታል፦ “አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆንህን አምናለሁ።”—ዮሐ. 11:27

3 ይህ አነጋገሯ እንደሚያሳየው ማርታ አስደናቂ እምነት ያላት ሴት ነበረች። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሷ የሚናገረው ጥቂት ነገር ቢሆንም እምነታችንን እንድናጠናክር ሊረዳን የሚችል ትልቅ ትምህርት ይዟል። እንዲህ ያልንበትን ምክንያት ለመረዳት ስለ ማርታ የሚናገረውን የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንመልከት።

“ትጨነቂያለሽ፣ ትጠበቢያለሽ”

4. ማርታ የምትኖረው ከእነማን ጋር ነበር? ቤተሰቡስ ከኢየሱስ ጋር ምን ዓይነት ቅርበት ነበረው?

4 ጊዜው አልዓዛር ከመሞቱ ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ነው። በወቅቱ አልዓዛር ጤነኛ የነበረ ሲሆን በቢታኒያ በሚገኘው ቤቱ አንድ ትልቅ እንግዳ ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስን ሊያስተናግድ ነው። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው አልዓዛር፣ ማርታና ማርያም አንድ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበረ ይመስላል። ማርታ ታስተናግድ የነበረበት መንገድ ጋባዧ እሷ እንደሆነች የሚያስመስል መሆኑና ስሟ ከሌሎቹ ቀድሞ የተጠቀሰባቸው ጊዜያት መኖራቸው አንዳንድ ተመራማሪዎች የሁሉም ታላቅ እሷ ሳትሆን አትቀርም የሚል ግምት እንዲያድርባቸው አድርጓል። (ዮሐ. 11:5) ከሦስቱ መካከል አግብቶ የነበረ ይኑር አይኑር የሚታወቅ ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ ሦስቱም የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች ነበሩ። ኢየሱስ ሕዝቡ እየተቃወመውና እየጠላው በይሁዳ ያገለግል በነበረበት ወቅት የእነማርታ ቤት ጥሩ ማረፊያ ሆኖለት ነበር። ኢየሱስ እዚያ ቤት ሲያርፍ ለሚያገኘው ሰላምና ለሚደረግለት እንክብካቤ ከፍተኛ አድናቆት እንደነበረው ምንም ጥርጥር የለውም።

5, 6. (ሀ) ማርታ፣ ኢየሱስ ሊጎበኛቸው በመጣበት በዚህ ወቅት ከሌሎች ይልቅ በሥራ ተጠምዳ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ማርያም፣ ኢየሱስ ቤታቸው የመጣበትን ይህን አጋጣሚ ምን ለማድረግ ተጠቀመችበት?

5 ማርታ ለእንግዶቹ የሚያስፈልገውን ነገር ለማሰናዳት ብዙ ሥራ ይጠብቃታል። ማርታ ሁልጊዜ ሥራ የሚበዛባትና ጉድጉድ ማለት የምትወድ ታታሪ ሴት ነች። ኢየሱስ ሊጎበኛቸው በመጣበት በዚህ ወቅትም እንደልማዷ ሽር ጉድ ማለት ጀምራለች። ማርታ ለዚህ የተከበረ እንግዳዋና ምናልባትም አብረውት ላሉት የጉዞ ጓደኞቹ የተለያዩ ምግቦችን በመሥራት ለየት ያለ ግብዣ ማዘጋጀት አስባለች። በዚያ ዘመን እንግዳ ተቀብሎ ማስተናገድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። ሰዎች አንድ እንግዳ ቤታቸው ሲመጣ ስመው ይቀበሉታል፤ ከዚያም ጫማውን አውልቀው እግሩን የሚያጥቡት ሲሆን ራሱንም ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት ይቀቡታል። (ሉቃስ 7:44-47ን አንብብ።) እንዲሁም ምቹ ማረፊያና ጣፋጭ ምግብ ያዘጋጁለታል።

6 በመሆኑም ማርታና ማርያም እንግዳቸውን ለመቀበል በተለያዩ ሥራዎች ተጠምደው ነበር። አንዳንዶች ከማርታ ይልቅ አስተዋይና ቁም ነገረኛ እንደሆነች አድርገው የሚያስቧት ማርያም መጀመሪያ ላይ እህቷን በሥራ ስታግዛት እንደቆየች ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ሲመጣ ግን ሁኔታው ተለወጠ። ኢየሱስ ይህ አጋጣሚ ሌሎችን ለማስተማር አመቺ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር፤ ደግሞም ያደረገው ይህንኑ ነው! በዘመኑ ከነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በተለየ መልኩ ኢየሱስ ሴቶችን ያከብር የነበረ ከመሆኑም ሌላ የስብከቱ ጭብጥ ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት በደስታ ያስተምራቸው ነበር። ማርያም ይህንን አጋጣሚ ለመጠቀም በጣም ስለጓጓች በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጣ እያንዳንዱን ቃል በጥሞና ታዳምጥ ጀመር።

7, 8. ማርታ ውጥረት የበዛባት ለምንድን ነው? በመጨረሻስ ብሶቷን የገለጸችው እንዴት ነው?

7 በዚህ ጊዜ ማርታ ምን ያህል ውጥረት እንደሚበዛባት መገመት አያዳግትም። ማርታ ያን ሁሉ ምግብ አዘጋጅታ ለማቅረብና እንግዶቿን ለማስተናገድ ወዲያ ወዲህ መዋከቧ ይበልጥ እንድትጨነቅና እንድትጠበብ አድርጓታል። አንዳንድ ነገሮችን ለማሰናዳት ስታልፍ ስታገድም እህቷ እሷን ከማገዝ ይልቅ ቁጭ ብላ ስታያት በሁኔታው በመበሳጨት በረጅሙ ተንፍሳ ወይም ፊቷ ተለዋውጦ አሊያም ተኮሳትራባት ይሆን? እንዲህ ብታደርግ አይፈረድባትም። ያንን ሁሉ ሥራ ብቻዋን ልትሠራው አትችልም!

8 አሁን ግን ማርታ ብስጭቷን አምቃ መያዝ አልቻለችም። እናም የኢየሱስን ንግግር በማቋረጥ “ጌታ ሆይ፣ እህቴ ሥራውን ሁሉ ለእኔ ጥላ ስትቀመጥ ምንም ግድ አይሰጥህም? እንድታግዘኝ ንገራት እንጂ” በማለት ብሶቷን ተናገረች። (ሉቃስ 10:40) ይህ ኃይለኛ ንግግር ነው። ኢየሱስ ማርያምን ተቆጥቶ ወደ ሥራዋ እንድትመለስ እንዲያዛት እየጠየቀች ነበር።

9, 10. (ሀ) ኢየሱስ ለማርታ ምን ምላሽ ሰጣት? (ለ) ኢየሱስ የተናገረው ነገር የማርታን ልፋት ከምንም እንዳልቆጠረው የሚያሳይ አለመሆኑን እንዴት እናውቃለን?

9 መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡ ብዙ ሰዎች እንደሚሰማቸው ሁሉ ማርታም የኢየሱስ ምላሽ አስገርሟት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ረጋ ባለ መንፈስ እንዲህ አላት፦ “ማርታ፣ ማርታ፣ ስለ ብዙ ነገር ትጨነቂያለሽ፣ ትጠበቢያለሽ። ይሁንና የሚያስፈልገው ጥቂት ወይም አንድ ነገር ብቻ ነው። ማርያም በበኩሏ የተሻለውን ነገር መርጣለች፤ ይህም ከእሷ አይወሰድባትም።” (ሉቃስ 10:41, 42) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ማርታ ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ እንደምትጨነቅ መናገሩ ነበር? ጥሩ ምግብ ለማዘጋጀት መልፋቷን ከምንም አልቆጠረውም ማለት ነው?

ማርታ ‘ስለ ብዙ ነገር ትጨነቅና ትጠበብ’ የነበረ ቢሆንም የተሰጣትን እርማት በትሕትና ተቀብላለች

10 በፍጹም! ኢየሱስ ማርታ ይህን ያደረገችው በፍቅርና በንጹሕ ልብ ተነሳስታ መሆኑን እንደተገነዘበ ግልጽ ነው። በተጨማሪም አንድን እንግዳ ለመቀበል ድል ያለ ድግስ ማዘጋጀት ስህተት እንደሆነ መናገሩ አልነበረም። በዚህ ግብዣ ላይ ከመገኘቱ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ማቴዎስ ባዘጋጀለት “ትልቅ ግብዣ” ላይ በደስታ ተገኝቶ ነበር። (ሉቃስ 5:29) እዚህ ላይ ሊተኮርበት የተፈለገው ጉዳይ ማርታ ያዘጋጀችው ግብዣ ሳይሆን ቅድሚያ የሰጠችው ለምን ነገር ነው የሚለው ነው። ትኩረቷ ሁሉ ያረፈው ሰፊ ግብዣ ማዘጋጀቷ ላይ ስለነበር ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ሳታስተውል ቀረች። ይህ ምን ነበር?

ኢየሱስ የማርታን መስተንግዶ በአድናቆት የተቀበለ ሲሆን ይህንም ያደረገችው በፍቅርና በንጹሕ ልብ ተነሳስታ መሆኑን ተገንዝቧል

11, 12. ኢየሱስ ለማርታ በደግነት እርማት የሰጣት እንዴት ነው?

11 የይሖዋ አምላክ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ እነማርታ ቤት የተገኘው ስለ እውነት ለማስተማር ነው። ማርታ ያዘጋጀችው ጣት የሚያስቆረጥም ምግብም ሆነ እሱን ለመቀበል ያደረገቻቸው ሌሎች መሰናዶዎች ከዚህ ሊበልጡባት አይገባም ነበር። ኢየሱስ፣ ማርታ እምነቷን ለማጠናከር የሚያስችላት ይህ ልዩ አጋጣሚ እያመለጣት እንደሆነ ሲያይ አዝኖ እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም፤ ያም ሆኖ ሊጫናት አልፈለገም። * እርግጥ ማርታ የራሷን ምርጫ ማድረግ መብቷ ቢሆንም ኢየሱስ ትምህርቱን ማዳመጥ ትታ እሷን እንድታግዛት ማርያምን እንዲያዛት መጠየቋ ግን ተገቢ አልነበረም።

12 ስለዚህ ኢየሱስ የማርታን ብስጭት ለማብረድ ስሟን ደጋግሞ ከጠራ በኋላ በደግነት እርማት የሰጣት ሲሆን ‘ስለ ብዙ ነገሮች መጨነቅና መጠበብ’ አስፈላጊ እንዳልሆነ ገለጸላት። በተለይ መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብ የሚያስችል አጋጣሚ በሚኖርበት ጊዜ አንድ ወይም ሁለት ዓይነት ሰብዓዊ ምግብ ማዘጋጀት ብቻ በቂ ይሆናል። ስለሆነም ኢየሱስ ማርያም ያደረገችውን ‘የተሻለ ምርጫ’ ማለትም ከእሱ የመማር መብቷን በምንም ዓይነት ሊወስድባት አይችልም!

13. ኢየሱስ ለማርታ እርማት ከሰጠበት መንገድ ምን ልንማር እንችላለን?

13 በማርታ ቤት ውስጥ ስለተከናወነው ሁኔታ የሚገልጸው ይህ አጭር ዘገባ በዛሬው ጊዜ ላሉ የክርስቶስ ተከታዮች ብዙ ትምህርት ይዟል። እኛም “መንፈሳዊ” ፍላጎታችንን ለማሟላት ጥረት ከማድረግ ምንም ነገር እንዲያግደን መፍቀድ አይኖርብንም። (ማቴ. 5:3) ማርታ የተወችውን የልግስናና የታታሪነት ምሳሌ መከተል የምንፈልግ ቢሆንም ይበልጥ ወሳኝ የሆኑ ነገሮች እስኪያመልጡን ድረስ እንግዳ ከመቀበል ጋር ለተያያዙ ያን ያህል አስፈላጊ ላልሆኑ ነገሮች ‘መጨነቅና መጠበብ’ አንፈልግም። ከእምነት አጋሮቻችን ጋር የምንገባበዝበት ዋነኛው ምክንያት ለመብላትና ለመጠጣት ሳይሆን እርስ በርስ ለመበረታታትና መንፈሳዊ ስጦታዎችን ለመለዋወጥ ነው። (ሮም 1:11, 12ን አንብብ።) እንዲህ የመሰለ የሚያንጽ ጊዜ ለማሳለፍ ቀለል ያለ ግብዣ ማድረጉ ብቻ እንኳ ሊበቃ ይችላል።

በጣም የምትወደው ወንድሟ ሞቶ ተነሳ

14. ማርታ እርማት በመቀበል ረገድ ግሩም ምሳሌ የምትሆነን እንዴት ነው?

14 ታዲያ ማርታ ኢየሱስ በደግነት የሰጣትን ተግሣጽ ተቀብላ በተግባር አውላ ይሆን? መልሱን ለማግኘት ብዙ ማሰብ አያስፈልገንም። ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ማርታ ወንድም የሚገልጸውን አስደናቂ ዘገባ ሲጀምር “ኢየሱስ ማርታንና እህቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር” በማለት ጽፏል። (ዮሐ. 11:5) ኢየሱስ ቢታንያ በሚገኘው በእነማርታ ቤት ከተጋበዘ ወራት አልፈዋል። በመሆኑም ማርታ፣ ኢየሱስ ፍቅራዊ ምክር ስለሰጣት እንዳላኮረፈችውም ሆነ እንዳልተቀየመችው በግልጽ ማየት ይቻላል። ከዚህ ይልቅ ምክሩን ከልብ ተቀብላለች። በዚህ ረገድም ቢሆን ለእኛ ግሩም የእምነት ምሳሌ ትሆነናለች፤ ደግሞስ ከመካከላችን አልፎ አልፎ እርማት የማያስፈልገው ማን አለ?

15, 16. (ሀ) ማርታ ወንድሟ በታመመ ጊዜ ምን አድርጋ ሊሆን ይችላል? (ለ) ማርታና ማርያም የነበራቸው ተስፋ መና የቀረው ለምንድን ነው?

15 ማርታ ወንድሟ በታመመ ጊዜ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትል አስታምማዋለች። ሥቃዩን ለማስታገስና ከሕመሙ እንዲያገግም ለመርዳት የምትችለውን ሁሉ አድርጋለች። አልዓዛር ግን ሕመሙ እየጠናበት ሄደ። ማርታና ማርያም ቀን ከሌት ከጎኑ ሳይለዩ ይንከባከቡት ነበር። ማርታ ድካም የሚነበብበትን የወንድሟን ፊት ባየች ቁጥር በደስታም ሆነ በሐዘን ወቅት አብረው ያሳለፏቸው በርካታ ዓመታት ፊቷ ላይ ድቅን ይሉባት እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።

16 ማርታና ማርያም ሁኔታው ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ሲረዱ ወደ ኢየሱስ መልእክት ላኩ። በወቅቱ ኢየሱስ እነሱ ካሉበት የሁለት ቀን መንገድ ገደማ ርቆ በሚገኝ ቦታ እየሰበከ ነበር። የላኩበት አጭር መልእክት “ጌታ ሆይ፣ የምትወደው ሰው ታሟል” የሚል ነበር። (ዮሐ. 11:1, 3) ኢየሱስ ወንድማቸውን እንደሚወደው ያውቁ ነበር፤ በመሆኑም ወዳጁን ለመርዳት የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ እምነት ነበራቸው። ኢየሱስ፣ አልዓዛር ከመሞቱ በፊት ይደርሳል ብለው ተስፋ አድርገው ይሆን? ከሆነ ተስፋቸው መና ቀርቷል ማለት ነው። ምክንያቱም አልዓዛር ሞተ።

17. ማርታ ግራ የተጋባችው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ወደ ከተማዋ እየቀረበ መሆኑን ስትሰማ ምን አደረገች?

17 ማርታና ማርያም ወንድማቸውን አልቅሰው ቀበሩት፤ በቢታንያና በዙሪያዋ የሚኖሩ በርካታ ሰዎችም እነሱን ለማስተዛዘን መጡ። ኢየሱስ ግን ወሬው የለም። ቀናት እየተቆጠሩ ሲሄዱ ማርታ ይበልጥ ግራ ሳትጋባ አትቀርም። በመጨረሻም አልዓዛር በሞተ በአራተኛው ቀን ኢየሱስ ወደ ከተማዋ እየቀረበ መሆኑን ሰማች። ምንጊዜም ፈጣን እርምጃ በመውሰድ የምትታወቀው ማርታ ሐዘን ላይ በነበረችበት በዚህ ወቅትም እንኳ የኢየሱስን መምጣት ስትሰማ ለማርያም ምንም ሳትነግራት እየተጣደፈች እሱን ለማግኘት ተነስታ ወጣች።—ዮሐንስ 11:18-20ን አንብብ።

18, 19. ማርታ ምን ተስፋ እንዳላት ገለጸች? አስደናቂ እምነት ነበራት የምንለውስ ለምንድን ነው?

18 ማርታ ጌታዋን ገና ስታየው “ጌታ ሆይ፣ አንተ እዚህ ኖረህ ቢሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር” በማለት እሷንም ሆነ ማርያምን ሲከነክናቸው የቆየውን ነገር ተናገረች። ያም ሆኖ ማርታ የነበራት ተስፋና እምነት አሁንም ቢሆን አልጠፋም። አክላም “አሁንም አምላክ የጠየቅከውን ነገር ሁሉ እንደሚሰጥህ አውቃለሁ” አለችው። ኢየሱስም ተስፋዋን ለማጠናከር “ወንድምሽ ይነሳል” አላት።—ዮሐ. 11:21-23

19 ማርታ ኢየሱስ የተናገረው ወደፊት ስለሚፈጸመው ትንሣኤ ስለመሰላት “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሳ አውቃለሁ” አለችው። (ዮሐ. 11:24) በትንሣኤ ተስፋ ላይ ያላት እምነት አስደናቂ ነው። ምንም እንኳ ትንሣኤ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በግልጽ የሰፈረ ትምህርት ቢሆንም ሰዱቃውያን ተብለው የሚጠሩ አንዳንድ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ትንሣኤ መኖሩን ይክዱ ነበር። (ዳን. 12:13፤ ማር. 12:18) ይሁን እንጂ ማርታ፣ ኢየሱስ ስለ ትንሣኤ ተስፋ እንዳስተማረ አልፎ ተርፎም የአልዓዛርን ያህል ሞተው የቆዩ ባይሆኑም እንኳ ሙታንን እንዳስነሳ ታውቃለች። ቀጥሎ ምን ሊከናወን እንደሆነ ግን የምታውቀው ነገር አልነበረም።

20. በ⁠ዮሐንስ 11:25-27 ላይ ሰፍሮ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ትልቅ ቁም ነገር ያዘለ ሐሳብና ማርታ የሰጠችው መልስ ምን ትርጉም እንዳላቸው አብራራ።

20 ከዚያም ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” በማለት ትልቅ ትርጉም ያዘለ ሐሳብ ተናገረ። በእርግጥም ይሖዋ አምላክ፣ ወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሙታንን እንዲያስነሳ ለልጁ ሥልጣን ሰጥቶታል። ኢየሱስ ማርታን “ይህን ታምኛለሽ?” ሲል ጠየቃት። እሷም በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የሰፈረውን መልስ ሰጠችው። ኢየሱስ መሲሕ ወይም ክርስቶስ እንደሆነ እንዲሁም የይሖዋ አምላክ ልጅና ነቢያት ወደ ዓለም እንደሚመጣ ትንቢት የተናገሩለት አካል እንደሆነ እምነት ነበራት።—ዮሐ. 5:28, 29፤ ዮሐንስ 11:25-27ን አንብብ።

21, 22. (ሀ) ኢየሱስ አዝነው ለነበሩት ሰዎች ስሜቱን የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) የአልዓዛር ትንሣኤ ምን ይመስል እንደነበር ግለጽ።

21 ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ዓይነት እምነት ሲመለከቱ ምን ይሰማቸዋል? ማርታ ቀጥሎ ሲከናወኑ የተመለከተቻቸው ነገሮች ለዚህ ጥያቄ የማያሻማ መልስ ይሰጣሉ። ማርታ እህቷን ለመጥራት በፍጥነት ሄደች። ከዚያም ኢየሱስ ከማርያምና አብረዋት ካሉት ሐዘንተኞች ጋር ሲነጋገር ስሜቱ ምን ያህል በጥልቅ እንደተነካ አስተዋለች። ያለ ምንም ይሉኝታ እንባውን በማፍሰስ ሞት የሚያስከትለው መሪር ሐዘን ምን ያህል እንደተሰማው ሲገልጽ ተመለከተች። ከዚያም ኢየሱስ ከወንድሟ መቃብር ላይ ድንጋዩን አንከባለው እንዲያነሱ ትእዛዝ ሲሰጥ ሰማች።—ዮሐ. 11:28-39

22 ምንጊዜም ምክንያታዊ የሆነችው ማርታ ወንድሟ ከሞተ አራት ቀን ስለሆነው አስከሬኑ እንደሚሸት በመግለጽ ተቃውሞዋን አሰማች። ኢየሱስም “ካመንሽ የአምላክን ክብር ታያለሽ ብዬ አልነገርኩሽም?” አላት። እሷም በማመኗ የይሖዋ አምላክን ክብር ለማየት በቃች። እዚያው እንደቆሙ ይሖዋ አልዓዛርን ከሞት እንዲያስነሳው ለልጁ ኃይል ሰጠው! በማርታ አእምሮ ውስጥ ፈጽሞ የማይረሳ ትዝታ ጥለው ያለፉትን የሚከተሉትን ነገሮች ለማሰብ ሞክር፦ ኢየሱስ “አልዓዛር፣ ና ውጣ!” በማለት ተጣራ፤ ከዚያም ከዋሻው ውስጥ ድምፅ የተሰማ ሲሆን አልዓዛር ከሞት ተነስቶ ከነመግነዙ ቀስ ብሎ እየተራመደ ከዋሻው ወጣ፤ ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ” ብሎ ትእዛዝ ሰጠ፤ በዚህ ጊዜ እሷና ማርያም በታላቅ ደስታ ተውጠው ወንድማቸው አንገት ላይ እንደተጠመጠሙ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዮሐንስ 11:40-44ን አንብብ።) አሁን ማርታ እንደ ድንጋይ ከብዷት ከነበረው ሐዘኗ ተገላገለች!

ማርታና ማርያም ወንድማቸው ከሞት ሲነሳ መመልከታቸው ማርታ በኢየሱስ ላይ እምነት በማሳደሯ እንደተካሰች ያሳያል

23. ይሖዋና ኢየሱስ ምን ሊያደርጉልህ ፈቃደኞች ናቸው? አንተስ ምን ማድረግ ይጠበቅብሃል?

23 ይህ ዘገባ እንደሚያሳየው የሙታን ትንሣኤ የሕልም እንጀራ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ልብን በደስታ የሚሞላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከመሆኑም ሌላ ከዚህ በፊት ተፈጽሞ የሚያውቅ ታሪካዊ ሐቅ ነው። (ኢዮብ 14:14, 15) ይሖዋና ልጁ ለማርታ፣ ለማርያምና ለአልዓዛር እንዳደረጉት ሁሉ ሰዎች ለሚያሳዩት እምነት ወሮታ መክፈል ያስደስታቸዋል። አንተም ጠንካራ እምነት ከገነባህ ወደፊት እንዲህ ያለ ወሮታ ይጠብቅሃል።

“ማርታ ታገለግላቸው” ነበር

24. ማርታ ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀሰችበት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የትኛው ነው?

24 የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ከዚህ በኋላ ስለ ማርታ የሚጠቅሰው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ወቅቱ ኢየሱስ በምድር ላይ ያሳለፈው የመጨረሻው ሳምንት መባቻ ነው። ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀውን መከራ ጠንቅቆ ስለሚያውቅ አሁንም በቢታንያ ወደሚገኘው ወደ እነማርታ ቤት ሄዶ በዚያ ትንሽ ለማረፍ አሰበ። ከዚያ በመነሳት ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደምትገኘው ወደ ኢየሩሳሌም በእግሩ መጓዝ ይችላል። ኢየሱስና አልዓዛር በሥጋ ደዌ በተያዘው በስምዖን ቤት ራት እየበሉ ነው፤ ማርታ ለመጨረሻ ጊዜ የተጠቀሰችው በዚህ ወቅት ሲሆን ዘገባው ‘ታገለግላቸው ነበር’ በማለት ስለ እሷ ጠቀስ አድርጎ ያልፋል።—ዮሐ. 12:2

25. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ጉባኤዎች እንደ ማርታ ያሉ እህቶችን በማግኘታቸው ተባርከዋል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

25 በእርግጥም ማርታ ታታሪ ሴት ነበረች! መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከማርታ ጋር የሚያስተዋውቀን በሥራ ተጠምዳ የነበረበትን አጋጣሚ በመጥቀስ ሲሆን ስለ እሷ የሚናገረው የመጨረሻ ዘገባም አብረዋት ያሉትን ለማስተናገድ የተቻላትን ያህል ጥረት ታደርግ እንደነበር ይገልጻል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የክርስቶስ ተከታዮች በጉባኤዎቻቸው ውስጥ እንደ ማርታ ያሉ ማለትም ራሳቸውን በማቅረብ ምንጊዜም እምነታቸውን በተግባር የሚያሳዩ መንፈሰ ጠንካራና ለጋስ እህቶች በመኖራቸው ተባርከዋል። ማርታ በዚህ ባሕርይዋ እስከ መጨረሻው ቀጥላ ይሆን? እንደዚያ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ይህ ደግሞ ወደፊት በሕይወቷ ውስጥ የሚያጋጥሟትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በጽናት እንድትወጣ ይረዳታል።

26. ማርታ የነበራት እምነት ምን እንድታደርግ ረድቷታል?

26 ከጥቂት ቀናት በኋላ ማርታ የምትወደው ጌታዋ ኢየሱስ በአሰቃቂ መንገድ ሲገደል የሚሰማትን ሐዘን በጽናት መቋቋም ነበረባት። ይህ ብቻ ሳይሆን በኋላ ላይ ኢየሱስን ያስገደሉት ግብዝ የሆኑት ነፍሰ ገዳዮች አልዓዛርንም ለመግደል ቆርጠው ተነስተው ነበር፤ ምክንያቱም የእሱ ከሞት መነሳት ብዙዎች በኢየሱስ እንዲያምኑ አድርጓል። (ዮሐንስ 12:9-11ን አንብብ።) ደግሞም ይዋል ይደር እንጂ በጣም የሚዋደደው የማርታ ቤተሰብ በሞት መለያየቱ አይቀርም። ሞት የእነማርታን ቤት ዳግመኛ ያንኳኳው እንዴትና መቼ እንደሆነ ባናውቅም ማርታ የነበራት ትልቅ እምነት እስከ መጨረሻው እንድትጸና ረድቷታል ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች ማርታን በእምነቷ መምሰላቸው የተገባ የሆነው ለዚህ ነው።

^ አን.11 በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ በአብዛኛው ሴቶች ትምህርት እንዲማሩ አይፈቀድላቸውም ነበር። ብዙውን ጊዜ የሚሰጣቸው ሥልጠና በቤት ውስጥ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ነበር። በመሆኑም ማርታ አንዲት ሴት አንድ መምህር እግር አጠገብ ተቀምጣ ስትማር ማየቷ እንግዳ ነገር ሆኖባት ሊሆን ይችላል።