በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ ሰባት

‘በይሖዋ ፊት እያደገ ሄደ’

‘በይሖዋ ፊት እያደገ ሄደ’

1, 2. ሳሙኤል የእስራኤልን ሕዝብ ሰብስቦ ባነጋገረበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል? ንስሐ እንዲገቡ ሊያነሳሳቸው የሚገባውስ ለምን ነበር?

ሳሙኤል ሕዝቡን በአንክሮ እየተመለከተ ነው። ሕዝቡ፣ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በነቢይነትና በፈራጅነት ሲያገለግል የኖረው ይህ ታማኝ ሰው ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል በጌልገላ ከተማ ተሰብስቧል። ወቅቱ በዘመናችን አቆጣጠር መሠረት ግንቦት ወይም ሰኔ ሲሆን የበጋው ወቅት ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። በአካባቢው ባሉት ማሳዎች ላይ የሚታየው የስንዴ አዝመራ ነጥቶ ለአጨዳ ደርሷል። በሕዝቡ መካከል ጸጥታ ሰፍኗል። ሳሙኤል የእነዚህን ሰዎች ልብ መንካት የሚችለው እንዴት ይሆን?

2 ሕዝቡ፣ የሠራው ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ የተገነዘበ አይመስልም። ሰብዓዊ ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው ሳሙኤልን ሲወተውቱት ቆይተዋል። እንዲህ ያለ ጥያቄ ሲያቀርቡ ለአምላካቸው ለይሖዋና የእሱ ነቢይ ሆኖ ለሚያገለግለው ሰው ከፍተኛ ንቀት ማሳየታቸው እንደሆነ አልተገነዘቡም። እንዲያውም ይሖዋ ንጉሣችን እንዲሆን አንፈልግም ያሉ ያህል ነበር! ታዲያ ሳሙኤል ንስሐ እንዲገቡ ሊያነሳሳቸው የሚችለው እንዴት ነው?

የሳሙኤል የልጅነት ሕይወት፣ መጥፎ ተጽዕኖ ቢደረግብንም እንኳ በይሖዋ ላይ እምነት ማዳበር የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል

3, 4. (ሀ) ሳሙኤል ስለ ወጣትነት ጊዜው የጠቀሰው ለምንድን ነው? (ለ) ሳሙኤል እምነት በማሳየት ረገድ የተወው ምሳሌ ለእኛ ጥቅም ያስገኝልናል የምንለው ለምንድን ነው?

3 ሳሙኤል “ዕድሜዬ ገፍቶአል፤ ጠጕሬም ሸብቶአል” በማለት ለሕዝቡ ተናገረ። እንደ ጥጥ የነጣው ፀጉሩ ሕዝቡ ሳሙኤል ለሚናገረው ነገር ይበልጥ ክብደት እንዲሰጠው የሚያደርግ ነው። ከዚያም ንግግሩን በመቀጠል “ከወጣትነት ጊዜዬ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ስመራችሁ ቈይቻለሁ” አላቸው። (1 ሳሙ. 11:14, 15፤ 12:2) ሳሙኤል ቢያረጅም የልጅነት ትዝታው አሁንም ከአእምሮው አልጠፋም። በዚያን ጊዜ ያደረጋቸው ነገሮች በደንብ ትዝ ይሉታል። ገና ታዳጊ ወጣት እያለ ያደረጋቸው ውሳኔዎች ሕይወቱን ሙሉ በአምላኩ በይሖዋ እንዲታመንና ለእሱ ያደረ እንዲሆን ረድተውታል።

4 ሳሙኤል እምነት በሌላቸውና ታማኝነት በጎደላቸው ሰዎች መካከል ለመኖር የተገደደባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ቢኖሩም እምነቱን ለመገንባትና ጠብቆ ለመኖር ይጥር ነበር። በዛሬው ጊዜም የምንኖረው እምነት የለሽና ምግባረ ብልሹ በሆነ ዓለም ውስጥ በመሆኑ በዚያን ዘመን እንደነበረው ሁሉ እምነትን መገንባት ተፈታታኝ ነው። (ሉቃስ 18:8ን አንብብ።) ስለሆነም ሳሙኤል ገና ከለጋ ዕድሜው ጀምሮ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

‘ብላቴናው በይሖዋ ፊት ያገለግል ነበር’

5, 6. የሳሙኤል የልጅነት ሕይወት ለየት ያለ የነበረው እንዴት ነው? ሆኖም ወላጆቹ አስፈላጊው እንክብካቤ እንደሚደረግለት እርግጠኞች የነበሩት ለምንድን ነው?

5 የሳሙኤል የልጅነት ሕይወት ለየት ያለ ነበር። ጡት ከጣለ ብዙም ሳይቆይ ምናልባትም በሦስት ወይም በአራት ዓመቱ ገደማ ከትውልድ ስፍራው ከራማ 30 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኘው በሴሎ ባለው የይሖዋ ቅዱስ ማደሪያ ማገልገል ጀመረ። ሕልቃና እና ሐና የሚባሉት ወላጆቹ ሕይወቱን በሙሉ ናዝራዊ በመሆን ለአምላክ ልዩ አገልግሎት እንዲያቀርብ ልጃቸውን ለይሖዋ ሰጡት። * ይህ ሲባል የሳሙኤል ወላጆች ልጃቸውን አይወዱትም ነበር ማለት ነው?

6 በጭራሽ! ልጃቸው በሴሎ ጥሩ እንክብካቤ እንደሚደረግለት ያውቁ ነበር። ሳሙኤል የሚሠራው ከሊቀ ካህናቱ ከዔሊ ጋር ስለነበር ዔሊ ሁኔታውን በቅርብ እንደሚከታተል ጥርጥር የለውም። እንዲሁም በማደሪያ ድንኳኑ የተለያዩ ሥራዎችን የሚያከናውኑ አንዳንድ ሴቶች ነበሩ።—ዘፀ. 38:8፤ መሳ. 11:34-40

7, 8. (ሀ) የሳሙኤል ወላጆች ለልጃቸው በየዓመቱ ምን ዓይነት ፍቅራዊ ማበረታቻ ይሰጡት ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች ከሳሙኤል ወላጆች ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

7 ሐናና ሕልቃናም ቢሆኑ ይሖዋን በጸሎት ለምነው ያገኙትን ውድ የሆነውን የበኩር ልጃቸውን ፈጽሞ አልረሱትም። ሐና፣ ወንድ ልጅ እንዲሰጣት አምላክን ለምናው የነበረ ሲሆን ልመናዋን ከሰማት ሕይወቱን ሙሉ ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርብ ለአምላክ እንደምትሰጠው ቃል ገብታ ነበር። ሐና በየዓመቱ ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ስትሄድ ሳሙኤል በዚያ ሲያገለግል የሚለብሰው አዲስ መደረቢያ እየሠራች ታመጣለት ነበር። ብላቴናው ሳሙኤል ወላጆቹ እየመጡ ሲጠይቁት በጣም እንደሚደሰት ግልጽ ነው። ወላጆቹ ልዩ በሆነው በዚያ ቦታ ይሖዋን ማገልገሉ ትልቅ መብት እንደሆነ አስተምረውት ስለነበር ከእነሱ የሚያገኘውን ፍቅራዊ ማበረታቻና መመሪያ ከፍ አድርጎ ይመለከተው እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም።

8 በዛሬው ጊዜ ያሉ ወላጆች ከሐናና ከሕልቃና ብዙ ትምህርት ማግኘት ይችላሉ። ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያሳድጉ ልጆቻቸው በሚያስፈልጓቸው ቁሳዊ ነገሮች ላይ ብቻ በማተኮር መንፈሳዊ ፍላጎታቸውን ችላ ማለታቸው የተለመደ ነገር ነው። የሳሙኤል ወላጆች ግን መንፈሳዊ ነገሮችን ያስቀደሙ ሲሆን ይህም በልጃቸው የወደፊት ሕይወት ላይ ይህ ነው የማይባል በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል።—ምሳሌ 22:6ን አንብብ።

9, 10. (ሀ) የማደሪያ ድንኳኑ ምን ይመስል እንደነበር እንዲሁም ሳሙኤል ለዚህ ቅዱስ ማደሪያ ምን ዓይነት ስሜት እንደነበረው ግለጽ። (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) ሳሙኤል ያከናውናቸው ከነበሩት ሥራዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? በዛሬው ጊዜ ያሉ ልጆች ሳሙኤል የተወውን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

9 ልጁ እያደገ ሲሄድና በሴሎ አካባቢ ያሉትን ኮረብታዎች እየተዘዋወረ ሲያይ በዓይነ ሕሊናችን መመልከት እንችላለን። ኮረብታዎቹ ላይ ሆኖ ከተማዋንና በግርጌዋ ተንጣሎ የሚታየውን ሸለቆ በሚቃኝበት ጊዜ የይሖዋን የማደሪያ ድንኳን መመልከቱ አይቀርም፤ በዚህ ወቅት ልቡ በደስታና በኩራት እንደሚሞላ ጥርጥር የለውም። የማደሪያ ድንኳኑ በእርግጥም ቅዱስ ቦታ ነበር። * በሙሴ አመራር ከ400 ዓመታት በፊት የተሠራው ይህ የማደሪያ ድንኳን በመላው ዓለም ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ የሚቀርብበት ብቸኛ ስፍራ ነበር።

10 ትንሹ ሳሙኤል የማደሪያ ድንኳኑን እየወደደው ሄደ። ከጊዜ በኋላ ራሱ በጻፈው ዘገባ ላይ “ብላቴናው ሳሙኤል ግን ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር” የሚል ሐሳብ ሰፍሯል። (1 ሳሙ. 2:18) ይህ ቀለል ባለ መንገድ የሚዘጋጅ እጅጌ የሌለው ቀሚስ ሳሙኤል በመገናኛው ድንኳን የካህናቱ ረዳት ሆኖ ይሠራ እንደነበር የሚጠቁም ሳይሆን አይቀርም። ሳሙኤል የካህናት ወገን ባይሆንም እንኳ ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ግቢ የሚያስገቡትን በሮች ማለዳ ላይ መክፈትንና አረጋዊውን ዔሊን መንከባከብን የመሳሰሉ ሥራዎች ነበሩት። ሳሙኤል ያገኘውን መብት በጣም ይወደው ነበር፤ እያደር ግን የልጅ አእምሮውን የሚረብሽ ነገር ያጋጥመው ጀመር። በይሖዋ ቤት ውስጥ በጣም መጥፎ የሆነ ነገር እየተፈጸመ ነበር።

ምግባረ ብልሹ በሆኑ ሰዎች ቢከበብም ንጽሕናውን ጠብቋል

11, 12. (ሀ) አፍኒን እና ፊንሐስ ኃጢአት ወደመፈጸም የመራቸው ዋነኛው ነገር ምንድን ነው? (ለ) አፍኒን እና ፊንሐስ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ምን ዓይነት ክፉ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ነበር? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

11 ሳሙኤል ገና በለጋ ዕድሜው ዓይን ያወጣ ክፋትና የሥነ ምግባር ብልግና ሲፈጸም ተመልክቷል። ዔሊ አፍኒንና ፊንሐስ የሚባሉ ሁለት ወንዶች ልጆች ነበሩት። የሳሙኤል ዘገባ “የዔሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር” በማለት ይናገራል። (1 ሳሙ. 2:12) በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጹት ሁለት ሐሳቦች የማይነጣጠሉ ናቸው። አፍኒን እና ፊንሐስ ይሖዋን የማይፈሩ በመሆናቸው “ምናምንቴዎች” ወይም ቃል በቃል ሲተረጎም “የከንቱነት ልጆች” ነበሩ። ይሖዋ ላወጣቸው የጽድቅ መሥፈርቶችና ብቃቶች ግድ አልነበራቸውም። ያን ሁሉ ኃጢአት ለመሥራት ያበቃቸውም ይኸው ነው።

12 የአምላክ ሕግ የካህናቱን ኃላፊነትና በአምላክ የማደሪያ ድንኳን ውስጥ መሥዋዕቶች የሚያቀርቡበትን መንገድ በተመለከተ የማያሻማ መመሪያ ይዟል። ይህ መሆኑም ተገቢ ነበር! ምክንያቱም በማደሪያ ድንኳኑ የሚቀርቡት መሥዋዕቶች፣ የይሖዋ ሕዝቦች በእሱ ፊት ንጹሕ አቋም እንዲኖራቸውና በረከቱንም ሆነ አመራሩን ለማግኘት ብቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ሲል አምላክ ኃጢአታቸውን ይቅር ለማለት ያደረገውን ዝግጅት የሚያመለክቱ ነበሩ። ይሁን እንጂ አፍኒን እና ፊንሐስ አብረዋቸው የሚያገለግሉት ካህናት ሕዝቡ ለሚያቀርባቸው መሥዋዕቶች ከፍተኛ ንቀት እንዲያድርባቸው አድርገዋል። *

13, 14. (ሀ) በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ይፈጸም የነበረው ክፉ ድርጊት ልበ ቅን በሆኑ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ እንደማይቀር እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? (ለ) ዔሊ የሊቀ ካህንነቱንም ሆነ የአባትነት ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ ሳይወጣ የቀረው እንዴት ነው?

13 ብላቴናው ሳሙኤል እንዲህ ያለው ከባድ ኃጢአት ያለ ምንም ዓይነት የእርምት እርምጃ ችላ ተብሎ ሲታለፍ፣ ዓይኑን ማመን አቅቶት ሁኔታውን በግርምት ሲመለከት በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ሳሙኤል፣ ድሃና ችግረኛ የሆኑ እንዲሁም የተጨቆኑ ሰዎችን ጨምሮ መንፈሳዊ ማጽናኛና ማበረታቻ ለማግኘት ብለው ወደዚያ ቅዱስ ድንኳን ቢመጡም አዝነው፣ ተጎድተው ወይም ተሸማቀው የተመለሱ ምን ያህል ሰዎችን ተመልክቶ ይሆን? ከዚህም በተጨማሪ አፍኒንና ፊንሐስ፣ ይሖዋ ስለ ፆታ ሥነ ምግባር የሰጠውን ሕግ በመናቅ በማደሪያ ድንኳኑ ከሚያገለግሉት አንዳንድ ሴቶች ጋር ዝሙት መፈጸማቸውን ሲያውቅ ሳሙኤል ምን ተሰምቶት ይሆን? (1 ሳሙ. 2:22) ምናልባትም ዔሊ እርምጃ እንደሚወስድ ተስፋ አድርጎ ይሆናል።

ሳሙኤል የዔሊ ልጆች የሚፈጽሙትን የክፋት ድርጊት ሲመለከት እጅግ ተረብሾ መሆን አለበት

14 ዔሊ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን ችግር ለማስተካከል የሚያስችል ከማንም የበለጠ ሥልጣን ነበረው። ሊቀ ካህናት እንደመሆኑ መጠን በማደሪያ ድንኳኑ ለሚፈጸመው ነገር ተጠያቂ ነበር። አባት እንደመሆኑ መጠን ደግሞ ልጆቹን የማረም ግዴታ ነበረበት። ደግሞም ልጆቹ ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንም ጭምር እየጎዱ ነበር። ይሁን እንጂ ዔሊ የሊቀ ካህንነቱንም ሆነ የአባትነት ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ ሳይወጣ ቀርቷል። ለልጆቹ ለዘብ ያለ ተግሣጽ ከመስጠት ያለፈ ነገር አላደረገም። (1 ሳሙኤል 2:23-25ን አንብብ።) ልጆቹ ግን ጠንከር ያለ ተግሣጽ ያስፈልጋቸው ነበር። ለፈጸሙት ኃጢአት ሞት ይገባቸው ነበር!

15. ይሖዋ ለዔሊ ምን ኃይለኛ የፍርድ መልእክት አስተላለፈ? የዔሊ ቤተሰቦችስ ለማስጠንቀቂያው ምን ምላሽ ሰጡ?

15 ሁኔታው የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ ስለነበር ይሖዋ፣ በስም ያልተጠቀሰን አንድ “የእግዚአብሔር ሰው” ለዔሊ ኃይለኛ የፍርድ መልእክት እንዲናገር ላከው። ይሖዋ ዔሊን “ከእኔ ይልቅ ልጆችህን የምታከብራቸው ስለ ምንድን ነው?” አለው። በመሆኑም አምላክ ክፉ ድርጊት ይፈጽሙ የነበሩት የዔሊ ልጆች በአንድ ቀን እንደሚሞቱና የዔሊ ቤተሰብም ታላቅ መከራ እንደሚደርስበት ሌላው ቀርቶ በክህነት አገልግሎት ውስጥ የነበረውን የተከበረ ቦታ እንኳ እንደሚያጣ ትንቢት አስነገረ። ታዲያ ይህ ኃይለኛ ማስጠንቀቂያ የዚያን ቤተሰብ አባላት ለውጥ እንዲያደርጉ አነሳስቷቸው ይሆን? ዘገባው ልባቸው ተነክቶ ለውጥ ስለማድረጋቸው የሚገልጸው ነገር የለም።—1 ሳሙ. 2:27 እስከ 3:1

16. (ሀ) በዘገባው ላይ ስለ ሳሙኤል እድገት የሚገልጹ ምን ሐሳቦች ሰፍረዋል? (ለ) እነዚህን ሐሳቦች ማንበብ ያስደስታል የምንለው ለምንድን ነው? አብራራ።

16 ይህ ሁሉ ምግባረ ብልሹነት በሳሙኤል ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሮ ይሆን? መጥፎ ታሪኮችን በያዘው በዚህ ዘገባ ውስጥ ስለ ሳሙኤል እድገት የሚገልጹ ብርሃን የሚፈነጥቁ ሐሳቦችን አለፍ አለፍ ብሎ እናገኛለን። በ⁠1 ሳሙኤል 2:18 ላይ እንደተገለጸው “ብላቴናው ሳሙኤል” በታማኝነት “በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል” እንደነበር አስታውስ። ሳሙኤል በዚያ ለጋ ዕድሜውም እንኳ ሕይወቱ ለአምላክ በሚያቀርበው አገልግሎት ላይ ያተኮረ ነበር። በዚሁ ምዕራፍ በቁጥር 21 ላይ “ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ” የሚል ደስ የሚያሰኝ ሐሳብ እናገኛለን። ሳሙኤል እያደገ ሲሄድ በሰማይ ከሚገኘው አባቱ ጋር የነበረውም ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መጣ። ከይሖዋ ጋር እንዲህ ያለ የጠበቀ ዝምድና መመሥረት በየትኛውም ዓይነት ምግባረ ብልሹነት ላለመሸነፍ የሚረዳ አስተማማኝ መከላከያ ነው።

17, 18. (ሀ) ክርስቲያን ወጣቶች ምግባረ ብልሹ የሆኑ ሰዎች ሲያጋጥሟቸው ሳሙኤል የተወውን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ሳሙኤል ትክክለኛ አካሄድ መምረጡን የሚያሳየው ምንድን ነው?

17 ሳሙኤል፣ ሊቀ ካህናቱም ሆነ የሊቀ ካህናቱ ልጆች ኃጢአት የሚሠሩ ከሆነ እሱም የፈለገውን መፈጸም እንደሚችል አድርጎ ሊያስብ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ በኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙትን ጨምሮ ሌሎች ምግባረ ብልሹ መሆናቸው ኃጢአት ለመሥራት በጭራሽ ሰበብ ሊሆን አይችልም። በዛሬው ጊዜ በርካታ ክርስቲያን ወጣቶች በዙሪያቸው ያሉ አንዳንድ ሰዎች ጥሩ ምሳሌ በማይሆኑበት ጊዜም እንኳ የሳሙኤልን አርዓያ በመከተል ‘በእግዚአብሔር ፊት ማደጋቸውን’ ቀጥለዋል።

18 ሳሙኤል እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ መከተሉ ምን ጥቅም አስገኝቶለታል? መጽሐፍ ቅዱስ “ብላቴናውም ሳሙኤል በአካልና በሞገስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እያደገ ሄደ” ይላል። (1 ሳሙ. 2:26) ከዚህ መመልከት እንደምንችለው ሳሙኤል በብዙዎች በተለይ ደግሞ በሕይወቱ ትልቅ ቦታ በሚሰጣቸው ሰዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ ነበር። ይሖዋም ቢሆን የታማኝነት ጎዳና በመከተሉ ይህን ብላቴና ከፍ አድርጎ ይመለከተው ነበር። ሳሙኤል በሴሎ የሚፈጸመውን ክፋት ሁሉ ለማስተካከል አምላኩ ይሖዋ እርምጃ እንደሚወስድ ያውቅ እንደነበር ጥርጥር የለውም፤ ይሁን እንጂ ‘ይህን የሚያደርገው መቼ ይሆን?’ የሚለው ጉዳይ ሳያሳስበው አልቀረም። ሆኖም አንድ ቀን ሌሊት የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ አገኘ።

“ባሪያህ ይሰማልና ተናገር”

19, 20. (ሀ) አንድ ቀን፣ ሌሊት ላይ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ሳሙኤል ምን እንዳጋጠመው ተናገር። (ለ) ሳሙኤል ድምፁ የመጣው ከየት እንደሆነ ማወቅ የቻለው እንዴት ነበር? ለዔሊስ ምን ዓይነት አመለካከት ነበረው?

19 ሊነጋ እየተቃረበ ቢሆንም ገና ጎህ አልቀደደም፤ የማደሪያ ድንኳኑም መብራት እንደበራ ነው። ኮሽታ በማይሰማበት በዚህ ጊዜ ሳሙኤል አንድ ድምፅ ሲጠራው ሰማ። ሳሙኤል በጣም ያረጀውና ዓይኖቹ ሊታወሩ የተቃረቡት ዔሊ የጠራው መሰለው። በመሆኑም ብላቴናው ከአልጋው በመነሳት ወደ አረጋዊው ሰው ‘እየሮጠ ሄደ።’ ይህ ልጅ ዔሊ ምን ፈልጎ እንደጠራው ለማወቅ ባዶ እግሩን እየተጣደፈ ሲሄድ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ? ሳሙኤል ዔሊን በአክብሮትና በደግነት ይይዘው እንደነበረ ማወቁ ያስደስታል። ዔሊ ብዙ በደል የፈጸመ ቢሆንም እንኳ አሁንም ይሖዋ የሾመው ሊቀ ካህናት ነበር።—1 ሳሙ. 3:2-5

20 ሳሙኤል ዔሊን ቀሰቀሰውና “እነሆኝ የጠራኸኝ” አለው። ዔሊ ግን እንዳልጠራው በመግለጽ ተመልሶ እንዲተኛ ነገረው። ሆኖም ይኸው ሁኔታ ከአንዴም ሁለቴ ተደገመ! በመጨረሻም ዔሊ ምን እየተከናወነ እንዳለ ተገነዘበ። በዚያ ዘመን ይሖዋ በራእይም ሆነ በነቢያት ተጠቅሞ ለሕዝቡ መልእክት ማስተላለፉ እንደ ብርቅ ይታይ ነበር፤ ይህ የሆነበትን ምክንያት ማወቅ አያዳግትም። አሁን ግን ይሖዋ በዚህ ልጅ አማካኝነት ለሕዝቡ እንደገና መናገር እንደጀመረ ዔሊ ተገነዘበ። በመሆኑም ሳሙኤልን ተመልሶ ሄዶ እንዲተኛና ይህን ድምፅ እንደገና ከሰማ ምን መልስ መስጠት እንዳለበት ነገረው። ሳሙኤልም የተባለውን አደረገ። ብዙም ሳይቆይ ያው ድምፅ “ሳሙኤል! ሳሙኤል!” በማለት ሲጠራው ሰማ። ብላቴናውም “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ።—1 ሳሙ. 3:1, 5-10

21. በዛሬው ጊዜ ይሖዋን መስማት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረጋችንስ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

21 በመጨረሻ፣ ይሖዋ በሴሎ እሱን የሚሰማ አገልጋይ አገኘ። ሳሙኤል በሕይወት በኖረበት ዘመን ሁሉ ይሖዋን ይሰማ ነበር። አንተስ እንዲህ ዓይነት ልማድ አለህ? ይሖዋን ለመስማት መለኮታዊ ድምፅ በሌሊት እንዲያናግረን መጠበቅ አይኖርብንም፤ በዛሬው ጊዜ የአምላክ ድምፅ ዘወትር ያናግረናል ማለት ይቻላል። ድምፁ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። አምላክን ይበልጥ ባዳመጥነውና የሚነግረንን ተግባራዊ ባደረግን መጠን እምነታችንም በዚያው ልክ እያደገ ይሄዳል። ሳሙኤልም ያደረገው ይህንኑ ነው።

ሳሙኤል ፍርሃት ቢሰማውም የይሖዋን የፍርድ መልእክት ለዔሊ በታማኝነት ተናግሯል

22, 23. (ሀ) ሳሙኤል በመጀመሪያ ለዔሊ መናገር አስፈርቶት የነበረው መልእክት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር? (ለ) ሳሙኤል ስሙ ይበልጥ እየገነነ የሄደው ለምንድን ነው?

22 በዚያ ሌሊት በሴሎ የተከናወነው ነገር በሳሙኤል ሕይወት ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ ብላቴና የአምላክ ነቢይና ቃል አቀባይ በመሆኑ ከይሖዋ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና መሥርቷል። መጀመሪያ ላይ ብላቴናው የይሖዋን መልእክት ለዔሊ መንገር አስፈርቶት ነበር፤ ምክንያቱም የሰማው ነገር በዚያ ቤተሰብ ላይ የተነገረው ትንቢት በቅርቡ ሊፈጸም መሆኑን የሚገልጽ የመጨረሻ የፍርድ መልእክት ነበር። ይሁን እንጂ ሳሙኤል እንደምንም ራሱን አደፋፍሮ መልእክቱን የተናገረ ሲሆን ዔሊም መለኮታዊውን ፍርድ መቀበሉን በትሕትና ገለጸ። ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ የተናገረው በሙሉ ተፈጸመ፤ እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ጋር ጦርነት ገጠሙ፤ አፍኒን እና ፊንሐስም በአንድ ቀን ተገደሉ። ዔሊም የይሖዋ ቅዱስ ታቦት እንደተማረከ ሲሰማ ሞተ።—1 ሳሙ. 3:10-18፤ 4:1-18

23 ሳሙኤል ግን ታማኝ ነቢይ በመሆኑ ስሙ ይበልጥ እየገነነ ሄደ። ዘገባው ይሖዋ ‘ከእርሱ ጋር እንደነበር’ ይገልጻል፤ አክሎም ይሖዋ፣ ሳሙኤል የተናገረው ትንቢት በሙሉ እንዲፈጸም ያደርግ እንደነበር ይናገራል።—1 ሳሙኤል 3:19ን አንብብ።

‘ሳሙኤል ወደ ይሖዋ ጮኸ’

24. ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ምን ዓይነት ውሳኔ አደረጉ? እንዲህ ማድረጋቸው ከባድ ኃጢአት የነበረው ለምንድን ነው?

24 ይህ ሲባል ታዲያ እስራኤላውያን የሳሙኤልን አመራር በመከተል ታማኝና ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያለው ሕዝብ ሆነው ነበር ማለት ነው? አይደለም። ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን በእነሱ ላይ ይፈርድ በነበረው ነቢይ ረክተው መኖር ስላልቻሉ ከዚያ የተሻለ ነገር እንደሚፈልጉ መግለጽ ጀመሩ። እነሱም እንደ ሌሎቹ ብሔራት በላያቸው ላይ ሰብዓዊ ንጉሥ ማንገሥ ፈልገው ነበር። ነቢዩ የይሖዋን መመሪያ በመከተል የጠየቁትን ፈጸመላቸው። ይሁን እንጂ ሳሙኤል እስራኤላውያን የኃጢአታቸውን ክብደት እንዲገነዘቡ ማድረግ ነበረበት። ሕዝቡ የናቁት ሰውን ሳይሆን ይሖዋን ነበር! ስለዚህ ነቢዩ ሕዝቡን ጌልገላ ላይ ሰበሰባቸው።

ሳሙኤል በእምነት የጸለየ ሲሆን ይሖዋም ነጎድጓድና ዝናብ በመላክ ምላሽ ሰጥቶታል

25, 26. አረጋዊው ሳሙኤል በጌልገላ የተሰበሰቡት ሰዎች ከባድ ኃጢአት መፈጸማቸውን እንዲገነዘቡ ያደረገው እንዴት ነው?

25 ሳሙኤል ውጥረት በነገሠበት በዚያን ወቅት በጌልገላ ለተሰበሰቡት እስራኤላውያን ሲናገር እኛም ከእሱ ጋር በቦታው እንደነበርን አድርገን እናስብ። አረጋዊው ሳሙኤል ሕይወቱን ሙሉ ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ እንደኖረ ለእስራኤላውያን አስታወሳቸው። ከዚያም ዘገባው “ሳሙኤል ወደ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ጮኸ” ይላል። ነቢዩ፣ ይሖዋን ነጎድጓድና ዝናብ እንዲልክ ለመነው።—1 ሳሙ. 12:17, 18

26 በዚያ የበጋ ወቅት ነጎድጓድና ዝናብ ከየት ሊመጣ ይችላል? እንዲህ ያለ ነገር ጨርሶ ተሰምቶ አያውቅም! ሕዝቡ ዝናብ መምጣት ስለመቻሉ ቅንጣት ታህል ተጠራጥረው ወይም በሳሙኤል ላይ አሹፈው ከነበረ ይህ ስሜታቸው ብዙም አልዘለቀም። ሰማዩ በአንዴ ጠቆረ። ኃይለኛው ነፋስ በማሳዎቹ ላይ ያለውን ስንዴ መሬት ላይ ረፈረፈው። ጆሮ የሚያደነቁር የነጎድጓድ ድምፅ ያስገመግም ጀመር። ከዚያም የጠቆረው ሰማይ ዶፉን ለቀቀው። ታዲያ እዚያ የተሰበሰቡት ሰዎች ምን ተሰማቸው? “ሕዝቡ ሁሉ እግዚአብሔርንና ሳሙኤልን እጅግ ፈሩ።” የፈጸሙት ኃጢአት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አሁን ገና ገባቸው።—1 ሳሙ. 12:18, 19

27. ይሖዋ፣ ሳሙኤል እምነት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ ለሚከተሉ ሰዎች ምን አመለካከት አለው?

27 ዓመፀኛ የሆነውን የዚህን ሕዝብ ልብ መንካት የቻለው ሳሙኤል ሳይሆን ይሖዋ ነበር። ሳሙኤል ከልጅነቱ ጀምሮ እስከ እርጅና ዘመኑ ድረስ በአምላኩ ታምኗል። እንዲህ በማድረጉም ይሖዋ ክሶታል። ይሖዋ ዛሬም ቢሆን አልተለወጠም። ሳሙኤል እምነት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ የሚከተሉትን ሰዎች አሁንም ይደግፋቸዋል።

^ አን.5 ናዝራዊነት የአልኮል መጠጥ አለመጠጣትንና ፀጉርን አለመቆረጥን ጨምሮ ከአንዳንድ ነገሮች መቆጠብን የሚያካትት ስእለት ነው። አብዛኞቹ ናዝራውያን እንዲህ ዓይነቱን ስእለት የሚሳሉት ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ሲሆን እንደ ሳምሶን፣ ሳሙኤልና መጥምቁ ዮሐንስ ያሉት ጥቂት ሰዎች ግን ሕይወታቸውን በሙሉ ናዝራውያን ሆነው ኖረዋል።

^ አን.9 ይህ ቅዱስ ማደሪያ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያለው ሲሆን በእንጨት አውታር ላይ የተዘረጋ ትልቅ ድንኳን ነበር ሊባል ይችላል። ይሁን እንጂ ድንኳኑ የተሠራው ምርጥ በሆኑ ቁሳቁሶች ይኸውም በአቆስጣ ቆዳ፣ ውብ የሆነ ጥልፍ በተጠለፈባቸው ጨርቆች እንዲሁም በብርና በወርቅ በተለበጡ ውድ እንጨቶች ነበር። ይህ ቅዱስ ድንኳን የሚገኘው አራት ማዕዘን ቅርጽ ባለው ግቢ ውስጥ ሲሆን በግቢው ውስጥ አስደናቂ የሆነ መሠዊያም አለ። ከጊዜ በኋላ በማደሪያው ድንኳን አጠገብ ካህናት የሚጠቀሙባቸው ሌሎች ክፍሎችም ሳይጨመሩ አልቀሩም። ሳሙኤል የሚተኛው በእንዲህ ዓይነቱ ክፍል ውስጥ የነበረ ይመስላል።

^ አን.12 ዘገባው ካህናቱ የሚቀርቡትን መሥዋዕቶች ይንቁ እንደነበር የሚያሳዩ ሁለት ምሳሌዎችን ይዟል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሕጉ ከመሥዋዕቱ ውስጥ የካህናቱ ድርሻ የትኛው እንደሆነ ለይቶ ይገልጽ ነበር። (ዘዳ. 18:3) ክፉዎቹ ካህናት ግን በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ከዚህ በጣም የተለየ አሠራር ይከተሉ ነበር። ካህናቱ፣ ሥጋው እየተቀቀለ ሳለ አገልጋዮቻቸውን በመላክ ከድስቱ ውስጥ ማንኛውንም ምርጥ ሥጋ በሜንጦ አውጥተው እንዲያመጡላቸው ያደርጉ ነበር! ሌላው ደግሞ ሰዎቹ መሥዋዕታቸውን በመሠዊያው ላይ እንዲቃጠልላቸው ሲያመጡ ክፉዎቹ ካህናት የመሥዋዕቱ ስብ ገና ለይሖዋ ከመቅረቡ በፊት አገልጋያቸው መሥዋዕት ከሚያቀርበው ሰው ላይ ጥሬ ሥጋ ነጥቆ እንዲያመጣላቸው ያደርጉ ነበር።—ዘሌ. 3:3-5፤ 1 ሳሙ. 2:13-17