በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ልደት የማያከብሩት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ልደት የማያከብሩት ለምንድን ነው?

 የይሖዋ ምሥክሮች ልደት የማያከብሩት እንዲህ ማድረጋቸው አምላክን እንደማያስደስተው ስለሚያምኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ልደት ማክበርን በቀጥታ ባይከለክልም ከልደት በዓል ጋር የተያያዙ አንዳንድ ወሳኝ እውነታዎችን ቆም ብለን እንድናስብና አምላክ በዚህ ረገድ ያለውን አመለካከት እንድናውቅ ያስችለናል። ከእነዚህ እውነታዎች መካከል አራቱን እንመልከት፤ እንዲሁም ከእነሱ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እንመርምር።

  1.   ልደት ከአረማውያን የመጣ በዓል ነው። ስለ በዓላት አመጣጥ የሚናገር አንድ መጽሐፍ (Funk & Wagnalls Standard Dictionary of Folklore, Mythology, and Legend) ልደት የማክበር ልማድ የመነጨው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ ይዟል፤ ይኸውም አንድ ሰው በተወለደበት ቀን “ክፉ መናፍስት እና ኃይሎች [እሱን] ለማጥቃት አጋጣሚ እንደሚያገኙ” ሆኖም “ግለሰቡ ከወዳጆቹ ጋር መሆኑና የመልካም ምኞት መግለጫ መስማቱ ጥበቃ እንደሚሆንለት” ይታመን እንደነበር ገልጿል። ዘ ሎር ኦቭ በርዝዴይስ የተባለው መጽሐፍ፣ በጥንት ዘመን የልደት ቀንን መመዝገብ “በኮከብ ቆጠራ” አማካኝነት “ዕጣ ፈንታን ለማወቅ አስፈላጊ” እንደነበር ገልጿል። መጽሐፉ አክሎ እንደገለጸው ከሆነ “በልደት ቀን የሚበሩት ሻማዎች [ልደቱን የሚያከብረው ግለሰብ] ጥሩ ዕድል እንዲገጥመው የሚያደርጉ ልዩ ምትኃታዊ ኃይል እንዳላቸው ይታመን ነበር።”

     ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ አስማትን፣ ሟርትን እና መናፍስታዊ ድርጊትን ያወግዛል። (ዘዳግም 18:14፤ ገላትያ 5:19-21) እንዲያውም አምላክ በጥንቷ ባቢሎን ላይ የፍርድ መልእክት ያስተላለፈበት አንዱ ምክንያት የከተማይቱ ነዋሪዎች በኮከብ ቆጠራ የመጠቀም ልማድ የነበራቸው መሆኑ ነው፤ ኮከብ ቆጠራ ደግሞ ከሟርት ድርጊቶች አንዱ ነው። (ኢሳይያስ 47:11-15) የይሖዋ ምሥክሮች የእያንዳንዱን ልማድ አመጣጥ ለማወቅ ከልክ ያለፈ ምርምር ባያደርጉም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ግልጽ መመሪያ በሚሰጥበት ጊዜ መመሪያውን በቸልታ አያልፉም።

  2.   የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ልደት አያከብሩም ነበር። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው የጥንቶቹ ክርስቲያኖች “የማንኛውንም ሰው የልደት ቀን ማክበር የአረማውያን ልማድ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱ ነበር።” ሐዋርያት እና ከኢየሱስ በቀጥታ የተማሩ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ክርስቲያኖች በሙሉ ሊከተሉት የሚገባ አርዓያ እንደተዉ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል።​—2 ተሰሎንቄ 3:6

  3.   ክርስቲያኖች እንዲያከብሩት የታዘዙት ብቸኛው በዓል ልደት ሳይሆን የሞት መታሰቢያ ይኸውም የኢየሱስን የሞት መታሰቢያ ነው። (ሉቃስ 22:17-20) ይህም የሚያስገርም አይደለም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የሞት ቀን ከልደት ቀን ይሻላል’ በማለት ይናገራል። (መክብብ 7:1) ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ፍጻሜ ላይ በአምላክ ፊት ጥሩ ስም አትርፎ ነበር፤ በዚህም ከተወለደበት ቀን የበለጠ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው የሞተበት ቀን መሆኑን በግልጽ አስመሥክሯል።​—ዕብራውያን 1:4

  4.   ልደቱን ያከበረ አንድም የአምላክ አገልጋይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሶ አናገኝም። ይህ ሊሆን የቻለው እንደው በአጋጣሚ ሳይጻፍ ስለተዘለለ አይደለም፤ ምክንያቱም አምላክን የማያመልኩ ሁለት ሰዎች ልደታቸውን እንዳከበሩ የሚገልጽ ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እናገኛለን። ይሁን እንጂ ሁለቱም የልደት በዓላት የተጠቀሱት በመጥፎ ነው።​—ዘፍጥረት 40:20-22፤ ማርቆስ 6:21-29

የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ልደት ባለማክበራቸው የቀረባቸው ነገር እንዳለ ይሰማቸዋል?

 እንደ ማንኛውም ጥሩ ወላጅ ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች ወላጆች፣ በማንኛውም የዓመቱ ቀናት ውስጥ ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅር በተለያየ መንገድ ይገልጻሉ፤ ይህም ስጦታ መስጠትን ወይም ተሰባስቦ መጫወትን ያጠቃልላል። በዚህ ረገድ የአምላክን ፍጹም ምሳሌ ይከተላሉ፤ እሱ ቀን ጠብቆ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ለልጆቹ መልካምን ነገሮችን ይሰጣል። (ማቴዎስ 7:11) የይሖዋ ምሥክር ልጆች የቀረባቸው ነገር እንዳለ እንደማይሰማቸው የሚያሳዩ ጥቂት አስተያየቶች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፦

  •   “ይበልጥ የምትደሰተው ሳታስበው ስጦታ ሲሰጥህ ነው።”​—ታሚ፣ ዕድሜ 12

  •   “ወላጆቼ በልደቴ ቀን ባይሆንም እንኳ በሌሎች አጋጣሚዎች ስጦታ ይሰጡኛል። ያልጠበቅኩት ስለሚሆን እንደዚህ ሲያደርጉ በጣም ደስ ይለኛል።”​—ግሪጎሪ፣ ዕድሜ 11

  •   “ለአሥር ደቂቃ ብቻ ኬክ በልቶ፣ መዝሙር ዘምሮ መለያየት ግብዣ ይባላል? እኔ ቤት ብትመጡ ግብዣ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አሳያችኋለሁ።”​—ኤሪክ፣ ዕድሜ 6