በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ አምስት

ለአምላክ ሕዝብ ጥብቅና ቆማለች

ለአምላክ ሕዝብ ጥብቅና ቆማለች

1-3. (ሀ) አስቴር ባሏ ፊት መቅረብ የፈራችው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ከአስቴር ጋር በተያያዘ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

አስቴር በሱሳ ቤተ መንግሥት ወደሚገኘው ውስጠኛ አደባባይ ስትቃረብ ራሷን ለማረጋጋት ሞከረች። ይህን ማድረግ ግን ቀላል አልነበረም። አንድ ሰው ቤተ መንግሥቱ የተገነባበትን መንገድ ሲያይ በአድናቆት መዋጡ አይቀርም፤ በበረዶ በተሸፈኑት የዛግሮስ ተራሮች አጠገብ በጣም ግዙፍ በሆኑ ዐለቶች ላይ በተገነባውና ጥርት ያለ ውኃ ያለውን የቾአስፔስን ወንዝ ቁልቁል ለማየት በሚያስችለው በዚህ ቤተ መንግሥት ግድግዳ ላይ በልዩ ልዩ ቀለማት ያሸበረቁ ክንፍ ያላቸው ኮርማዎች፣ ቀስተኞችና የአንበሳ ምስሎች ተቀርጸው ይታያሉ፤ ከዚህም ሌላ ከድንጋይ የተሠሩ ጌጠኛ ዓምዶችና ግዙፍ የሆኑ ሐውልቶች ይገኛሉ። የሚታየው ነገር ሁሉ ራሱን “ታላቅ ንጉሥ” ብሎ የሚጠራውና አስቴር ልታነጋግረው የመጣችው ሰው ያለውን ታላቅ ኃይል ሁሉም ሰው እንዲገነዘብ ለማድረግ ታቅዶ የተሠራ ይመስላል። ይህ ታላቅ ንጉሥ የአስቴር ባል ነው።

2 አስቴር ይህን ንጉሥ ልታገባ ቻለች? የትኛዋም ታማኝ አይሁዳዊት ወጣት እንደ ጠረክሲስ ያለ ሰው ላገባ እችላለሁ የሚል ሐሳብ ፈጽሞ ወደ አእምሮዋ ሊመጣ አይችልም! * ጠረክሲስ እንደ አብርሃም ያሉ ግለሰቦችን አርዓያ ለመከተል የሚጥር ሰው አልነበረም፤ አብርሃም የሚስቱን የሣራን ቃል እንዲሰማ አምላክ የሰጠውን ትእዛዝ በትሕትና ተቀብሏል። (ዘፍ. 21:12) ይህ ንጉሥ የአስቴር አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋም ሆነ ስለ ሕጎቹ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። ይሁንና ጠረክሲስ፣ አስቴር ልታደርገው ያሰበችውን ነገር የሚከለክለውን ሕግ ጨምሮ የፋርስን ሕግ በሚገባ ያውቃል። ለመሆኑ አስቴር ልታደርግ ያሰበችው ምንድን ነው? ሕጉ የፋርስ ንጉሥ ሳይጠራው ወደ እሱ የገባ ማንኛውም ሰው በሞት እንዲቀጣ ያዛል። አስቴር ባትጠራም ወደ ንጉሡ ልትገባ ነው። አስቴር፣ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው ንጉሥ ሊያያት ወደሚችልበት ወደ ውስጠኛው አደባባይ እየተቃረበች ስትመጣ ወደ ሞት እያመራች እንደሆነ ሳይሰማት አልቀረም።—አስቴር 4:11⁠ን እና 5:1ን አንብብ።

3 አስቴር ሕይወቷን ለአደጋ የሚያጋልጥ እንዲህ ያለ እርምጃ ለመውሰድ የወሰነችው ለምንድን ነው? ይህች ግሩም ባሕርይ ያላት ሴት ካሳየችው እምነት ምን እንማራለን? በቅድሚያ ግን አስቴር የፋርስ ንግሥት ለመሆን የበቃችው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የአስቴር የኋላ ታሪክ

4. የአስቴር የኋላ ታሪክ ምን ይመስላል? ከመርዶክዮስ ጋር መኖር የጀመረችውስ እንዴት ነው?

4 አስቴር የሙት ልጅ ነበረች። ‘ሀደሳ’ የሚል ስም ስላወጡላት ወላጆቿ እምብዛም የምናውቀው ነገር የለም፤ ሀደሳ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ባርሰነት” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ይህ ተክል ማራኪ የሆነ ነጭ አበባ ያወጣል። የአስቴር ወላጆች ሲሞቱ የሥጋ ዘመዷ የሆነ መርዶክዮስ የተባለ አንድ ደግ ሰው አስቴርን ይንከባከባት ጀመር። አስቴር፣ ለመርዶክዮስ የአጎቱ ልጅ ስትሆን መርዶክዮስ በዕድሜ በጣም ይበልጣታል። መርዶክዮስ አስቴርን ወደ ቤቱ ከወሰዳት በኋላ እንደ ገዛ ልጁ አድርጎ አሳደጋት።—አስ. 2:5-7, 15

መርዶክዮስ ባሳደጋት ልጅ እንዲኮራ የሚያደርገው በቂ ምክንያት ነበረው

5, 6. (ሀ) መርዶክዮስ አስቴርን ያሳደጋት እንዴት ነው? (ለ) አስቴርና መርዶክዮስ በሱሳ ምን ዓይነት ሕይወት ይመሩ ነበር?

5 ግዞተኛ አይሁዳውያን የሆኑት መርዶክዮስና አስቴር የሚኖሩት የፋርስ መዲና በሆነችው ከተማ ነበር፤ በዚህች ከተማ ሲኖሩ በሃይማኖታቸውና የሙሴን ሕግ ለመከተል በሚያደርጉት ጥረት የተነሳ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሳይጠሉ አይቀሩም። ይሁንና መርዶክዮስ በተደጋጋሚ ጊዜ ሕዝቡን ከችግር ስላዳነውና ወደፊትም ሕዝቡን ስለሚያድነው ይሖዋ ስለተባለው መሐሪ አምላክ ያስተምራት ስለነበር ከአስቴር ጋር በጣም ይቀራረቡ እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም። (ዘሌ. 26:44, 45) አዎ፣ አስቴርና መርዶክዮስ ከልብ ይዋደዱና ይተማመኑ ነበር።

6 ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው መርዶክዮስ በሱሳ በሚገኘው ቤተ መንግሥት ውስጥ አንድ ዓይነት ኃላፊነት የነበረው ሲሆን ከሌሎቹ የንጉሡ አገልጋዮች ጋር ዘወትር በቤተ መንግሥቱ በር ላይ ይቀመጥ ነበር። (አስ. 2:19, 21፤ 3:3) አስቴር የልጅነት ዕድሜዋን እንዴት እንዳሳለፈች የምናውቀው ነገር ባይኖርም በዕድሜ ለሚበልጣት ለመርዶክዮስ የሚያስፈልገውን ትሠራለት እንዲሁም መኖሪያ ቤቱን ጥሩ አድርጋ ትይዝለት እንደነበር ብንናገር ስህተት አይሆንም፤ ቤታቸው የሚገኘው ከንጉሡ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ ካለው ወንዝ ማዶ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሰፈር ሳይሆን አይቀርም። ምናልባትም አስቴር የወርቅና የብር አንጥረኞች እንዲሁም ሌሎች ነጋዴዎች ዕቃዎቻቸውን ወደሚሸጡበት በሱሳ ወዳለው የገበያ ስፍራ መሄድ ያስደስታት ይሆናል። እነዚህን የቅንጦት ዕቃዎች እንደ ተራ ነገር የምታይበት ጊዜ እንደሚመጣ ልትገምት እንኳ አትችልም፤ አዎ፣ ወደፊት ምን እንደሚጠብቃት የምታውቀው አንዳች ነገር አልነበረም።

‘እጅግ የተዋበች’ ሴት

7. አስጢን ከንግሥትነቷ የተሻረችው ለምንድን ነው? ከዚያስ ምን ተደረገ?

7 አንድ ቀን በሱሳ ከተማ በንጉሡ ቤት ውስጥ ስለተፈጠረ አስደንጋጭ ሁኔታ የሚገልጽ ወሬ ተናፈሰ። ጠረክሲስ ለመኳንንቱ ባደረገው ድል ያለ ግብዣ ላይ ምግብና የወይን ጠጅ በገፍ እንዲቀርብ አድርጓል፤ ከዚያም ንጉሡ፣ ለሴቶች ብቻ ባዘጋጀችው ግብዣ ላይ የነበረችውን ውቧን ንግሥት አስጢንን ወደ ግብዣው እንድትመጣ አስጠራት። አስጢን ግን ለመሄድ ፈቃደኛ ሳትሆን ቀረች። ለውርደት የተዳረገውና በቁጣ የገነፈለው ንጉሥ፣ አስጢን እንዴት መቀጣት እንዳለባት ከአማካሪዎቹ ጋር ተነጋገረ። ውጤቱስ ምን ሆነ? አስጢን ከንግሥትነቷ ተሻረች። በመሆኑም የንጉሡ አገልጋዮች በመላ አገሪቱ እየተዘዋወሩ ቆንጆ ልጃገረዶችን መፈለግ ጀመሩ፤ ንጉሡም ከእነዚህ ልጃገረዶች መካከል አዲሷን ንግሥት ይመርጣል።—አስ. 1:1 እስከ 2:4

8. (ሀ) መርዶክዮስ አስቴር እያደገች ስትሄድ ስጋት አድሮበት ሊሆን ይችላል የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ አካላዊ ውበትን አስመልክቶ የሚሰጠውን ሚዛናዊ ምክር እንዴት ተግባራዊ ማድረግ የምንችል ይመስልሃል? (በተጨማሪም ምሳሌ 31:30⁠ን ተመልከት።)

8 ትንሿ አስቴር እያደገችና ውበቷ ይበልጥ እየወጣ በሄደ መጠን መርዶክዮስ በስስት ዓይን ሲመለከታት በዓይነ ሕሊናችን መሳል እንችላለን፤ በዚህ ወቅት በአንድ በኩል ኩራት በሌላው በኩል ደግሞ የስጋት ስሜት እንደሚያድርበት የታወቀ ነው። ዘገባው “ይህች ልጃገረድ በተክለ ሰውነቷም ሆነ በመልኳ እጅግ ውብ ነበረች” ይላል። (አስ. 2:7) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ውበት ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ ይገልጻል፤ አካላዊ ቁንጅና በራሱ የሚያስደስት ነገር ቢሆንም ጥበብና ትሕትና ሊታከልበት ይገባል። ካልሆነ ግን እብሪት፣ ኩራትና ሌሎች መጥፎ ባሕርያት በልብ ውስጥ እንዲያቆጠቁጡ ሊያደርግ ይችላል። (ምሳሌ 11:22ን አንብብ።) ይህ እውነት መሆኑን የሚያሳይ ነገር አጋጥሞህ ያውቃል? አስቴርስ ውበቷ ይጠቅማታል ወይስ ይጎዳታል? ይህ ጊዜ የሚያሳየው ነገር ይሆናል።

9. (ሀ) የንጉሡ አገልጋዮች አስቴርን ሲያገኟት ምን አደረጉ? አስቴርና መርዶክዮስ መለያየት በጣም ከብዷቸው ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው? (ለ) መርዶክዮስ፣ አስቴር ይሖዋን የማያመልክ አረማዊ ሰው እንድታገባ የፈቀደው ለምንድን ነው? (በሣጥኑ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ተመልከት።)

9 አስቴር የንጉሡ አገልጋዮች ዓይን ውስጥ ገባች። አስቴርን ከመርዶክዮስ በመነጠል ከሰበሰቧቸው ሌሎች ወጣት ሴቶች ጋር ከወንዙ ማዶ ወዳለው ታላቅ ቤተ መንግሥት ወሰዷት። (አስ. 2:8) አስቴርና መርዶክዮስ እንደ አባትና ልጅ ይቀራረቡ ስለነበር መለያየቱ ለሁለቱም በጣም ከብዷቸው መሆን አለበት። መርዶክዮስ፣ ያሳደጋት ልጅ ይሖዋን የማያመልክ ሰው (ንጉሥም እንኳ ቢሆን) እንድታገባ አይፈልግም ነበር፤ ሆኖም ሁኔታው ከአቅሙ በላይ ነበር። * አስቴር ከመወሰዷ በፊት መርዶክዮስ የሰጣትን ምክር በትኩረት አዳምጣ መሆን አለበት! በሱሳ ወደሚገኘው ቤተ መንግሥት ስትወሰድ በአእምሮዋ ውስጥ ብዙ ጥያቄዎች ሳይጉላሉ አይቀሩም። አስቴር ምን ዓይነት ሕይወት ይጠብቃት ይሆን?

“በሚያዩዋት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አገኘች”

10, 11. (ሀ) አስቴር መኖር የጀመረችበት አዲስ አካባቢ በቀላሉ ተጽዕኖ ሊያሳድርባት ይችል የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) መርዶክዮስ የአስቴር ደህንነት ያሳስበው እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው?

10 አስቴር ለእሷ አዲስና እንግዳ የሆነ ዓለም ውስጥ ገባች። የምትኖረው ከመላው የፋርስ ግዛት ከተሰበሰቡ “ብዙ ልጃገረዶች” ጋር ነበር። የእነዚህ ወጣቶች ባሕል፣ ቋንቋና አስተሳሰብ በእጅጉ የተለያየ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ወጣቶቹ፣ ሄጌ ለተባለ ባለሥልጣን በኃላፊነት የተሰጡ ሲሆን ይበልጥ እንዲዋቡ ለማድረግም አንድ ዓመት የሚፈጅና ጥሩ መዓዛ ባላቸው ዘይቶች መታሸትን የሚያካትት ሰፊ ዝግጅት ተደርጎላቸዋል። (አስ. 2:8, 12) በዚያ ያለው መንፈስና የአኗኗር ዘይቤ ወጣቶቹ ሴቶች ከመጠን በላይ ስለ መልካቸው እንዲያስቡ እንዲሁም የኩራትና የፉክክር መንፈስ እንዲያድርባቸው ሳያደርግ አይቀርም። ታዲያ ይህ ሁኔታ በአስቴር ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን?

11 በምድር ላይ የመርዶክዮስን ያህል ለአስቴር የሚጨነቅ ሰው ሊኖር አይችልም። ዘገባው፣ መርዶክዮስ ሴቶቹ ወደሚኖሩበት ቤት የቻለውን ያህል በመቅረብ በየዕለቱ ስለ አስቴር ደህንነት ለማወቅ ይጥር እንደነበር ይገልጻል። (አስ. 2:11) ምናልባትም በዚህ ቤት ውስጥ የሚኖሩ አገልጋዮች በሚያደርጉለት ትብብር ስለ እሷ የሚያገኘው የተወሰነ መረጃ የአባትነት ኩራት እንዲሰማው ሳያደርግ አይቀርም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

12, 13. (ሀ) ከአስቴር ጋር አብረው ያሉት ሰዎች ለእሷ ምን ዓይነት ስሜት ነበራቸው? (ለ) አስቴር አይሁዳዊ መሆኗን ለማንም እንዳልተናገረች ማወቁ መርዶክዮስን አስደስቶት ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

12 ሄጌ በአስቴር ሁኔታ እጅግ ስለተማረከ ሰባት ሴት አገልጋዮችንና በሴቶቹ ቤት ውስጥ ከሁሉ የተሻለውን ክፍል በመስጠት ታላቅ ፍቅራዊ ደግነት አሳያት። እንዲያውም ዘገባው “አስቴር በሚያዩዋት ሁሉ ዘንድ ሞገስ አገኘች” ይላል። (አስ. 2:9, 15) ሰው ሁሉ እንዲህ በአድናቆት የተዋጠው በቁንጅናዋ ብቻ ነበር? አይደለም፤ አስቴርን ተወዳጅ ያደረጓት ሌሎች ነገሮችም ነበሩ።

አስቴር ከአካላዊ ውበት ይበልጥ ትሕትና እና ጥበብ ትልቅ ዋጋ እንዳላቸው ታውቅ ነበር

13 ለምሳሌ ያህል፣ “መርዶክዮስ እንዳትናገር አዞአት ስለ ነበር፣ አስቴር የየት አገር ሰውና የእነማን ወገን እንደ ሆነች አልገለጸችም” የሚል ሐሳብ እናነብባለን። (አስ. 2:10) መርዶክዮስ አስቴር አይሁዳዊ መሆኗን እንዳትናገር አሳስቧት ነበር፤ እንዲህ ያደረገው የፋርስ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ለእሱ ወገኖች ከፍተኛ ጭፍን ጥላቻ እንዳላቸው በማስተዋሉ ሳይሆን አይቀርም። አስቴር በአካል ከእሱ ብትርቅም እንኳ እንደ ቀድሞው ሁሉ አሁንም በጥበብ እንደምትመላለስና ታዛዥ እንደሆነች ማወቁ ምንኛ አስደስቶት ይሆን!

14. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ወጣቶች የአስቴርን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

14 በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች የወላጆቻቸውንም ሆነ የአሳዳጊዎቻቸውን ልብ ማስደሰት ይችላሉ። ብስለት በጎደላቸው፣ መጥፎ ሥነ ምግባር ባላቸው ወይም ዓመፀኛ በሆኑ ልጆች የተከበቡ ቢሆኑም ወላጆቻቸው አጠገባቸው በማይኖሩበት ጊዜም እንኳ ጎጂ ተጽዕኖዎችን መቋቋምና የሚያምኑባቸውን ትክክለኛ መሥፈርቶች በጥብቅ መከተል ይችላሉ። እንዲህ በማድረግ እነሱም ልክ እንደ አስቴር በሰማይ የሚኖረውን አባታቸውን ልብ ያስደስታሉ።—ምሳሌ 27:11ን አንብብ።

15, 16. (ሀ) አስቴር በንጉሡ ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ የቻለችው እንዴት ነው? (ለ) አስቴር በሕይወቷ ውስጥ ካጋጠማት ለውጥ ጋር ራሷን ማስማማት ከባድ ሊሆንባት የሚችለው ለምንድን ነው?

15 አስቴር ንጉሡ ፊት የምትቀርብበት ጊዜ ሲደርስ ራሷን ይበልጥ ለማስዋብ ያስፈልገኛል ብላ የምታስበውን ማንኛውንም ነገር የመጠየቅ ነፃነት ተሰጥቷት ነበር። እሷ ግን ሄጌ ከነገራት ውጭ ምንም ባለመጠየቅ ጭምት መሆኗን አሳይታለች። (አስ. 2:15) የንጉሡን ልብ ለመማረክ ውበት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ተገንዝባ ይሆናል፤ ልክን ማወቅና ትሕትና በዚያ ቤተ መንግሥት ውስጥ እምብዛም የማይታዩ ባሕርያት እንደሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ታዲያ እንዲህ ዓይነት አመለካከት መያዟ ትክክል ነበር?

16 ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ንጉሡ ከሌሎቹ ሴቶች ሁሉ ይበልጥ አስቴርን ወደዳት፤ ከሌሎቹ ደናግልም ሁሉ ይልቅ በእርሱ ዘንድ ሞገስንና መወደድን አገኘች። ስለዚህ የእቴጌነት ዘውድ በራሷ ላይ ጫነላት፤ በአስጢንም ፈንታ ንግሥት አደረጋት።” (አስ. 2:17) ትሑት የሆነችው ይህች አይሁዳዊት ወጣት በሕይወቷ ውስጥ ካጋጠማት ለውጥ ጋር ራሷን ማስማማት ከባድ እንደሚሆንባት ምንም ጥርጥር የለውም፤ ምክንያቱም ንግሥት ሆና ተሹማለች፤ በሌላ አነጋገር በወቅቱ በምድር ላይ ካሉት ነገሥታት መካከል ኃያል የሆነው ንጉሥ ሚስት ሆናለች! ታዲያ ንግሥት መሆኗ እንድትኮራና እንድትታበይ አድርጓት ይሆን? በፍጹም!

17. (ሀ) አስቴር እንደ አባት ሆኖ ላሳደጋት ለመርዶክዮስ ታዛዥ መሆኗን ያሳየችው በየትኞቹ መንገዶች ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ የአስቴርን ምሳሌ መከተላችን እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

17 አስቴር እንደ አባት ሆኖ ላሳደጋት ለመርዶክዮስ ታዛዥ መሆኗን ቀጥላለች። ከአይሁዳውያን ጋር ያላትን ዝምድና ሚስጥር አድርጋ ይዛው ነበር። በተጨማሪም መርዶክዮስ፣ ጠረክሲስን ለመግደል የተጠነሰሰውን ሴራ ባወቀ ጊዜ አስቴር ንጉሡን እንድታስጠነቅቅ የነገራትን መልእክት በታዛዥነት አድርሳለች፤ በዚህም የተነሳ ሴራው ሊከሽፍ ችሏል። (አስ. 2:20-23) ከዚህም ሌላ የትሕትናና የታዛዥነት መንፈስ ማሳየቷን በመቀጠል በአምላክ ላይ እምነት እንዳላት አሳይታለች። ሰዎች ታዛዥነትን አቅልለው በሚያዩበት እንዲሁም የእምቢተኝነትና የዓመፀኝነት መንፈስ በሰፈነበት በዛሬው ጊዜ የአስቴርን ምሳሌ መከተላችን እጅግ አስፈላጊ ነው! በእርግጥም እውነተኛ እምነት ያላቸው ሰዎች ልክ እንደ አስቴር ታዛዥነትን ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።

የአስቴር እምነት ተፈተነ

18. (ሀ) መርዶክዮስ ለሐማ ለመስገድ ፈቃደኛ ሳይሆን የቀረው ለምን ሊሆን ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) በዛሬው ጊዜ አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የመርዶክዮስን ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው?

18 ሐማ የሚባል አንድ ሰው በጠረክሲስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ተሰጠው። እንዲያውም ንጉሡ ዋነኛ አማካሪው በማድረግና በግዛቱ ውስጥ ሁለተኛውን የሥልጣን ቦታ በመስጠት ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመው። ከዚህም በላይ ንጉሡ፣ ሰዎች ለዚህ ባለሥልጣን እንዲሰግዱለት ትእዛዝ አስተላለፈ። (አስ. 3:1-4) ይህ ሕግ በመርዶክዮስ ላይ ችግር ፈጠረበት። ንጉሡን መታዘዝ እንዳለበት ያምናል፤ ይሁንና ይህን ለማድረግ ሲል የአምላክን ትእዛዝ መጣስ እንደሌለበትም ያውቃል። ሐማ አጋጋዊ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል። ይህም ሲባል ሐማ የአማሌቃውያን ንጉሥ የነበረውና የአምላክ ነቢይ የሆነው ሳሙኤል የገደለው የአጋግ ዝርያ ነው ማለት ነው። (1 ሳሙ. 15:33) አማሌቃውያን እጅግ ክፉ ከመሆናቸው የተነሳ የይሖዋና የእስራኤላውያን ጠላቶች ሆነው ነበር። አማሌቃውያን በብሔር ደረጃ አምላክ ጥፋት የወሰነባቸው ሕዝቦች ነበሩ። * (ዘዳ. 25:19) ታዲያ አንድ ታማኝ አይሁዳዊ ለአንድ አማሌቃዊ እንዴት ሊሰግድ ይችላል? መርዶክዮስ ይህን ሊያደርግ አይችልም። ደግሞም ከአቋሙ ፍንክች አላለም። ዛሬም ቢሆን አምላክን በታማኝነት የሚያገለግሉ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዥያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” የሚለውን መመሪያ በጥብቅ ይከተላሉ።—ሥራ 5:29

19. ሐማ ምን ለማድረግ ፈለገ? ንጉሡንስ ያግባባው እንዴት ነበር?

19 ይህ ሁኔታ ሐማን እጅግ አስቆጣው። ይሁንና መርዶክዮስን ማስገደል የሚችልበትን መንገድ መፈለግ ብቻ በቂ መስሎ አልታየውም። የመርዶክዮስን ወገኖች በሙሉ ለመደምሰስ ቆርጦ ተነሳ! በመሆኑም ሐማ ስለ አይሁዳውያን መጥፎ ወሬ በመናገር ንጉሡን አግባባው። ማንነታቸውን እንኳ ሳይጠቅስ በሕዝቡ መካከል ‘ተሠራጭተውና ተበታትነው የሚኖሩ’ ተራ ሰዎች እንደሆኑ አድርጎ ለንጉሡ ነገረው። ይባስ ብሎም ንጉሡ ያወጣቸውን ሕጎች እንደማያከብሩ ተናገረ፤ ይህ ከሆነ ደግሞ እነዚህ ሰዎች ስጋት የሚፈጥሩ ዓመፀኞች ናቸው ማለት ነው። ሐማ፣ በግዛቱ ውስጥ የሚገኙትን አይሁዳውያን በሙሉ ለማስገደል የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት እንደሚያስገባ ተናገረ። * ጠረክሲስም ሐማ ማንኛውንም ትእዛዝ ማውጣትና ትእዛዙን በማኅተም ማጽደቅ እንዲችል የቀለበት ማኅተሙን ሰጠው።—አስ. 3:5-10

20, 21. (ሀ) ሐማ ያወጣው አዋጅ መርዶክዮስን ጨምሮ በፋርስ ግዛት ውስጥ በሚኖሩት አይሁዳውያን ላይ ምን ስሜት አሳደረ? (ለ) መርዶክዮስ አስቴርን ምን እንድታደርግ ተማጸናት?

20 ከዚያም መልእክተኞች፣ በአይሁድ ሕዝብ ላይ ስለተላለፈው የሞት ፍርድ የሚገልጸውን መልእክት በመላው የፋርስ ግዛት ለማድረስ በአራቱም ማዕዘን በፈረሶቻቸው ሽምጥ መጋለብ ጀመሩ። ይህ አዋጅ ከፋርስ ርቃ በምትገኘው በኢየሩሳሌም ሲሰማ በነዋሪዎቹ ላይ ምን ስሜት ፈጥሮ ሊሆን እንደሚችል ገምት፤ በወቅቱ ኢየሩሳሌም የመከላከያ ቅጥር ያልነበራት ሲሆን ከባቢሎን ግዞት የተመለሱ አይሁዳውያን ቀሪዎች ከተማዋን መልሰው ለመገንባት እየተፍጨረጨሩ ነበር። መርዶክዮስ ይህን አስደንጋጭ ዜና ሲሰማ በኢየሩሳሌም ስለሚኖሩትና በሱሳ ስለሚገኙት ወዳጅ ዘመዶቹ አስቦ ሊሆን ይችላል። በጭንቀት የተዋጠው መርዶክዮስ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለበሰ፤ በራሱም ላይ ዐመድ ነስንሶ ወደ ከተማዋ መሃል በመውጣት ድምፁን ከፍ አድርጎ አለቀሰ። ሐማ ግን እሱ ባመጣው ጦስ የተነሳ በሱሳ የሚገኙ በርካታ አይሁዳውያንና ወዳጆቻቸው የተሰማቸው ድንጋጤ ምንም ግድ ሳይሰጠው ከንጉሡ ጋር የወይን ጠጅ ለመጠጣት ተቀመጠ።—አስቴር 3:12 እስከ 4:1ን አንብብ።

21 መርዶክዮስ አይሁዳውያንን ለማዳን አንድ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ያውቃል። ግን ምን ማድረግ ይችላል? አስቴር፣ መርዶክዮስ ያጋጠመውን ጭንቀት ሰማች፤ ልብስም ላከችለት፤ እሱ ግን ሊጽናና አልቻለም። አምላኩ ይሖዋ፣ የሚወዳት አስቴር ከእሱ ተነጥላ እንድትወሰድና የአንድ አረማዊ ገዢ ሚስት እንድትሆን የፈቀደው ለምን እንደሆነ ለረጅም ጊዜ ሲያሳስበው ቆይቶ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን ምክንያቱ ሳይገለጥለት አይቀርም። መርዶክዮስ፣ አስቴር ወደ ንጉሡ ገብታ “ስለ ሕዝቧ” ጥብቅና በመቆም ንጉሡን እንድትለምነው የሚማጸን መልእክት ላከባት።—አስ. 4:4-8

22. አስቴር ንጉሡ ፊት መቅረብ የፈራችው ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

22 አስቴር መልእክቱ ሲደርሳት በድንጋጤ ክው ብላ መሆን አለበት። ይህ አጋጣሚ እምነቷን በእጅጉ የሚፈትን ነበር። ለመርዶክዮስ ከላከችው ምላሽ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው አስቴር በጣም ፈርታ ነበር። የንጉሡ ሕግ ምን እንደሚል አስታወሰችው። አንድ ሰው ሳይጠራ ንጉሡ ፊት ቀረበ ማለት ሕይወቱን አጣ ማለት ነው። እንዲህ ዓይነት ጥፋት የፈጸመ ሰው በሕይወት መትረፍ የሚችለው ንጉሡ የወርቅ ዘንጉን ከዘረጋለት ብቻ ነው። አስጢን ንጉሡ ፊት እንድትቀርብ ስትጠራ አሻፈረኝ በማለቷ ከደረሰባት ዕጣ አንጻር አስቴር ንጉሡ ርኅራኄ ያሳየኛል ብላ የምትጠብቅበት ምን ምክንያት ይኖራል? አስቴር ላለፉት 30 ቀናት ንጉሡ ወደ እሱ እንድትገባ እንዳልጠራት ለመርዶክዮስ ነገረችው! አመሉ የማይጨበጠው ይህ ንጉሥ ለረጅም ጊዜ ያልጠራት ከመሆኑ አንጻር በእሱ ዘንድ ያላትን ተወዳጅነት እንዳጣች አድርጋ ብታስብ የሚያስገርም አይሆንም። *አስ. 4:9-11

23. (ሀ) መርዶክዮስ የአስቴርን እምነት ይበልጥ ለማጎልበት ምን አላት? (ለ) መርዶክዮስ የተወው ምሳሌ ሊኮረጅ የሚገባው ነው የምንለው ለምንድን ነው?

23 መርዶክዮስ፣ አስቴር ያላትን እምነት ይበልጥ ለማጎልበት ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጣት። እርምጃ ሳትወስድ ብትቀር አይሁዳውያን ከሌላ ምንጭ መዳን እንደሚያገኙ በእርግጠኝነት ነገራት። ሆኖም በአይሁዳውያን ላይ የተነሳው ስደት ገፍቶ ከመጣ አስቴርስ ብትሆን እንዴት በሕይወት እተርፋለሁ ብላ ልትጠብቅ ትችላለች? በዚህ ጊዜ መርዶክዮስ፣ ሕዝቡ ተጠራርጎ እንዲጠፋም ሆነ የገባው ቃል ሳይፈጸም እንዲቀር ፈጽሞ በማይፈቅደው በይሖዋ ላይ ከፍተኛ እምነት እንዳለው አሳይቷል። (ኢያሱ 23:14) ከዚያም መርዶክዮስ ለአስቴር “አንቺ ንግሥት ለመሆን የበቃሽው ለዚህ ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” የሚል ጥያቄ አቀረበላት። (አስ. 4:12-14) መርዶክዮስ የተወው ምሳሌ ሊኮረጅ የሚገባው አይደለም? መርዶክዮስ በአምላኩ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ተማምኖ ነበር። እኛስ?—ምሳሌ 3:5, 6

የሞትን ፍርሃት ያሸነፈ እምነት

24. አስቴር እምነትና ድፍረት ያሳየችው እንዴት ነው?

24 አስቴር ቁርጥ ያለ ውሳኔ የምታደርግበት ሰዓት ደረሰ። የአገሯ ሰዎች ለሦስት ቀን አብረዋት እንዲጾሙ እንዲያደርግ መርዶክዮስን ጠየቀችው፤ በመልእክቷ መደምደሚያ ላይ “ከጠፋሁም ልጥፋ” በማለት እምነትና ድፍረት የሚንጸባረቅበት የማያወላውል ሐሳብ የተናገረች ሲሆን ይህ አባባል እስከ ዛሬ ድረስ በብዙዎች ዘንድ ይታወቃል። (አስ. 4:15-17) በእነዚያ ሦስት ቀናት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ልባዊ ጸሎት አቅርባ መሆን አለበት። በመጨረሻም ወሳኙ ሰዓት ደረሰ። አስቴር ምርጥ የሆነውን የክብር ልብሷን የለበሰች ሲሆን ንጉሡ ሲያያት ደስ እንዲሰኝባት ስትል የምትችለውን ነገር ሁሉ አደረገች። ከዚያም እሱ ወዳለበት ለመሄድ ተነሳች።

አስቴር የአምላክን ሕዝቦች ለመታደግ ስትል ሕይወቷን አደጋ ላይ ጥላለች

25. አስቴር ባሏ ፊት በቀረበችበት ወቅት ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበር ግለጽ።

25 በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው አስቴር ንጉሡ ወደሚገኝበት አደባባይ ሄደች። የተሰማት ጭንቀትና ደጋግማ ታቀርብ የነበረው ጸሎት አእምሮዋንና ልቧን ተቆጣጥሮት እንደነበር መገመት አያዳግትም። ከዚያም ጠረክሲስን ዙፋኑ ላይ ሆኖ ማየት ወደምትችልበት ወደ ውስጠኛው አደባባይ ገባች። ጥቅልል ያለው ፀጉሩ ዙሪያውን በከበበውና በአራት ማዕዘን ቅርጽ በተከረከመው ጢሙ በተሸፈነው ፊቱ ላይ የሚነበበውን ስሜት ለማንበብ ሳትሞክር አትቀርም። ጥቂት መጠበቅ አስፈልጓት ከነበረ እንኳ ይህ ጊዜ በጣም ረዝሞባት ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። የሆነ ሆኖ ጊዜው አለፈና ባሏ ተመለከታት። ሁኔታው ያልጠበቀው እንደሚሆንበት ምንም ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም ፊቱን ፈታ አደረገ። ከዚያም የወርቅ ዘንጉን ዘረጋላት!—አስ. 5:1, 2

26. እውነተኛ ክርስቲያኖች ልክ እንደ አስቴር ደፋር መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? አስቴር የወሰደችው እርምጃ የተልእኮዋ መጀመሪያ የሆነው ለምንድን ነው?

26 አስቴር የመጣችበትን ጉዳይ እንድትናገር ተፈቀደላት። ለአምላኳም ሆነ ለሕዝቧ ጥብቅና በመቆምና እምነት በማሳየት ረገድ እስከ ዛሬ ድረስ ላሉ የአምላክ አገልጋዮች ግሩም ምሳሌ ትታለች። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ላሉ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች ከፍተኛ አድናቆት አላቸው። ኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮቹ ተለይተው የሚታወቁት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ በሚንጸባረቅበት ፍቅር እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:34, 35ን አንብብ።) እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ማሳየት ልክ እንደ አስቴር ደፋር መሆንን ይጠይቃል። ይሁንና አስቴር በዚያ ቀን ለአምላክ ሕዝቦች ስትል የወሰደችው እርምጃ የተልእኮዋ መጀመሪያ ብቻ ነበር። አስቴር፣ የንጉሡ የቅርብ አማካሪ የሆነው ሐማ መሠሪ ሰው መሆኑን ባሏን ልታሳምነው የምትችለው እንዴት ነው? ሕዝቧን ለማዳን ምን ማድረግ ትችል ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ መልስ ያገኛሉ።

^ አን.2 ቀዳማዊ ጠረክሲስ በአምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. መጀመሪያ ላይ የፋርስን ግዛት ያስተዳድር የነበረ ንጉሥ ነው።

^ አን.9 በምዕራፍ 16 ላይ የሚገኘውን “ስለ አስቴር የሚነሱ ጥያቄዎች” የሚል ርዕስ ያለውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.18 ከአማሌቃውያን መካከል “የቀሩት” በንጉሥ ሕዝቅያስ የግዛት ዘመን ተደምስሰው ስለነበር ሐማ በሕይወት ተርፈው ከነበሩት ጥቂት አማሌቃውያን ውስጥ አንዱ ሳይሆን አይቀርም።—1 ዜና 4:43

^ አን.19 ሐማ 10,000 መክሊት ብር ለመስጠት ቃል የገባ ሲሆን ይህ ገንዘብ በዛሬው ጊዜ ባለው የዋጋ ተመን ቢሰላ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ይሆናል። ንጉሡ በእርግጥ ቀዳማዊ ጠረክሲስ ከሆነ ሐማ ያቀረበው ገንዘብ እጅግ አጓጉቶት ሊሆን ይችላል። ጠረክሲስ ለረጅም ጊዜ ሲያቅድ የቆየውን ግሪኮችን የመውጋት ሐሳቡን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልገው ነበር፤ ሆኖም ይህ ጦርነት ለከፍተኛ ኪሳራ ዳርጎታል።

^ አን.22 ቀዳማዊ ጠረክሲስ ስሜቱ የሚለዋወጥ ግልፍተኛ ሰው በመሆኑ ይታወቃል። ግሪካዊው የታሪክ ምሁር ሄሮዶተስ፣ ጠረክሲስ ከግሪክ ጋር ስላደረገው ጦርነት በጻፈው ታሪክ ላይ ስለ ንጉሡ ባሕርይ የሚገልጹ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጠቅሷል። ንጉሡ በሄሌስፖንት ወሽመጥ ላይ መርከቦችን በመደርደር ድልድይ እንዲሠራ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። ድልድዩን ማዕበል ባፈረሰው ጊዜ ጠረክሲስ መሃንዲሶቹ አንገታቸው እንዲቀላ ያዘዘ ከመሆኑም ሌላ ከፍ ባለ ድምፅ እርግማን በሚነበብበት ጊዜ አገልጋዮቹ ውኃውን በመግረፍ ሄሌስፖንትን “እንዲቀጡ” መመሪያ ሰጥቷል። ይህ ጦርነት በተካሄደበት ጊዜ አንድ ባለጸጋ ሰው ልጁ ከውትድርና ግዳጅ ነፃ እንዲሆን ሲለምነው ጠረክሲስ ልጁ ለሁለት እንዲቆረጥ ያዘዘ ከመሆኑም ሌላ መቀጣጫ እንዲሆን አስከሬኑ ሌሎች በሚያዩት ስፍራ እንዲቀመጥ አድርጓል።